ጉዳፍና ትግስት ለመጨረሻ እጩነት ይጠበቃሉ ለተሰንበት በስፖርታዊ ጨዋነትና መዲና በአዲስ ኮከብ ሽልማቶች የመጨረሻ እጩ ሆነዋል
በ2023 የዓለም አትሌቲክስ ኮከቦች ሽልማት 4 የኢትዮጵያ አትሌቶች በሴቶች ምድብ በ3 የተለያዩ ዘርፎች በመታጨት ትኩረት ስበዋል።
በዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ላይ ባለፈው አንድ ወር በዓለም አትሌቲክስ ማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች ድምፅ ሲሰበሰብ ቆይቷል። በሴቶች ምድብ ከቀረቡ 11 እጩዎች መካከል በዓለም አትሌቲክስ ማህበር ኦፊሴላዊ የፌስ ቡክ፤ ኢንስታግራም፤ ትዊተርና ዮቲውብ ገፆች ላይ በተለይ አራት እጩዎች ከፍተኛ ድምፅ አሰባስበዋል። የኬንያዋ ፌዝ ኪፕየገን፤ የአሜሪካዋ ሻካሪ ሪቻርድሰን፤ እንዲሁም ጉዳፍ ፀጋይና ትግስት አሰፋ ናቸው። ኢትዮጵያውያኑ ከመጨረሻዎቹ ሶስት እጩዎች ተርታ ለመግባት ሰፊ እድል አላቸው።
በዓለም አትሌቲክስ ማህበር ኦፊሴላዊ ማህበራዊ ገፆች በተሰበሰበው ድምፅ ፌስቡክ ላይ የኬንያዋ ፌዝ ኪፕየገን ከ75ሺ በላይ ላይክ በመሰብሰብ ስትመራ፤ የአሜሪካዋ ሻካሪ ሪቻርድሰን ከ52ሺ በላይ ላይክ በማግኘት ትከተላለች ኢትዮጵያውያኑ ጉዳፍ ፀጋይ ከ39ሺ በላይ እንዲሁም ትግስት አሰፋ ከ33ሺ በላይ ላይኮችን አግኝተዋል። በኢንስታግራም ደግሞ ሻካሪ ከ57ሺ በላይ በመውሰድ ቀዳሚ ስትሆን ኪፕየገን ከ39ሺ በላይ ፤ ጉዳፍ ከ9500 በላይ እንዲሁም ትግስት ከ5200 በላይ ላይኮችን ሰብስበዋል። በውድድር ዘመኑ በረጅም ርቀት 5ሺ ሜትርና የማራቶን ውድድሮች ሁለት የዓለም ሪከርዶች ያስመዘገቡት የኢትዮጵያ አትሌቶች ጉዳፍ ፀጋይና ትግስት አሰፋ የኮከብነቱን ሽልማት ለሰባተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ቢያነጣጥሩም የአሸናፊነት ግምቱ ለኬንያዋ ፌዝ ኪፕየገን እያጋደለ መጥቷል።
በዓለም አትሌቲክስ በተለያዮ ዘርፎች ከታጩ አትሌቶች ኮከቦችን ለመምረጥ የሚሰበሰበው ድምፅ ሶስት ባለድርሻ አካላትን ያካትታል። የዓለም አትሌቲክስ ደጋፊዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚሰጡት ድምፅ፤ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎችና የዓለም አትሌቲክስ ምክርቤት አባላት ደግሞ በኢሜል በሚሰጡት ድምፅ ይሳተፉበታል። ከዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና ከዓለም የአትሌቲክስ ደጋፊዎች የሚሰበሰበው ድምጽ እያንዳንዳቸው 25 በመቶ ድርሻ ሲኖራቸው የመጨረሻውንውጤት50% የሚሸፍነው ዳግም የአለም አትሌቲክስ ምክርቤት አባላት የሚሰጡት ነው።
በሌላ በኩል በ2023 የዓለም አትሌቲክስ ኮከቦች ሽልማት ለተሰንበት በስፖርታዊ ጨዋነትና መዲና በአዲስ ኮከብ ሽልማቶች የመጨረሻ እጩ ሆነዋል። በዓመቱ የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት ላይ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ከመጨረሻዎቹ ሶስት እጩዎች አንዷ ሆናለች። በሐንጋሪ ቡዳፔስት ላይ በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ10ሺ የብር ሜዳልያ መጎናፀፏ ይታወሳል። በውድድሩ የመጨረሻ ሜትሮች ላይ ወድቃ የነበረችውን የሆላንድ አትሌት ሲፋን ሐሰን በማፅናናት ያሳየችው ምስጉን ተግባር ተደንቆላታል። በመጀመሪያ ከነበሩት 6 እጩዎች ከለተሰንበት ጋር የመጨረሻ እጩ ሆነው በዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና ላይ ተፎካካሪውን ሽልማት በመስጠት ያደነቀው የኬንያው ዳንኤል ኢዜንዮ እንዲሁም በ10ሺ ሜትር ውድድር ለሁሉም ተወዳዳሪዎች ማበረታቻ በመሥጠት የተከበረችው እንግሊዛዊቷ ጄሲካ ዊነር ጁድ ናቸው። አትሌት ለተሰንበት ግደይ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የኒውዮርክ ማራቶን ሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች። በዚህ ውድድር ላይ ኬንያዊቷ ሔለን ኡብሪ ያሸነፈች ሲሆን፤ አትሌት ለተሰንበት ከውድድሩ በኋላ በተሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “ሔለን ጠንካራ አትሌት ናት። ከእሷ ጋር ጥሩ ውድድር ማድረጋችን ያስደስተኛል።” በማለት ተናግራለች። በ2023 የዓለም አትሌቲክስ አዲስ ኮከብ ምርጫ ላይ ደግሞ ከመጨረሻው እጩዎች ተርታ የገባችው የ21 ዓመቷ መዲና ኢሳ ናት።
በዓለም አገር አቋራጭ በወጣቶች የብር ሜዳሊያ፤ በዓለም ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር 6ኛ እንዲሁም በዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮንሺፕ ዲፕሎማ ማግኘቷ የመጨረሻ እጩ አድርጎታል።ለሽልማቱም ባስመዘገበችው ውጤት ከፍተኛ እድል ያላት ይመሰላል። ተፎካካሪዎቹ በዓለም ሻምፒዮና በ3ሺ መሠናክል የነሐስ ሜዳልያ የወሰደችውና በ5ሺ ሜትር አራተኛ ደረጃ የነበራት የኬንያዋ ፌዝ ቺሮቲችና በዓለም ሻምፒዮና 7ኛ ደረጃና በሀ20 የአውሮፓ ሻምፒዮን የሆነችው የሰርቢያዋ አንጀሊና ቶፒክ ናቸው።