Sunday, 12 November 2023 20:20

ከዓለም ሳንባ ሥር

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(2 votes)

 ሀ. መዘዘኛ ድርሰት አልወድም
ግትርትር አባቴ፣ በዚህ ውዥንብር መሀል አርፈህ ተቀመጥ መባሉን ችላ ብሎ ሠፈር ካልቀየርኩ እሞታለሁ አለ፤ የመሞቻ ዕድል አልነበረውም። ሠፈር የመቀየር ዕድል ስላመቻቸ (በግትርነት) ቀየርን። ከይሲ ነው፤ አካይስትም ጭምር፤ ከአያንቱ አናጠበኝ።
ሁሉም ነገር ደባብቶኛል፤ አለመታዘዝ ግብሬ ሆኗል። ፍቅር ያጣ ሰው ሰላም ቢያጣ ምኑ ይጎድላል? የደበተው ሰው አይታዘዝም፤ ወይም ከድባቴ ምልክቶች አንዱ አለመታዘዝ ይመስለኛል።
*  *  *
ወታደሮች ትጥቅ አንግበው ከተማውን እንደ ክረምት አግቢ ወረውታል። ክንፋቸው ይርገፍና፤ ሰዓት እላፊ ብለው ያንገረግባሉ ደግሞ። ታዲያ እኔ ምን ገዶኝ? ጉርምስናም መጥቷል፤ ለዚህ ማስረጃው ደግሞ ብብቻዬ ላብ ማካፋት ጀምሯል። እንደውም የብብት ዳይፐር ሳያስፈልገኝ አይቀርም። ካላመንክ እንካ ብብቴን አሽት… እና ሰው ከቤት መውጣት ቢፈራም በዓለም ሳንባ አደባባዮች እታያለሁ (አባቴ ቢቃወምም)። አልፈራም ነበር።
…መሀል ከተማ፣ እፎይታ ባርና ሬስቶራንት ቢራ እጠጣለሁ፤ ከጀርባዬ የሸጎጥኩትን መጻሕፍ አወጣሁ። መላጣው ባሬስታ በጥርጣሬ ያየኛል፤ ራሱ እንደ ኩላሊት የለሰለሰ ነው። መጻሕፍ ስለያዝኩ ሰላይ መስዬው በቄንጥ ይሰልለኛል።
ነን ኦፍ ማይ ቢዝነስ!
‹‹መለያየት ሞት ነው›› የሚል ርዕስ ያለው መጻሕፍ ነው፤ ርዕሱ የዘፈን ስለሆነ ወድጄአለሁ መሰለኝ፤ የደራሲው ማንነት ‹‹ዓለማየሁ ገላጋይ›› እንደሆነ አወኩ፤ እንዴት ያለ ቆንጆ ሥም ነው ጃን! ከሰቀዘኝ ድባቴ እንደሚገላግለኝ ቀልቢያዬ ነግሮኛል።
ባሬስታው ብርጭቆ የሚያጥብ በመምሰል እንደ ሀባብ የለደለደ ራቁት ራሱን ወደ እኔ አቅጣጫ አስግጎ አጨንቁሮብኛል።  
ችላ ብዬው እጄ እንዳመጣልኝ ገለጥኩ፡-
‹‹በሥነ-ጽሑፍ መንገድ ላይ ከዳኛቸው ወርቁና ከአዳም ረታ ጋር›› በሚል ርዕስ መዘዝ የሚመዝ ቦታ አጋጠመኝ…
…መቀመጫዬን አደላድዬ ወደ ጉዳዩ ተከታለፍኩ፡-
ዓለማየሁ በዚህ አርዕስት አዳም ረታ ላይ ሒሳዊ ጥቃት ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ያዝኩት። ለአዳም የተተኮሰው ተባራሪ አረር ወዳጆቹን እንደፈጃቸው ዕሙን ሆነ…
ዷ…
‹‹ማነህ፣ ድራፍት ድገም!››
እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ዳኛቸው ወርቁ ስለ አዳም ረታ ሐሞት ተግቷል፣ ጅራፍና ቡጢም ቀምሷል…
‹‹ድራፍቱን!››
…ስለ አዳም በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ‹‹አደፍርስ›› በሚባል ደሙ አንጽቶታልም። እንሆኝ አዳም ‹‹በግራጫ ቃጭሎች›› ከፍርግርግ ትረካ ይልቅ ሰንጠረዥ ከልሎ አራት ትዕይንቶችን በአንዴ እንዲያስኬድ ዳኛቸው ቤዛ ሆኗል…
ጭልጥ…
…ሌላው ጉቤው ወላ የአበበ ቢቂላ ወዳጁ መዝገቡ ዱባለ የወዳጁን የወሰንን ቤት ያካለለበትን የተሸነካከለና ቅጥ-አንባሩ የጠፋ መስመር ዳኛቸው ‹ፂወኒ› በፍቅረኛዋ ከተከዳች አንስቶ የገጠማትን የሀሳብ ንውዘት ለማሳየት ‹‹አደፍርስ›› ላይ ተጠቅሞታል…
ትን ብሎኝ ልሞት!
‹‹ምን ነካህ?››
አስተናጋጁ ወደ‘ኔ አጨነቆረ፤
‹‹ወዲህ ነው››
…ብሎም በሦስት ዋና፣ ዋና ገጸ-ባሕሪያት እና በሌላ በአልፎ-ሂያጅ የሚደረግ ትረካን የአዳም ‹‹ማሕሌት›› እና የዳኛቸው ‹‹አደፍርስ›› ላይ ቅልብጭ ብለው እናገኛለን…
‹‹ሒሳብ፣ ሒሳብ››
ውልቅ!
*  *  *
ከስካር ውልብታ በኋላ…
…ቆይ፣ ቆይ አዳም ረታ የዳኛቸው ወርቁን ፈለግ ቢከተል ሕጸጹ እምን ላይ ነው? እኔ እንጃ።
      ለ. የከሰመ ከንፈር አልወድም
‹‹ያ-ወይን የተሾመ ጽዋ የመሰለ ከናፍርሽ በምን አስማት ከሰመ?›› ብዬ ልጠይቃት እልና (ሴት ናትና እንዳትከፋ) ዝም እላለሁ…
…የእናንተ እግዚሔር ለቆንጆ ሴት ቆንጆ ከንፈር ቀምሞ መሥራቱን አላቆመም ነበር፤ ነገር ግን ከዚያ ውብ ከንፈር ላይ አዋቂ ነን ባዮች ለምን ፈውስ እንዳልቀመሙ ሳስብ ግራ ይገባኛል።
ምድረ ንውዝ ብቻ!
እንዲህ ሆነ… ሠፈር ከቀየርን ቆይቶ፣ ቆይቶ አያንቱ ቀጫጭን ጭኖችዋ ግዛታቸው ተስፋፍቶ፣ አንድ ሉሉ የሚያክል ቂጧ መዓት ሆኖ የዓለም ሳንባ አደባባይ ላይ ስትንጎማለል አገኘኋት።
ሌጣ ልቤ በላብ መልክ ልታፈተልክብኝ ሆነ!
ከላይ ከነአብርሃም ሥጋ ቤት አካባቢ እንደመጣች አወኩ። በግራ እጅዋ በጥቁር ላስቲክ የተጠቀለለ ነገር ይዛለች። ስጠጋት የበግ ሥጋ ሸተተኝ። በቀኝ እጅዋ ደግሞ ትንሽዬ ጥላ አንግታለች። ከጥላው እጄታ የተነሳ ቀጭን ጥቁር ክር የቀኝ እጅዋ አጽቅ ላይ ተንጠልጥሏል።
በቀኝ እጅዋ የጥላዋን የስቅላት ቅጣት በውዝወዛ እየተወነች የቴሌውን መንገድ ልትያያዝ ግራ ቀኝ ቃኘች።የምር ደነቀኝ፤ በፊት ሳውቃት ከንፈረ-ፍሕሶ ነበረች። አያንቱ የዓለም ሳንባ የከንፈር ሻምፒዮን። አያንቱ ክፋይ ሮማን አፍ! ዛሬ ግን (ውበትም እንደ ጤዛ ነውና) ከንፈሯ ወይቦ ውኃ እንደነካው የጠላ ቂጣ አኮፍኩፎ፣ ንብርብር ደባደቦ መስሎ ድፎ፣ እንደ አያቴ የካፓርት ክሳድ ተንከርፍፎ…
…አንጀቴን በላቺኝ። እግዚሔሩ ላያጠና ለምን ውበት ይከናንባል? ሸልሞ ሲያበቁ መርገም አያስተዛዝብም? አዪ ምነው፣ ልናደድ እንዴ?
ሮጥ ብዬ እጄን ዘረጋሁላት።
‹‹ይቅርታ!››
‹ይቅርታ› አባባሏ ይቅር ያሰኛል። አንቺ የማር ሥራ፣ አንቺ ጠብደል ቂጣም፣ አንቺ ሎሚ ሽታ….
‹‹አዩ!›› አልኩ እኔ የዓለም ሳንባዋ አራዳ
በአግራሞት ዘለስ ብላ አየቺኝ፤ ቆመች።
አቋቋሟን ሳይ ልቤ ልትቆምብኝ ሆነ።
‹ሂድ፣ ሂድ› ቀጭቃጫው ውስጤ…
…ሄድኩ
‹‹አዩ የኔ ዋልታ››
‹‹የኔ ወስላታ፤ ሰው አይናፍቅህም?››
‹ስንትና ስንት ዘባተሎ ከንፈር ያለቸው ባለሙዳ ከናፍራሞችን ያየ ዓይኔ፣ አይቶም ሕማምና ሰቀቀን የተረፈው ዓይኔ፤ ወይን የሾሙት ጽዋ የመሰለ ከንፈርሽን በዓይኖቹ ነክቶ ተፈውሶአልና፤ ቃል ለምድር፣ ቃል ለሰማይ› የያዝኩትን በልቤ ይዤ ቡና ወደሚጠጣበት ሄድን።
ወብቋታል፤ ከሙቀቱ መናር የተነሳ ፊቷ ደመቅመቅ ብሏል። ጎኗ ተቀምጬ ለሶስተኛ ጊዜ ቡና እጠጣለሁ። ከአንገትጌዋ ወረድ ብሎ፣ ትከሻዋን አካሎ፣ ከብብቷ ሥር የሚነሳው አየር ነፋሻማ ብርጉድ ያጥነኛል፤ አንቺ ደብረ ከርቤ!
*  *  *
በአጋጣሚ ተገናኝተው፣ ወይም ከማይዘልቁት ሰው ጋር መነካካት መጨረሻው ጸጸት ቢሆንም ናፍቃኛለች። አያንቱ ምኔ ነች ግን? ድዷ፣ ጀርባዋ፣ ጥፍርዋ፣ ቁርጭምጭሚቷ ሁሉ ውዶቼ ናቸው…
…ስልክ መታሁላት…


Read 508 times