Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 October 2011 15:32

በኢትዮጵያ ድርቅ አለ ረሀብም አለ፤ ኢኮኖሚውም መንግሥት እንደሚለው እያደገ አይደለም የፖለቲካ ምሕዳሩም ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠቧል ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ መድረክ የተሰጠ መግለጫ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት፤ ፕሬዚዳንቱንና ጠ/ሚኒስትሩን ጨምሮ ለ”ፓርላማ” ተብየው የፓርቲያቸው አባላት ስብስብ፤ አዲስ አዓመት ጉባኤ መክፈቻን ምክንያት በማድረግ ሰፋፊ ዲስኩሮችን ሲያስደምጡን መሰንበታው የሚታወቅ ነው፡፡ በእነዚህ ዲስኩራቸው ያልዳሰሱት የሕይወት ዘርፍ ባይኖርም፤ በተለይ ስለ ድርቅና ረሃብ፤ ስለድህነትና እርዳታ ፈላጊዎች፤ ስለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ስለታቀዱት የልማት ፕሮጀክቶች፤ ወዘተ ብዙ ከማለታቸውም በላይ ለመንግሥታቸውና ሥርዓታቸው “ጠላት” የሚሏቸውንም ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በሽብርተኛነት ከሰዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ መድረክ እና አባል ድርጅቶቹን መጨመራቸው በእጅጉ አስገርሞናል፤ ለሁኔታውም ገላጭ የሚሆነው የአበው አባባበልም “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ነው እንላለን፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተዓማኒነት ካለው ትርጉም በወጣ የፈጠራ ትንታኔም በኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ እጦትና እጥረት ስላስከተለውም ሁኔታ ሲያብራሩ ሰንብተዋል፡፡ 
የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት በአንድ ሕብረተሰቡ ውስጥ ረሃብ መኖሩን የሚያረጋግጠው መሠረታዊ ዕለታዊ ጉልበት /ኢነርጂ/ ለማስገኘት አስፈላጊ የሆነውን የምግብ መጠን በመመገብ ቀላል ተግባራትን ለማከናወን የሚያበቃ ኃይል እንዳላቸው እና፤ ክብደታቸውም ላላቸው ቁመት በዝቅተኛ ስሌት ተመጣጣኝነት አለው ወይ? የሚለውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ የሚያሳየው አርሶ አደሩ ያለችውንም ኩርማን መሬት በረሃብ ምክንያት ማረስ ያቃተውና የምግብ እጥረት ደግሞ በተለይም በህፃናት እና እናቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ ይታወቃል፤ የሕፃናት ዕድገት እንደሚቀጭጭ፤ የአእምሮአቸው እድገት እንደሚያዘግም፤ የሰውነት ተፈጥሮአዊ የመከላከያ ሃይል ባለመጎልበቱ በቀላሉ ለበሽታዎች ተጋላጭ የመሆን አደጋ እንደሚደርስባቸው፤ በረሃብ የሚጠቁ እናቶች ደግሞ የሚወልዷቸው ህፃናት ክብደታቸው አናሳ ስለሚሆን ለሞት እንደሚጋለጡ የተረጋገጡ መረጃዎች አሉ፡፡ ይህንን ሳይንሳዊ እውነታ “አንድም በረሃብ የሞተ ሰው የለም” ከሚለውና ሃላፊነት ከጐደለው የመንግሥት አባባል ጋር ስናስተያየው፣ በኑሮ ምቾት የናወዙ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ማንነት መገንዘብ ይቻላል፤ ከዚህም በላይ በዜጐች ላይ የሚከሰተውን ሞት መንስኤውን መመርመር የጤና አገልግሎቱ አካል ባልሆነበት ሀገር፤ዜጎች “በረሃብ አልሞቱም” ብሎ በማን አለብኝነት ማወጃቸው ትርፉ ትዝብት መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ በሌላ አንጻር “የለጋሾች የእህል እርዳታ መምጣት የጀመረው በሶማሌ ክልል ሰው መሞት ከጀመረ በኋላ ነው” ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሰጠው መረጃ ጋር “አንድም ሰው በረሃብ አልሞተም” የሚለው የምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ትእቢት አዘል ንግግር እንደሚጣረስ ነጋሪ የሚሻው ጉዳይ አለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ሀገራችን ውስጥ በተከሰተው የረሃብ ጉዳይ ላይ “መረጃና ማስረጃ” ይቅረብ ከተባለ የመረጃው ምንጭ አንደኛውና ብቸኛው የችግሩ ሰለባ እየሆነ ያለው ሕዝባችን ነው፡፡ ይህ ትክክለኛ “መረጃና ማስረጃ” ሊገኝ የሚችለው በየአካባቢው “ልማትን አስፋፍቻለሁ” እያለ ለሹመትና ሽልማት ከሚሽቀዳደመው ሞራለቢስ፤ ሆድ አደር የኢህአዴግ ካድሬ ሪፖርት ሳይሆን ገለልተኛ የሆነ የባለሞያ ቡድን በቀጥታ ከሕዝቡ ውስጥ ገብቶ መረጃውን ሲሰበበስብ ነው፡፡ ስነ-ምግባር አልባ ካድሬውማ ከለጋሽ ሀገሮችና ድርጅቶች የተገኘውን ዕርዳታ ሁሉ ሽጦና በልቶ፣ የተረፈውን በረሃብ የተመቱ ዜጎችን በኢህአዴግ ደጋፊነትና ተቃዋሚነት በመፈረጅ ለፖለቲካ ድጋፍ መግዣነት በማዋሉ ለሚገጽመው የአድሎአዊነት ወንጀል እንደሌለበት ጋሃድ የወጣ ጉዳይ ነው፡
ሌላው በረሃብም ሆነ በሌሎች ማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ የመረጃ ምንጭ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች መሆናቸው አጠያያቂ እንዳለመሆኑ፤ ቢቢሲ የሚባለው ዕውቅ የመገናኛ ባልደረቦች በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያለውን ሁኔታ ተዟዙረው በመቃኘትና ተጨባጭ መረጃ በመሰብሰብ፤ ተደብቆ ያለው “አረንጓዴ” የረሃብ ሁኔታ የከፋ መሆኑን ለዓለም ህብረተሰብ ይፋ ማድረጋቸው፤ መንግሥት በጉዳዩ ላይ የሚያደርገውን ፖለቲካዊ መከላከል ሚዛን ማሳጣቱን ሁሉም ይገነዘበዋል፡፡
ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ “የተራቡ ሰዎች በአሜሪካም፤ በአውሮፓም፤ አሉ በማለት የሕዝባችንን መራብ፤ መታረዝና መጠለያ አጥቶ በየሜዳው መውደቅ ላይ የሚያላግጠው ጨካኝ መንግሥት ሊወዳደሩ የማይችሉ ሁኔታዎችን በማወዳደር ላይ እንዳለ ሊገነዘበው ይገባል፡፡ በአሜሪካና በአውሮፓ የምግብ ዕርዳታ የሚሻው ወገን በተለያዩ መንግስታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት የዕርዳታ አቅርቦቱ እንደሚቀርብለት፤ በተለይም አውሮፓ ውስጥ “የምግብ ባንክ” ተብሎ በአውሮፓ ህብረት የሚደገፍ አገልግሎት እንዳለ እየታወቀ፤ የሀገራችንን ሁኔታ ከዚህ ጋር ለማወዳደር መሞከር ስሜተ-ቢስ የፖለቲካ ብልጣብልጥነት ከመሆን አያልፍም እንላለን፡፡
ሰሞኑን መንግሥት በስፋት ካናፈሳቸው ዐበይት ጉዳዮች መካከል፤ተዓማኒነት በሌላቸው የፈጠራ መረጃዎች ላይ የተመሠረቱ የልማት፤ የዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥርና ሌሎችም ከገለልተኛ አጥኚዎች ሪፖርቶች ጋር የማይጣጣሙ አሐዞች መኖራቸው አስገራሚ ሆኖ አግኝተናል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በጥቂቱ እንደሚከተለው እንጠቅሳለን፡፡
በ2001 እና በ2002 በተደረገው የእህል ጥናት ዳሰሳ፤ የ7 በመቶ ዕድገት ታይቷል ብሎ መንግሥት ሲያውጅ በገለልተኛ አካላት፤ ማለትም፤ በአለም የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) እና በአለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) የተደረገው ጥናት ግን የምርት ዕድገቱ በ4.5 በመቶ መቀነሱን አሳይቷል፡፡ የእነዚህ አሃዞች መለያየት አንደምታው እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ማንም ይገነዘበዋል፡፡ ይኸውም መንግሥት “የእህል ምርቱ በከፍተኛ መጠን ስለጨመረ የምግብ እህል እጥረት አይኖርብኝም” በማለት ዕርዳታ አልጠይቅም የሚል አቋም ለመውሰድ ምክንያት ሊሆነው ነው፡፡ በሌላ አንጻር የዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ካለው የእህል ምርት እጥረት ተነስቶ ለኢትዮጵያ እርዳታ ለማሰባሰብ እንዳይንቀሳቀስ መንግስት ይገታዋል ማለት ነው፡፡ ይህም በረሃብ የተጐዳው ሕዝብ ፈጥኖ ደራሽ ዕርዳታ እንዳያገኝ ሳንካ ፈጥሮ እንደነበር የ2003 ዓ.ም ሁኔታ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የዚህም ውጤት መንግሥት የዕርዳታ ፈላጊው ቁጥር 2.5 ሚሊዮን ብቻ ነው እያለ ቆይቶ፤ ይህ አሃዝ ከ4.5 ሚሊዮን በላይ መሆኑን ዘግይቶ ለመቀበል መገደዱና ከዚህም የተነሳ ቁጥሩ እጀግ በጣም ብዙ የሆነ ሕዝብ ለረሃብና ቸነፈር መጋለጡ ነበር፡፡ እንደዚሁም በመንግሥትም ወገን ለመጠባበቂያ መያዝ የነበረበት 405 ሺህ ሜትሪክ ቶን የእህል ክምችት በእጅጉ አንሶ ለመገኘቱ የምርት ዕድገቱ የተሳሳተ አሃዝ አስተዋጽኦ እንደነበረው መገመት ይቻላል፡፡
ላለፉት 5 ዓመታትና ከዚያም በፊት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ከ11 በመቶ በላይ ነበር የሚለው የመንግሥት መረጃ፤ ገለልተኛ የዓለም አቀፍ የፋናንስ ተቋማት ማለትም አይ ኤም ኤፍ (IMF) እና የአለም ባንክ (WB) ከደረሱበት ከ7--8 በመቶ በላይ ያልሆነ የዕድገት ትመና ከፍተኛ ልዩነት ማሳየቱን ያጤንነው ጉዳይ ነው፡፡ በእኛ ግምት የመንግሥት ሥሌት ትኩረቱ በአዲስ አበባና በሌሎችም ትላልቅ ከተማዎች ውስጥና አካባቢዎች፤ ከኢህአዴግ ጋር ባላቸው ቁርኝት ተጠቅመው የሀገሪቱን ሃብት እና ንብረት መሬት፤ የባንክ ብድር፤ ከቀረጥ ነጻ መሆን ወዘተ የሚዘርፉ ሙሰኞችን መበልፀግ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት መለኪያ አድርጎ መጠቀሙ ይሆናል፡፡ ይህም ሆኖ የኢህአዴግን የቢዝነስ ኢምፓየር (EFFORT) የሀብት ዕድገትና ክምችትን በዚህ ስሌቱ ውስጥ አስገብቷል ብሎ ለመገመት ደግሞ የመረጃ ማዕቀቡ እንደማያስችለን መላው ሕዝባችን ይገነዘበዋል እንላለን፡፡
ቀጣዩን የ5 ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገት በሚመለከት መንግሥት “በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን” (GTP) አማካይነት ከ11-15 በመቶ ዕድገት አስመዘግባለሁ የሚለው እወጃው ደግሞ ከ6ኛ8 በመቶ በላይ ዕድገት ሊታይ አይችልም ከሚለው የ IMF እና WB ጣምራ አጥኚ ቡድን ያለመጣጣሙ ኢህአዴግና መንግሥቱ ተዓማኒነት የሌለው ተስፋ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እየመገቡት መሆኑ በሁሉም ወገኖች ዘንድ ሊታወቅ ይገባል እንላለን፡፡
የምግብ እህል እርዳታን በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ውስጥ የሚፈልጉ ተረጂዎችን በሚመለከትም፣ የኢህአዴግ መንግስት አሃዝና የዕርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች አሃዝ በስፋት የተለያዩ መሆናቸው በእጅጉ ያሳስበናል፤ ይኸውም የመንግሥት ስሌት ተረጂው ሕዝብ ቁጥር ከ1.3 ሚሊዮን በላይ አይበልጥም ሲል፤ የእርዳታ ድርጅቶች ትንበያ ከ3.4 ሚሊዮን በላይ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ እንደዚሁም የዕርዳታ ፈላጊው ቁጥር በአርሶ አደሩና በአርብቶ አደር በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚቀንስ መንግሥት ሲተነብይ፤ የእርዳታ ሰጪዎች ቀመር ግን የአርብቶ አደሩ ተረጂ ቁጥር መቀነስ እንደማይችል ያሳያል፡፡ ይህ የተረጂው ቁጥር በስፋት ያለመቀነሱ እውነታ ከ11-15 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዘግባለሁ ከሚለው የመንግሥት የተጋነነ ፖለቲካዊ መረጃ ጋር ያለመጣጣሙ፣ በረሃብ ሊጠቃ የሚችለውን ሕዝብ ለመታደግ በቂ የቅድሚያ ዝግጅት እንዳይደረግ ስለሚያደርግና አንደምታው የከፋ ስለሚሆን መድረክን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡
ሊከናወኑ ስለመቻላቸው አሳማኝ መረጃ በበጀት የተደገፈ ዕቅድ ያልቀረበላቸው፣ እርካሽ ሙገሳን በመሻት የሚወጠኑ የልማት ፕሮጀክቶች ጉዳይ ባዶ ተሰፋ የመሆናቸው ሁኔታ በ IMF/WB አማካሪዎች ተተችቷል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡፡
የገጠር መንገዶች ግንባታ 75 ሺህ ኪሎ ሜትር ሆኖ እያንዳንዱን ቀበሌ ለማዳረስ የተገባው ቃል ፤በተግባር እስካሁን በሚታየው ስንነሳ የማይሳካ ተስፋ ሆኖ ይቀራል የሚል ስጋት አለን፡፡
የባቡር መስመር ዝርጋታን በሚመለከት 2400 ኪሎ ሜትር እናከናውናለን የተባለው የተጋነነ ዕቅድ ሆኖ እንደሚቀር መገመት አይከብድም፡፡
የአርሶ አደሩን የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጥና የማምረት አቅሙን በእርሻ ግብዓትና በመስኖ የመደገፍ ተግባር በዕቅዱ ውስጥ ገዝፎ የተቀመጠ ሆኖ ሳለ፤ በተግባር ግን ከይስሙላነት ያለማለፍና አርሶ አደሩ በይዞታነት ያለማው መሬቱና ንብረቶቹ ለዋስትና የያለመብቃታቸው ሁኔታ እና የግብርና ግብአቶች አቅርቦት ነጻ ባለመሆን በኢህአዴግ የንግድ ድርጅቶች ቁጥጥር ሥር መሆንና ስርጭቱ በፖለቲካ ተፅዕኖ ስር መውደቅ ለዕድገት የማያበቃ መሆኑ አሳሳቢ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ለምግብ እህል ማምረቻ የሚሆኑ በመቶ ሺህ ሄክታሮች የሚገመቱ ለምና ውሃ ገብ መሬቶችን ለውጭ ባለሀብቶች ነፃ ሊባል በሚችል ዋጋ፤ ፤ለረዥም አመታት፤ አሳልፎ መስጠታቸውና ምርቶቹም ለውጭ ፍጆታ የመሆናቸው ጉዳይ፤ የሀገራችን ሕዝብ በምግብ ራሱን የመቻሉን ዕድል ያመከነው መሆኑ እጅግ አሳስቦናል፡፡
ይህ እርምጃ ለሀገርና ሕዝብ የሚያስገኘው ጥቅም እጅግ አናሳ የመሆኑ ጉዳይ ስጋታችንን በእጅጉ ያጐላዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፡-
በደኖች፤ በዱር እንስሳት፤ በወንዞች ላይ በሚያደርሱት ጉዳት የአካባቢ የተፈጥሮ ውድመት የሚያደርሱ መሆናቸው፤
አርሶ አደሩን የሚጠቅሙና ለአነስተኛ እርሻ የሚውሉ የማምረቻ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡ መሆናቸው ፤
በጉልበት ሠራተኝነት ለሚሠማራው ዜጋ የሚከፍሉት ደመወዝ ዝቅተኛ መሆኑን፤
ለምግብ እህል ማምረቻ ሊውል የሚችለውን ለም መሬት ለባዮ ፊውል (Bio-fuel ) ማምረቻ እርሻ ማዋላቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በዚህ ረገድ በደመ-ነፍስ አመራር በሀገሪቱ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርሱ ከሰነበቱ በኋላ በቅርቡ ዲስኩራቸው “ሁኔታውን እያጣራን እርምጃ እንወስዳለን ወዘተ” ማለት መጀመራቸው በሀገሪቱ መልካምና ብቃት ያለው አስተዳደር ለመጥፋቱ ጉልህ ማሳያ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር መጥፋት በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ በተጨማሪ የማህበራዊ ፍትህን በማሳጣት፤ ዜጎች ለሀገሪቱ ሀብት በፍትሐዊነት ተደራሽ እንዳይሆኑ በተለይም በየከተማዎቹ የመኖሪያ ቤት በማጣት በየሜዳው እየተገፉ መሆናቸው እጅግ አሳሳቢ ሆኗል፡፡
6. ከ40 በመቶ የማያንሰውን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር የማያበቃ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እየተከተሉ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን (GTP) አማካይነት የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ከድህነት ስለማውጣት ማውራት ተገቢ እንደማይሆን የአይ.ኤም. ኤፍ እና ዓለም ባንክ አማካሪዎች ቡድንን ሂስ መድረክም የሚጋራው ነው፡፡
7. የመድረክ አባል ድርጅቶች ለረዥም ዓመታት፤ መድረክ ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት “ግብርና መር ኢንዱስትራላዜሽን” የሚባለውን የኢሕአዴግ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሲተቹ እና አማራጫቸው ግብርናንና ኢንዱስትሪው ጐን ለጐን እኩል ትኩረት ተሰጥቷቸው ከአገልግሎት ዘርፉ ጭምር የሚስፋፉበት ፖሊሲ እንዲቀየስ ሲታገሉ የመቆየታቸው ትክክለኛነት በቅርቡ በአይ.ኤም/አፍ እና የአለም ባንክ አማካሪ ቡድን መረጋገጡ፤ ኢህአዴግ “ተቃዋሚዎች አማራጭ ፖሊሲ የላቸውም ወዘተ” የሚለውን ፕሮፓጋንዳ እርቃኑን ማስቀረቱ ሊጤን የሚገባ ክስተት ነው፤ ስለሆነም ኢህአዴግ የኢንዱስትሪ ሴክተሩን በማስፋፋት ረገድ የሚያሳየው ዳተኝነት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እየገደለው መሆኑ ታውቆ፣ በዚህ ረገድ ለፖሊሲ ለውጥ የምናደርገው ትግላችን ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እናምናለን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጥቅምት 9 ቀን 2004 ዓ.ም በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው፣ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በፓርላማው መክፈቻ ዕለት የመንግሥትን አቋም አስመልክተው በአደረጉት ንግግር ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያቸው የዳሰሱአቸው ጉዳዮች በርካታ ቢሆኑም በተለይ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ምህዳርን፤ ሽብርተኝነትን፤ መልካም አስተዳደርንና ሙስናን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ እንደተለመደውም በሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና በግል ፕሬሱ ላይ ጠንካራ ዘለፋና ዛቻ አሰምተዋል፡፡ በዚህ ከአንድ የሀገር መሪ በማይጠበቅ ንግግራቸው ላይ ልዩ ትኩረትና ሰፊ ጊዜ ወስደው የተናገሩት፣ መድረክን በማብጠልጠልና በማስፈራራት ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፓርቲያቸው ኢህአዴግ፤ በሀገራችን ያለው ፖለቲካዊ ምህዳር ችግር እንደሌለበትና የጨዋታ ሕግን ተከትሎ መሄድ ለፈለገ ሁሉ ምቹ እንደሆነ ደጋግመው ለማስረዳት ሞክረዋል፤ ሆኖም በተጨባጩ የሚታየው ሁኔታ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ፓርቲያቸው ኢህአዴግ ኢትዮጵያ በአንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭነት መመራት እንዳለባት ከወሰነ ውሎ አድሯል፤ ከኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር ውጭ ያለው ፖለቲካ ሁሉ “የጥፋት ፖለቲካ ነው” በማለት ያለሃፍረት በአደባባይ ለፍፈዋልና፤ ይህን አቋማቸውን ተግባራዊ ለማድረግም ባለፉት 20 ዓመታት የዴሞክራሲን ደብዛ የሚያጠፉ በርካታ ተከታታይ እርምጃዎች ወስዷል፤ በተለይ ከምርጫ 97 ዓ.ም በኋላ በፓርቲያችን ውስጥ ከተፈጠረው ድንጋጤ በመነሳት የፖለቲካ ምህዳሩን ሙሉ በሙሉ የሚዘጉ እርምጃዎችን ወስዷል፤ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ማዕከላት ይሆናሉ ብለው የገመቷቸውን ሁሉ የሚያጠፉና የሚቆጣጠሩ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ የሲቪል ማህበረሰቡንና የንግድ ማህበረሰቡን፤ የአካዳሚ ማህበረሰቡን፤የግል ጋዜጦችና እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ ጭራሽ የሚያጠፉ ወይንም የሚቆጣጠሩ አዋጆችና መመሪያዎች አጽድቀው ተግባራዊ አድርገዋል፤ በእነዚህ አዋጆችና መመሪያዎች አማካይነት ተፎካካሪ የፖለቲካ ማዕከላትን መቆጣጠር ሲያቅታቸው ሕገ-መንግሥቱን በሚጥስ አግባብ፣ የእስር የግድያና ድብዳባ እርምጃ በመውሰድ ሊያጠፏቸው ሞክረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፓርቲያቸው ኢህአዴግ የፖለቲካ ምህዳሩ ችግር የለበትም ቢሉም በተለይ በአሁኑ ጊዜ ከማናቸውም ወቅት በላይ ምህዳሩን የሚያጠቡ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ሕሊና ላለው ዜጋ ሁሉ ግልጽ ነው፡፡ የተደራጁ ሃይሎችና ማዕከላትን መቆጣጠሩ አልበቃ ብሏቸው እያንዳንዱን ቤተሰብና እያንዳንዱን ዜጋ ለመቆጣጠር ያስችለናል ያሉትን ስልት ነድፈው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ የልማት ሰራዊት ኔት ወርክ ብለው የሚጠሩት አደረጃጀት የዚሁ እያንዳንዱን ቤተሰብ እና ዜጋ ለመቆጣጠር የቀየሱት ስልት ማስፈጸሚያ ነው፡፡ መንደር፤ ጎጥ ቤተሰብ፤ ትምህርት ቤት፤የሥራ ቦታ፤ወዘተ በየአምስት ሰው እየተደራጀ እያንዳንዷን እንቅስቃሴ ሪፖርት እንዲያደርጉ እያደረጉ ነው፡፡ ቤተሰብ ሳቀይር በአንድ ጠርናፊ እየተማከለ እያንዳንዷን የእንቅስቃሴ ውሎ ለበላዩ እንዲያስተላልፍ ይደረጋል፡፡ መጠሪያው ልማት ቢባልም ዓላማው መረጃ ማሰባሰብና ማቀበል ስለሆነ ከስለላ መዋቅርነት የተለየ አይደለም፡፡ ታዲያ በዚህ አግባብ እያንዳንዱን ዜጋ ለመቆጣጠር እየተሠራ ባለበት ወቅት፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ችግር የለበትም ብሎ መናገሩ እጅግ የሚያስገምትና የሚያሳፈር ነው፡፡ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብን በተመለከት የመጨረሻ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው በቅርቡ በሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ነጻ ጋዜጦች ላይ በስመ አሸባሪነት የተጀመረው ዘመቻ ግልጽ ማስረጃ ነው፡፡ የመድረኩ የአመራር አባላት የሆኑ በእነ አቶ በቀለ ገርባ፤አንዱአለም አራጌ፤ አቶ ኤልባና ሌሊሳ ወዘተ የተወሰደው እርምጃና እንደነ ርዕዮት ዓለሙ የመሳሰሉት ጋዜጠኞች ላይና በሌሎችም በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተቀናቃኝን የማጥፋት እንቅስቃሴ አካል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከታሰሩ አራት ወራት ባስቆጠሩ አባሎቻችን ላይ እስካሁን ድረስ ማስረጃ እያሰባሰብን ነው እየተባለ ጉዳያቸው ለፍርድ ቤት መቅረብ አለመቻሉ፤ ኢህአዴግ ያሰራቸው በቂ ማስረጃ ኖሮት ክስ መስርቶባቸው ሳይሆን ከአሠራቸው በኋላ ወንጀለኛነታቸውን የሚያሰኝ ማስረጃ እያሰባሰበ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ኢህአዴግ ራሱ ከሳሽ እራሱ መስካሪ፤ አስመስካሪና ራሱ ወሳኝ በሆነበት ሂደት ደግሞ አንዱን ንፁህ ዜጋ ከሶ ማስመስከርና “ወንጀለኛ” ነው ብሎ ማስፈረድ የሚያቅተው አይሆንም፡፡ ስለሆነም ነው ጠ/ሚኒስትሩ ለይስሙላ እንኩዋን የፍርድ ቤቶችን ክርክርና ውሳኔ ሳይጠብቁ እነዚህን ተጠርጣሪ የሚሏቸውን “አሸባሪ” በማለት የፈረጇቸው፤ ይህ ቅድመ ፍርድ ቤት አቋማቸው ደግሞ ፍርድቤቱም ከሳቸው ቃል የማይወጣ እንደሆነ ያመለክታል፡፡
ኢህአዴግ የፖለቲካው ምህዳር ከማንኛውም ጊዜ በላይ እንዲጠብና ጭራሽ እንዲዳፈን ለማድረግ ቆርጦ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ የሚወስደው እርምጃ በእነዚህ የመድረክ አባላትና ጋዜጠኞች ላይ ብቻ ተወስኖ አልቀረም፤ በሃቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይ በመድረክ ላይ የታወጀው የማጥፋት ዘመቻ፤ በየቀኑ በየክልሉና በየመንደሩ እየተካሄደ ነው፡፡ እንዲያውም በዚህ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አንዱ ግብ መድረክን የመሳሰሉ ተቃዋሚዎችን ማጥፋት እንደሆነ የደህንነት ሰራተኞቻቸውና ካድሬዎቻቸው በይፋ ሲያወሩ ይደመጣሉ፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱን የድርጅት አባል እየተከታተሉ ከተቻላቸው በማባበል ካልሆነ ደግሞ በማስፈራራት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ እንዲታቀብ ለማድረግ እየጣሩ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም በዓረና እና በአንድነት አባላት ላይ የተፈጸሙት የእስርና ከሥራ የማባረር እርምጃዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የዓረና ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆነው አቶ ጐይቶም ፀጋዬ ያለአግባብ ከአስተማሪነት ሥራው ተባርሯል፡፡ የዓረናን በራሪ ወረቀቶች ሲያሰራጭ የነበረው አቶ አማረ ተወልደም በሁመራ ለእስር ተዳርጓል፡፡ ሌሎችም በርካታዎች በደህንነት ሠራተኞች እየተጠሩ ከባድ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በሌሎች የመድረክ አባል ድርጅቶች አባላት ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና ወከባ ተመሳሳይ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ ይህን በመድረክ አባላት እና በሌሎች ሀቀኛ ድርጅቶች አባላት ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በንግግራቸው አለመጥቀሳቸው የትዝብት ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ትልቅ ሀገራዊ ሁኔታ ወደጐን ትተው “አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በሽብር ተግባር ተሰማርተዋል” ማለታቸው ከነባራዊ እውነታ ምን ያህል የራቁ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ፓርቲያቸው በተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅት አባላትና በሕዝቡ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ሽብር ወደ ጎን ትተው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በተለይ መድረክን በሽብረትተኝነት መክሰሳቸው የሚያስገርም ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተለይ ደግሞ መድረክን በሻቢያ ነጭ ለባሽነት ለመክስስ ሞክረዋል፡፡ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” እንዲሉ በሻዕቢያ ነጭ ለባሽነት የሚጠረጠሩትና ሀገር የሚውቃቸው የኢህአዴግ መሪዎች ሆነው እያለ መድረክን በዚህ ለመክሰስ መሞከሩ አሳፋሪ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፤ ኢህአዴግ ከሻዕቢያ ጋር ለመታረቅ እየተማጸነ ባለበት በአሁኑ ጊዜና እንኩዋን መድረክ የኢትዮጵያን ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ የአልጀርሱ ስምምነት መሰረዝ እንዳለበትና የአሰብ ወደብ ባለቤትነት ጉዳይ ድርድርና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሊደረግበት እንደሚገባ የፖለቲካ አቋም የያዘ ፓርቲ ነው፡፡ በመሆኑም መድረክ የሻዕቢያ ተላላኪ ሊሆን ቀርቶ ከሻዕቢያ ጋር ሊያስማማው የሚችል ባህሪና አቋም የለውም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በሻዕቢያ ተላላኪነት እና ከሻዕቢያ ጋር በማበር በሽብር ፈጣሪነት ሊከሱት እየሞከሩ ያሉት መድረክ፤ ሻዕቢያ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ምን ያህል እንደሚጠላ ስለሚያውቁ ብቻ ነው፡፡ በዚህም ይህን ሕዝብ በሻዕቢያ ላይ ያለውን ጥላቻ ወደ መድረክ ለማዞር የቀየሱት ስልት ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ሙስናን ከስሩ ስለማድረቅና መልካም አስተዳደር ስለማስፈን ተናግረዋል፡፡ የምክር ቤት ስብሰባዎችና የኢህአዴግ ስብሰባዎች በተካሄዱ ቁጥር እየባሰበት ስላለው ሙስናና፤ ብልሹ አስተዳደር ያልተነሳበት ወቅት የለም፤ እንደተለመደው መልካም አስተዳደርና ሙስናን ከምንጩ እናደርቀዋለን፤ ብልሹ አስተዳደርን እንመነግላለን፡፡ የሚል ነው፡፡ የዚህ አይነት የተለመደ ተስፋ ቢሰጥም “የአሣ ግማቱ ከጭንቅላቱ” እንደሚባለው ለተንሰራፋው ሙስና ዋና አራማጆች የኢህአዴግ አመራሮችና ሹማሙንቶቻቸው እንዲሁም የውሸት መፈክር የሚያስተጋቡት ካድሬዎቻቸው ሆኖ እያለ ራሳቸውን ያርማሉ ማለት ጭራሽ ዘበት ነው፡፡ የብልሹ አስተዳደር አራማጆችም እነዚህ በዘመድ አዝማድና በአካባቢ ልጅነት የሚሠሩ ሰዎች የሚፈጥሩት ችግር ነው፤ ደጋግመን እንዳልነው ሙስና እራሱን መታገል አይችልም፤ ብልሹ አስተዳደርም ራሱን መታገል አይችልም፡፡ ሙስናና ብልሹ አስተዳደር ሊወገዱ የሚችሉት እውነተኛ ዴሞክራሲ ሲሰፍን፤ ዜጐች በነጻነት ማሰብና መደራጀት ሲችሉ የሕግ የባላይነት ሲከበር ነው፡፡ ኢህአዴግ የነዚህ ሁሉ ፀር እንጂ አራማጅ ፓርቲ ሊሆን አልቻለም፡፡
ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤ ወደፓርላማ በሚቀርቡበትና ጋዜጣዊ መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት ሁሉ ተቃዋሚዎቻቸውን ለማሰርና ለማጥፋት እንደሚሹ ሳይገልፁ አያልፉም፤ በተለይም ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል በማራመድ የሚታወቀውንና ነገር ግን ለፓርቲያቸው ማጐብደድ ያልቻለውን መድረክ ሲዘልፉ ይደመጣሉ፡፡ ከዚህ ሌላ ተዳክመው ያሉትን ነፃ ጋዜጦች ይረግማሉ፤ የዚህ ሁሉ መነሻ ፓርቲያቸው ሙስናን መዋጋት፤መልካም አስተዳደርን ማስፈን ሰብአዊና ዴሞክራሲዊ መብቶችን ማስከበር የሕግ የባላይነትን ማስጠበቅ ስላቃተው ነው፤ ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂው ሀገርን በፍጹም አምባገነንነት እያስተዳደረ ያለው አገዛዛቸው መሆኑን በመሸሽ፣ በተቃዋሚዎች ላይ ለማላከክ ስለሚጥሩ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሕን ማረጋገጥና የዜጎችን ክብር ማስጠበቅ አቅቶታል፤ ስለሆነም ነው የኢህአዴግ ስርዓተ-መንግሥት በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሳይውል ሳያድር መተካት አለበት የምንለው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብና የኢህአዴግ አባላት መገንዘብ ያለባቸው በሀገራችን ሥር እየሰደደ ላለው ችግር ተጠያቂው ኢህአዴግ እንጂ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያለመሆናቸው ነው፡፡
በመሆኑም፤ መድረክ የኢህአዴግ እስር፤ ወከባና ጫና ወዘተ ሁሉ ተቋቁሞ በሀገራችን መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚታገል፣ ሃላፊነት የሚሰማውና የሰከነ አመራር ያለው ድርጅት እንደሆነ መላው ሕዝባችን የሚያውቀው ጉዳይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል እንላለን፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ
ጥቅምት 17 ቀን 2004 ዓ.ም
አዲስ አበባ

 

Read 2715 times Last modified on Saturday, 29 October 2011 15:37