እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው… በቃ ዘመኑ እንዲህ ሆነ ማለት ነው እንዴ… በቃ እኮ ሰው አየኝ አላየኝ ማለት መተፋፈር ምናምን ሁሉ ቀረ ማለት ነው? የእውነት እኮ እንደኔ ያለው በጋቢ ላይ ካፖርት መደረብ ‘ፋሺን’ የሚመስለው ‘ፕሪሚቲቭ’ ሰው.፣ ስምንተኛው ሺህ የደረሰ ቢመስለው አይገርምም፡፡ ኧረ እንደውም የእኛ ባስ ስለሚል ስምንተኛው መሆኑ ቀርቶ አስራ ስድስተኛው ሳይሆን አይቀርም፡፡ስሙኝማ… ስንት ነገር አምልጦናልሳ! አንዳንዴ ለአይን ያዝ ሲያደርግ በቦሌ መንገድ ‘ዎክ’ ሳጧጡፍ [ልጄ….ለእኛ ለእኛ ቦሌም ፓሪስም አንድ ናቸው] አንዳንድ ነገር አየት አደርግና ሲገርመኝ ያመሻል፡፡ እንዴ… ሰው እንዴት እንዴት ነው የሚያደርገው!
አንድ ወዳጄ አንድ ቅዳሜ ምሽት ቦሌ አካባቢን ሲያስስ አምሽቶ ኖሮ በማግስቱ ምን አለኝ መሰላችሁ? “የቆመ መኪና ሲመጣ ብቻ እየለየ የሚወዘውዝ መሬት መንቀጥቀጥ አለ እንዴ?” እኔ… በቃ ጭጭ አልኳ፡፡ ተናግሮ ከአናጋሪ ይሰውራችሁ፡፡
እና… ይኸውላችሁ ግርም የሚል ዘመን ነው፤ድሮ ድሮ “ሎሚ ብወረውር…” ተብሎ ነበር አሉ፤ ነገርዬው የሚያልቀው፡፡ የዘንድሮ ሰው… ልጄ ሎሚ የሚያክል ድንጋይ ይወረውር እንደሁ እንጂ … ብቻ አለመያዝ ነው፡፡ አሀ…‘ፋይል ለመክፈት’ ስንት ጣጣ አለ፡፡
አለላችሁ …. አንዳንዱ ሲያምጥ ከርሞ አንድ ቡና በወተት በትልቅ ብርጭቆና ዳበስ ዳበስ አርጎ ወፈር ያለ የልጅ ምሳ ሊሆን የሚል ቦምቦሊኖ ይጋብዛል፡፡ [ነገርዬዋ ማመልከቻ ቢጤ መሆኗ ነው] ታዲያ ልክ ሻኛው የሚገላበጥ የሀረር ሰንጋ የጣለላት ይመስል (ለነገሩ ዘንድሮ አይሞከረም!) “እንዴት ነው ታዲያ… ይመችሻል!” ይልላችኋል፡፡ ኧረ!... በቦምቦሊኖ ተመቸ! የእንትን ሰፈር ልጆች ቢሆኑ ኖሮ የዚህ ዓይነቱን ስልቻ ሙሉ ቦምቦሊኖ አሸክመው “በቀረበህ መንገድ ወደ ኬንያ…ወይ ኡጋዳ ተሰደድ…” ነበር የሚሉት፡፡
በስዋሂሊኛ ‘ይመችሻል!’ ምን እንደሆነ ስለማያውቅ አርፎ ይቀመት ነበር፡፡ ደግሞ ሌላው አለላችሁ… ተንከርፍፈህ ኑር ተብሎ ርግማን የተጣለበት የሚመስል፡፡ ጧት ይጠብቅና ከኮልፌ ኮከብ ጽባህ ቢሆን እኳን ይሸኛል፡፡ የትምህርት ሰዓት ሲያቅ ደግሞ
ቤት ይመልሳል፡፡ ምን አለፋችሁ እግሩ ስር ጎማ አልተገጠመም እንጂ ሶስት ቁጥር ታርጋ ካቻማሊ በሉት፡፡
አንድ ወዳጄ “እንዲህ ዓይነቱን…. እስኩል ባስ በለው” ነው ያለኝ፡፡ስሙኝማ ደግሞ አለላችሁ… ግርም የሚል ፍጡር፡፡ ፊልም የለ ትያትር የለ ሙዚቃ
የለ… የፈረደባትን ከጎኑ አድርጎ ድፍን አዲስ አበባን በእግር ሲያካልል ይውልላችኋል፡፡ በቃ “በእግር መጓዝ ጤንነት ነው…” እያለ ፀሀይ የለ፣ ቁር የለ ብቻውን የከተማውን ማስተር ፕላን ሲከልል የሚውል ነው የሚመስለው፡፡ የምር ግን… አንዳንዴ በቃ ነጩ ባንዲራ ቀረ እንጂ የሰላምም ተጓዥ ይመስላል፡፡ ‘ዎክ’ ሌላ ‘መንክራተት’ ሌላ፡፡እኔ የምለው … ነገርዬው ሁሉ እንደ ድሮ የተመለሰባቸው ቦታዎች አሉ እንዴ!
የመሀል አራዳ ውስጥ አዋቂዎች ሲነግሩኝ እዚያ አካባቢ “ትዝ አለኝ የጥንቱ” ዓይነት ጨዋታ አለ አለ፡፡ የት መሰላችሁ? አውቶብስ ፌርማታ፡፡ አንዳንዱ ቀኑን ሙሉ አውቶብስ ፌርማታ አይጠፋም አሉ፡፡ ምን አለፋችሁ… በቃ ሽፍቱ ያደረሰ ትኬት ቆራጭ ይመስል አላፊ አግዳሚውን ሲያይ ይውላል፡፡ እኔ’ኮ ሲኒማ ኢትዮጵያ አጠገበ ያለ ሁሉ ሰው አውቶብስ ጠባቂ ይመስለኝ ነበር፡፡ ለካስ ሌላም ጨዋታ አለ፡፡
ስሙኝማ የአንዳንዱ አራድነት ግርም የሚል ነው፡፡ [አንድ ጊዜ በዚህ ቢለኝ በዚያ የሆነ… ጥሬ ነገር የሆንኩበት ወዳጄ “አንተ ሰውዬ… አራድነትህን ሸጠህ በላኸው እንዴ!” ብሎኛል፡፡ እኔ የምለው ‘አራድነት’ ለ‘ፕራይቬታይዜሽን’ የሚቀርበው መቼ ነው? አንተ እንትና… ላንተ አራድነት የሚወጣው ጨረታ አይደለም ሶስቴ አሥራ ሶስቴ ነበር የሚሰረዘው! የእውነት ላንተ የሆነ ኤን.ጂ.ኦ በጣሳ የአራድነት እርዳታ ቢሰፍርልህ ይሻላል፡፡]እናላችሁ አንዳንዱ ኮተቤ አካባቢ ቆሞ “ስድስት ቁጥር አለፈች እንዴ?” ይላል፡፡ [ኧረ! ብልጥ ተሁኖ ልብ ውልቅ! ‘አይ የእንትን ሊዎንቺና ነች ያመለጠችህ’ ማለት ነበር፡፡]ስሙኝማ… ሴቶች ሰብሰብ ያሉበት አካባቢ ሲደርሱ የሚሸልሉ ወንዶች አይጥሟችሁም? በቃ… እኮ አሪፍ አክተሮች ናቸው፡፡ አረማመድ እግር ስር ስፕሪንግ የተገጠመ ነው የሚመስለው፡፡ አንዳንዱ ግንባሩን ከስክሶ እንዴት እንደሚኮሳተር!...
ብቻ ማን እንደሚነግራቸው እንጃ አንዳንዶች ሴቶች ኮስታራ ወንድ ይመቻቸዋል የሚል ፈሊጥ አላቸው፡፡ [ይኸው እኛ ስንት ዘመን ስንኮሳተር እንኳን ልንመቻቸው… መንገድ ተሻግረው ነው የሚያልፉት፡፡ እኔ እንደውም አንዳንዴ ኮስተር ብዬ ሸለልኩ ስል ለልጆቻቸው እየጠቆሙ “አያ ጅቦ መጣ…” ሳይሏቸው አይቀሩም፡፡]ስሙኝማ አንድ ነገሩ ሁሉ አልሆነ ያለው ወንደላጤም አለ አሉ፡፡ ምን አለ መሰላችሁ?
“ገንዘባችሁ ሁሉ አለቀ በሻይ ትዳሩን ሳናየው ዓለምን ሳናይ!”ታዲያ እኛ ከለከልን! አይ ሸጋው ወንደላጤ… አንተ ታዲያ ዘላለምክን የሰው ሆድ በስሙኒ ሻይ የምታነፍረው…የሻይ ቅጠል እርሻ የለህ፡፡ አንተ የዘጋኸውን እንጀራህን የምን “አላሳዝንም ወይ…” ነው፡፡ ገና በጠዋቱ በሻይ ላይ ሙጭጭ ያልከው በኋላ እኮ “ዋናው ነገር ፍቅሩ ነው…” እያልክ ቦምቦሊኖ አብረን እንግመጥ ከማለት አትመለስም!
ልጄ ድሮ ድሮ… ስንት ጣጣ ነበር፡፡ አንዷን እሺ ከማሰኘት የዓለም ባንክ ብድር ማስፈቀድ ይቀል ነበር - የምር፡፡ ያኔ እኮ… የወንዱም ሽለላ አሪፍ ነበር፡፡ ፀጉር ኖራቸውም ልኖራቸውም መሀል ላይ መከፈሏ አይቀርም፡፡ ካስፈለገም የሆነ ወፈር ያለ የእንግሊዝኛ ልብ ወለድ ይያዛል፡፡ አሀ… እንግሊዘኛ የሚያውቅ ‘አለመታወቂያ እንዲያልፍ’ ይፈቀድለታላ፡፡ ስሙኝማ… አንድ ወዳጄ መሀል ላይ ፀጉራቸውን የሚከፍሉ ሰዎችን ምን ትላቸው መሰላችሁ? “ሹል ቴክስ፡፡”ደግሞ አለላችሁ ብልጥነት ሞልቶ ይተርፈውና በብልጢኛ “ስምሽ መቅደላዊት
አይደለም?” ሲል ይጠይቃል፡፡ አጅሪትም “አይ አይደለም ፎዚያ ነው” ትለዋች፡፡ እሱ ምን ይላል መሰላችሁ? “አይ… ብዙም አልራቅሁም፡፡” ከዛ በብልጢኛ አሳሳቅ ይስቅና “ያው … መቼም ሞትና ትውውቅ አንድ ቀን ነው…” ይልና ብቻ ምን ለፋችሁበሴኮንድ ዘጠኝ ቃላት ይናገራል፡፡እኔ የምለው… አንዳንዶቻችሁ “እምቢ” ስትባሉ ድርቅና ነው እንዴ! በቃ ችክክ የሚል አለላችሁ፡፡ ነጋ ጠባ ከርቀት ይከተላታል፡፡ ምን አለፋችሁ ክላሺንኮቭ ቀረች እንጂ አንጋች ነው የሚመስለው፡፡በዛ ሰሞን እኔና ጓደኛዬ አንድ ሚኒ ባስ ውስጥ ሆነን… በቃ
“ፍቅር የተራበ” ዓይነት ድራማ ስናይ ነበር፡፡ አይተዋወቁም፡፡ ወንድዬው… ታዲያ በቃ የህይወት ታሪኩን ይዘረዝርላታል፡፡
እሷ ሆዬ… በተመስጦ ሳይሆን በመገረም ነበር የምታየው፡፡ አለ አይደለም… በሆዷ “ሰው እንዲህ ሞዛዛ ሆኖ ይፈጠራል?” የምትል ነው የሚመስለው፡፡እናላች…ኮሚክ ዘመን ሆኗል፡፡ አንዳንዱ የማያውቃትን “ሹራቡ ያምርብሽ…”
ይላል፡፡ “ፒንክ ቀለም እወዳለሁ፡፡” ኧረ! ታዲያ ጨርቅ ተራ አትሄድም! አይ ሽጋው ወንደላጤ… ገንዘቤ ሁሉ በሻይ አለቀ አለ! እንትን ሰፈር ብትሄድ ምን የመሰለ በሶ አለ መሰለህ፡፡ አሀ… የላጥካትን ጨጓራ ራስህ ጠግናታ! ስሙኝማ… እስቲ ቦሌ ሄጄ አስራ ዘጠኝ ቁጥርን ልጠብቅ፡፡ ማን ያውቃል…
‘ፒንክ’ ሹራብ ይመጣ ይሆናል!