Sunday, 04 February 2024 00:00

ከ19ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በፊት

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

✒️አዘጋጇ ግላስኮው 53 ሚሊዮን ፓውንድ ወጭና እስከ 67 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ
113 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጣው ኤምሬትስ አሬናና አብይ ስፖንሰሩ ሶኒ
✒️የኢትዮጵያ የበላይነት በ2022 ቤልግሬድ 9 ሜዳሊያዎች (4 ወርቅ፣ 3 ብርና 2 ነሃስ)
✒️ከግላስጎ በፊት 59 ሜዳልያዎች (31 የወርቅ፤13 የብርና 15 የነሐስ) ከዓለም 3ኛ ከአፍሪካ 1ኛ
✒️ገንዘቤ 5 የወርቅ ሜዳሊያዎች መሠረትና ኃይሌ 4 የወርቅ ሜዳሊያዎች
✒️ 3 የሻምፒዮናው ክብረወሰኖች በኢትዮጵያውያን እንደተያዙ ናቸው
19ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ3 ሳምንት በኋላ በስኮትላንድ ዋና ከተማ ግላስጎ ይካሄዳል። ሻምፒዮናው በ26 የውድድር ተግባራት 130 በላይ አገራትን የሚወክሉ 650 አትሌቶች ይሳተፉበታል። የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ስፖርት አድማስ ይህን ዓለምአቀፍ ውድድር በስፍራው ተገኝቶ እንዲዘግብ በዓለም አትሌቲክስ ማህበር ከተጋበዙ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች አንዱ ነው። ከዚህ በታች የቀረበው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናውን አዘጋጅ አገርና ከተማ መሠናዶ፤ ኢትዮጵያዊ ከሁለት ዓመት ከዓለም አንደኛ የሆነችበትን የላቀ ውጤት፤ ባለፉት 18 የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች አጠቃላይ የሜዳልያ ስብስብና በኢትዮጵያ አትሌቶች የተመዘገቡ ከፍተኛ ውጤቶችና ክብረወሰኖችን የሚዳስስ ነው።
አዘጋጇ ግላስኮው 53 ሚሊዮን ፓውንድ ወጭና እስከ 67 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ
113 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጣው ኤምሬትስ አሬናና አብይ ስፖንሰሩ ሶኒ
የዓለም ሻምፒዮናው በዮናይትድ ኪንግደም ሲካሄድ ለ3ኛ ጊዜ ሲሆን በ2003 እና በ2018 እኤአ ላይ በርሚንግሃም ሁለት ሻምፒዮናዎችን አስተናግዳ  ነበር።  ስኮትላንድ የዓለም አትሌቲክስ ውድድርን በግላስጎ በማስተናገድ የመጀመሪያዋ ነው። በ2022 ላይ በቻይና ሊካሄድ የነበረው ሻምፒዮና ከተሰረዘ በኋላ አዘጋጅነቱን ለማግኘት ከስኮትላንድ ጋር ፖላንድና ካዛኪስታን ተፎካክረዋል።
ግላስጎ  በ1990 እና በ2019 እኤአ ላይ የአውሮፓ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎችን ከማስተናገድ በቀር በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ውድድሮች መስተንግዶ ብዙም ልምድ የላትም። በ3 ቀናት ውስጥ የሚካሄዱትን ውድድሮች የሚያስተናግደው ለሰር ክሪስ ሆይ መታሰቢያ የተደረገውና በተለምዶ ”ኮመንዌልዝ አሬና” ተብሎ በሚጠራው ስታዲየም ሲሆን  በስፖንሰርሺፕ ምክንያት “ኤምሬትስ አሬና” ተብሎ ይታወቃል። እስከ 5500 ተመልካች የሚይዘው ዘመናዊ ስታድየም  በ2009 እኤአ ላይ ሙሉ  አገልግሎት መሥጠት የጀመረ ሲሆን ለግንባታው እስከ 113 ሚሊዮን ፖውንድ ወጭ ሆኖበታል።
ሻምፒዮናውን  ለማካሄድ የስኮትላንድ መንግስት እስከ 36 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲሁም የስኮትላንድ ከተማ ምክርቤት እስከ 16 ሚሊዮን ፖውንድ ወጭ ማድረጋቸውን የዘገበው   ዘስኮትማን የተባለው ጋዜጣ  ሲሆን ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ መድረክ በአገሪቱ መዘጋጀቱ ምንም አይነት ትርፍ አያስገኝም በሚል ተችቷል።ዘ ሄራልድ የተባለው ጋዜጣ በበኩሉ ከወራት በፊት ባሰራጨው ሪፖርት ሻምፒዮናው  ለግላስጎው 67 ሚሊዮን ፓውንድ የሚገመት ገቢ እንደሚያስገኝ፤ ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻ መሆኗን የሚያጠናክር ፤ እንዲሁም ዓለምአቀፍ ተቀባይነቷን የሚጨምር ይሆናል።
የሻምፒዮናው አብይ ስፖንሰር የኤሌክትሮኒክስና የቴክኖሎጂ ኩባንያ የሆነው ሶኒ ኮርፖሬሽን ነው። ለ3 ዓመት በሚቆይ የስፖንሰርሺፕፕ ውል ከዓለም አትሌቲክስ ጋር ለመስራት የተፈራረመው ሶኒ በ2025 እኤአ  ላይ ቶኪዮ እስከምታስተናግደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ይሰራል።
የኢትዮጵያ የበላይነት በ2022 ቤልግሬድ
9 ሜዳሊያዎች (4 ወርቅ፣ 3 ብርና 2 ነሃስ)
18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ2 ዓመት በፊት በሰርቢያ መዲና ቤልግሬድ ሲካሄድ ኢትዮጵያ ከ138 አገራት መካከል 9 ሜዳሊያዎች 4 ወርቅ፣ 3 ብርና 2 ነሃስ በመሰብሰብ ከዓለም አንደኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። በ18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በመወከል 14 [5 ወንድ እና 9 ሴት] አትሌቶች   በ800፣ በ1500 እና በ3000 ሜትር ተወዳድረው ነበር። በሴቶች 6 ሜዳሊያዎች [2 ወርቅ፣ 2 ብር እና 2 ነሐስ] እንዲሁም በወንዶች 3 የወርቅ ሜዳሊያዎች  [2 ወርቅ፣ 1 ብር] ተመዝግበዋል።
የወርቅ ሜዳሊያ የተጎናፀፉት 4 አትሌቶች ሰለሞን ባረጋ በ3,000 ሜትር፤ለምለም ሃይሉ በ3,000 ሜትር ፤ ጉዳፍ ጸጋዬ: በ1500 ሜትር እና ሳሙኤል ተፈራ በ1500 ሜትር ነበር። ሶስት የብር ሜዳሊያዎችን ለሜቻ ግርማ በ3,000 ሜትር፤ ፍሬወይኒ ሃይሉ: 800 ሜትርና አክሱማይት እምባዬ በ1500 ሜትር ሲቀዳጁ 2 የነሐስ ሜዳሊያዎችን ደግሞ ሂሩት መሸሻ በ1500 ሜትር እንዲሁም እጅግአየሁ ታዬ በ3,000 ሜትር ተጎናጽፈዋል።

ከግላስኮው በፊት 59 ሜዳልያዎች (31 የወርቅ፤13 የብርና 15 የነሐስ)
ከዓለም 3ኛ ከአፍሪካ 1ኛ
በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አህጉር በሁለቱም ፆታዎች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት። ባለፉት 18 የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በ17ቱ በመሳተፍ በሜዳልያ ስብስብ ከዓለም 3ኛ ከአፍሪካ 1ኛ ሆና ተቀምጣለች። ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ታሪክ 59 ሜዳልያዎችንን (31 ወርቅ 13 ብርና 15 ነሐስ) ተገኝተዋል። ባለፉት 18 የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ የኢትዮጵያ ቡድን በወንዶች ምድብ  23 ሜዳልያዎች (12 ወርቅ 3 ብርና 8 ነሐስ)  እንዲሁም በሴቶች ምድብ 30 ሜዳልያዎች (15 ወርቅ 8 ብርና 7 ነሐስ) ተመዝግበዋል።
ገንዘቤ 5 የወርቅ ሜዳሊያዎች መሠረትና ኃይሌ 4 የወርቅ ሜዳሊያዎች
3 የሻምፒዮናው ክብረወሰኖች በኢትዮጵያውያን
በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ በሁለቱም ፆታዎች ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው  5 የወርቅ ሜዳልያዎችን በ1500 እና በ3000 የሰበሰበችው  ገንዘቤ ዲባባ ናት፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ ደግሞ ከኢትዮጵያ አትሌቶች  በወንዶች ምድብ ከፍተኛውን ውጤት የያዘው በ3ሺ ሜትር 3 እንዲሁም በ1500 ሜትር 1 በድምሩ 4 የወርቅ ሜዳልያዎች በመውሰድ ነው። አትሌት  መሰረት ደፋር ደግሞ በ7 ሻምፒዮናዎች ላይ በመወዳደር በኢትዮጵያ ከፍተኛውን ተሳትፎ ያስመዘገበች ሲሆን በ3000 ሜትር 4 የወርቅ 1 የብርና 1 የነሐስ በድምሩ 7 ሜዳልያዎችን በመጎናፀፍ ደማቅ ታሪክ አስመዝግባለች፡፡ አትሌት መሃመድ አማን በሻምፒዮናው ልዩ ክብረወሰን ያስመዘገበ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሲሆን  በ2012 እኤአ ላይ በ18 ዓመት ከ61 ቀናት እድሜው በ800 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ በማሸነፍ ወጣቱ ሻምፒዮን ሆኖ ነው፡፡
የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 3 ክብረወሰኖች በኢትዮጵያውያን ተመዝግበዋል፡፡ የመጀመሪያው በ3000 ሜትር በ1997 እኤአ ኃይሌ ገብረስላሴ በፈረንሳይ ፓሪስ ላይ 7፡34.71 በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው ነው። በ2022 እኤአ  ላይ ደግሞ በሰርቢያ ቤልግሬድ በ1500 ሜትር በሁለቱም ፆታዎች የሻምፒዮናውን ሪከርዶች ሁለት የኢትዮጵያ አትሌቶች የያዙ ሲሆን በወንዶች ሳሙኤል ተፈራ 3፡32.77 እንዲሁም በሴቶች ጉዳፍ ፀጋይ በ3:57.19 በሆነ ጊዜ አስመዝግበዋል።

Read 809 times