Saturday, 27 January 2024 00:00

ጭፍን ስሜታዊነት- አርበኝነትና ጀግንነት አይደለም

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(4 votes)

ጭፍን ስሜታዊነትና የጅምላ ፍረጃ፣…. ጠቃሚና ውጤታማ፣ የጀግንነትና የአርበኝነት አርማ መስሎ እንደሚታየን ለመረዳት፣… የጥቂት ዓመታት ገጠመኞችን ማስታወስ ወይም ሰሞነኛ  ክስተቶችንና ዜናዎችን መታዘብ እንችላለን፡፡
ከአሜሪካ መንግስት ወይም ከአውሮፓ ህብረት በኩል የሆኑ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ ላይ ትችት ሲሰነዘሩ፣ አንዳች የሚያስቀይም መግለጫ በአንዲት ገፅ ጽፈው ሲያስነግሩ፣ እንዴት እንደሚያንገበግበን አስቡት፡፡
በቃ፣…“ታሪካዊ ጠላቶቻችን” ብለን እናወግዛቸዋን፡፡ በጅምላ፣ በደፈናውና በስሜት እንወነጅላቸዋለን፡፡ ደመኞቻችን ሆነው ይታዩናል በዝባዦች፣ እብሪተኞች፣ ዘራፊዎች፣ የቅኝ ግዛት ጥመኞች… የውንጀላና የስድብ ቃላት በእሩምታ እንለቅባቸዋለን፡፡
ከዓመት ዓመት ኢትዮጵያ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ የእህል እርዳታና የኢኮኖሚ ድጋፍ የምታገኘው ከአሜሪካ መንግስት እንደሆነ እንረሳዋለን፡፡ እስከ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ተጨማሪ ድጋፍ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ከአውሮፓ ህብረት በኩል እንደሆነም እንዘነጋዋለን፡፡
በዓለም ባንክ በኩል በየዓመቱ የሚመደበው እርዳታና ብድርም፣ በአብዛኛው ከአሜሪካና ከአውሮፓ የተለገሰ ገንዘብ መሆንስ? ይህንም አንቆጥረውም። ሊያጠፋንና አገራችንን ሊያፈርሱ ዘላለም የማያሴሩ ናቸው ብለን እናወግዛቸዋለን። ለዘላለሙ እንኮንናቸዋለን- እስኪበርድልን ድረስ።
በጭፍንና በጅምላ የማውገዝ ስሜታዊነት ይመቸናል፡፡ መጥፎነቱን  ግን ጭፍንና ችኩል ውንጀላ፣ አንዳንዴ  ውለታ ቢስነት ስለሚሆን ብቻ አይደለም፡፡ ጎጂ ስንፍና መሆኑም ጭምር ነው የጭፍን ውንጀላ ክፋቱ፡፡
ጥቃትና ጉዳት ከየትኛውም አቅጣጫ ሲመጣ፣ ከአሜሪካ ወይም ከአውሮፓ በኩል ሲመጣም በዝምታና በትህትና አሜን ብለን መቀበል እንደሌለብን አያከራክርም፡፡ ከአሜሪካም ይሁን ከአውሮፓ ህብረት በኩል፣ ከግብፅና ከሶማሊያ ወይም ከየመንና ከሱዳን በኩል፣ በየትኛው ሰበብ ኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘረ የኢኮኖሚና የጦርነት ጥቃትን ወይም ጎጂ ሀሳብን መመከት፣ መግታትና መከላከል ተገቢ ነው፡፡ ከቀና ዜጎች ይጠበቃል፡፡ ለመንግስት ደግሞ ሀላፊነቱና ስራው ነው፡፡
ጥቃትን መከላከል፣ ጉዳትን ማስቀረት የሚቻለው ግን፣ ትብብሮችንና ድጋፎችን የሚያመክን ጭፍን ጥላቻ በማግለብለብ አይደለም፡፡ ወዳጅነትን የማይዘነጋ፣ ደጋፊዎችንና ባለውለታዎችን የማይጋፋ የጥቃትና የጉዳት መከላከያ ዘዴ ሁሌም እንዳለ መገንዘብ አዋቂነት ነው። ለዚህ መትጋትም ብልህነት ነው። ግን ከባድ የዘወትር ጥረትን ይጠይቃል። ጭፍን ውንጀላና ፍረጃ ግን ቀላል ነው። ለስንፍና ይመቻል።
የተወሰኑ የአሜሪካ መንግስት ባስልጣናትና ተቋማት፣ ወይም የተወሰኑ የምክር ቤት አባላትና የወቅቱ ፕሬዚዳንት፣ ኢትዮጵያን የሚጎዳ አሉታዊ ቃል ሊናገሩ፣ ጎጂ ውሳኔ ላይ ሊፈርሙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን፣… ሁሉም የአሜሪካ ተቋማትና ሁሉም ባለስልጣናት ኢትዮጵያ ላይ ጥርሳቸውን ነክሰዋል ወይም ጦራቸውን ሰብቀዋል ማለት አይደለም፡፡
የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ኢትዮጵያን የሚጎዳ ውሳኔ ሲያመጣ የዚያው አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በብርቱ ሲቃወም አይተናል።
በህዳሴ ግድብ ዙሪያ፣ የአሜሪካ መንግስት  ጣልቃ የገባበትን መጥፎ አጋጣሚ በምሳሌነት አስታውሱ፡፡
በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል የጋራ ስምምነት እንዲፈጠር አሜሪካ በታዛቢነት የድርድር መድረክ ታመቻቻለች የሚል ሐሳብ ነበር አጀማመሩ ላይ፡፡
በእርግጥ የአሜሪካ መንግስት የድርድር መድረክ ሲያዘጋጅ፣ የሦስት አገራት ባለስልጣኖችን ለመጋበዝ ብቻውን እንዳልሆነ ግልጽ ነው። የጋባዥነት ድርሻው የድርድር ወንበሮችን የማቅረብ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት፣ ከዚያም ወደ ዳኝነት የመንሸራተት ጣጣ ሊመጣ እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡
በወቅቱ የአሜሪካ መንግስት ከግብፅ በኩል ትልቅ ውለታ የሚፈልግበት ጊዜ ስለነበር፣ በኢትዮጵያ ላይ ሚዛናዊ ያልሆነ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ምን ይጠየቃል?
በእስራኤልና በአረብ መንግስታት መካከል እርቅ ለማውረድና የወዳጅነት ስምምነት ለማፈራረም የአሜሪካ መንግስት እየተሯሯጠ የነበረበት ጊዜ ነበር ወቅቱ፡፡
“ትልቅ ታሪካዊ የሰላም ስኬት” ለማስመዝገብ እጅግ ጓጉቷል። ለዚህም የግብፅ መንግስትን ትብብር ያስፈልጋል። በዚያ ላይ እንደሌሎች የአረብ አገራት የሱዳን መንግስትም ከእስራኤል ጋር የእርቅ ስምምነት እንዲፈርም ማባበያ ጉርሻ ያስፈልጋል፡፡ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ ላይ ጫና የማሳደር ሐሳብ የመጣውም እዚህ ላይ ነው።
 የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በጋራ ከተስማሙ በኋላ እንዲከናወን…. የሚልም ነው ዋናው የመደራደሪያ ሀሳብ፡፡
 ላይ ላዩን ሲያዩት ክፉ ሀሳብ ባይመስልም ግብጽ ወይም ሱዳን እስካልተስማሙ ድረስ የህዳሴ ግድብ ባዶውን ይቀራል ማለት እንደሆነ አስቡት፡፡ ከጋራ ስምምነት በኋላ ኢትዮጵያውያን ከአባይ ወንዝ ውሃ መጠጣት ይችሉ እንደማለት ነው። የግብፅና የሱዳን ባለስልጣናት ባይስማሙ፣ ድርድሩ ለአመታት ቢጓተት፣ ግድብ ውኃ እንደጠማው እድሜውን ይጨርሳል?
መደራደሪያ ይሆናል ተብሎ የቀረበው ሐሳብ ፍርደገምድል ነው። በዚያ ላይ፣  የወቅቱ የአሜሪካና የግብፅ የውለታ ቅብብሎሽ ለኢትዮጵያ አመቺ አልነበረም - አስጊ እንጂ፡፡
እንዲያም ሆኖ፣ የኢትዮጵያ መንግስት  “አልነጋገርም፣ አልደራደርም” ብሎ በማወጅ ከአጣብቂኝ መውጣት ይችላል ማለት አይደለም፡፡ ለንግግርና ለድርድር ፍቃደኛ አልሆነም የሚል ፍረጃ ለጉዳት ይዳጋልና፡፡ አልደራደርም ማለት ለጦርነት ቅስቀሳ የሚያገለገግል ማመካኛም ይሆናል፡፡
አልነጋገርም ማለት አያዋጣም፡፡
ድርድሩ ደግሞ በሚዛናዊ ሀሳብ ላይ የተመሰረተ አልነበረም፡፡  የአባይ ወንዝ መዝጊያና መክፈቻ ቁልፍ ለግብፅና ለሱዳን ብቻ የሚያስረክብ የምርኮ ሀሳብ ነው- መደራደሪያ ተብሎ የቀረበው ሀሳብ፡፡
እና ምን ይሻላል? ማምለጫ መፍትሄ አልተገኘም፡፡ ከጥቂት የድርድር ሙከራዎች በኋላ ነገሩ ፈረሰ፡፡
ኢትዮጵያ  የስምምነት ድርድር አፈረሰች ተባለች፡፡ የአሜሪካ መንግስት የተወሰነ የእርዳታ ቅነሳ ለማድረግ ወሰነ፡፡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ጫናዎች አጋጥመዋል፡፡ ወደ አሜሪካ ከቀረጥ ነፃ ሸቀጦችን የመሸጥና የመላክ እድል የአፍሪካ አገራትን ለመደገፍ ተብሎ የተፈጠረ አሰራር ቢሆንም ኢትዮጵያ ላይ እንዲታገድባት ተደርጓል፡፡ ትልቅ ጉዳት ነው፡፡
እንግዲህ ምን ይባላል?
ያው፣ እንደተለመደው፣ “ታሪካዊ ጠላቶቻችን ዶለቱብን፤ ደመኖቻችን አሴሩብን” እያልን ማማረር፣ መራገምና መፎከር እንችላለን፡፡ ደግሞም አምርረን ተራግመናል፤ ዝተን ፎክረናል ብዙዎቻችን፡፡ ግን መፍትሄ አላመጣልንም፡፡
የተቃና የጠራ የመርህ መስመር፣ የተሰተካከለ የማያሻማ ሚዛን ለሁሉም የኑሮ መስክ ያስፈልጋልና፣ በፖለቲካም ላይ የግድ ነው፡፡
እናም፣ መጥፎ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ፣ አሳዛኝ ጉዳት ቢያደርሱም እንኳ፣ የመርህና የሚዛን ግንዛቤያችንን ለማሻሻል ልንጠቀምባቸው ይገባል።  የመፍትሄ ፍንጮችን ሁሉ መመርመርና መሞከር እንደሚኖርብን ልንማርባቸው ይገባል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ሌላ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሌላ!
በአዳራዳሪነት ወይም በታዛቢነት ከአሜሪካ መንግስት የተወከሉት ባስልጣናትና ተቋም ማንና ምን እንደሆኑ ተመልከቱ፡፡
 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አይደለም በታዛቢነት የመጣው፡፡ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ነው ለታዛቢነት የተመደበው፡፡ ከዚያም አደራዳሪ ልሁን አለ፡፡ በመጨረሻም እንደ ዳኛ ሆኖ በኢትዮጵያ ላይ እርዳታ እቀንሳለሁ፤ ድጋፍ እቆርጣለሁ ብሎ ፈረደ፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አደራዳሪ ቢሆን ኖሮ፣ ባለስልጣናት የዚህን ያህል ለግብፅ በማድላት ኢትዮጵያ ላይ ለመፍረድ አይቸኩልም ነበር፡፡ ለምን?
የአሜሪካ መንግስት ጠቅላላ ፖሊሲና ዝንባሌ ወዲህኛው ወይም ወዲያኛው ያጋደለ ቢሆንም እንኳ፣ ሁሉም ሚኒስቴሮች፣ ሁሉም ተቋማትና ባለስልጣናት አንድ አይነት አቋም አይኖራቸው፡፡ አንዱ ለዘብተኛና ዘገምተኛ ይሆናል። ሌላኛው ችኩልና ግልፍተኛ ይሆናል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ጋር የበርካታ ዓመታት ግንኙነት አለው፡፡ ወደፊትም በብዙ ጉዳዮች ላይ እንደሚገናኝ ያውቃል፡፡ ከየትኛው አገር ጋር በችኮላ የመቀያየም ዝንባሌ አያዘወትርም፡፡
ኢትዮጵያ ደግሞ ትልቅ አገር ናት፡፡
በአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም በአፍሪካ አህጉር ለአሜሪካ ሁነኛ ተባባሪ ልትሆን የምትችል አገር ናት፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር የመቀያየም፣ በአፍሪካ አገራት ዘንድ እንደ አድሏዊ ሆኖ የመታየትና የመቆጠር ፍላጎት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ጎልቶ አይታይም፡፡
አምባሳደሮቹና መልዕክተኞቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ተሰሚነት እንዲያጡ አይፈልግም፡፡ በሱዳን ወይም በሶማሊያ ውስጥ የጦርነት ችግር ሲፈጠር ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል የዕለት ተዕለት ድጋፍ ለማግኘት ይመኛል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፡፡
ሌላ ሌላውን ሁሉ ትተን፣ የውጭ አገር ዲፕሎማቶች ፉክክርን ማየት እንችላለን?
 ኢትዮጵያ ውስጥ ከሌሎች አምባሳደሮች ሁሉ ልቆና ቀድሞ በኢትዮጵያ መንግስት ዘንድ የክብር መስተንግዶ የሚያገኝ ዲፕሎማት ማን ነው? የባስልጣናት በሮችና ጆሮዎች የሚከፈቱለት ማን ነው? የቻይና ነው? የአረብ ኤሜሬትስ ነው? የአውሮፓ ነው? ወይስ የአሜሪካ አምባሳደር?
ይህን የተሰሚነት ክብር ማጣት አይፈልግም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡ እናም በትንሽ በትልቁ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመጣላት ብዙ አይቸኩልም፡፡
የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ግን፣ ከኢትዮጵያ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የለውም፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ቢቀያየም ምንም ጥቅም አይቀርበትም፡፡ ምንም ጉዳት አይደርስበትም፡፡ ጫና ለማሳደርና በችኮላ ለመፍረድ ምን ያግደዋል? ልጓም አይኖረውም፡፡
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ኢትዮጵያ የተዛባ የድርድር አጣብቂኝ ውስጥ ለመግባት ብትገደድ እንኳ፣ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ሳይሆን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን በታዛቢነት እንዲከታተል ጥያቄ ብታቀርብ ይሻል ነበር፡፡
በዚህ መንገድ ስኬታማ መሆንና ከማዕቀብ ማምለጥ ይቻል ነበር ብለን በእርግጠኛነት ለመናገር ባንችል እንኳ፣ ውጤታማ የመሆን ዕድልን የሚሰጥ የሙከራ አማራጭነቱ ግን አያጠራጥርም፡፡  
እንዲህ አይነት የመፍትሄ አማራጮች፣ በአስተዋይነት የማሰብና በጥበብ የመስራት ትጉህነትን ይጠይቃሉ፡፡ ወደ ጭፍን የጅምላ ፍረጃ የምንቸኩል ከሆነ ግን፣ የመፍትሄ መንገዶች አይታዩንም፡ እንዳይታዩን አይናችንን እንጋርድባቸዋለን፡፡
“ታሪካዊ ጠላቶቻችንና ደመኞቻችን” ብለን በጭፍን ማውገዝና መወንጀል በጣም ቀላል ነው፡፡ አስተዋይና ጥበበኛ መሆንን አይጠይቅም - ጭፍንነት፡፡ ማሰብንና መትጋትን አይጠይቅም- የጅምላ ጥላቻ፡፡


Read 1034 times