Friday, 17 November 2023 20:06

“የአክሊሉ የህይወት ጉዞ በምስል” የፊታችን እሁድ ይመረቃል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ከዶክተር ጌታቸው ተድላ  ጋር በትብብር ያዘጋጁት ጸሀፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን የሚዘክር መርሃ ግብር፣ የፊታችን  እሁድ  ከጠዋቱ  3 ሰዓት ጀምሮ  በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ይካሄዳል፡፡

የጸሀፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ቤተሰቦች  የመርሃ ግብሩ  አጋር ሲሆኑ፤ በዕለቱ ‹‹የአክሊሉ የህይወት ጉዞ በምስል››  የተሰኘ በዶክተር ጌታቸው ተድላ  የተሰናዳ መጽሐፍም ይመረቃል ተብሏል፡፡

የተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ እዝራ እጅጉ ለአዲስ አድማስ  እንደተናገረው፤ በሚመረቀው መጽሐፍ ውስጥ እጅግ አስደናቂ የሆኑ የአክሊሉ የህይወት ጉዞን የሚያሳዩ 166 ፎቶግራፎች ተካትተዋል፡፡ ዶክተር ጌታቸው  መጽሐፉን ለማዘጋጀት ሁለት አመት እንደፈጀባቸው ታውቋል፡፡

በመጽሐፉ የምረቃ ሥነ-ስርአት ላይ ዶ/ር ያእቆብ አርሳኖ፤ ዶ/ር ፍሬህይወት ስንታየሁና ሌሎች ምሁራንም የአክሊሉ ሀብተወልድን አስተዋጽኦ የሚያስረዱ ሲሆን፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተጋበዙ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችም ይታደማሉ ተብሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ከወጣትነታቸው አንስቶ ሀገራቸውን በዲፕሎማሲ ያገለገሉ ሲሆን፤ በተለይም በኢትዮጵያ የባህር በር ህጎች እንዲወጡ፤ ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር  እንድትቀላቀል ትልቅ ስራ የሰሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡  አክሊሉ ሀብተወልድ፣ 60ዎቹ የቀዳማዊ  ኃይለስላሴ ባለሥልጣናት በግፍ ሲገደሉ ህይወታቸውን ያጡ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ የአክሊሉ ሀብተወልድን አሻራ ለትውልዱ ለማስተላለፍ ባለፉት  ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ያከናወነ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ስለ አክሊሉ ሀብተወልድ በኦድዮ ሲዲ እና በዲቪዲ ታሪካቸው  በዘጋቢ ፊልም እንዲሰራጭ ማድረጉ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተጨማሪም የዋሉት ውለታ በእንግሊዝኛም ተዘግቦ እንዲቀርብ አድርጓል፡፡  ባለፉት 8 አመታት፣ ከ59 ጊዜ በላይ የአክሊሉ ሀብተወልድ አስተዋጽኦ በመገናኛ ብዙኃን እንዲዘገብም ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን  የመሪነት ሚናውን ተወጥቷል፡፡

ይህ ፕሮጀክት አሁን ላለበት ደረጃ እንዲበቃ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ልጅ  አቶ አምዴ አካለወርቅ ትልቁን የአንበሳ ድርሻ የሚወስዱ ሲሆን  በመቀጠል ደግሞ ከ10 አመት በፊት የአክሊሉን የእስር ቤት ማስታወሻ ወደ እንግሊዝኛ  የመለሱት ዶክተር ጌታቸው ተድላ  ለእኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ  መታወቅና መታወስ የበኩላቸውን ተወጥተዋል፡፡

Read 1314 times