Saturday, 03 February 2024 00:00

የአ.አ ዩኒቨርስቲ የባህል ማዕከል ያዘጋጀው አገራዊ ፌስቲቫል የፊታችን ሰኞ ይከፈታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የባህል ማዕከል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ባህል ማዕከላት የሚሳተፉበትና የፊታችን ሰኞ ጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም የሚከፈት አገራዊ ፌስቲቫል ማዘጋጀቱ ተገለፀ፡፡
ፌስቲቫሉ ለተከታታይ ሦስት ቀናት  የሚቆይ ሲሆን፤ መክፈቻው ሰኞ ከአመሻሹ 11 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ድረስ በዩኒቨርስቲው የፋውንቴይን መናፈሻ አውድ ፊት ለፊት ለዚሁ ዓላማ ታስቦ በተዘጋጀ መድረክ ላይ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደደመቀ የሚቆይ ነው ተብሏል፡፡
 “ከዚህ በኋላም ዩኒቨርስቲዎች በየተራ ሃላፊነት ወስደው የሚያዘጋጁት ክብረ-በዓል ሆኖ ይቀጥላል፡፡ በሂደትም ምስራቅ አፍሪካን፣ አፍሪካን፣ ሌሎች አህጉራትን… ደረጃ በደረጃ እያካተተ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበር “ኢንተርናሽናል ፌስቲቫል” እንዲሆን ለማስቻል ታቅዷል” ብሏል፤ የባህል ማዕከሉ ከትላንት በስቲያ ሃሙስ ባሰራጨው መግለጫ፡፡
“ይህ ሲሆን የአገራችን ዓይነተ- ብዙ ባህላዊ እሴቶች፣ ኪነጥበባዊና ሥነጥበባዊ የፈጠራ ውጤቶች፣ ብሎም ደግሞ አገራዊ የቱሪስት መስህቦች በማስተዋወቅ ረገድ የሚጫወታቸው የገፅታ ግንባታ ሚናዎች በዓይነትም፣ በይዘትም፣ በቅርፅም እጅግ በርካታ እንደሚሆኑ ይታመናል” ብሏል የባህል ማዕከሉ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የባህል ማእከል በኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ታሪክ አንጋፋውና ግንባር ቀደሙ እንደመሆኑ መጠን፣ አገራዊ ሃላፊነቱም የዚያኑ ያህል እጅግ በጣም ከባድ እንደሆነ እናምናለን ያለው ማእከሉ፤ ይህንኑ እምነታችንን መሰረት በማድረግም የሁሉንም ዩኒቨርስቲዎች የባህል ማዕከል ያቀናጀ “አገር - አቀፍ የዩኒቨርስቲዎች ባህል ማዕከላት ጥምረት”ን ለመመስረት የሚያስችለውን የፈር - ቀዳጅነት ሚና ሲጫወት ቆይቷል ብሏል፡፡
“በውጤቱም እነሆ ዛሬ በዓይነቱም ሆነ በግብሩ የመጀመሪያ በሆነው ታላቅ አገራዊ ፌስቲቫል ላይ በአንድነት ለመታደም ጫፍ ላይ ደርሰናል” ብሏል ማዕከሉ በመግለጫው፡፡



Read 555 times