Saturday, 10 February 2024 09:49

ጥል ያጣ ጠጅ ያድላል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በፈረንሳይ አገር፤ የውበት እንብርት በምትባለው በፓሪስ በጣም ተደናቂ ከሚባሉት እይታዎች መካከል የ”ኤፍል ታወር” (የኤይፍል ሰማይ-ጠቀስ ሀውልት እንደማለት  ነው) አንዱ ነው፡፡ ይህ ልዩ ቅርፅ ያለው የብረት አፅመ - ሀውልት የተሰራው ለ1889 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) የፓሪስ ኤግዚቢሽን እንዲሆን ተብሎ ነበር፡፡ ቁመቱ 320 ሜትር ነው፡፡ ዋነኛው መሀንዲስና መሰረታዊው የዲዛይን ነዳፊ ኤይፍል ጁስታቭ (1832-1923) ይባላል፡፡ “ኤይፍል ታወር” የሚለው ስያሜ እንግዲህ ከሰውዬው ስም የመነጨ ነው ማለት ነው፡፡ አሜሪካን አገር በኒውዮርክ የሚገኘውን የነፃነት ሐውልት (Statue of Liberty) ዲዛይን የነደፈውም ይሄው መሀንዲስ ነው፡፡
የ”ኤፍል ታወር”ን ሐውልት ዲዛይን ለማውጣት መጀመሪያ በፓሪስ ያሉ ዲዛይን አውጪዎች በሙሉ እንዲወዳደሩ ማስታወቂያ ወጥቶ ነበር፡፡ ከተወዳደሩት መካከል በወቅቱ ታላቅ ነው የሚባለው አንድ ሰዓሊም ይገኝበታል፡፡ ይህ ሰዓሊ ማንም የሚበልጠኝ የለምና የማሸንፈው እኔ ነኝ ብሎ በእርግጠኝነት ኮርቶ የተቀመጠ ነበር፡፡
ውጤቱ ግን እንደጠበቀው አልሆነም፡፡ ያልገመተው ዲዛይነር አሸነፈ፡፡ ሰዓሊው በጣም ተበሳጨ፡፡ ከቤቱ መውጣት ሁሉ አስጠላው፡፡ ከቀን ቀን የኤፍል ታወር በፓሪስ ሰማይ ግዙፉን ቅርፁን ሽቅብ መዝዞ እየተንጠራራ ይታይ ጀመር፡፡ በመጨረሻም ሀውልቱ እጅግ አምሮ ከየአቅጣጫው ጎልቶ እንደሚታይ ሆኖ ቆመ፡፡
ታዲያ ሁሌ ጠዋት ጠዋት፣ ያ ተሸናፊ ሰዓሊ ከቤቱ ሲወጣ “ኤፍል ታወር” ገዝፎ ቆሞ ያየዋል፡፡ ይናደዳል፡፡ ስለዚህ አቅጣጫ ይቀይራል፡፡ ያ የብረት ኃውልት ግን ከተቀየረው አቅጣጫም ሆኖ ሲያየው በዚያም በኩል አፍጥጦ ያየዋል፡፡ በቆመበት አቅጣጫ ሁሉ የ”ኤፍል ታወር” ይታየዋል፡፡ “ይህንን ሐውልት የማላይበት የት ልድረስ?” ይላል፡፡ በድፍን ፓሪስ በተለያየ አቅጣጫ ለመዝናናት በሄደ ቁጥር “ኤፍል ታወር” ብቅ ይላል፡፡ ሰዓሊው ጨነቀው፡፡ በየትም አቅጣጫ ቢዞር ሀውልቱን ያየዋል፡፡ ስለሆነም የመሸነፍ ህመሙን ያስታውሰዋል፡፡ ለህሊናው ሁከት ይሆንበታል፡፡ ቡና እንኳን ለመጠጣት ወጥቶ የ”ኤፍል ታወር”ን ሳያይ ቡና ቤት መቀመጥ አልቻለም፡፡
አንድ ቀን አንድ ሀሳብ መጣለት፡፡ “ለምን ከሰማይ - ጠቀሱ ሀውልት ስር ያለው ካፌ ሄጄ ቡና አልጠጣም?” አለ፡፡ ፈጥኖ ወደዚያች ካፌ ሄደ፡፡ ቡናውን አዝዞ እየጠጣ ሳለ፣ በሁሉም አቅጣጫ ቢመለከት የ”ኤፍል ታወር” ጨርሶ የለም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ እፎይ ብሎ ደስ እያለው ቡናውን ጠጣ! እነሆ በመጨረሻ ከጠላው እውነት ሥር መቀመጡ የተሻለ ሆኖ አገኘው፡፡
***
መሸነፍን አለመቀበል ለህሊና ውጋት ይዳርጋል፡፡ አንድ ወቅት ትልቅ ነበርኩና የሚበልጠኝ አይፈጠርም ብሎ ማሰብም ከፍተኛ ችግር ላይ ይጥላል፡፡ ያፈጠጠውን እውነት አልቀበልም ማለትና ከእውነት ለመሸሽ መሞከር፤ መከራ ማየትን ያስከትላል፡፡ ላያመልጡ ነገር ቁም-ስቅል ማየትን ያመጣል!
በተደጋጋሚ የሚሰሩ ስህተቶች ከአንዴ ከሁለቴ በላይ እርምት ይደረግባቸዋል ተብሎ ተመልሰው እዚያው የሚገኙ ከሆነ ወይ ከአራሚ፤ ወይ ከታራሚው፣ አሊያም ከስርዓቱ አንዳች መሰረታዊ ጉድለት አለ ማለት ነው፡፡ ይሄን ያልመረመረ እስከ ፍፃሜ ውድቀቱ ድረስ ከችግር ወደ ችግር ሲሸጋገር እንዲኖር ይገደዳል፡፡ ዕጣ-ፈንታው የሽግግር ዘመን ብቻ ይሆናል፡፡ አንዳንድ የሹመት ወንበሮች በተደጋጋሚ ሰው ተመድቦባቸው በተደጋጋሚ ፈጣን ሽረት ይደርስባቸዋል፡፡ ወንበሮቹም የሽግግር ወንበር ይመስላሉ ለማለት ይቻላል፡፡ ለመፍትሄው ሌላ ሰው የመመደብን ችግር እንጂ የአሰራሩን አሊያም የስርዓቱን እንከን የማየት ባህል ገና አልተለመደም፡፡ ይሄ የግድ መለመድ አለበት፡፡
ስብሰባ በተባለ ቁጥር “የመኖር ወይም አለመኖር” ጥያቄ የሚደቀንባቸው አያሌ ሹማምንት ናቸው! እንደ እውነቱ ከሆነ ለጊዜው ነው እንጂ እውነቱ የታወቀ እለት እርቃን መቅረት አለ- “የአይጥ ጧፍ ድመት ሲገባ ይጠፋል” ነዋ ነገሩ!
አንዳንዱ የራሱ ሳያንስ የሩቅና የቅርብ የስጋም፣ የድርጅትም ዘመዶቹን በዙሪያው ሰብስቦ ሌላ የሙስና፣ የኢ-ዲሞክራሲያዊነት፣ የኢ-ፍትሀዊነት፣ የአስተዳደር ደካማነት ማዕከል ለመፍጠር የሚውተረተር ይመስላል፡፡ እንዲህ መሰሉን ጉልበተኛ ተጠልሎ በማን አለብኝነት ዘራፍ ሲል ይውላል፡፡ “የጠገበ ሌባ ቃጭል ያንጠለጥላል” እንዲሉ ቀኑ ደርሶ “ከተከበረ” መንበሩ እስኪወርድ በአደባባይ ግነን በሉኝ ማለት የሙጥኝ ይላል፡፡ የማታ ማታ ከነዘመድ አዝማዱ የወረደ እለት ጉዳዮች ሁሉ ወደ መጀመሪያው እርከን ይመለሳሉ፡፡ (Back to Square one) ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ ማለት እንግዲህ ይሄ ነው፡፡ሌላም ብርቱ ችግር አለ፡፡ እንደ ቅዱስ መፅሐፍ ቃል የሚደረደሩ ቃላት የስብሰባ አሸንክታብ ሆነው እንዳይቀሩ ልብ ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የተሳሳተ የእድገት ስዕል ይሰጣልና መጠንቀቅ ይበጃል፡፡ ጧት ማታ የሚነበነቡት ቃላት የወረት ፀሎት እንዳይሆኑ ተግባራዊነታቸውን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ የገዛ ራስን ጥላ እስከመሸሽ፣ ደረቁን እውነት የማላይበት የት ልድረስ እስከማለት የደረሰ ጥፋት ውስጥ መዘፈቅ ይከተላል፡፡ በየቢሮው ስብሰባ ተካፍሎ መመለስ፣ ልዩ ማዕረግ ያስገኘላቸው የሚያስመስሉ አያሌ አለቆች አሉ፡፡ የስብሰባዎቹን ቃላት መደጋገምን እንደ እውቀት መለኪያ መውሰድም እጅግ አደገኛ ህፀፅ አለው፡፡ መተግበር ዋና ነገር ነው፡፡ እንዴት መተግበር እንዳለበት ማውጠንጠንም ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ በተከታታይ በታዩ ኢትዮጵያዊ ለውጦች ውስጥ ሁሉ የቃል-ጥናት ዋና መሳሪያ ሆኖ ታይቷል፡፡ የካድሬ ደቀ - መዛሙርትና የቢሮ ንቃት-ሃዋርያት ድግምት እስኪመስሉ ድረስ እንዲያንገፈግፉ መደረጋቸው አሌ አይባልም፡፡  የቢሮክራሲው ቁንጮ ቢሮክራሲውን እየረገመ ለሌላ አገር ቢሮክራሲ የቆመ ያስመስላል፡፡ አንዳንዴ ከናካቴው የሚወቀስ የጠፋበት ጊዜም ይፈጠራል፡፡ ነብሱን ይማረውና ሌኒን “ጠላቶቻችን ቋንቋችንን ወስደውብናል፣ ቅያሬ ቋንቋ ሊኖረን ይገባል” ያለው እንዲሁ ተቸግሮ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ዛሬም ያንኑ ፈለግ የያዘ ይመስላል፡፡
የሚገርመው ግን ዋናው ትኩረት የሚደረገው የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች ማለትም-የማያቋርጠው ድርቅ ላይ፣ የተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ጥፋቶች ላይ፣ ዞሮ-ገጠም የዕዳ ጣጣ ላይ፣ ስራ አጥነት፣ በሽታና ርሀብ ላይ አይደለም፡፡ ወደፊት እነሱን የሚፈቱ የሚመስሉ ነባቤያዊ ልፈፋዎች (theoretical rhetorics) የጥንትና ያሁኖቹ፣ የሩቅ ያሁኖችና የቅርብ ያሁኖች፣ ያደባባይ ቃላት ሽመናዎች (coinages) አስገራሚ ነው፡፡ አንዱ “ሂስና ግለሂስ” ሲል ሌላው “ግምገማ፤” አንዱ “ኅብረት” ሲል፣ ሌላው “ውህደት”፣ አንዱ “ግንባር” ሲል ሌላው “ቅንጅት” ወዘተ… መድብለ ፓርቲና የብዙሃን ፓርቲ፣ ኮንፈረንስና ጉባዔ፣ ውጤት - ተኮርና አመርቂ ውጤት፣ ዕሳቤና ግንዛቤ፣ አንጃና ውሁዳን፣ ማንቃትና ማስረጽ፣ በመዋቅር ማውረድና መመደብ፣ ሰብሳቢና ጠርናፊ፣ ምዝበራና ሙስና፣ ታክቲክና ስትራቴጂ፣ ሚሽንና ቪዥን፣ ፓርቲሲፔሽንና ህብረ-ሱታፌ፣… እነዚህን መሰል ቃላት እንደየአመራሩ ይፈበረካሉ፣ ይፈለፈላሉ፡፡ መረሳት የሌለበት ግን ይሄን ሁሉ ለመረዳት የሚችልና በተግባርም ማራመድ ያለበት ህዝብ ወሳኝ መሆኑን ነው፡፡ ህዝብ ያልተረዳው ነገር የፖለቲከኞች መሻኮቻ እንጂ መሬት - የያዘ (terre a terre) እና ረብ-ያለው ጉዳይ አይሆንም፡፡ የፒራሚዱ አናት ላይ ያሉ ኅሩያን ህዳጣን (ጥቂቶች ምርጦች) ብቻ ለውጥን የትም አያራምዱትም፡፡
እያንዳንዱ ድርጅት ወይም ፓርቲ በህዝብ አኗኗርና በሀገር እድገት ላይ ምን ያስከትላል ሳይል “ወቅታዊው መፈክር ያታግላል አያታግልም”፣ “ሀሳቡ ባይተገበርም ሰውን ካነጋገረ ተሳትፎን ያጎለብት የለም ወይ?” “በጉዳዩ ላይ አባላት ይተጋገላሉ አይተጋገሉም፣…” በሚል አይነት የራስን መንገድ ብቻ ባማከለ አካሄድ መጓዝ፣ ዞሮ ዞሮ ለግራ-መጋባትና ለአተካሮ ሊዳርግ፣ ኋላም ጥላቻን ሊፈጥር እንደሚችል መገንዘብ ከብዙ ውዝግብ ያድናል፡፡ አለበለዚያ ግን “ጥል ያጣ ጠጅ ያድላል” እንደተባለው ወቅታዊ አቧራ በማስነሳት ብቻ ላያቆም ይችላልና መጠንቀቅ ደግ ነው!! እንደ ሰዓሊው እውነቱ ስር ለመደበቅም ቢሆን ጊዜው መርፈድ እንደሌለበት አለመዘንጋት ነው!

Read 1411 times