አንድ በጣም ጥንቁቅና የንሥር ዐይን አለው የሚባል የጉምሩክ የኬላ ተቆጣጣሪ፣ ኬላ ተሻግሮ የሚመጣ አንድ ከባድ መኪና ያያል፡፡ ሹፌሩን ተጠራጠረው፡፡ ስለዚህ እንዲወርድ ትዕዛዝ ሰጠው፡፡ ሹፌሩ ወረደ፡፡ ኬላ ተቆጣጣሪው ሹፌሩን ፈተሸ፡፡ ከዚያ መኪናውን መበርበር ጀመረ፡፡
ወንበሩን አንስቶ ስሩን አየ፡፡ ኪሶቹን ፈተሸ፡፡ የጎማ ማስቀመጫዎችን አገላብጦ አየ፡፡ ምንም የኮንትሮባድ እቃ አላገኘበትም፡፡ ስለዚህ ምንም ጥርጣሬው ባይለቀውም እያመነታ እንዲያልፍ ፈቀደለት፡፡በሚቀጥለው ሳምንት ያው ሹፌር በኬላው በኩል አቋርጦ መጣ፡፡ ያም ተቆጣጣሪ ዛሬስ አያመልጠኝም ብሎ ውስጥ ውጪውን ከፋፍቶ በረበረ፡፡ አንዳችም የኮንትሮባንድ ዕቃ አላገኘበትም፡፡ በዓመት ውስጥ ባሉት ሳምንታት በሙሉ ያ ሹፌር ይመጣል፡፡
በመጣ ቁጥር ተቆጣጣሪው ሙሉ ፍተሻ ያደርግለታል፡፡ በኤሌክትሮኒክ መፈተሻ ዘዴ - በኤክስሬይ መመልከቻ፣ ውሃ ውስጥ በድምፅ ሞገድ አማካኝነት በሚፈተሽበት በሶላር መሳሪያ ጭምር አጥብቆ ይፈትሸዋል፡፡ ሹፌሩ ግን በየሳምንቱ ማለፉን ቀጥሏል፡፡ ተቆጣጣሪው የበለጠ ይጠረጥራል፡፡ የበለጠ ይፈትሸዋል፡፡ ሆኖም ምንም በሚሥጥር የጫነው ነገር አልተገኘም፡፡ በየጊዜው ያለፍቃዱ የይለፍ ምልክት መስጠት ብቻ ሆነ ምርጫው፡፡ከዓመታት በኋላ ተቆጣጣሪው ጡረታ መውጪያው ጊዜ ደርሰ፡፡ ያ ሹፌር እንደልማዱ ከባድ መኪናውን እያምዘገዘገ መጣ፡፡ተቆጣጣሪው ሹፌሩን እንዲወርድ ጠየቀውና ከመኪናው ራቅ አድርጎ ወሰደው፡፡ ከዚያ “የኮንትሮባንድ እቃ የምታሻግር ሰው መሆንህን በደምብ አውቄያለሁ፡፡ ለመካድ ብለህ አትጨነቅ አደራህን፡፡ በጭራሽ አትሞክረው፡፡ ዋናው ነገር እኔ ይሄን ሁሉ ዓመት ፈትሼ ፈትሼ ምንም ነገር ሳላገኝብህ መቅረቴ ነው፡፡ አሁን የጡረታ መውጫዬ ሰዓት ደረሰ፡፡ ስለሆነም ይህን ሥራ ለቅቄ መሄዴ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አንተ ምንም ብትሰራ የኔ ማወቅ ከእንግዲህ ፋይዳ የለውም፡፡ ሆኖም በጣም ረቂቅ የፍተሻ ስራ አዋቂ ነው እየተባልኩ ከአንዴም ሁለቴ የምስጉን ሰራተኝነት ሽልማት ያገኘሁ ነኝ፡፡ የሚገርመው ግን የአንተን የኮንትሮባድ ስራ በጭራሽ ልደርስበት አልቻልኩም፡፡ እንደው ለህሊናዬ ብለህ ምን ዕቃ እየጫንክ እንደምታልፍ እባክህ ንገረኝ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ሹፌሩም የሚገርም መልስ ነው የሰጠው፡-
“ከባድ መኪና እያመጣሁ እሸጣለሁ፡፡ አንተ ውስጡን ትፈትሽና ራሱን ከባድ መኪናውን ግን ታሳልፍልኛለህ ጥሩ ፈታሽ ነህ፡፡”
****
የኮንትሮባንድ ዕቃ በመፈለግ ዋናውን ከባድ መኪና ስናሳልፍ ብዙ ዘመን አልፏል፡፡ በሀገራችን ዋናው እያለ ጥቃቅኑን ነገር ካላየን ስንል በርካታ ግዙፍ እንከኖች ያመልጡናል፡፡ ዐይናችን በጥቃቅኖቹ ነገሮች እየታወረ ትልቁን ነገር እንስተዋለን፡፡
በቅርንጫፉ ላይ ስንንጠላጠል ዋናው ግንድ ላይ እንዴት እንውጣ፣ ማ ይውጣ ስንል ጀንበር ትተኛለች፡፡ ዋናው ኩባያ እንዳይጠየቅ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ ላይ ማተኮር ውጤት ተኮር አያሰኝም፡፡ ዋና ባለሥልጣን እያለ ተከታዮ ላይ ማነጣጠር ደግ አይደለም፡፡ የምሥራቅ አፍሪካን ሙሉ ስዕል ሳናይ ኢትዮጵያ ብቻ ነጥለን፣ አሊያም ኤርትራን ብቻ ነጥለን ለመመልከት መጣር አንዳች የተለከፈ ደም በተወሰነ ያካል ክፍል ብቻ ይዘዋወራል ብሎ እንደማሰበ ይሆናል፡፡ (an infected blood, an infected body እንደተባለው ነው፡፡) መላውን አካል ራቅ ብሎ ማየትን የመሰለ ነገር የለም፡፡ አንዳንዴ የአገር ጉዳይ እንደውሃ ቅብ ስዕል ራቅ ብለው ካላዩት ፍንትው ብሎ ዐይን አይገባም፡፡ ሆኖም ከሩቅ አስተውለው ሲያበቁ ቀርቦ ለመዳሰስ ካልደፈሩ ደግሞ አጉል ነው፡፡ “የሩቁ የሚሳልበትን የቅርቡ አርሶ ይበላ” ይሏልና፡፡የአፍሪካ “ኩታ - ገጠም አገሮች ያንድ ሳንቲም ሁለት ገፆች ናቸው የሚባለውን ያህል፣ የየአገሩ ባለስልጣናትም “አብ ሲነካ ወልድ ይነካ” የሚለውን ዓይነት ናቸው፡፡ ኃያላኑም ቢሆኑ ከትላንት ወዲያ በቀጥታ ቅኝ አገዛዝ፣ ትላንት በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ፣ ዛሬ በኢኮኖሚ ትብብር/በግሎባላይዜሽን፣ አሊያም በስፖንሰርነት “እየተንከባከቡ” (globalized babysitting) ግዙፏን አፍሪካ ሸንሽኖ በመልክ በመልክ፣ አለያም በአቀማመጥ አቧድኖ ድህነቷን “ለማስታመም” ሌት ተቀን ይባዝናሉ፡፡ አፍሪካ ግን “ዛር ነው በሽታዋ” እንደተባለው ነች፡፡
ካገሩ ልጆች በቀር የሚያድናት ያለም አይመስል፡፡ የአፍሪካ አገሮች የየግል ኪሳቸውን ሲፈትሹ ዋናውን የኮንትሮባንድ ከባድ መኪና ይዞ የሚገባውን ሰውዬ የአለማየት ዕዳቸውን እንደተሸከሙ ይኖራሉ፡፡ ባለሥልጣናቱ በሙስና ከመበልፀግ የራቀ ርእይ ሳይኖራቸው፣ የዲሞክራሲ፣ የሰላምና የፍትህ መፈክር ይዘው “ረዥም ዘንግ ባይመቱበት ያስፈራሩበት” ማለቱን እንደ ኑሮ ዘዴ ኮርተውበታል፡፡ ሲመች በጅምላ ሳይመች በችርቻሮ መቸብቸብ ነው ነገረ-ሥራቸው ሁሉ፡፡ የአፍሪካ ተጎራባች አገሮች ችግር እንደተስቦ ከአንዱ ወደ አንዱ ተዛማች ነው፡፡ ሆኖም አንዷ የአፍሪካ አገር በጦርነት ስትለበለብ ሌላዋ የአፍሪካ አገር “በርጩማ የምታሰራ እንጨት እሳት ላይ ባለው እንጨት ትስቃለች” እንደሚባለው ተረት ነው፡፡ የሙስና ሆነ ሌላ ዓይነት የምዝበራ ተግባር ላይ የተሰማ የሚመዘበረው ነገር በጣመው ቁጥር ትኩረቱ የግል እርካታው ላይ ነውና (ሙስናዊ ውጤት - ተኮርነት እንዲሉ) እታያለሁ፣ ከዛሬ ነገ ይነቃብኛል፣ የሚል ሥጋት አይኖረውም፡፡ ሀገር ቁልቁል ባደገች ቁጥር በገዛ አበሳዋ ተተብትባ ስታቀረቅር እኔን አታየኝም በሚል በኮንትሮባንድ ከባድ-መኪና የሚጓዘው ሹሬር ቁጥር እየበዛ ሲሄድ “ኬላው ተሰበረ!” እያለች ከመዝፈን በስተቀር አስተዋይ ዜጋ ለመፍጠር የምትችል አገር አይኖረንም፡፡ ከቶውኑም ጥቃቅኑን ኪስ እየፈተሸ ሲውል ዋና ኪስ የማያይ ዐይን አገር ያስጠቃል፡፡ በየትናንሾቹ ሙልሙል “ድሎች” (ውጤቶች) ሹሙኝ ሸልሙኝ ሲል ትልቁን የሀገር ዳቦ አሰርቆ ሲያበቃ እንዳማረበት ሰው አደባባይ ወጥቶ ሲቆም ማስቀየሙን የማያስተውል በርካታ ነው፡፡ “አጥንት የሚግጥ፣ መጋጡን እጂ የጥርሱን ማግጠጥ አያይም” የሚባለውም የዚህ ብጤው ነው፡፡