Saturday, 27 January 2024 00:00

የድምጻዊ ካሣሁን እሸቱ “ይሁን” አልበም ተለቀቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአርቲስት ካሣሁን እሸቱ “ይሁን” የተሰኘ የሙዚቃ አልበም ትላንት መለቀቁ ተገለጸ፡፡ አርቲስቱ የአልበሙን መለቀቅ አስመልክቶ ባለፈው ሰኞ  በሸራተን አዲስ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፤ ኪነት ኢንተርቴይንመንት ከአዲስ ሚውዚክ መልቲሚዲያ ጋር በመተባበር ይህን ”ይሁን” የተሰኘ  የድምጻዊ ካሣሁን እሸቱ የሙዚቃ አልበም ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡በዚህ የድምጻዊው አዲስ የሙዚቃ አልበም ላይ በግጥም እራሱ አርቲስት ካሣሁን እሸቱ፣ አንጋፋው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) እና መሰለ ጌታሁን፤ በዜማ ደግሞ አቤል ጳውሎስ፣ ድምጻዊ ካሣሁን እሸቱ፣ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) የተሳተፉ ሲሆን፤ በቅንብር አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ፣ አቤል ጳውሎስ፣ ካሙዙ ካሣ፣ ሚካኤል ሃይሉና መሃመድ ኑርሁሴን፤ በሚክሲንግ ሰለሞን ሃ/ማርያምና ፍሬዘር ታዬ፤ በማስተሪንግ ደግሞ አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ ተሳትፈውበታል፡፡አዲሱ አልበም 15 በተለያዩ ስልቶች የተቀነቀኑ ዘፈኖችን ያካተተ ሲሆን፤ ድምጻዊው በዚህ አልበም ስለ ሃገር፣ ስለ ምስጋና  እና ስለ ተስፋ ማቀንቀኑ ተነግሯል፡፡
እዚህ ለመድረሴ የጋሞ አባቶች ምርቃት የመንገዴ ጠራጊ ነው ብሎ የሚያምነው ድምጻዊ ካሣሁን እሸቱ፤ ተወልዶ ያደገው በውቧ የመዋደድና የመከባበር ተምሳሌት በሆነችው አርባምንጭ ከተማ ነው፡፡
 አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ የሙዚቃ ህይወቱን የጀመረው ቦሌ አካባቢ በሚገኘው ላየን ክለብ ከላፎንቴኖች ጋር በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ነበር፡፡ ድምጻዊው በአንቲካ ባርና ሬስቶራንት ለ6 ዓመት፣ በመሣፍንት ቤት ደግሞ ለ5 ዓመታት በድምጻዊነት መሥራቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የድምጻዊ ካሣሁን እሸቱ ”ይሁን“ የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ አልበም፣ በትላንትናው ዕለት በራሱ የዩቲዩብ ቻናል (ካሣሁን እሸቱ ካስዬ) እንደሚለቀቅ ተጠቁሟል፡፡  

Read 1194 times