Saturday, 27 January 2024 00:00

በ2024 የዓለም ግማሹ ህዝብ ድምፁን ይሰጣል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

· ዲሞክራሲ የሚፈተንበት ዓመት ነው ተብሏል
· በመላው ዓለም 4 ቢሊዮን ህዝብ ድምፁን ይሰጣል
· ከ60 በላይ አገራት ውስጥ ምርጫ ያካሂዳል
· በዓመቱ መጨረሻ ዲሞክራሲ መቀጠሉ አጠራጥሯል


የአንድ ወር ዕድሜ ብቻ ያስቆጠረው የፈረንጆች 2024 ዓ.ም በዓለማችን በታሪክ እጅግ በርካታ ምርጫዎች የሚካሄድበት ዓመት ነው። ምርጫ ብቻ ግን አይደለም። ተቃውሞ፣ ጦርነት፣ አምባገነንነት፣ ሥርዓት አልበኝነት አክራሪነት ወዘተ ዓለምን እንዳያናውጣት ተሰግቷል።  መረጃዎች እንደሚጠቀሙት በ2024 ዓ.ም ከ60 በላይ አገራት ውስጥ ምርጫዎች የሚካሄዱ ሲሆን፤ የዓለምን ግማሽ የሚወክል (4 ቢሊዮን ገደማ) ህዝብ ወደ ምርጫ ጣቢያ በማምራት፣ ለፕሬዚዳንታዊ፣ ለፓርላማና ለአካባቢያዊ ምርጫ ድምጹን ይሰጣል፡፡
ዘንድሮ የሚካሄዱ የዓለማችን ምርጫዎች ከግዙፉ የህንድ የበርካታ ቀናት የህግ አውጭ ምርጫዎች (በዓለም ላይ ትልቁ) እስከ የኢንዶኔዥያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ (የዓለም ትልቁ የአንድ ቀን ምርጫ) እንዲሁም ትን የሰሜን ሜቆዶኒያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚደርስ ተጠቁሟል።
ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒቲ እንደሚለው፤ የ2024 ምርጫ በዓለማችን ሦስተኛ ዲሞክሲያዊ አገር በሆነችው አይስላንድ የሚካሄደውን ነፃና ፍትሃዊ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫም ያካትታል፡፡ ከነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ጋር እምብዛም ትውውቅ በሌለበት ሰሜን ኮሪያም ምርጫ ይደረጋል፡፡
ባንግላዲሽ 2024ን የተቀበለችው ለዓመቱ የመጀመሪያው የሆነውን አብይ ምርጫ በማድረግ ሲሆን፣ በውጤቱም ሼክ ሃሲና ለአራተኛ ተከታታይ የሥልጣን ዘመን በጠ/ሚኒስትርነት ተመርጠዋል፡፡ ችግሩ ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ አይደለም በሚል ቅሬታ ራሳቸውን ማግለላቸው ተዘግቧል፡፡
ራስዋን በምታስተዳድረው የታይዋን ደሴት ደግሞ ባለፈው ጥር 13 ቀን 2024 ዓ.ም ለአገሪቱ ወሳኝ የሆነው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተካሂዷል፡፡ ደሴቷን በሃይል ወደ ግዛቴ እጠቀልላሁ የሚለው የቻይና መንግስት ማስፈራሪያ በምርጫው ላይ ቁጥር ጥላውን ማጥላቱ አልቀረም፡፡  በምርጫውም የገዢው  ዲሞክራቲክ ተራማጅ ፓርቲ እጩ ሆነው የቀረቡት ላይ ቺንግ ቴቱ አሸንፈዋል፡፡ የእሳቸው ድል ግን ለቻይና አስደሳችና ተወዳጅ አልሆነም። እንደውም በታይዋንና በቻይና መካከል ያለውን ውጥረት እንዳያባብሰው ነው የተፈራው።
በመጪው የካቲት ደግሞ ኢንዶኔዥያ 277 ሚ. ህዝብ ባለቤት የሆነችው አዲስ ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ተዘጋጅታለች፡፡ በዚሁ ወር ፓኪስታን የፓርላማ ምርጫ (የህግ አውጪዎች) የምታደርግ ሲሆን በዚህ መሃል ግን የተቃዋሚ መሪና የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ኢምራን ክሃን “የመንግስት ምስጢር አሾልከዋል” በሚል ተከሰው አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ እሳቸው ግን ክሱን እንዳልፈፀሙ ይሞግታሉ፡፡
በመጋቢት ወር እንዲሁ ሩሲያውያን ፕሬዚዳንታቸውን ይመርጣሉ፡፡ ታዛቢዎች ግን በሥልጣን ላይ ያሉት ቭላድሚር ፑቲን በእርግጠኝነት እንደሚያሸንፉ ከወዲሁ ተንብየዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱም የምርጫው ሂደትና የመንግስት  መገናኛ ብዙሃን በቁጥጥራቸው ሥር መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
“ፑቲን ምንም ዓይነት እውነተኛ ተቃዋሚ ሊኖራቸው አይችልም” የሚሉት የአውሮፓ ተሃድሶ ማዕከል ባልደረባ ኢያን ቦንድ፤ “እሳቸውን የሚደግፍ ድምፅ መሰጠቱን ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉት ሁሉም የአስተዳደር ማሽኖች በቁጥጥራቸው ሥር ናቸው፤ እናም ቢያንስ እስከ 2030 ድረስ፣ ሌላ ስድስት ዓመት ፑቲን አብረውን ይዘልቃሉ” ብለዋል፡፡ በዚያ ላይ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በእስር ቤት ነው የሚገኙት።
የዓለም ትልቋ ዲሞክራሲ በምትባለዋ ህንድ ደግሞ በሚያዚያና ግንቦት ወር የፓርላማ ምርጫዎች ይደረጋሉ፤ ጃናታ በቢሃራቲያ ፓርቲ (BIP)፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ሥር፡፡ አንጋፋው ህንዳዊ የፖለቲካ ጋዜጠኛ ፑሽ ሳራፍ፤ ተቃዋሚዎች በምርጫው ለማሸነፍ እንደሚታገሉ ያምናል፡፡ ነገር ግን በአንድነት ከቆሙ ነው ይላል፡፡
ህብረት ካልጠፋና በአንድነት ካልታገሉ ግን ጠንካራ አደረጃጀት ያለውን የጠ/ሚኒስትሩን ፓርቲ የማሸነፍ ዕድል አይኖራቸውም-ብሏል (አንጋፋው ጋዜጠኛ)። ሰሜን 2 ቀን 2024 ዓ.ም ደግሞ በሜክሲኮ ፕሬዚንታዊ ምርጫ ይካሄል። ይህም ለአገሪቱ አዲስ ምዕራፍ የሚያበስር ነው ተብሏል፡፡ “ምክንያቱም ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ሜክሲኮን ልትመራ የምትችልበት እድል በመፈጠሩ ነው፡፡” ይላል-የሜክሲኮው የህዝብ አስተያየት ተንታኝ ፓትሪኮ ሞሬሎስ፡፡ የሜክሲኮ ገዢ ፓርቲ የቀድሞዋን የሜክሲኮ ሲቲ ከንቲባ ክላውድያ ሼይባምን በእጩነት መርጧል፡፡
ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ህዝብ የሚወክለው የአውሮፓ ህብረትም የፓርላማ ምርጫ በሰኔ ወር እንደሚካሄድ ተጠቁሟል። የህዝብ አስተያየት እንደሚጠቁመው፤ ፈረንሳይን፣ ጀርመንንና ጣሊያንን ጨምሮ በበርካታ አገራት ውስጥ ለቀኝ ክንፍ ህዝበኛ ፓርቲዎች እንደገና ድጋፉ እያደረገ መጥቷል፡፡
“የቀኝ አክራሪ ወገኖች በአውሮፓ ምርጫ ጥሩ ቦታ ይኖራቸዋል፡፡ ይሄ ማለት ግን የአውሮፓን ፓርላማ እስከመምራት ድረስ አይደለም፤ የአውሮፓን ፓርላማ የሚመራ ማንኛውም ሰው ግን እነሱ የሚናገሩትንና የሚሰሩትን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል፡፡” ሲሉ በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ የዓለማቀፍ ፖለቲካ ፕሮፌሰር የሆኑት አናንድ ሜኖን ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡
ብሪታን በበኩሏ ከ2024 መጨረሻ በፊት ምርጫ ለማካሄድ ዕቅድ ይዛለች፡፡ የተቃዋሚው የሌበር ፓርቲ መሪ ኬይር ስታርመር፣ ለ14 ዓመታት የዘለቀውንና አምስት የተለያዩ ጠ/ሚኒስትሮች የተፈራረቁበትን የኮንሰርቫቲቭ አገዛዝን ከአመራርነት ለመግታት አልመዋል ምርጫውን በማሸነፍ፡፡
“ሁሉን ነገር የብሬክዚት ጦርነት ተቆጣጥሮት ነበር፤ ከዚያ ደግሞ ኮቪድ -19 ወረርሽኝ መጣ፤ አሁን የኑሮ ውድነት ቀውስ ውስጥ ገብተናል፡፡ የመንግስት አለመረጋጋት አጋጥሞና …. አለመረጋጋት ራሱ የፖለቲካ ጉዳይ ሆኗል” ብለዋል፤ ፕሮፌሰር ሜኖን፡፡
አሜሪካ ደግሞ በህዳር 2024 ዓ.ም በእጅጉ የሚጠበቀውንና በውዝግብ የተሞላውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ታካሂዳች፡፡ አሜሪካውያን ፕሬዚዳንታቸውን ከዲሞክራቱ ጆ ባይደን ወይም ከሪፐብሊካኑ ዶናድ ትራምፕ አንዱን እንደሚመርጡ ይጠበቃል፡፡ የጆ-ባይደን አስተዳደር ግን እስከ ምርጫው የሚያደርሰው አይመስልም። የብዙዎቹ ስጋትና ቀድሞወን ፕሬዚዳንት እስር ቤት በመወርወር ከምርጫው እንዳያስወጡት ነው። ሂደቱን ደግሞ ጀምረውታል። የፖለቲካ ተንታኞች ዓመቱ የምርጫ የመሆኑን ያህል ዲሞክራሲም የሚፈተንበት ነው የሚሉት ወደው አይደለም።
በ2024 የሚካሄዱ ምርጫዎች፣ ምርጫ በሚያካሂዱ አገራት ብቻ ሳይሆን ምርጫ በማያካሂዱም አገራት ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ሜኖን ይናገራሉ፡፡
“አዎ፤ ሁሉም ፖለቲካ አካባቢያዊ ነው፤ ነገር ግን ዓለማቀፋዊ አዝማሚያዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ የስደተኞች ጉዳይ (ኢሚግሬሽን) በዓለም ላይ በሚደረጉ በርካታ ምርጫዎች ላይ በብዛት ይገለጣል፡፡ በአውሮፓ ምርጫ ይገለፃል፤ በብሪታንያ ምርጫም ይገለጣል” ብለዋል፤ ሜሞን በሰጡት ፖለቲካዊ ትንተና፡፡
“እውን ዴሞክራሲ በአደጋ ላይ ነው?!”
ምንም እንኳን በ2024 በመላው ዓለም በ64 አገራት ምርጫ ቢካሄድም፤ ዲሞክራሲም የሚፈተንበት ዓመት ነው ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡ የዴሞክራሲ መገለጫ የሆነው ምርጫ በሚካሄድበት በዚህ ዓመት “ዴሞክራሲ በአደጋ ላይ ነው” የሚለው አነጋገር ተቃርኖ ግን አይደለም። ዓመቱን በምርጫ የጀመረችው ባንግላዲሽ፤ ጠ/ሚኒስትሯን ለ4ኛ ጊዜ የመረጠችው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከምርጫ ባገለሉበት ሁኔታ ነው ከምርጫው ቀደም ብላ የተቃዋሚ አባላትን፡፡
ሌላው ቀርቶ በዴሞክራሲ ብዙም የማትታማውና ለቀረው ዓለም አርአያ የነበረችው አሜሪካ፣ በዘንድሮ ምርጫ “ዴሞክራሲ በአደጋ ላይ ነው” እያለች ነው፡፡ የዴሞክራቱ እጩ ጆን ባይደንና የሪፐብሊኩ ዶናድ ትራምፕ እርስ በእርስ “የዴሞክራሲ ስጋት” በሚል እየተወራረፉ ነው፡፡ ሰሞኑን ፕሬዚዳንት ባይደን በምርጫ ቅስቀሳ ላይ “Democracy is on the ballot” ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል፡፡ የኖቤል የሰላም ተሸላሚና የምርምር ጋዜጠኛ ማሪያ ሬሳ በቅርቡ እንደተናገሩት፤ “ዲሞክራሲ መኖሩን ወይም መሞቱን በ2024 መገባደጃ ላይ እናውቃለን፡፡”


Read 712 times