Saturday, 20 August 2011 10:13

መልዕክቱን ትቶ መልዕክተኛውን!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ ከቢቢሲ የቀረበበትን ስሞታ የተሳሳተ የማይረባና ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ያዘለ በማለት በተለመደው ቁጣው አስተባብሏል፡፡ወትሮውንም ከአለም አቀፉ የወሬ ምንጭ ተቋማት አፍ ተለይቶ የማያውቀው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የጦርነትና የስደት ስንክሳር ገና እንኳ ተወርቶ ሳያበቃ
የረሀብና የዕልቂት ዜና ደግሞ የመላው አለም የመነጋገሪያ አጀንዳ ሊሆን በቅቷል፡፡ እንደየአለም የምግብ ድርጅት ግምት 11.3 ሚሊዮን የሚሆኑ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ህዝቦች ከዛሬ 65 አመት ወዲህ ታይቶ ባልታወቀ ከፍተኛ ድርቅ ተጠቅተውና የሚላስ የሚቀመስ ነገር አጥተው፣ ጠኔ ከዛሬ ነገ ሳይሆን ከአሁን አሁን ፈጀዋችሁ እያላቸው በሞትና በህይወት መካከል ይገኛሉ፡፡

አስከፊነቱ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም በተባለለት በዚህ እጅግ አስከፊ ረሀብ፣ የታላላቅ ዓለምአቀፍ የዜና ምንጮችን ትኩረት በአሁኑ ሰዓት ሶማሊያ ከኢትዮጵያ የተረከበችው ትመስላለች፡፡ የሁሉም ሚዲያዎች ዓይንና ጆሮ በሶማሊያ ረሀብተኞችና የረሀብ ስደተኞች ላይ ሆነዋል፡፡
የአለም የዜና አውታሮች በሶማሊያ ረሀብና ረሀብተኞች ላይ ትኩረት መስጠት የሀገራችንን የራዲዮና የቴሌቪዥን ማሰራጫዎች ትኩረትም በእጅጉ የማረከ ይመስላል፡፡ በየጊዜው የሚቀርበው የወቅቱ የችጋርና የረሀብ ዜና ሶማሊያ ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑ የግብርና ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ከረጅም ማቅማማት በኋላ የገለልን የአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የረሀብ ተጎጂዎች፣ በሆነ ተዓምር ከገጠማቸው ችግር የተላቀቁና ኢትዮጵያን ችግሩ ያልነካት ወይም መጣሁብሽ እያለ ሲያስፈራራት ቆይቶ ድንገት እሷን ትቶ በጀርባዋ ወደ ሶማሊያ ጓዙን ጠቅልሎ ገባ እንዴ እንድንል አድርጐናል፡፡
ባለፈው ሰሞን በቢቢሲ ቴሌቪዥን ለአለም ህዝብ አይንና ጆሮ የቀረበው ፕሮግራም ግን ይህን የሀገራችን ሚዲያዎችና መንግስት የሶማሊያ ችግር ብቻ አስመስለው ለማቅረብ የሞከሩት ጉዳይ ላይ ድንገተኛ አቧራ አስነስቷል፡፡
የቢቢሲ የዜና ድርጅት News Night በተባለው ፕሮግራሙ፤ በሀገራችን ያለውን የድርቁን ሁኔታና የእርዳታ አቅርቦቱን በተመለከተ ..ወደ ኢትዮጵያ ቱሪስት መስለው በገቡ  ጋዜጠኞች የተሠናዳ መርማሪ ዘገባ ነው.. በሚል ባለፈው ሰሞን ለአለም አይንና ጆሮ አብቅቷል፡፡ በዚህ ዘገባውም መንግስት ከለጋሽ ሀገራትና ድርጅቶች በተለይም ከእንግሊዝ መንግስትና ከአውሮፓ ህብረት በየአመቱ የሚቀበለውን በቢሊዮን ዶላር የሚገመት የእርዳታ እህልና ገንዘብ በዋናነት ለራሱ ድብቅና ግልጽ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያነት በመጠቀም፣ ተቃዋሚዎቹንና የተቃዋሚዎቹን ደጋፊዎች ይቀጣበታል የሚል ስሞታ አቅርቧል - የዚህ ችግር ሠለባ ናቸው የተባሉ ሰዎችን እማኝ በማድረግ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ ከቢቢሲ የቀረበበትን ስሞታ የተሳሳተ የማይረባና ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ያዘለ በማለት በተለመደው ቁጣው አስተባብሏል፡፡ መንግስት ያለ አንዳች ገደብና ከልካይ በሚቆጣጠረው የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን፣ ለቢቢሲ በሰጡት የእማኝነት ቃል የተነሳ ክፉኛ ሲብጠለጠሉ የከረሙት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ባወጡት ይፋ መግለጫ፤ የመንግስትን ማስበተባበያ ሀሰትና ረብየለሽ በማለት በሀገሪቱ ያለውን የረሃብ ሁኔታ ለማወቅ የግድ ድርቁ ወደተከሰተባቸው አካባቢዎች መሄድ ሳያስፈልግ፣ እዚህ በዋና ከተማይቱ በአዲስ አበባ ያለውን የእለት ጉርስ ያጣ የችግረኛ ብዛት በማየት ብቻ በቀላሉ መረዳት ይቻላል ሲሉ ለማስተባበያው ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡
የቢቢሲ ዘገባና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ይፋ እማኝነት ክፉኛ የከነከነው መንግስት፤ ንዴቱንና ቁጣውን ለማብረድ ይመስላል ነገርየውን አሁንም አለቀቀውም፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የቀረበበትን ስሞታ በማጣጣልና ስሞታ አቅራቢዎቹንና ተባባሪዎቻቸውን ሁሉ በማውገዝና በመራገም ላይ ይገኛል፡፡
እንዲህ ያለው የመንግስት እልህ ዋነኛ ምንጩ ለዘመናት ክፉኛ የተጠናወተው የአሞግሱኝና የግነን በሉኝ ክፉ አባዜው ነው፡፡ ለተከታታይ አመታት ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገብኩ፤ የግብርና ምርቱንም በየአመቱ በሠላሳና አርባ በመቶ እያሳደግሁ፣ በመላው አፍሪካ አጃኢብ ያሰኘና መላ አለሙን ጉድ ባስባለ ፍጥነት በእድገት ጐዳና እየገሰገስኩ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በቀን ሶስቴ ሊመገብ ይቅርና ለአንድ ጊዜም ቢሆን ሆዱን ሳይሆን አይኑን እንኳ የሚያጠግብ ዳቦ በልቶ የማያውቀውን ምስኪን አርሶ አደር በከፍተኛ ቁጥርና ፍጥነት የባለ ብዙ ሚሊዮን ብር ባለቤትነት እንዲሸጋገር አድርጌአለሁ፡፡ ስለዚህ ስለበለስ ግነን በሉኝ፤ በሙገሳ ጃሎ እያላችሁ ሸልሉልኝ የሚል ክፉ አመል ለተጠናወተው መንግስታችን በእርግጥም የቢቢሲ ዘገባ  ቅስም የሚሠብርና ጉንጭ የሚያቀላ የሀፍረት ስሜት በፈጥር አይገርምም፡፡ ለምን ቢሉ ሲለን የነበረውና እውነታው አራምባና ቆቦ ሆኗላ፡፡  አሁን ከቢቢሲና ለቢቢሲ የእማኝነት ቃላቸውን ከሠጡት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጋር የተፈጠረው አተካሮ መልእክቱን ትቶ መልእክተኛውን ማጥቃት እየመሰለ የመጣ ይመስላል፡፡ ችግሩ መኖሩ ታውቆ በይፋ ከተገለፀ በኋላ በተከሰተው ችግር የተነሳ የችግረኛ ዜጐቻችን ህይወት እንዳይጠፋ ቀበቶንና መቀነትን ጠበቅ አድርጐ፣ በሙሉ ልብና ጉልበት መረባረብ እንጂ ገመናችንን ፀሐይ መታው ለሚለው አጓጉል የደሀ ኩራት መጨነቅና መጠበብ ጊዜ ከማባከን በቀር ምንም ፋይዳ እንደሌለው የታወቀ ነው፡፡በሚሊዮን  የሚቆጠሩ ህዝቦችን ለችግር የሚዳርግ የተለያየ ሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት፣ መንግስታት የሚሞገሱትም ሆነ የሚወቀሱት አደጋው ከመድረሱ በፊት ተከላክሎ ለማስቀረት አሊያም ከደረሰ በኋላ የአደጋውን ሰለባዎች ከከፋ ጉዳት ለመታደግ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ መጠን ልክ ነው፡፡ ስራውን በሚገባ የሠራ የሚሞገሰውን ያህል ሀላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ያልቻለው ደግሞ የእርዳታ እጁን አጥብቀው በሚሹትና በሚጠባበቁት ዘንድ መወቀሱና መረገሙ በአለማችን ታሪክ ዘንድ ትናንት የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ነገም የሚኖር ግልጽ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን የእኛ መንግስት ምንጊዜም ከሙገሳና ከምስጋና፣ ከዝማሬና ሽብሸባ በቀር ለምን ትችትና ወቀሳን ሰምቼ በሚል መፈጠሙ አንድ ነገር እንድንጠረጥር አስገድዶናል፡፡ ምናልባት መንግስታችን የተቋቋመውና የሚመራው በመላእክት ስብስብ ይሆን እንዴ?
በፖለቲካ አለመግባባት የተነሳ በተፈጠረ ችግር ዜጐች በታጣቂዎች ሲቀጠፉ በፓርላማ የምንሰማው፣ ዳግመኛ የዜጐች ህይወት እንዳይቀጠፍ ምን ይደረግ የሚል ውይይት ሳይሆን ሞቱ የተባሉት ዜጐች ቁጥር አንሷል፤ የለም በዝቷል የሚል አሳዛኝ ንትርክን ነው፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በየጊዜው የድርቅ አደጋ ተከሰተ ሲባል አደጋው ዳግመኛ እንዳይከሰት ወይም ዜጐች ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ምን ዘዴ እንቀይስ የሚል ውይይት ሳይሆን ለረሃብ የተጋለጠው ህዝብ ቁጥር ይሄን ያህል ነው አይደለም የሚል ሃፍረተቢስ ሙግት ብቻ ነው፡፡ በክፉ ደዌ ተይዞ ለመሞት ለሚያጣጥር ሰው የሚበጀው ከሚያሰቃየው ደዌ የሚፈውሰው የህክምና እርዳታ እንጂ ከሞተ በኋላ የሚቀበርበት ሳጥንና መቃብሩ ላይ የሚቀመጥለት የአበባ ጉንጉን እንዳልሆነ መናገር የአንባቢን የማስተዋልና የመረዳት ችሎታ በእጅጉ አሳንሶ እንደመገመት Yö«‰L””ሆኖም ግን አሁን እኛም ያለንበት ሁኔታ ከዚህ ብዙ የተለየ አይደለም፡፡ በበሽታ የሚሰቃየውን ሰው ወደ ተገቢው የህክምና ቦታ ከመውሰድ ይልቅ ከሞተ በኋላ የሚቀበርበት ሳጥን ከእንጨት ወይስ ከወርቅ ይሰራ፤ መቃብሩ ላይ የሚቀመጥለት አበባ ከኒውዘርላንድ ይምጣ ወይስ ከሀገር ውስጥ ይሁንለት እያልን ክርክር የገጠምን ይመስላል፡፡ አሁን በቁጭት ያንገበገበን ገመናችንን ለምን ቢቢሲ አየብን የሚለው እንጂ የተወሰነ አካባቢ በተደጋጋሚ ድርቅ የሚመታበት አርሶ አደር ለአንድ አመት የሚያርሰው ቢያጣ ሸምቶ እንኳ ይህን ክፉ ቀን ማለፍ አቃተው በሚል እልህ አለመሆኑ ነው፡፡
ሌላው ሊያሳፍረን እየተገባ ነገር ግን አይናችንን በጨው አጥበን ድርቅ የምንልበት ኮሚክ ነገራችን፣ ልናስወግደው እየተገባን በራሳችን ድክመት ማስወገድ ባልቻልነው ድርቅ ሳቢያ ይልሱት ይቀምሱት ላጡት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወት መታደጊያ የሚሆን እህልና ሌላም እርዳታ በጠየቅናችሁ መጠንና ሰዓት አልሰጣችሁንም ብለን፣ የልመና አኮፋዳችንን ሸጉጠን፣ እጃችንን የዘረጋንባቸውን ለጋሽ ሀገራትንና ድርጅቶችን ባደባባይ ለመውቀስና ለማማት መድፈራችን ነው፡፡ ይህ አጉል ድፍረት ከሞራልም ሆነ ከስነ ምግባር አኳያ ጥሩና ተመራጭ አይደለም፡፡
ይህን አሳፋሪ ድርቅና በሚመለከት መንግስታችን በሚገባ ሊረዳውና ሊገነዘበው የሚገባ ዋነኛ  ጉዳይ ህዝቡን የመመገብ ኃላፊነት ያለበት የሀገሬው መንግስት እንጂ ለጋሽ ሀገራትና ድርጅቶች አለመሆናቸውን ነው፡፡
ልግስናና ዕርዳታ የሚመነጨው ከለጋሹና ከረጂው የሞራልና የስነ ምግባር እሴት ውስጥ ነው፡፡ የሚከናወነውም እነዚህ የሞራልና የስነ ምግባር እሴቶች ከሚፈጥሩት ፈቃደኝነት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ለጋሽና ረጂ ሀገራትና ድርጅቶች በአደጋና በችግር ጊዜ የተጠቂውን ሀገር መንግስትና ህዝብ ይደግፋሉ እንጂ የመንግስትን ሚናና ኃላፊነት መተካት ጨርሶ አይችሉም፡፡
የእኛ መንግስት በእርዳታ ጠባቂነት ሌላውን ይከሳል እንጂ የእርዳታ ጠባቂነት ችግር ዋኛው ሰለባ መንግስት ራሱ ነው፡፡ ለዚያውም የጠየኳችሁን ሁሉ ባልኩት ሰዓት አልሰጣችሁኝም በሚል የለመናቸውን ሁሉ እየወቀሰና በቁጣ እያጉረመረመ፡፡ያሉብንን የተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ ችግሮች መንግስት ከእኛም ሆነ ከሌላው የደበቀ መስሎት እንዲያው በባዶ ሜዳ ይጨነቃል እንጂ የጉዳዩ ባለቤት የሆንነው ዜጐች ግን እያንዳንዱን ነገር ብጥርጥርጥር አድርገን እናውቃታለን እኮ! ከእያንዳንዱ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግሮች ጋር ዕለት ተዕለት ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ እየታገልን የምንኖረው እኛው እኮ ነን፡፡ ችጋርና ጠኔ ሲመጣ የእርዳታውን ስንዴና ዘይት እንዴትና ማን እንደሚያድለን የምናውቀውም እኛው ራሳችን ነን፡፡
ወጥረው አላፈናፍን ባሉን ችግሮቻችን ዙሪያ መንግስት የፈለገውን ያህል ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ሊያሳምነን ቢታትርም ከማንም የበለጠ እውነቱን እናውቃለን፡፡ እንዴት ቢሉ. . . በወሬ ሳይሆን በተግባር እየኖርነው ነውና፡፡ በተግባር ችግሩንም፤ ረሃቡንም፣ የኑሮ ውድነቱንም እየተቃመስነውም ያለነው እኛ እኮ ነን፡፡ (የእነበቢሲ ዘገባ ለውጥ አያመጣም ለማለት ነው)
እናም መንግስት ሊሰማን ፈቃደኛ ከሆነ አንደኛ እነ ቢቢሲ ለምን ገበናዬን አወጡት ከሚል ንትርክ ተላቅቆ የረሃብ ሰለባ የሆኑ ዜጐችን ነፍስ ለማትረፍ ይታትር፡፡ ከየአቅጣጫው የትችት በትር የሚሰነዝሩበት ላይ የአፀፋ በትር ለመሰንዘር ሲሞክር ዋነኛ ተግባሩን እየዘነጋ ነው፡፡ የዜጐችን አሳሳቢ ችግር መቅረፍ ነው የመንግስት ቀዳሚ ተግባሩ፡፡ መንግስታችንን ሊያሳስበው የሚገባው የቢቢሲና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ወቀሳና ነቀፋ ሳይሆን በእውን ለድርቅና ለረሃብ የተጋለጠው ህዝባችን ጉዳይ ነው፡፡ እናም መልዕክቱን ችላ ብሎ መልዕክተኛውን ማጥቃት ለመንግስት አይበጀውም እላለሁ፡፡

Read 2126 times