• ፈቃድ አሰጣጡን የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ከአባል ፌዴሬሽኖች ተረክቦታል
• ፌዴሬሽኑ አምና ከአትሌት ማናጀሮች ክፍያ 4 ሚሊየን 668 ሺህ 299 አስገብቷል።
• በ2016 እኤአ ላይ ደግሞ እስከ 4.5 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ እቅድ ነበረው።
• የአትሌትና የአትሌት ተወካይ የውል ስምምነት ሁለት ዓመት ገደብ ተሰጥቶታል።
• በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የሚንቀሳቀሱ ዋና ዋናዎቹ የአትሌቶች ተወካዮች ከ20 በላይ ናቸው።
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር የአትሌት ተወካዮች ላይ ያወጣውን አዲስ ህግና አሰራር መተግበር ጀምሯል። ይህን አስመልክቶ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሰሞኑን ለባለድርሻ አካላት በለጠፈው ማስታወቂያ ከአትሌት ተወካዮች ጋር በተያያዘ ምንም አይነት መረጃ በፌደሬሽኑ በኩል እንደማይኖር በመጥቀስ ፤ አገልግሎት መሥጠት የማይቻልበት ደረጃ መደረሱን አመልክቷል። በዓለም አትሌቲክስ እውቅና ያላቸው የአትሌት ተወካዮች ከፌዴሬሽኑ ጋር ውል በመፈፀም የሚያገኟቸውን የተለያዮ አገልግሎቶች እንደማይሰጥም ገልጿል። የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ለአትሌት ተወካዮች የተማከለ የፈቃድ አሰጣጥ ስርዓት በአባል ፌዴሬሽኖች አስተዳደር ላይ ለመዘርጋት የወሰነው ከ3 ወራት በፊት ነው። አዲሱን አሰራር መተግበር ከጀመረ ደግሞ ሳምንት ሆኖታል። በአለም አትሌቲክስ ምክር ቤት የፀደቀው አዲስ ህግ የአትሌት ተወካዮች (AR) በማንኛውም ውድድር ዓለም አቀፍ ደረጃ ጠብቀው እንዲሰሩ የሚያደርግ ነው። የአለም አትሌቲክስ ፕሬዝደንት ሴባስቲያን ኮ እንደተናገሩት የአትሌት ተወካዮችና አትሌቶች በስራ ግንኙነታቸው በሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎች ላይ ጥናትና ምክክር ከተካሄደ በኋላ የአሰራር ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በዓለም አትሌቲክስ ባለድርሻ አካላት በእኩልነት የሚያስተዳድር ቁጥጥርና ስርዓት መዘርጋቱ የተሻለ ውጤት ማምጣቱን እንደሚያምኑበትም ገልፀዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለአትሌት ተወካዮች በሚሰጠው አገልግሎት የሚያገኘውን ገቢ ያሳጣዋል። ከወር በፊት በተደረገው የፌደሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በተሰራጨው ሪፖርት በ2015 ዓ.ም ላይ ከአትሌት ማናጀሮች ክፍያ 4 ሚሊየን 668 ሺህ 299 ማግኘቱን አመልክቶ ነበር። በ2016 እኤአ ላይ ደግሞ እስከ 4.5 ሚሊየን ብር የመሰብሰብ እቅድ ነበረው።
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በ2024 የውድድር ዘመን ላይ የአትሌት ተወካዮች በድረገፁ በቀጥታ ምዝገባ እንዲያከናውኑና ፈቃድ እንዲያገኙ ወስኗል። ቀደም ሲል ይህን አገልግሎት አባል ፌዴሬሽኖች ይፈፅሙት ነበር። የአትሌት ተወካዮች የፈቃድ አሰጣጥ ሂደት የአለም አትሌቲክስ ከፍተኛ የስራ ሃላፊ ለመሆን ከሚያስፈልጉት መሥፈርቶች ጋር ተመሳሳይ ሲሆኑ፤ ከአትሌት ውክልና ጋር የተያያዙ ልዩ መስፈርቶችም ይካተቱበታል። በአለም አትሌቲክስ የተዋቀረው ፓናል በመሥፈርቶቹ መሠረት አስፈላጊ የማጣራት ስራውን የሚያካሂድ ሲሆን የፍቃድ አሰጣጥ ሂደቱን ለማቀላጠፍም በኦፊሴላዊ ድረገፁ online portal ተከፍቷል።
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ባወጣው አዲስ መመሪያ የአትሌት ውክልና በፕሮፌሽናል ደረጃና ስነምግባሩን በጠበቀ መንገድ እንዲካሄድ ይፈልጋል። ፈቃድ የሚሰጠው የአትሌት ተወካይ ለመሆን በቅድሚያ በዓለም አትሌቲክስ ማህበር ድረ-ገጽ የሚገኘውን ቅፅ መሙላት ይኖርበታል። ከዚያም የጽሁፍ ፈተና የሚሰጥ ሲሆን ተጨማሪ መሥፈርቶችን በማሟላት ፈቃዱን በማግኘት በዓለም አትሌቲክስ ማህበር ኦፊሴላዊ ዝርዝር ውስጥ መግባት ይቻላል። የአትሌት ተወካዮች ለአገልግሎት የሚጠየቁት ዓመታዊ ክፍያን ለዓለም አትሌቲክስ ማህበር ሲሆን እንደ በቂ ካፒታል እንዳላቸው የሚያረጋግጥ የባንክ ሰነድ እንዲያስመዘግቡ ይጠየቃሉ። የዓለም አቀፍ የመድህን ዋስትና አያይዘውም ማቅረብም አለባቸው። ፈቃድ ያገኘው የአትሌት ተወካይ ከዓለም አትሌቲክስ ጋር ውል ይይዛል፤ በየውድድር መደቡ ዓለምአቀፍ ደረጃ የገቡ አትሌቶቹን ያስመዘግባል፤ ከዚያም የዓለም አትሌቲክስ በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ላይ መሣተፍ ይችላል።የዓለም አትሌቲክስ ይፋ ባደረገው መመሪያ መሠረት አንድ አትሌትና የአትሌት ተወካይ ወደ ስምምነት የሚገቡበት ከፍተኛው የጊዜ ገደብ ሁለት አመት ሲሆን ለአንድ አመት ሊራዘም ይችላል። አትሌቶችም ራሳቸውን እንዲወክሉ ይፈቀድላቸዋል።
የአትሌት ተወካዮች በሚኖራቸው ሃላፊነት ለስፖርቱ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። አትሌቶች በሩጫ ዘመናቸው በፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚሰሩ ናቸው። የአትሌቶችን ጥቅም በማስከበር ብራንዳቸውን በመገንባት ይንቀሳቀሳሉ። በማህበራዊ ሚዲያዎች አትሌቶቻቸውን ያስተዋውቃሉ። የውድድር እድሎችን በመፍጠርና መርሃ ግብር ይነድፋሉ ፤በተሳትፎ ክፍያ እና በስፖንሰርሽፕ ገቢያቸው ላይ ድርድሮችን በመጨረስ ያግዟቸዋል። በውል ስምምነቱ በተወሰነው ፐርሰንት መሰረት አትሌቶች ከሚያገኙት ገቢ የኮሚሽን ክፍያቸውን ይወስዳሉ።
የአትሌት ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መመርያው ተግባራዊ እንደሚሆን የሚገልፀው ደብዳቤ ከወጣ በኋላ የተለያዩ ቅሬታዎችን አንስተዋል። ፌዴሬሽኑ ደብዳቤውን ያወጣው በዓለም አትሌቲክስ ማህበር ውስጥ በተጣለበት የአባልነት ግዴታ ነው። ከዚህ አንፃር አንዳንድ አስተያየት ሠጭዎች ፌዴሬሽኑ ከአትሌቶችና ከአትሌት ተወካዮች ጋር ውይይት ማድረግ ይኖርበታል ማለታቸው ልክ አይደለም ። የዓለም አትሌቲክስ ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ ያፀደቀውን ህግ መቀየር ስለማይቻል ሙሉውን ተቀብሎ የውድድር ዘመኑን መቀጠል ብቻ ነው። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለአትሌቶች ተወካዮች የሚሰጠው ግልጋሎት ሙሉ ለሙሉ አልተቋረጠም። ለኤምባሲዎች ደብዳቤ የማይፅፍ ቢሆንም በፓስፖርትና ተያያዥ የኢምግሬሽን ጉዳዮች ከአትሌቶችና ወኪሎቻቸው ጋር መስራቱን ይቀጥላል። ከዓለም አትሌቲክስ ማህበር ከሚያወጣው ደረጃ ውጭ የሆኑ ውድድሮችን ለመሣተፍ በሚያስፈልገው ሂደት ላይ ፌዴሬሽኑ ተሳታፊ ነው።
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የሚንቀሳቀሱ ዋና ዋናዎቹ የአትሌቶች ተወካዮች ከ20 በላይ ሲሆኑ አሰራራቸው ግልፅነት የጎደለውና ከስፖርት ባለድርሻ አካላት ብዙ ትችት የሚቀርብበት ነው። አትሌቶችን በውድድሮች ጫና ውስጥ በመክተት ያለእድሜያቸው ሩጫ እንዲያቆሙ ያስገድዳሉ ተብለው ተወቅሰዋል፤ አትሌቶች ዜግነታቸውን ቀይረው ለሌላ አገር እንዲሮጡ በማግባባትም መሥራታቸውም ብዙዎችን የሚያበሳጭ ሲሆን ከአበረታች መድሐኒት በተያያዘ አትሌቶችን ባለመጠበቅና ጭራሽኑ ለችግሩ በማጋለጣቸው ታምተውበታል። ወቅቱን የጠበቀ እውቀትና የስልጠና መንገድ የሚከተል የአትሌት አስተዳደር ባለመፍጠርም ተነቅፈዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በትራክ፤ በልምምድ ካምፖችና ማዕከሎች አለመስፋፋት መጎዳቱ ይታወቃል። የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ያመጣው አዲስ አሰራር እንደመልካም አጋጣሚ መጠቀም ያስፈልጋል። ፌዴሬሽኑ ከአትሌት ተወካዮችና ከማናጀሮች ጋር በቅርበት የሚሰራበትን ሁኔታ መፍጠር ይኖርበታል። በኬንያ አትሌቲክስ ውስጥ ያሉ አሰራሮችና ውጤታማ ተመክሮዎችን መነሻ ማድረግ ይቻላል። ኬንያ ውስጥ በአትሌቶች ተወካዮችና የስፖርት ትጥቅና ሌሎች ምርቶች የሚያቀርቡ ኩባንያዎች የተገነቡ መሠረተልማቶች አሉ። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ መንግስትና በጣት የሚቆጠሩ አትሌቶች ከገነቧቸው የስፖርት መሠረተልማቶች በቀር የተሠራ ነገር የለም።
Saturday, 06 January 2024 21:42
የአትሌት ተወካዮችና አዲሱ የአሰራር አቅጣጫ
Written by ግሩም ሰይፉ
Published in
ስፖርት አድማስ