Sunday, 17 December 2023 20:23

ታጥቆ እንዳይጠብቅ ወይኔ ወይኔ እያለ ይኖራል!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አንበሳና ሦስት አሽከሮቹ አነር፣ ተኩላና ቁራ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ አንድ ቀን ምግብ ፍለጋ በመዘዋወር ላይ ሳሉ አንድ ግመል አገኙ፡፡ ግመል ከዚያ ቀደም አይተው አያውቁ ስለነበር፣ ይሄ ምን ይሆን? ሲሉ እርስ በርስ ተጠያየቁ፡፡ ግር ስላላቸው አነር ጠጋ ብሎ ጠየቀው፡፡ ግመል መሆኑን ነገራቸው፡፡ ነጋዴ መንገደኞች በዚህ ጫካ በኩል ይዘውት መጥተው በመካከል እንደተጠፋፉም አስረዳቸው፡፡ አነር፣ ተኩላና ቁራ ባዩትና በሰሙት እየተገረሙ ሄደው ለጌታ አንበሳ ነገሩት፡፡ አንበሳም “ይምጣና ከእኛ ጋር ይኑር፡፡ እኔ እጠብቀዋለሁ፡፡ እንከባከበዋለሁ፡፡ ሂዱና ወደዚሁ አምጡት” ሲል ትዕዛዝ - አከል ሀሳብ አቀረበ፡፡
አሽከሮቹ ሄደው ለግመል ነገሩት፡፡ ግመል በጣም ተደሰተ፡፡ አብሯቸው ለመሄድ ዝግጁ መሆኑንንም ገለጠላቸው፡፡ አሽከሮቹ ግን በሁኔታው አልተደሰቱም፡፡ ምነው ቢሉ… ሌላ ተመጋቢ አፍ ተጨመረ ማለት ነው፡፡ ግመሉ የመጣ ሰሞን ጌታ አንበሳ ድንገተኛ ፍልሚያ ከዝሆን ጋር ገጠመ፡፡ በዚህም ፍልሚያ ክፉኛ ቆሰለ፡፡ ስለዚህም ቁስሉ እስኪሽር ከዋሻ መዋል ጀመረ፡፡ አሽከሮቹም ከየትም ከየትም ብለው እሱን መመገብ ግዴታቸው ሆነ፡፡
አሳዛኙ ነገር ግን የጫካው ታዳኝ ሁሉ ቀስ በቀስ ተመናምኖ እየተሟጠጠ ሄደ፡፡ ውሎ አድሮም ከናካቴው የሚላስ የሚቀመስ ጠፋና አረፈው፡፡ ጌታ አንበሳ “እኔ ሄጄ የሚበላ ልፈልግ እንጂ እንዲህ እየተራብኩ ቁስሌ እንዴት ይድናል?” አለ። አሽከሮቹ “በጭራሽ
አይሆንም! አንተ አርፈህ መተኛት አለብህ፡፡” አሉት፡፡
አንበሳውም፤ “በሉ እንግዲያው ዘወር ዘወር ብላችሁ የሚበላ አምጡልኝ - ወደሌላም ሰፈር ሄዳችሁ ቢሆን ሞክሩ!” አላቸው፡፡
“ኧረ አንተን ብንጠብቅና ብናስታምም ይሻላል ጌታ አንበሳ”
“መጀመሪያ ምግብ ፈልጉ!”
አሽከሮቹ ምግብ ፍለጋ ወጡ፡፡ በየጫካው ሁሉ ዞሩ፡፡ ግን ምንም አጡ፡፡ ተኩላው፤ “እዚህ ምንም የለም እባካችሁ፡፡ ከንቱ ልፋት ነው!” አለ፡፡ ቁራው ቀበል አድርጎ “እውነት ነው እዚህ ምንም ነገር የለም፡፡ ቤት ግን ምን የመሰለ ግመል አለን‘ኮ” አለ፡፡ “እሱንማ እንዳንቋደስ ጌታ አንበሳ ግመሉ እንዳይነካ፤ እኔ አጠብቅልሃለሁ ብዬ ነው ያመጣችሁት ቃል - አባይ መሆን የለብንም ብሎናል‘ኮ፡፡ ስለዚህ ግመሉ በመበላቱ አይስማማም”
“ለማንኛውም ወደቤት እንሂድና ማታችንን እንንገረው፡፡ እኔ ግን ቆይ ታያላችሁ አንድ ዘዴ እዘይዳለሁ!” አለ አነር፡፡ ተያይዘው ወደ ቤት ተመለሱና የሆነውን ሁሉ ለጌታ አንበሳ ነገሩት፡፡ አቶ አንበሳ እጅግ አድርጎ አዘነ፡፡ “ከእንግዲህ እንዴት አድርጌ ቁስሌን ላድነው ነው!” ሲል አማረረ፡፡ አነር ብድግ ብሎ “አንተ ጌታችን በረሃብ ስትሞት ዝም ብዬ አላይም፤ እኔ አድንሃለሁ፡፡” አለ፡፡
“እንዴት?” አለ ጌታ አንበሳ “እኔን ብላኝ” ሲል አነር ራሱን ለጌታው ሊሰዋ አቀረበ፡፡
“በጭራሽ አላደርገውም፡፡ ባለፉት ዓመታት ሁሉ በታማኝነት ያገለገልኩኝ ታዛዤን ንክች አላደርግም!”፡፡
ተኩላ ድንገት ብድግ ብሎ፤“ጌታዬ፤ ከተራብክ በቃ እኔን ብላኝ” ሲል ጥያቄ አቀረበ፡፡ አንበሳም “አንተንማ ልበላ አልችልም፡፡ ለብዙ ዓመታ በቅንነት ስታገለግለኝ የቆየህ ወዳጄ’ኮ ነህ!” አለ፡፡
ቁራም ተራውን ተነስቶ “ጌታ አንበሳ እኔን ብትበላኝ ነው የሚሻለው”አንበሳ ትንሽ ኮስተር እንደማለት ብሎ “ወዳጆቼ ጅል አትሁኑ እንጂ፡፡ አንተንም ቁራን ልበላህ አልችልም፡፡ የብዙ ጊዜ ታማኝ አገልጋዬ ነህ፡፡ በዚያ ላይ እፍኝ የማትሞላ አናሳ ፍጥረት ነህ” ብሎ ተቆጣ፡፡
ግመሉ ያደረጉትን ውይይት ሁሉ ሲያዳምጥ ቆይቶ “እንግዲህ ጌታ አንበሳ ማንኛችንንም የመብላት ፍላጎት የለውም ማለት ነው፡፡” አለ ለራሱ፡፡ “ስለዚህም እኔም እንደሌሎቹ ‘እኔን ብትበላኝስ?’ ብዬ ብጠይቀው ተገቢ ይሆናል፡፡ “ጌታ አንበሳ ሆይ ምናልባት እኔን
ብትበላኝ ሳይሻል ይቀራል?” ሲል ጠየቀ ግመል፡፡“አንተን?” አለ አንበሳ በመደነቅ፡፡


“አዎ እኔን !” አለ አቶ ግመል፡፡“ግመል የጠየቀው ትክክለኛ ጥያቄ ነው!” አለ አነር፡፡“በጣም እንጂ!” አለ ተኩላ፡፡“ከዚህ የበለጠ ልባዊና ዕውነተኛ ጥያቄ ከየትም ሲገኝ አይችልም! ከሆነ እንዲያውም አሁኑኑ መፈፀም ነው ያለበት” አለ ቁራ፡፡ ውሳኔው ፀደቀ፡፡ አንበሳው ግመሉን እንዴት እንደሚበላው ለማሰብ ቀርቶ ዐይኑን እንኳን ሳይጨፍን ሶስቱ አገልጋዮቹ ግመሉን ዘነጣጥለው መሬት ላይ ዘረጉት፡፡ የልባቸው ሞላ፡፡ግን የአንበሳውን ድርሻ ለመውሰድ ያደፈጠ ልቡን ብቻ አምኖ የሚጓዘው በርካታው ክፍል ነው፡፡ የኢትዮጵያን ችግር እንፈታለን ለህዝቡም ፍትህ ርትፅ እናመጣለታለን፣ ዲሞክራሲን እንናጎናጽፈዋለን፣ ባረንጓዴው ዘመቻ አረንጓዴ ተፈጥሮን እናነጥፋለን፣ ፈጣን ልማት እናመጣለን የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫትነቷን እናረጋግጣለን፣ ከመከላከል ወደማጥቃት ተሸጋግረናል፣ (ማርሽ ያለውና ማርሽ የሌለው) መልካም አስተዳደር ከልሂቅ እስከደቂቅ እናዳርሳለን፣ አንድም ጥይት የማይተኮስባት ሰላማዊ አገር ይኖረናል፣ በቀን ሶስቴ በልተን የምናድርባት ኢትዮጵያ ትሆናለች ወዘተ ቃል - ይገባል፡፡ ማተብ ይታሰራል! በስራ ትርጓሜው የለም! ባለፈው ዘመን እንደተባለው፡፡ “የምንለውን ብለናል የምናደርገውን
እንጀምር!” ማለት ይከተላል - ቃል ይገባል ቃል ይሻራል፡፡ አደራ ያስቀምጧል መልሰው አደራ ይበሏል! የችግር ቀን አንዱ “ግመል” እዳውን በራሱ ከፍሎ ሌሎች ረሀባቸውን ያስታግሳሉ፡፡ ችግራችንን ፈትተናል ብለው ያምናሉ፡፡ ጉዳዩ ግን ዞሮ ዞሮ “በወተት አምሮት የታመመ፣ ጮጮ ሙሉ ውሃ ግጥም አደረገ!” እንደተባለው ነው፡፡ “በሌላ ወገን ደስ አይበላችሁ ምጣዶች፣ ልንጋግረው ያሰብነውን አገነፋነው!” በሚል ዓይነት ፍልሚያ አንድም ወንዝ መሻገር አይቻልም፡፡ ከቶም የእያሪኮ ጩኸት ነው፡፡ አንድን ሀገራዊ ጉዳይ እነ እገሌን ድል ለመምታት፣ እነ እገሌን “ኩም” ለማድረግ፣ እነ እገሌን “አፍ - ለማስያዝ”፣ እነ እገሌን ገና ሳያቆጠቁጡ ለማስቀረት፣ በሚል ቀመር ከተጓዝን ጊዜያዊ ደስታን ብቻ እንደሚሰጠው የወይን ትፍስህት አላፊ ጠፊ የሞቅታ ጉዞ ይሆናል፡፡

ከቶውንም በተደጋጋሚ የሚታየውን የቅርብ - ራዕይ ችግር (Myopia) በሩቅ አሳቢ ዕይታ ለመተካት ስራዬ ተብሎ ካልተደከመ ብዙ ፀፀተኛና፣ ብዙ አስተዛዛኝ ሰዎችን በዙሪያ በመሰብሰብ ከንፈርን ከመምጠጥ ያለፈ ትርጉም ያለው ለውጥ አይመጣም፡፡ “እህህ እያሉ ምንቸት ሙሉ ጎመን ይጨርሳሉ” ነውና በታማኝነት በቀረቤታ፣ በ”አብሮኝ ደክሞ የት ላድርሰው” ዓይነት አንድም ሙያውን አጥቶ አንድም ቦታውን ሰቶ ዓይነት የቢሮክራሲ መዋቅር ቅንበባ ለሰው ኃይልም ፍጆታ ለመልካም አስተዳደርም ቀረፃ አመቺ ጥርጊያን አያመጣም፡፡ ከአንድ መስሪያ ቤት ወደሌላው ፕወዛም፣ ጥረዛ፣ ከፌቴ ራቅ ይበልልኝ ለማለት ያህል ካልሆነ “ከመጥበሻው ወደ እሳቴ” ከመሆን አያልፍም፡፡ ከነ ሥነ አዕምሮአዊ አሉተኝነት ከእነብሶት - ምሬቱ ፣ ከእነዳተኝነቱ፣ ከእነነገር ሰሪነቱ፣ ከነመበደል - መገፋቱ የውስጥ አፍራሽ ግብረ - ሃይል የመፍጠርን ያህል ይሆናል፡፡ ጉልቻ መቀያየሩ ቀረና ወጡን መቀያየር እንደማለት ያለ ሀገራዊ ምፀት ወይም ክፍለ - ከተማዊ ስላቅ እንዳይሆን መጠንቀቅ ነበር። ሰሞኑን “ዓለም ባንክን ያመነ ብር ዘገባ” የሚለው
መፈክር እጄ አመድ አፋሽ ነው። የሚሉ ሰራተኞችን ያስዘገነ እንዳይሆን መጠንቀቅ በተገባ ነበር፡፡ የሀገራችን ሰው ተዘጋጅቶ መጠበቅን በየዘመኑ እየዘነጋው ዋናና ትርፉን እየቀላቀለ ለኪሳራ ሲዳረግ በርካታ የለውጥ ወቅቶችን ተሻግሯል፡፡ ካልታዘልኩ አላምንም በሚል
የተጠራጣሪነት መንፈስ ተሸብቦ መመካከር ሲሻው ሳይመካከር፣ መደራጀት ሲያስፈልገው ሳይደራጅ፣ መጠየቅና መሞገት ሲገባው እጁን አጣጥፎ፣ “ወቸ ጉድን”ና “ጉድ-አንድ ሰሞን ነው”ን እያዜመ ኩሬንም ባህርንም እኩል እየዋኘ፣ እየበረደውም እየለበለበውም፤ እኔ
ቀጭኑ አዳሜ ቢተራመስ አይሞቀኝ አይበርደኝ” እያለ በመጨረሻ ለውጡ እንደደራሽ - ውሃ ሲወስደው እዬዬን ባህል ሲያደርገው ይኸው አራት ለውጥ ተቆጠረ፡፡ በእንጉርጉሮው ጠባይ አንፃር የድርጅቱም የግለሰቡም፣ የፓርቲውም ማህበሩም የዜማ ቅኝቱ አንድ መሆኑ
ወይ የያሬድ አገር ያሰኛል፡፡ “ታጥቆ እንዳይጠብቅ ወይኔ ወይኔ እያለ ይኖራል” የሚለው ተረትም የዚሁ ቅኝት አንድ ምት ነው!

Read 858 times