“ኢትዮጵያን ወክዬ መመረጤ ትልቅ ደስታ ነው የሰጠኝ....”
በዓለምአቀፍ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ፌዴሬሽን እውቅና ያገኙት ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ
ከዚህ ቀደም በነበረው እትም የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ ከዓለምአቀፍ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ፌዴሬሽን (FIGO) እውቅና ማግኘታቸውን አስመልክቶ በህክምና ሙያ ውስጥ ስለተጓዙበት መንገድ፣ ልምድ እና ተሞክሮ ለንባብ ማቅረባችን ይታወሳል። የዚህ ቀጣይ ክፍል እንሆ ለንባብ ቀርቧል።
ዓለምአቀፍ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ፌዴሬሽን (FIGO) ለሴቶች የጽንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስቶች ሽልማት እና እውቅና መስጠት የጀመረው እ.ኤ.አ በ1997 ነበር። ይህ ሽልማት እና እውቅና የሚሰጠው በሙያው ላይ ሳይንሳዊ ምርምር ላደረጉ እንዲሁም በአገልግሎት ዘመናቸው ለሴቶች፣ እናቶች እና ህፃናት ጤና ላይ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ነው። ባለሙያዎቹ የሰሩት ሳይንሳዊ ምርምር እና አገልግሎት በሀገር አቀፍ ወይም በዓለምአቀፍ ደረጃ ሊሆን ይችላል።
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ ከ30 ዓመታት በላይ በህክምና ሙያ ውስጥ ቆይተዋል። ለዚህም አገልግሎታቸው ዓለምአቀፍ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ፌዴሬሽን (FIGO) እ.ኤ.አ በ2023 እውቅና ሰቷቸዋል። ዶ/ር ሰላማዊት ለረዥም ዓመታት ያገለገሉበትን የፅንስ እና ማህፀን ህክምና “ከምታምጠው ሴት ጋር አብሮ አምጦ፣ ከምታለቅሰው ጋር አብሮ ተጨንቆ፣ በማንኛውም ሰአት አገልግሎቱ ለሚያስፈልጋቸው ሴቶች እና ህፃናት ደርሶ እንዲሁም የእራስን ቤተሰብ እና ምቾት በመተው ለ30 ዓመታት መቆየት ቀላል አይደለም” በማለት ገልፀውታል። የፅንስ እና ማህፀን ህክምና አድካሚ ስራ ቢሆንም ውጤቱ ግን ደስታ እንደሚሰጥ ነው ባለሙያዋ የተናገሩት።
ዓለምአቀፍ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ፌዴሬሽን (FIGO) ሽልማት እና እውቅና ያበረከተው ከ16 ሃገራት ለተመረጡ የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስቶች ነው። ሽልማቱ የተበረከተላቸው የህክምና ባለሙያዎች በዋነኝነት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት የተመረጡ ናቸው። ከአፍሪካ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቱኒዝያ እና ኢትዮጵያ ተካተዋል። ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ በነበራቸው የህክምና አገልግሎት እውቅና ሲያገኙ የኢትዮጵያን ስም አስጠርተዋል። “ከኢትዮጵያ ሲባል የሚሰጠው ክብር ቀላል አይደለም፤ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ሀገር እየተጠቀሰ ሲጠራ ሀገሬን ወክዬ ነው ለካ የሄድኩት ብያለው” ብለዋል ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ። አክለውም “ኢትዮጵያን ወክዬ መመረጤ በጣም ትልቅ ደስታ ነው የሰጠኝ፤ ለወደፊት ለሚመጣው ትውልድም ተስፋ የሚሰጥ ነው” በማለት ተናግረዋል። እንደ ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ ንግግር ከዚህ በኋላም በሚፈለገው ሁሉ በሙያቸው ለማገልገል ዝግጁ ናቸው።
የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ እንደተናገሩት ከፌዴሬሽኑ ያገኙት እውቅና ብቻ ነው። “ጥቅሙ ኢኮኖሚካል አይደለም፤ ከፊጎ የጠበቅነው እና የሰጡን ነገር የለም፤ ነገር ግን ለ30 ዓመታት ለሰራሁት ስራ እውቅና ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም” ብለዋል ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ። እንደ የህክምና ባለሙያዋ ንግግር ከዓለምአቀፍ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ፌዴሬሽን እውቅና ማግኘት በቀጣይም በሙያው ላይ ለመስራት ብርታት ይሰጣል። ስለሆነም በዓለምአቀፍ ደረጃ መመስገናቸው እና እውቅና ማግኘታቸው ለ30 ዓመታት የነበረው ልፋት እና ድካማቸው ዋጋ እንዳገኘ ነው የተሰማቸው።
“ጥቁር አንበሳ የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ተማሪ በነበርኩበት ወቅት የእጅ ጓንት እጥረት ስለነበር እየቀቀልን እንጠቀም ነበር፤ ጓንት ሲያልቅ ደግሞ በሳቭሎን(የደም ንክኪ እያለው) እናቶችን አዋልደናል” በማለት ከህክምና መስጫ ቁሳቁስ ጋር በተያያዘ ያጋጠማቸውን ችግር ተናግረዋል። እንዲሁም ፓሊስ ሆስፒታል ባገለገሉበት ወቅት በተለያየ ምክንያት የሙያ አጋሮቻቸው በስራ ላይ ባለመኖራቸው ለ2 ዓመታት በብቸነት የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ሆነው አገልግለዋል። እናም ከ30 ዓመታት በላይ ባገለገሉበት የህክምና ሙያ ውስጥ የበፊት እና የአሁኑን አነፃፅረው “የምንጠብቀን ያህል ባይሆንም ለውጥ አለ” ብለዋል። ከዚህም ውስጥ ቅድመ ወሊድ የህክምና ክትትል ማድረግ፣ በህክምና ተቋም ውስጥ መውለድ፣ የተለያዩ የበሽታ አይነቶችን(ቅድመ ካንሰር) ምርመራ እና ህክምና ማድረግ የሚጠቀስ ነው። በተጨማሪም የህክምና መስጫ ተቋም፣ የህክምና ባለሙያ ብዛት፣ የህክምና መስጫ ቁሳቁስ፣ መድሃኒት እና አስፈላጊ የህክምና ግብአቶች ላይ መሻሻል መኖሩን ባለሙያዋ ተናግረዋል።
የዓለም አቀፍ የፅንስ እና ማህፀን ሀኪሞች ፌዴሬሽን ሽልማት እና እውቅና የሰጠው ለሴት የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስቶች ነው። ከሴትነት እና ከህክምና ሙያ ጋር በተያያዘ ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ እንደተናገሩት ሴት የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት መሆን በታካሚዎች ዘንድ ያለው ተቀባይነት አዎንታዊ ነው። ታካሚዎቹ ሴቶች በመሆናቸው የህክምና ባለሙያዋም ሴት ብትሆን ይመርጣሉ። ነገር ግን አንዳንድ ታካሚዎች ወንድ የህክምና ባለሙያ እንደሚመርጡ ዶ/ር ሰላማዊት ተናግረዋል። ዶ/ር ሰላማዊት እንደተናገሩት ሴቶች እድሉን ካገኙ ጎበዞች ሲሆኑ አሁን ላይ በብዛት በህክምና ሙያ ውስጥ እየተሸለሙ ያሉትም ሴቶች ናቸው። “ሴት ሆኖ ሀኪም መሆን ጥሩ ነው፤ ሴት በተፈጥሮዋ አዛኝ፣ ሩሩህ እና ጠንቃቃ ናት” ብለዋል ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ።
ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ ባለትዳር እና የ2 ልጆች እናት ናቸው። የቤተሰብ ሀላፊ ሆኖ የህክምና ባለሙያ መሆን ቀላል አለመሆኑን ባለሙያዋ ተናግረዋል። የህክምና ሙያ የሚፈልገው ጊዜ እና አሰራር ከተለያዩ የቤተሰብ እንዲሁም ከማህበራዊ ህይወት እንዲገለሉ ያደርጋል። በበዓላት እለት፣ ቅዳሜ እና እሁድ እንዲሁም ለሊት እና ቀን በስራ ላይ የማሳለፍ ሁኔታ ይኖራል። ይህም የቤተሰብ ሀላፊነትን ለመወጣት አዳጋች ያደርገዋል። ስለሆነም ይህን ሁኔታ ለመቋቋም በባለሙያው ዙሪያ ያለ ሰው ድጋፍ ያስፈልጋል። እንደ ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ ንግግር የትዳር አጋራቸው እና ልጆቻቸው ድጋፍ ያደርጉላቸዋል። ቤት ውስጥ ያለ ስራ ከመስራት ጀምሮ ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያግዟቸዋል። የሚደግፍ ቤተሰብ በዙሪያ ከሌለ ሙያው ላይ መቆየት ከባድ መሆኑን ዶ/ር ሰላማዊት ተናግረዋል።
የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ “በመጀመሪያ ደረጃ እዚህ ለመድረሴ አምላኬን አመሰግናለው” ብለዋል። ቀጥለውም ለአባታቸው አድማስ በዛብህ፣ ለባለቤታቸው ወንድይፍራው መኮንን(ዶ/ር) ፣ ለልጆቻቸው ዶ/ር ይስሙህ ወንድይፍራው እና ሚካኤል ወንድይፍራው እንዲሁም በዙሪያቸው ላሉ ሰዎች በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል። ከዚህ በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ በተለይም በኢትዮጵያ ላሉ ሴቶች ዶ/ር ሰላማዊት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ለዚህም እንደ ምክንያታት ያስቀመጡት ሴቶች(እናቶች) የሚከፍሉት ዋጋ ቀላል አለመሆኑን ነው። “እንደ ሴትነቴ እንዲሁም የፅንስ እና የማህፀን ሀኪም እንደ መሆኔ የእናቶች ስቃይ ቀላል አለመሆኑን ስለምረዳ ለሚከፍሉት ዋጋ ሁሉ ምስጋና አቀርባለው” ብለዋል ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ።
ሰዎች የሚወዱትን ስራ የሚሰሩ ወይም የሚሰሩትን ስራ የሚወዱ ከሆነ የሚሰራው ስራ ውጤታማ እንደሚሆን ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ ተናግረዋል። እንደ የህክምና ባለሙያዋ ንግግር ምስጋና፣ ሽልማት እና ሌላ ጥቅም ታስቦ ሳይሆን በቅንነት መስራት ያስፈልጋል። መሰራት ያለበት ከተሰራ ሽልማት እና እውቅና ጊዜውን ጠብቆ ይመጣል። “እኔም ሳላስበው ነው ይህን እውቅና ያገኘሁት፤ መስራት እና ከልብ ማገልገል ጥሩ ነው” ብለዋል ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ። ስለሆነም ወጣት (ሙያውን እየጀመሩ ያሉ) የህክምና ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ በማለት የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰላማዊት አሻግሬ መልዕክት አስተላልፈዋል።
Saturday, 06 January 2024 21:15
በዓለምአቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኙት ኢትዮጵያዊት ዶ/ር...
Written by ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Published in
ላንተና ላንቺ