Sunday, 10 December 2023 20:47

ገበሎ ራሱን ቢነቀንቅ ንግግር የሚያውቅ ይመስላል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በቻይናዎች ዘንድ የሚታወቅ አንድ ተረት አለ፡፡ አንድ ብልጥ ብርቱካን - አዟሪ አመቱን ሙሉ ያጠራቀመውን ብርቱካን ባወጣ ሰዓት ሰው ሁሉ እንደጉድ እየተሻማ በእጥፍ ዋጋ ይገዛዋል፡፡ ብርቱካን ለመግዛት የሚሻማውን ሰው ያስተዋለ፤ አንድ፤ የከተማውን ሀብት ዘርፈዋል በመባል የሚታሙ ትልቅ ሰው፤ ወደ ብርትኳን - አዟሪው መጥተው በርከት አድገው ይገዛሉ፡፡
ቤታቸው ገብተው ልጠው ሲበሉ ግን በእዛኞቹ ብርቱካኖች የበሰበሱና የደረቁ ሆነው ያገኙዋቸዋል፡፡ በዚህም ተናደው የበሰበሱትን ብርቱካኖች ይዘው ወደ ብርቱካን - አዟሪው ይመጡና፤
“ስማ የሚያማምሩ ብርቱካኖች ናቸው እያልክ ለአገሩ ሁሉ የሸጥካቸው ብርቱካኖች የበሰበሱ ሆነው አግኘሁዋቸው፡፡ እኮ ልበላቸው እንጂ ለአማልክት መስዋእት ላቀርባቸው አልገዛሁዋቸውም!”
ብርቱካን - አዟሪው፤
“እኔ እንግዲህ ለአመታት የኖርኩት እነዚህን አይነት ብርቱካኖች በመሸጥ ነው፡፡ ማንም ደምበኛዬ አጭበረበርከኝ ብሎኝ አያውቅም፡፡ ለመሆኑ በእኔ ላይ ስህተት ፍለጋ የተነሱት እርሶ ራስዎ ማነዎት? እስከዛሬ ሲበሉት የኖሩት ብርቱካን ዛሬ እንዴት መበስበሱ ታየዎት? ብዙ ትላልቅ የሚመስሉ ሰዎች ከተማችንን ለአደጋ እያጋለጧት ነው፡፡ የሚያስታርቁ መስለው የሚያጣሉ ሽማግሌዎች አሉ፡፡ መዝባሪዎችን የሚያወግዙ ግን ራሳቸው መዝባሪ የሆኑ የተከበሩ ሰዎች አሉ፡፡ በሚያማምሩ ፈረሶች ላይ የሚቀመጡ በየጉራንጉሩ ጥፋት ሲያደርሱ የሚገኙ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ በአጠቃላይ የእኔን ብርቱካን የሚመስሉ ብዙ ሰዎች ሞልተዋል፡፡ እነዚያ ትላልቅ ሰዎች ማጋለጥ ሲገባዎት ወደ እኔ ትናንሽ ብርቱካች መምጣትዎ ተገቢ ነው? አንድ ነገር ልብ ይበሉ፡፡ በሰው ላይ ጥቃቅን ስህተት ሲፈልጉ የራስዎን ተራራ የሚያህል በደል እንዳያጋልጡ ይጠንቀቁ! ከተማችን እስከዛሬ የኖረችው በዚህ ዘዴና ጥንቃቄ መሆኑንንም አድርሱ” አላቸው፡፡ ትልቁ ሰው ነገሩ ገብቷቸው፤ የበሰበሱትን ብርቱካኖች ይዘው ድምፃቸውን አጥፍተው ወደቤታቸው ተመለሱ፡፡   
***
የትናንሽ ሰዎች ስህተት በማሳየት የራሳቸውን አሣር የሚህል ጥፋት የሚሸፋፍኑ ትላልቅ ሰዎች ያሉባት አገር ወደ ብልፅግና ሳይሆን ወደ ከፋ ድህነት መሄዷ አሌ አይባልም፡፡ እንዲህ ያለ ሽፍጥ የተጠናወታት አገር ልማቷ ልፋት ይሆንባታል፤ “ሣር ስትፈልግ ውላ አሣር የማያጋጥማት” ትሆናለች፡፡ ለስህተታቸው ምሁራዊ መጎናፀፊያ የሚያጠልቁ፤ ውስጡን - ለቄስ መሆናቸውን በታዋቂነት ካባ በመሸፈን የሚኖሩ፤ እስከጊዜው አዎን አዎን ይላሉ እንጂ አገርን ለፍሬ፤ ህዝብን ለተደላደለ ኑሮ አያበቁም፡፡ እንቅፋትም ሲመታቸው “ፖለቲካ ድረሽ!” የሚሉና ለወደቀው ዕቃ ሁሉ ፖለቲካን ዋስ የሚያደርጉም በልቶ ለማደርና የሰላም እንቅልፍን ለሚመኝ ህዝብ ፋይዳ አይፈይዱለትም፡፡ የሚያወሩ አፎች እንጂ የሚሰሩ እጆች የላቸውምና!
“ቄስ ካናዘዘው እድሜ ያናዘዘው ይበልጣል” ይሏልና ሀገራችን ካሳለፈቻቸው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሂደቶች አያሌ ነገሮችን አይታለች፡፡ ከባለአፍ ባለጤግ፣ ከባለሰይፍ ባለእርፍ፤ እንደሚበጃት አስተውላለች፡፡ ከድንፋት ብልሃት እንደሚበጃት ተገንዝባለች፡፡ ከጡጫ ምንጫ እንደሚሻላት አውቃለች፡፡ በሸንጎ ከሚወራረፋና በዐላማ ከሚጠላለፍ የፖለቲካ መሪዎች ይልቅ፤ ከልብ የሚወቃቀሱ፣ መልካም ስራን የሚያወድሱ ግልፅ መሪዎች እንደሚያድኗት አጢናለች፡፡ ከለበጣ አስብሰባና እሰጥ -አገባ ይልቅ አጎንብሶ አፈሯን መማስና ፍሬዋ ማፈስ፤ አውሎ እንደሚያሳድራት ጠንቅቃ አውቃለች፡፡ ከሁሉም በላይ የሚናገሩለት ሳይሆን የሚናገር፣ በስሙ የሚሰራለት ሳይሆን ራሱ የሚሰራ ህዝብ እንዲሚኖራት ማስፈለጉን ከታሪክም፣ ከተግባርም ተምራለች፡፡
ያለንበት ወቅት ወሳኝ ነው- በፖለቲካዎችም በኢኮኖሚያዊም ገፁ፡፡ መፈክሮች አፍአዊ ሳይሆኑ ልባዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ የወቅቱ ጥሪዎቻችን (order of the day) በአግባቡ የታመነባቸው መሆን እዳለባቸው ሁሉ ተግባራዊ ትርጓሜያቸውም የህሊና ታማኝነትንና ልባዊ ፅናትን ይጠይቃ፡፡ ዲሞክራሲያዊነትን ከዲፕሎማሲያዊነት ጋር በብስለት ማቀናጀትን ወቅቱ ግድ ይላል፡፡ ያም ሆኖ በዲፕሎማሲያዊነት ስም ማጎብደድና እጅ - መስጠት እንደማይገባ ሁሉ፤ “ድርድር ለምኔ” ብሎ በልሂቅ በደቂቁ ላይ ዘራፍ ማለትም ፍፁም አደገኛ ነው፡፡ ብዙ በጮህን ቁጥር የተደመጥን መምሰሉ ለግብዝነት እንዳይዳርገን ሰብሰብ ብሎ  ማሰብ ተገቢ ነው፡፡

ደረጃው ይመጥንም አይመጥንም የጥያቄ  መብዛትና፤ በስብሰባ ያለመርካት ጉርምርታ ቢያይል፤ እውነትነቱን ተገንዝቦ በሆደ-ሰፊነት መቀበል የመልካም አመራር መለኪያ ነው፡፡ የሃያላን መንግስታት ጫና ብራኳችንን መስበር የለበትም፡፡ የእነርሱ መልእክተኞችና ጉዳይ አስፈፃሚ መሆም ወደራስ ህልውና መሸርሸርና ከተረጂነት ወደ ፍፁመተ ተገዢነት (absolute servitude) ወደ መሸጋገር እንዳይዘልቅ ማመዛዘን ያባት ነው! የምናወሳው ግልፅነተ ፣ ከግልብነት እንዳይምታታ ከአፋችን የማይጠፋው ተጠያቂነት ከተጠቂነት ጋር እንዳይደባለቅ መጠንቀቅ በጣም ተገቢ ነው፡፡ የተደከመበት ሁሉ ፍሬው ሳይታይ ሌላ አዲስ እቅድ በላይ በላዩ በማከል አንዱም ሳይጨበጥ ቀርቶ የወረት ልማት እንዳየሆን በቅርብ መከታተል ይገባ፡፡ አለበለዚያ “መሞኝ ጠምቃ አስቀም፣ ውሃ ትጠጣለች” እንደሚባው እዳይን መጀመራችንን እያወደስን፣ መጨረሻችንን ሳናስረግጥ እንዳንቀር ልብ ብሎ መጓዝ ያሻል፡፡ እሺ እሺ የሚሉ አያ ናቸውና ሀሳዊውን እሺታ ከእሙናዊው እሺታ መለየት ያስፈልጋ፡፡


ከቶውንም ግትርነት ለማንም አይበጅም፡፡ ጊዜንም ቦታንም ሳያስተውሉ ግትር መሆን ከግብዝነት አይለይም፡፡ ስናስተምር እየተማርንም መሆን አለበት፡፡ ሹም፤ ዜጋ የሚሆንበት ጊዜ እንዳለና ዜጋም ሹም የሚሆንበት ሰአት እንደሚኖር ማስተዋል ደግ ነው፡፡ ተለዋዋጭ ሂደቶች ተለዋዋጭ ክስተቶችን ሊያመጡ እንደሚችሉ ከልብ ማመን ለመቻቻል ችግሮችን በውይይት ለመፍታትና ፅንፈኛ-አክራሪነትን ለመግታት ያመቻል፡፡ ለምንም ነገር ግንባራችንን አናጥፍም ብሎ መፈጠም አላግባብ አቅም ይፈጃል፡፡ ብልሃትን ያመነምናል፡፡ በባዶ ሜዳ ዘራፍን ያበዛል፡፡ ትንፋሽ ይጨርሳል፡፡ የመንገኝነት ስሜት የሚጎዳንን ያህል የጀሌነት ስሜትም በሳል-እይታን (critical) ይጋርዳል፡፡ የየግል እድገትን ያቀጭጫል፡፡ የመሪነት ክህሎት (leadership quality) እንዳይኖረን ያደርጋል፡፡ እነዚህን ሁሉ በአግባቡ መርምረን በአግባቡ ለመጠን መገኘት ያሻል፡፡ በዚህኛው ዘመን አንድ እርምጃ ለመራመድ እንዳንችል የሚደርጉ ከአመት አመት የማይለወጡ፣ በትልቅነት ካባ ትንንሾችን እያወገዙ የሚኖሩ ከእድሜ እድሜ ቅንጣት የማይሻገሩ ቢቀሰቅሷቸው የማይነቁ ቢጭሩባቸው የማይነዱ እንደነበሩ ያሉ ግለሰቦች ቡድኖችና ፓርቲዎች ከቶም ለለውጥ ጋሬጣ ናቸው፡፡ ለእድገት እንቅፋት ናቸው፡፡ ለመረጃና ለእውቀትም የተዘጋ በር መሆናቸው ይታወቃ!
ያም ሆኖ በየአደባባዩ - አውቃለሁ ተምሬያለሁ፣ በቅቻለሁ፣ ስሜና ማዕረጌ የስራዬ ምስክር ነው የምናገረው ቢገባወም ባይገባውም ህዝብ ሊከተለኝ ይገባል እያ መድኩን ባገኙና፣ የቴሌቪዥን “ካሜራ - ማን” ባውዛ ባዩ ቁጥር እየተስተካከሉ ብዙ ብዙ ማውራትን የማይታክቱ መበርከታቸው ዛሬ ገሀድ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ድርጊታቸው “ገበሎ ራሱን ሲነቀንቅ ንግግ የሚያውቅ ይመስላል” ከሚለው ተረት አይዘልም፡፡
 

Read 953 times