Saturday, 30 December 2023 19:51

“ብትር ፈርተን ነው እንጂ፤ የእናቶቻችንን መዋያማ እናውቀዋለን”፤ አለች ጥጃ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በአንድ አፈ-ታሪክ ውስጥ የሚገኝ የስድስት ሰዎችና የአንድ ትእቢተኛ ንጉሥ ታሪክ አለ፡፡ እንዲህ የሚል፡፡ አንድ መልካም እውቀት ያለው፣ አገሩን ከልቡ የሚወድና በሰራዊቱ ውስጥ በጀግንነት ያገለገለ ጎበዝና ብልህ ወታደር ጦርነቴ እንዳበቃ ለመጓጓዣ ያህል ብቻ ፍራንክ ሰጥቶ፤ ትእቢተኛው ንጉሥ ያባርረዋል፡፡
ወታደሩ በጣም አዝኖ “ንጉሱ እንዴት እንዲህ ጉድ ይሰሩኛል? እኔን የሚመስሉ ሰዎች ፈልጌ፣ እኒህን ንጉስ ያለ የሌለ ሀብታቸውን እንዲያስረክቡኝ አድርጌ ሙልጭ አወጣቸዋለሁ!” ብሎ ዝቶና ተቆጥቶ በእልህ ካገሩ ይወጣል፡፡
 ከዚያም በአንድ ጫካ ውስጥ እየተጓዘ ሳለ አንድ እጅግ በጣም ግዙፍ ሰውዬ ሳር የሚያጭድ ይመስል በተአምረኛ እጁ የጫካውን ግንድ ሁሉ እየገነደሰ ሲሸከም ያገኘዋል፡፡ “ወዳጄ ኃይል ጉልበት አለህና ለምን አብረን ሆነን ችሎታችንን አቀናጅተን በዓለም ውስጥ የተሳካላቸው ሁለት ሰዎች አንሆንም?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ግዙፉ ሰው በሃሳቡ ተስማምቶ ተከተለው፡፡
ጥቂት እልፍ እንዳሉ አንድ አነጣጣሪ አዳኝ ያገኛሉ፡፡ አዳኙ “ከስንትና ስንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ የአንዲትን ትንኝ ግራ ዓይን ለመምታት እያነጣጠርኩ ነው” ይላቸዋል፡፡ “ችሎታችንን ብናቀናጅኮ በአለም ውስጥ ሶስት የተሳካላቸው ሰዎች እንሆናለን፡፡ እባክህ አብረን እንሂድ” አሉት፡፡ እሺ ብሎ ተከተላቸው፡፡ አሁንም እልፍ እንዳሉ አንድ ትልቅ ዛፍ ጫፍ ላይ ወጥቶ የተቀመጠ ሰው ያገኛሉ፡፡ “እዚያ ዛፍ ጫፍ ላይ ተቀምጠህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጀግናውና ብልሁ ወታደር ጠየቀው፡፡ ሰውዬውም “ከብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሰባት በንፋስ የሚሰሩ ወፍጮዎች ይታዩኛል፡፡ አቅም አጥተው መሽከርከራቸውን አቁመዋል፡፡ ስለዚህ እነሱን ለማሽከርከር በተአምራዊ ኃይሌ ለመጠቀም አንዱን የአፍንጫዬን ቀዳዳ ደፍኜ በሌላኛው ስተነፍስ ወዲያው መዞር ይጀምራሉ” አላቸው፡፡ “በል ና አብረን እንሂድ፤ እኔ ብልህና ጀግና ወታደር ነኝ፡፡ እነዚህም እንዳንተው ችሎታ ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ አራታችን አንድ ብንሆን አለምን ለማሸነፍ እንችላለን” አለው፡፡ አውሎ ንፋስ ከአፍንጫው ማፍለቅ የሚችለው ሰውም ደስተኛ ሆነ፡፡
ጥቂት እንደተጓዙ በቀኝ እግሩ ብቻ የቆመና ግራ እግሩን ከጉልበቱ ፈትቶ መሬት ያጋደመ ሰው ያገኛሉ፡፡ “እግርህ ተቆርጦ እንዴት ተመችቶህ ቆምህ?” አለና ጠየቀው ብልሁ ጀግና፡፡ “እኔ ከወፎች የበለጥኩ ሯጭ ነኝ፡፡ ሁለቱንም እግሬን ከተጠቀምኩ ንፋስም አይቀድመኝም፡፡ ስለዚህ ረጋ ብዬ ለመሄድ እንድችል አንዱን እግር አውልቄ አስቀምጠዋለሁ” ይላል፡፡ “ተከተለንና አምስታችን ችሎታችንን አቀናጅተን አለምን እናሸንፍ” ይለዋል ብልሁ ጀግና፡፡ ሯጩም ተስማምቶ አብሯቸው ይጓዛል፡፡
 በመጨረሻ መንገድ ላይ ያገኙት አንድ ባርሜጣውን በአንድ ጆሮው ላይ ያንጠለጠለ ሰው ነበር፡፡ እሱም ለምን እንደዚያ እንዳደረገ ሲጠይቁት፣ ባርሜጣውን አስተካክሎ ካጠለቀ በኋላ በአካባቢው ያለውን ነገር ሁሉ እንደበረዶ ማቀዝቀዝ እንደሚችል ነገራቸው፡፡ “ስድስታችን አንድነት ቢኖረን አለምን እናሸንፋለንና አብረን እንሁን” አለው ብልሁ ጀግና፡፡ በሀሳቡ ተስማምቶ አብረው ሆኑ፡፡
ተሰብስበው ወደ እብሪተኛው ንጉስ ሲሄዱ ንጉሱ አዲስ አዋጅ አውጀው ደረሱ፡፡ አዋጁም “ከሴት ልጄ ጋር ሮጦ ተሽቀዳድሞ ያሸንፈ ባሏ ይሆናል፡፡ ሩጫው ካልተሳካለት ግን እንገቱ ይቆረጣል” የሚል ነበር፡፡ ብልሁ ጀግናም “የእኔ ሯጭ ያለጥርጥር ይቀድማታል” ሲል በኩራት ተናገረ፡፡ ንጉሱም “ቢሸነፍ ግን ያንተ ሯጭ ብቻ ሳይሆን ያንተም የራስህ አንገት ጭምር ይቆረጣል” ሲሉ ያስፈራሩታል፡፡ ውድድሩ ሩቅ ቦታ ወዳለ የውሃ ጉድጓድ ሮጦ ውሃ በባልዲ ቀድቶ ይዞ መምጣት ነው፡፡ የንጉሱ ልጅ እጅግ በጣም ፈጣን ሯጭ ናት፡፡ ንጉሡ ይተማመኑባታል፡፡
ሯጩ እግሩን ገጣጠመና ውድድሩ ተጀመረ፡፡ መቼ ሄደ ሳይባል በንፋስ ፍጥነት ሮጦ ውሃውን ቀዳና ሲመለስ ትንሽ አረፍ ልበል፤ ብሎ መንገድ ላይ ተኛ፡፡ እንዳይዘናጋና ብዙ እንቅልፍ እንዳይወስደው የሞተ ፈረስ የራስ-ቅል አግኝቶ ያንን ተንተራሰ፡፡ ሆኖም እንቅልፍ ይዞት ጭልጥ አለ፡፡ የንጉሱ ልጅ ገና ጉድጓድ እየሄደች ሳለች ተኝቶ አገኘችው፡፡
የሱን ባልዲ ውሃ ወደራሷ ባልዲ ገልብጣ ወደ ቤተመንግስት ገሰገሰች፡፡ ይህን ሁኔታ አነጣጣሪው ተኳሽ አየ፡፡ ስለዚህ በልዩ ችሎታው አነጣጥሮ ሯጩ የተንተራሰውን የፈረስ - ራስ- ቅል ነጥሎ መታው፡፡ ይሄኔ ሯጩ ነቃ፡፡ ባልዲው ባዶ መሆኑን ሲያይ ተንኮሉ ገብቶት እንደ ንፋስ በርሮ ውሃውን ይዞ የንጉሱን ልጅ ቀድሟት ገባ፡፡
ንጉሱ ተናደዱ፡፡ “ለዚህ ለጭባም ልጄን አልሰጥም!” አሉ፡፡ ስለዚህ ሌላ መላ መቱ፡፡ “በሉ የደስ ደስ ብሉ ጠጡ፡፡ ከዚያ ምቹ አልጋ ባለው ክፍል ተኙ፡፡ ጠዋት ልጄን ትረከባላችሁ” ይላሉ፡፡
ስድስቱ መንገደኞች በልተው ጠጥተው ተኙ፡፡ ለካ የተኙበት ቤት ከብረት የተሰራና በሩ ከተዘጋ መውጫ የሌለው ኖሯል፡፡ የንጉሱ አሽከር ከቤቱ ስር ካለው ምድር-ቤት ሆኖ እሳት ከስር እንዲያነድድና በብረቱ ግለት ታፍነው እንዲሞቱ ትእዛዝ ተቀብሎ ኖሮ እሳቱን ለቀቀባቸው፡፡ ሆኖም ባለባርሜጣው ጓደኛቸው ተንኮሉ ስለገባው ባርሜጣውን አስተካክሎ ሲያደርገው ብረቱ ሁሉ እንደበረዶ ቀዘቀዘና እሳቱም ሊያቀልጠው አልቻለም፡፡
ጠዋት ንጉሱ መጥተው ሲያዩ ስድስቱ ጓደኛሞች በሰላም ሲስቁ ሲጫወቱ አገኟቸው፡፡ በገኑ!! ጮሁ!! በንዴት አሽከራቸውን ትዕዛዜን አልፈፀምክም በሚል እንዲገደል አደረጉ፡፡
ሊሸነፉ መሆናቸውን ሲያውቁም ብልሁን ጀግና ጠርተው “በልጄ ፈንታ የፈለግኸውን ጠይቀኝ አደርግልሃለሁ!” አሉት፡፡ ብልሁ ሰውም “አሽከሬ ሊሸከመው የሚችለውን ያህል ወርቅ ይስጡኝ” አላቸው፡፡ ንጉሱ በጣም ተደሰቱ፡፡ “አሽከርህ መሸከም ካልቻለ ግን ሀብቴን ትመልሳለህ፡፡ በዚህ እንስማማ” አሉት፡፡ ብልሁ ጀግና ተስማማ፡፡ ንጉሱም ልባቸው ጮቤ ረገጠች፡፡ ከዚያ አንድ ዘዴ ፈጠሩ፡፡ የአገሩን ልብስ ሰፊዎች በሙሉ ሰብስበው ሰው ሊሸከመው የማይችል ትልቅ ከረጢት ስፉ ብለው አዘዙ፡፡
ልብስ ሰፊዎች እንደታዘዙት ትልቅ ድንኳን የሚያህል ከረጢት ሰፉ፡፡ ንጉሱ ያለ የሌለ ዕንቁ፣  ወርቅ ጌጣ ጌጥና ብር ሁሉ እንዲሞላ አዘዙና ተሞልቶ ተዘጋጀ፡፡
ያ የጫካውን ግንድ ሁሉ ሲሸከም የነበረው ግዙፍ ሰው ባንዴ ድንኳን አከሉን ከረጢት አንጠልጥሎ ስድስት ጓደኛሞች መንገድ ጀመሩ፡፡ ንጉሱ ተናደዱ፡፡ እብድ ሆኑ፡፡ አይኔ እያየ ምድረ-አቅመ ጎዶሎ፣ ምድረ-ጭባ ሀብቴን አይወስድ ብለው ፈረሰኛ ወታደሮች ሄደው፣ ስድስቱን መንገደኞች ገድለው ወርቁን ይዘው እንዲመጡ በቁጣ ያዝዛሉ፡፡
ፈረሰኞቹ ስድስቱ ተጓዦች ጋ ደርሰው፤ “እጅ ወደላይ!! በሰላም ሀብቱን አስረክቡ! አለዚያ እንጨርሳችኋለን!” ይሏቸዋል፡፡
በዚህን ጊዜ ከአፍንጫው አውሎ-ንፋስ ለማውጣት የሚችለው ተጓዥ፣ አንዱን የአፍንጫውን ቀዳዳ በእጁ ይዞ አንዴ ሲተነፍስ ወታደሮቹ ከእነ ፈረሳቸው ድምጥማቸው ጠፋ!
ንጉሱ የሆነውን ሁሉ ሲሰሙ በንዴት የቤተ-መንግስቱን ሰው ሁሉ በትንሽ በትልቁ ሰበብ አንገቱን እየቆረጡ የቅርብ ወዳጆቻቸውን ሳይቀር እየተነኮሱ፣ ጠበ -እየጫሩ ገድለው ጨረሱ፡፡
በመጨረሻም በነገሥኩበት አገር ውርደት አላይም ብለው ወደሌላ አገር ተሰደዱ፡፡ በተሰደዱበት አገር ሳሉ አእምሯቸው ተነካ፡፡ ይሄው እስከዛሬ ከእንቅልፋቸው በባነኑ ቁጥር “ልጄን ለማንም ጭባ አልሰጥም!” እያሉ ይጮሃሉ!!
***
ለአገሩ ለህዝቡ የሰራ የማይገፋባት፣ የማይገለልባት የማይበደልባት አገር ታስፈልገናለች፡፡ መሪ አለቃ ሃላፊ እብሪት ሲጠናወተው የማይታይባት አገር ታሻናለች፡፡ አቅማቸውን አቀናጅተው ለመስራት ለውጥ ለማምጣት የሚጥሩ “ተአምረኛ” ልጆች ያሉዋት አገር የታደለች ናት፡፡ በዋና ጉዳይ በድሎ በአናሳ ጉዳይ የሚያባብል የማይኖርባት አገር መልካም ቤት ናት፡፡ “ራሴን መትቶኝ እግሬን ቢያክልኝ ምንም አይገባኝ” የማይባልባት አገር ብትኖረን እንፀድቃለን፡፡ ሀገራችን የቅርብ ወዳጁን የማይንቅ የማይሰድብ፤ የቅርብ አጋሩን የማይርቅ፤ ድንገት ጎህ ቅዳጅ ላይ ዘራፍ የማይል፤ ድንገት ጀንበር መጥለቂያ ላይ ደሞ የማይሸማቀቅ እውነተኛ ሰው በመብራት የምትፈልግበት ዘመን ነው፡፡ ህዝብና አገር መሳለቂያ እንዳይሆኑ ስለእውነታቸው ከልብ የሚሟገቱ፣ ፈጠንኩ ብሎ የተመነጠቀውን ተመለስ ለማለት የሚደፍሩ፤ እየተራመደ መስሎ የሚያነክሰውን ወይ ዝለቅ ወይ ራቅ ለማለት የማይራሩ፤ የፈረደ መስሎ የሚሞዳሞደውን ውረድ ለማለት አይናቸውን የማያሹ ደመ መራራ ሹማምንት እንደሚያስፈልጉ ሁሉ ከአሻንጉሊትነት ነፃ የሆኑ ዲፕሎማሲን ግን የተካኑ ልባቸው ያልተደፈነ አእምሯቸው ያልተሸፈነ፣ እንቅፋት በመታቸው ቁጥር “መድኃኒት አድርገውብኝ ነው” የማይሉ፤ አለቃ ባስነጠሰ ቁጥር “መፈክር ይማርህ!” ብለው የማያላዝኑ ልባም ሰዎች የሚፈለጉበት ሰዓት ነው፡፡ ጉልበት እብሪት ንፉግነት ፣ ‘እኔ ብቻ አዋቂ’ ማለት፤ ‘እጁን ያወጣ ወዬለት’ ማለት ወደ ሰላም ሳይሆን ወደ ግጭት፤ ወደ መቀራረብ ሳይሆን ወደሽሽት የሚያመራ ነው፡፡ በዚሁ ፈር የልባቸውን ለመናገር ድፍረት ያጡ እየበረከቱ ከመጡ “ብትር ፈርተን ነው እንጂ የናቶቻችንን መዋያማ እናውቀዋለን” አለች ጥጃ የሚሉ ሰዎች የምናፈራባት አገር ብቻ ናት የምትኖረን፡፡
አንድ ጊዜ አንድ አዋቂ “ሞተር ብስክሌተኛ ማለት ምን ማለት ነው?” ተብሎ ሲጠየቅ የሚሄድ ሰው ነው” ብሎ ነበር፡፡ የሰማነውን በየልቦናችን ያሳድርልን፡፡

Read 1240 times