ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችው በጦርነት የተዳከመች ጊዜ ነው የባሕር በር እጦት ደግሞ ‹‹እርግማን›› ነው
የባሕር በር የሌላቸው አገራት፣ ዕጥፍ ድርብ መከራ ያያሉ ብለናል። ግን በደፈናው ሳይሆን ነገሩን ዘርዝረን በመረጃ ልንጨብጠው ይገባል። ለዚህም፣ ከበርካታ ዓመታት ጥናቶችና ሪፖርቶች ውስጥ በጥንቃቄ ተለቅመውና ተነጥረው የወጡ ዋና ዋና የቁጥር መረጃዎችን እንመለከታለን።
እንግዲህ፣ በጥቅሉ ጀምረነዋል። የባሕር በር እጦት፣ በየትኛውም ዘመንና ለማንኛውም አገር፣ ዕጥፍ ድርብ ዕዳ እንደሆነ ሰምተናል።
በአንድ ወገን፣ የአገር ውስጥ ምርቶችን በቅናሽና በፍጥነት ለዓለም ገበያ ማድረስ ይከብዳቸዋል። የባሕር በር ለሌላቸው አገራት፣ የማጓጓዣ ወጪ በ50% ይጨምራል። እንዲያውም ከዚያም በላይ እንደሚከብድ በአሳማኝ በመረጃዎች እናያለን፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡
የማጓጓዣ ጊዜ በዕጥፍ ይጓተታል። የድንበርና የኬላ ፍተሻ፣ የመጫኛና የማውረጃ ጣጣ ይበዛባቸዋል። በዚህ በዚህ ምክንያትም ባህር አልባ አገራት ለኢንቨስትመንት ተመራጭ አይሆኑም። ሁሌም የውጭ ምንዛሬ እንዳጠራቸው ነው።
በሌላ ወገን ደግሞ፣ ከውጭ የሚያስገቡት ምርት ላይ፣ ገንዘባቸው የሚቃጠለው መንገድ ላይ ነው፡፡ ለማጓጓዣ ዋጋና ለውጣውረድ ኪሳቸው ይራቆታል። በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ሳቢያ የሚያዩት መከራ ሳያንስ፣ በጎረቤት አገራት በኩል ለመሻገር፣ ለማጓጓዝና ለማስተላለፍ፣ በውጭ ምንዛሬ ለመክፈል ይገደዳሉ።
የኢትዮጵያ የ2022 “የኢምፖርትና የኤክፖርት” ቁጥሮችን በምሳሌነት መጥቀስ እንችላለን። የምርትና የቁሳቁስ ኤክስፖርት፡ 4 ቢሊዮን ዶላር።
የምርትና የቁሳቁስ ኢምፖርት፡- 16.7 ቢሊዮን ዶላር።
በድምር የቁሳቁሶቹና የምርቶቹ ጠቅላላ ዋጋ፤ 20.7 ቢሊዮን ዶላር ነው።
ለትራንስፖርት የተከፈለው ዶላርስ? ከ5.7 ቢሊዮን ዶላር ይበልጣል (ይሄ የዓለም ባንክ መረጃ ነው)።
የዕቃዎቹን ዋጋ ተመልከቱ፡፡ የማጓጓዣ ክፍያውንም ተመልከቱ፡፡ ሁለቱን በማነጻጸር ብቻ፣ የኢትዮጵያን የባሕር በር ችግር ምንኛ ከባድ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። የባሕር በር ቢኖራት፣ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማዳን ትችል እንደነበር በማሰብም ነገሩን ማገናዘብ ይቻላል።
የባሕር በር ያላቸው የአፍሪካ አገራት፣ የማጓጓዣ ወጪያቸው ከ10 እስከ 13% ነው። የኢትዮጵያ ግን ከ20% በላይ ነው።
በእርግጥ በጣም የባሰባቸውም አሉ። እነ ማሊ፣ እነ ቡርኪናፋሶ፣… ከመቶ ዶላር ውስጥ፣ 70 ዶላር ለዕቃ መግዣ፣ 30 ዶላር ለማጓጓዣ ይከፍላሉ።
የአምናና የካቻምና መረጃዎችን ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ኋላ አርባ ወይም ሠላሳ ዓመት ተመልሰን የየዘመኑን መረጃ ብንመለከት፣ “የባሕር በር እጦት” ከሚሉት “እርግማን” የሚያላቅቅ መላ እንዳላገኙ ማየት እንችላለን። ሩብ ወይም ሲሶ ንብረታችሁ በትራንስርት ቀልጦ የሚቀር ከሆነ ምን እርግማን እንጂ ምን ይባላል?
As a land-locked country, transportation costs form a much higher proportion of industrial costs than in countries with sea access;… These costs cause an immediate rise of 30-40% in prices of locally manufactured goods. (ማሪታይምሪቪው እ.ኤ.አ የ1995 ዓመታዊ ሪፖርት ገጽ 107)።
የቡርኪናፋሶና የማሊ ብቻ፣ ወይም የአንድና የሁለት ዓመት ብቻ አይደለም ችግሩ። እ.ኤ.አ በ1980 ላይም፣ የማጓጓዣ ወጪያቸው፣ ወገብ የሚሰብር እንደነበር ሪፖርቱ ይጠቅሳል። ጊዜው ከአርባ ዓመት በፊት መሆኑ ነው፡፡ የባህር በር የሌለው የአፍሪካ አገር ምን ዓይነት መከራ እንደሚገጥመው ለመረዳት እልፍ አእላፍ ቁጥሮች በሪፖርቱ ተደርድረዋል፡፡ ሁለት ሶስቱን ብቻ ተመልከቱ፡፡
ከዓለም ዙሪያ ሸቀጣ ሸቀጥ ለማስመጣት 130 ሚሊዮን ዶላር እንደተከፈለ ይነግረናል። 55 ሚሊዮን ዶላሩ ግን ለማጓጓዣ ነው ይለናል። 85 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው ለሸቀጣ ሸቀጦቹ ግዢ። ከመቶ ዶላር ውስጥ ሠላሳ ዶላር ለትራንስፖርት ይውላል ማለት የዚህን ያህል ከባድ ዕዳ ነው።
የባህር በር የሌላቸው አገራት፣ የአገር ውስጥ ምርቶችን ወደ ውጭ በፍጥነትና በቅናሽ ዋጋ መላክ ስለሚቸግራቸው፣ በኢኮኖሚ የማደግ ዕድላቸው ይዳከማል። ኢንቨስትመንትን በስፋት መሳብና መማረክ አይችሉም።
እንደምንም ተሟሙተው ወደ ዓለም በሚልኳት ምርት የሚያገኟት ዶላር ደግሞ፣ ከውጭ አገራት ነዳጅም ይሁን ብረታብረት ገዝተው ለማስገባት ሲሞክሩ፣ ሩብ ያህል ገንዘባቸው በትራንስፖርት ተበልቶ ይቀራል።
በዚህ ሁኔታ እንዴት ኢኮኖሚያቸው ሊያድግ ይችላል? አፍሪካ ውስጥ የባሕር በር የሌላቸው አገራት፣ “የድሀ ድሀ” መሆናቸውስ ምን ይገርማል?
ግጭትና መፈንቅለ መንግሥት፣ ትርምስና ጦርነት የማያጣቸው አገራትን አስታውሱ - ማሊ፣ ማላዊ፣ ኒጀር፣ ቡርኪናፋሶ፣ ብሩንዲ፣ ቻድ፣ ሴንትራል አፍሪካ፣… ደቡብ ሱዳን። እነዚህ ሁሉ አገራት የባሕር በር የላቸውም።
ዘመን ያልሻረው “እርግማን”?
የባሕር በር እጦትና መዘዙ፣ በ50 ዓመታት ውስጥ አልተለወጠም። ያኔም ዛሬም፣ ሸክምነቱ ያልተቃለለ ተጨባጭ እውነታ ነው። የቅርብ ዓመታትን ከመመልከታችን በፊት፣ ትንሽ ሻገር ብለን የማሪታይም የ2000 ዓመታዊ ሪፖርት ውስጥ በገጽ 67 የሰፈረውን መረጃ ማየት እንችላለን።
The imports of African landlocked countries continued to suffer from high freight costs, … the ratio of Malawi remained at 39%, while for Mali and Rwanda the ratio was 30% each, and for Burkina Faso and Chad it was in the range of 21 to 26%.
በ2001 ሪፖርት ደግሞ የኢትዮጵያ ስም ተነስቷል። የአፍሪካ የማጓጓዣ ክፍያ፣ በአማካይ ከዕቃው ዋጋ 12% ያህል እንደሆነ ይጠቅስና፣ የባሕር በር የሌላቸው አገራት ግን፣ የማጓጓዣ ሸክማቸው ከ20% በላይ እንደሆነ ይገልጻል። ከእነዚህ መካከልም ኢትዮጵያ አንዷ ናት።
…freight costs in African developing countries, however, continued slowly but steadily on an upward trend from 11.5% in 1998 to 12.0% in 1999. Freight ratios for Burkina Faso, Burundi, Chad, Ethiopia, Malawi and Mali were all greater than 20% (ገጽ 62)።
ልዩነቱን ተመልከቱ። “ያደላቸው” አገራት ላይ የማጓጓዣ ወጪ ከዕቃው ዋጋ 5% ገደማ ነው። የአፍሪካ አገራት አማካይ ግን 12%? ብዙ ነው። ግን የሁሉም አፍሪካውያን ሸክም እኩል አይደለም።
የባሕር በር ላላቸው የአፍሪካ አገራት የትራንስፖርት ሸክም ቀለል ይላል። ከ10% በታች ነው። የባሕር በር ለሌላቸው ግን፣ ከ20% በላይ። ዕጥፍ የዕዳ ሸክም ማለትስ ይሄ አይደለም ወይ?
እንደገና ዓሥር ዓመት ተሻግረን የ2013 ዓመታዊ የማሪታይም ሪፖርት እንመልከት። የኮንተይነር የማጓጓዣ ዋጋዎችን በንጽጽር ያቀርባል - ሪፖርቱ።
ከ2005 እስከ 2007
የባሕር በር ላላቸው ድሀ አገራት…
የአንድ ኮንቴይነር አማካይ የማጓጓዣ ዋጋ፡ 1000 ዶላር።
የባሕር በር ለሌላቸው አገራትስ?
የአንድ ኮንተይነር አማካይ የማጓጓዣ ዋጋ፡ 2200 ዶላር።
ዕጥፍ ያህል ነው ልዩነቱ።
ከዚያ ወዲህ የትራንስፖርት ዋጋ ጨምሯል።
ከ2008 እስከ 2011
የባሕር በር ላላቸው ድሀ አገራት…
የአንድ ኮንቴይነር አማካይ የማጓጓዣ ዋጋ፡ 1250 ዶላር።
የባሕር በር ለሌላቸው አገራትስ?
የአንድ ኮንተይነር አማካይ የማጓጓዣ ዋጋ፡ 2700 ዶላር።
አዎ፤ የማጓጓዣ ዋጋ በየጊዜው ይጨምራል፤ ይቀንሳል።
ያልተቀየረው ነገር፣ የባሕር በር የሌላቸው አገራት፣ ለማጓጓዣ ከዕጥፍ በላይ የሚከፍሉ መሆናቸው ነው።
የአገር ውስጥ ምርቶችን ለዓለም ገበያ ለማድረስ ደግሞ ዕጥፍ ጊዜ እንደሚፈጅባቸውም ሪፖርቱ ይገልጻል (ገጽ 141)።
እንዲያውም፣ ከአማካይ የማጓጓዣ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር እላፊ ክፍያ እጅግ ከተጫናቸው 8 የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ እንደሆነች ሪፖርቱ ያሳያል (ገጽ 142)።
ወደ 2015 ተሻግረንም ሌላ ዓመታዊ ሪፖርት እንመልከት።
ዕቃ ለመግዛትና ወደ አገር ለማስገባት ከሚውለው ገንዘብ ውስጥ፣ 11.5 እስከ 12.5% ይህሉ የማጓጓዣ ክፍያ እንደሆነ ይገልጻል - ሪፖርቱ። ለአፍሪካ አገራት በአማካይ መሆኑ ነው። ታዲያ የአንድ ዓመት መረጃ አይደለም።
ከ1985 እስከ 2014 ድረስ፣ የሠላሳ ዓመት መረጃ በማጠቃለል ነው እውነታውን በሰንጠረዥ የሚያሳየን (ገጽ 55)።
የባሕር በር የሌላቸው አገራት የተሸከሙት ዕጥፍ የማጓጓዣ ወጪም፣ የዚያኑ ያህል በሠላሳ ዓመታት “ወገብ ሰባሪነቱ” እንዳልተለወጠ መረጃው ያረጋግጣል።
ከማሪታይም የአርባ ዓመታት ሪፖርቶች ውስጥ የተወሰኑትን እያገላበጥን አይተናል።
“የባሕር በር እጦት”፣ አያድርስባችሁ የሚያሰኝ ክፉ ሸክም እንደሆነ ተመልክተናል።
የዓለም ንግድ ድርጅት ከዓመት በፊት ያወጣው ሪፖርትም ይህን የረዥም ዘመናት እውነታ እንደገና የሚያረጋግጡ መረጃዎችን በማካተት ይፋ አድርጓል።
ከዓለም ባንክ ዓመታዊ መረጃዎች ላይም ተመሳሳይ መልእክቶችን እናገኛለን።
ኢትዮጵያ ለትራንስፖርት አገልግሎት በዶላር የምትከፍለው ዋጋ፣ “ከላኪና ከአስመጪ ዕቃዎች ዋጋ ጋር ሲነጻጸር”፣ 14 መቶ ገደማ ነበር። ይሄ ከሰላሳ ዓመት በፊት ነው፡፡ ከዚያ ወዲህስ?
የሚጓጓዣ ወጪ፣ ዛሬ ከ20% በላይ ሄዷል። እስከ 25% ደርሷል። የ2022 ቁጥሮችን ተመልከቱ።
በዓመት 5.7 ቢሊዮን ዶላር ለትራንስፖርት መክፈል ለኢትዮጵያ ቀላል ነው? “የኢምፖርትና የኤክስፖርት” ዕቃዎች ዋጋ ተደማምሮ፣ 20 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው። የስንት ዶላር ዕቃ በስንት ዶላር ትራንስፖርት እንደሆነ አያችሁ?
እንግዲህ፣ ባለፈው ሳምንት በቀረበው ጽሑፍ፣ በዓባይ ወንዝ ውኃና በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ስንነጋገር፣ ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ምንኛ ወደ ኋላ እንደቀረች በቁጭት የሚገልጹ ቁጥሮችን ተመልክተናል።
ከአፍሪካ ድሀ አገራት በታች ከወለል ስር ላይ ናት ኢትዮጵያ። የአፍሪካ አማካይ ደረጃ ላይ ለመድረስ፣ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል በአምስት ዕጥፍ ማደግ አለበት።
የሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸር 3 ዕጥፍ ነው።
የግብፅ ደግሞ 15 ዕጥፍ።
አዎ ያስቆጫል። ግን የእነሱ ከፍ ማለቱ አይደለም የሚያስቆጨው። ዕጥፍ ድርብ ከፍ ቢልላቸው እሰዬው ነው። ሌሎችን ዝቅ በማድረግ ምንም ትርፍ አይገኝም፡፡ ኤሌክትሪክና የባህር በር ይብዛላቸው ለኛም ይተርፋሉ፡፡ የኢትዮጵያ ትንሳኤና ህዳሴም ለጎረቤቶች ይተርፋል፡፡
ይልቅስ፣ሊያስቆጨን የሚገባው፣ ትልቋ አገር ኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣቷና የኤሌክትሪክ ደሀ መሆኗ ነው። በእርግጥ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም።
ከ25 ዓመታት በፊት፣ የግብፅ የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸር 30 ዕጥፍ ነበር። ከዚያ ወዲህ ባሉ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ደህና ግስጋሴ ስለታየ፣ ልዩነቱ ወደ 15 ዕጥፍ ወርዷል። ግን አሁንም ገና ብዙ ይቀራል።
ኤሌክትሪክ፣ ከቀጥተኛ አገልግሎቱ በተጨማሪ የኢኮኖሚ ዓቅም መለኪያ፣ የብልጽግና ሞተር መሆኑ ሲታይ፣ እንዲሁ በዋዛ የሚታለፍ አይደለም።
የአገር ኢኮኖሚና የዜጎች ኑሮ ነው የኤሌክትሪክ ጉዳይ። ማለትም የዓባይ ወንዝ ውኃ፣ ለኢትዮጵያ የድኽነትና የእድገት ጉዳይ ነው።
የባሕር በርም እንደዚያው ነው። የደም ስር ነው። የኢኮኖሚና የኑሮ ጉዳይ ነው፡፡
ያለ ዓባይ ውኃና ያለ ባሕር በር፣ ኢትዮጵያ አይሆንላትም። ለነገሩ ሌሎች አገራትም አይሆንላቸውም። ያለ ባሕር በርና ያለ ኤልክትሪክ እንዴት ይኮናል?
ኢትዮጵያን የመሰለ የረዥም ዘመናት ባለ ታሪክ አገር፣ በሕዝብ ብዛት ከዓለማችን ቀዳሚ ደርዘን አገራት መካከል አንዷ የሆነች ትልቅ አገርማ፣… እንዴት ልትዘልቀው ትችላለች? ችግር መፈጠሩ አይቀሬ ነው። በጊዜ ሂደትም፣ ብዙ ዜጎችን የሚከነክንና የሚቆረቁር ከባድ ውርደት ሆኖ መታየቱም አይቀሬ ነው።
በአጭሩ የተጨባጭ ኑሮ እንዲሁም የክብር ጉዳይ እየሆነ መምጣቱ አያጠራጥርም - አገሪቱ ካልፈራረሰችና ብትንትኗ ከልወጣች በስተቀር።
እንዲህ ማለት ግን፣ መፍትሄ የሌለው ችግር ይፈጠራል ማለት አይደለም፡፡ ወደ ጦርነት መግባት የግድ ይሆናል ማለትም አይደለም፡፡
እንዲያውም በተቃራኒው፣ ጦርነትን ከሩቁ የሚያስቀር መፍትሄ ነው የሚበጀን የሚበጃቸው፡፡ ደግሞም ኢትዮጵያ ውስጥ ደህና ግስጋሴ የታየው እስከ ህዳሴ ግድብ የደረስነው ለጥቂት ዓመታት በተገኘው የሰላም ጊዜ ነው፡፡
የባህር በር ያጣችው ደግሞ በጦርነት በተዘፈቀችበትና በተዳከመችበት ጊዜ ነው፡፡
በአጭሩ ጦርነትን ከሩቁ የሚያስቀር ሰላምን የሚሰፍን መፍትሄ ላይ ነው ማተኮር ያለብን፡፡
ከጎረቤቶች ጋር ሰላም ለመሆን ዘዴው ምንድ ነው? በተለይ ደግሞ እዚሁ አገር ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነቶችን ለማስቀረት ሁነኛው መላ ምን እንደሆነ በጊዜ ማወቅ አለብን፡፡
አለበለዚያ ነገሩ ሁሉ ከንቱ ይሆናል፡፡
መሆን የለበትም፡፡
ኢትዮጵያ ትልቅ ባለ ታሪክ አገር ናት፡፡ ወደፊትም ትችላለች፡፡
Saturday, 30 December 2023 19:53
ሰላም ካለ የባሕር በር ይኖረናል
Written by ዮሃንስ ሰ
Published in
ነፃ አስተያየት