Thursday, 16 November 2023 15:07

12ኛው ዓለማቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፈረንስ በህዳር ወር ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

12ኛው ዓለማቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፈረንስ በህዳር ወር ይካሄዳል

12ኛው ዓለማቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፈረንስ “ኢትዮጵያ ለግብርና ምርት ፍላጎትዎ አስተማማኝ ምንጭ” በሚል መሪ ቃል፣ ህዳር 11 እና 12 ቀን 2016 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል እንደሚካሄድ ተገለፀ።

ኮንፈረንሱን የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር፣ ከኢፌዲሪ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንደሚያዘጋጁት ተጠቁሟል።

የኮንፈረንሱን አጠቃላይ ዝርዝር ሁኔታ አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ረፋድ ላይ የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር፣ ርብቃ ህንፃ 7ኛ ፎቅ ላይ  በሚገኘው ፅ/ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ለሁለት ቀናት በስካይላይት ሆቴል በሚካሄደው ኮንፈረንስ ላይ 400 የአገር ውስጥ ላኪዎች፣ የእርሻ ግብአትና ማሽነሪ አቅራቢዎች፣ የጉምሩክ አስተላላፊዎች፤ እንዲሁም ከ20 የተለያዩ አገራት የሚመጡ ከ100 በላይ ዓለማቀፍ ምርት ገዢ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል። ከእነዚህ አገራትም ውስጥ ቤልጂየም፣ ቻይና፣ ግብፅ፣ ህንድ፣ እስራኤል፣ ጃፓን፣ ፓኪስታን፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ሲንጋፖር፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ ዩክሬን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ኡዝቤኪስታን፣ ጣሊያን፣ ናይጀሪያና ቡርኪናፋሶ ይገኙበታል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር አመራሮች በመግለጫው ላይ እንዳመለከቱት፤ ዓለማቀፍ ገዢዎችን፣ የአገራችን የዘርፍ ምርት ላኪዎችን፣ የእርሻ ምርት ግብአት አቅራቢዎችን፣ ከፍተኛ የመንግስት ተቋማትና የተለያዩ  አገልግሎት ሰጪዎችን  በአንድ መድረክ በማገናኘት የንግድ ትስስር መፍጠር ከኮንፈረንሱ ዓላማዎች አንዱ ሲሆን፤ ተሳታፊዎች በዘርፉ ያለውን  ዓለማቀፍ የንግድ አጠቃላይ ሁኔታ (የአቅርቦት ፍላጎትና ዋጋ አዝማሚያዎች) በተመለከተ የተሟላ መረጃ እንዲያገኙ ማስቻልም ሌላው  የኮንፈረንሱ ዓላማ ነው ተብሏል።

ኮንፍረንሱን የሀገር ውስጥ ላኪዎች የንግድ ግንኙነታቸውን በላቀ ሁኔታ ለማጠናከር እንዲሁም አዳዲስ የንግድ ግንኙነቶችን ለመመስረት እንደሚጠቀሙበት የተገለፀ ሲሆን ፤ በተጨማሪም ቀጣይ  የሽያጭ ውሎችን ለመፈራረም ከፍተኛ ዕድል ይፈጥርላቸዋል ተብሏል፡፡

ሀገሪቱ ዘርፉን እንድታሳድግ በመንግሥት የታቀደውን ዕቅድ ከማሳካት አንፃርም ኮንፈረንሱ ከፍተኛ አስዋፅኦ እንደሚያበረክት የማህበሩ አመራሮች ጠቁመዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ 14 ፅሁፍ አቅራቢዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ፅሁፎች እንደሚያቀርቡም ታውቋል፡፡

የማህበሩ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የግብርና ምርቶች የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ ምርቶች መካከል  ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ አገሪቱ በ2015 በጀት ዓመት 147, 205 ቶን ቅባት እህሎች ወደ ውጭ በመላክ 253,344,754 ዶላር ገቢ አግኝታለች፡፡ በዚሁ በጀት ዓመት 377,261 ቶን የጥራጥሬ ምርቶች ወደ ውጭ ተልከው፣ 310,568,278 ዶላር ገቢ መገኘቱም ታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት በህዳር ወር 11ኛው የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፈረንስ በሸራተን አዲስ ሆቴል መካሄዱን ያስታወሰው የማህበሩ መግለጫ፣ በኮንፈረንሱ ላይ ከ435 በላይ ገዢዎች፣ ላኪዎች፣ አስመጪዎችና አገልግሎት ሰጪዎች መሳተፋቸውን እንዲሁም ከ250 በላይ ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በስኬት መጠናቀቁን አውስቷል፡፡

 

 የቴሌግራም ቻናልችንን  በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Read 1147 times