Saturday, 02 March 2024 21:01

ጥርስ የሌላት፣ ጥርስ ያላትን ነክሳ፣ አነካከስ ታስተምራለች

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አንድ ታዋቂ የንጉሥ አጫዋች፤ የንጉሱ ባለሟሎች፣ መሣፍንቱና መኳንንቱ እንዲሁም ባለሌላ ማዕረግ ባለሥልጣናት በሚገኙበት፣ ከግብር በኋላ በሚካሄደው የመዝናኛ ሰዓት እንደ ሁልጊዜው ጨዋታ ያመጣል፡፡ ከመጠጡ ገፋ ተደርጎ የሚጠጣበት ሰዓት በመሆኑ ሳቁና ውካታውም ለከት የለውም፡፡ እንደልብ ይጮሃል፡፡ ከአፍ ለቀቅ ይባላል፡፡ ታዲያ ያ አጫዋች፣ በጥያቄ መልክ ነው ለዛሬ ቀልዱን ያቀረበው፡፡
አጫዋች፡- “ከዝቅተኛ መደብ ያለ ሰው ለምሳሌ ኩሊ፣ እንጨት - ፈላጭ፣ መንገድ - ጠራጊ ወዘተ ሲሰክር ምን ይባላል?” አንዱ ባለሟል ይመልሳል፡- “ጢምቢራው ዞረ! ተንጀባረረ ነዋ የሚባለው” ሁሉም ሳቀ፡፡
አጫዋች፡- “ትክክል ነው፡፡ እሺ፤ በመካከለኛው መደብ ያለ ሰው፤ ለምሳሌ ዝቅተኛ የመንግስት ሰራተኛ፣ ትናንሽ ነጋዴ፣ ወታደር ወዘተ ሲሰክር ምን ይባላል?”
አንዱ ይመልሳል፡- “ጣጥ አለ! ጢዝ አለ! ድብን አለ!” ይባላል አለ፡፡ ሁሉም ሳቁ፡፡
አጫዋቹም፡- “በትክክል ተመልሷል!” አለና ወደ ጥያቄው አመራ፡፡ “እሺ የመካከለኛው መደብ አባላት እንደ መካከለኛ ነጋዴ፣ መኮንኖች፣ የመ/ቤት የቢሮ ኃላፊዎች፣ ምሁራን ሲሰክሩስ ምን ይባላሉ?”
አንድ ትልቅ ሰው ይነሱና ይመልሳሉ፡- “ሙክክ ብሏል! እሳት ገብቶታል! እንግሊዝ ይደባልቃል!” አሉ፡፡
አጫዋቹም፡- “በትክክል ተመልሷል!” አለና ወደሚቀጥለው ጥያቄ ሄደ፡፡ “እሺ የከፍተኛው መደብ አባላት ማለትም መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ሚኒስትሮቹ፣ ስመ-ጥሮቹ ነጋዴዎቹ ወዘተ ሲሰክሩ ምን ይባላሉ?”
ከመኳንንቱ አንዱ ተነሱና መለሱ፡- “ሞቅ ብሏቸዋል! ጨዋታ ጨዋታ ብሏቸዋል! ትንሽ ወሰድ አድርገዋል! ትንሽ መሸት አድርገው ነበር!” ይባላል አሉና ተቀመጡ፡፡ ሁሉም ሳቁ፡፡
አጫዋቹ፡- “ብራቮ! በትክክል ተመልሷል!  ወደ መጨረሻው ጥያቄ እንሄዳለን፡፡ ንጉሱ ሲሰክሩስ ምን ይባላሉ?”
ሁሉም ፀጥ አሉ፡፡ እጅ የሚያወጣ ሰው ጠፋ፡፡ “ሞክሩ! ሰዓት አላችሁ” ቢል ትንፍሽ የሚል ጠፋ፡፡ ስለዚህም አጫዋቹ፤
“እሺ፤ እኔ እራሴ እመልሰዋለሁ” አለና “ንጉሡ ሲሰክሩ ‘አልጠጡም፤ ግን ደስ ብሏቸዋል’ ነው የሚባለው” አለ፡፡ ሰው በሳቅ ሞተ፡፡
ንጉሡ ስለድፍረቱ ተናደው አጋፋሪው ፀጥታ እንዲያስከብር አዘዙ፡፡
ንጉሥ፡- “አሁን ላጠፋኸው ጥፋት የማያወላዳ ቅጣት ያስፈልግሃል!”
አጫዋች፡- “ምን አጠፋሁ ንጉሥ ሆይ?”
ንጉሥ፡- “አስቀህብኛል!”
አጫዋች፡- “የሳቁት የእርስዎ ሰዎች’ኮ ናቸው፣ የተሰበሰበው ህዝብ’ኮ ነው፤ ንጉሥ ሆይ?!”
ንጉሡ የባሰውን ስለተናደዱ ግንባራቸው ላይ ያሉ ስሮቻቸው ሁሉ እንደቀንድ ቆሙ፡፡ ማንም ያልገመተው ፍርድም ፈረዱ፡፡
“1ኛ ስለ አጫዋቼ - አሁን ላጠፋኸው ጥፋት ሞት ተፈርዶብሃል፡፡ ሆኖም የምትሞትበትን መንገድ የመምረጥ እድል ሰጥቼሃለሁ!
2ኛ የሳቃችሁ ባለሟሎቼና ሹማምንቶቼ በሙሉ፤ የንብረታችሁን አንድ አራተኛ ለእኔ ገቢ ታደርጋላችሁ!
አሁን አጫዋቼ፤ የምትመርጠውን አሟሟት ተናገር” አሉ፡፡ አጫዋቹም ተነስቶ፤
“ንጉሥ ሆይ፤ እኔ የምመርጠው አሟሟት አርጅቶ መሞትን ነው!”
ንጉሡ ከት ብለው ስቀው “የመረጥከው የሞት አይነት ተፈቅዶልሃል!” አሉትና ወደ መኳንንቱና መሳፍንቱ ሲዞሩ፤ ሁሉም ደንግጠውና አኩርፈው ቆመዋል፡፡ ንጉሡም “በዚህ በአሁኑ ቀልድ ከእኔ ጋር ባለመሳቃችሁ የንብረታችሁ ሩብ ይወረሳል ብዬ ፈርጄ የነበረው ተሻሽሎ ግማሽ ንብረታችሁን እንድትሰጡኝ ፈርጃለሁ!”
ሁሉም ለጥ ብለው እጅ ነሱ - አጫዋቹም ጭምር፡፡
***
ቢስቁበት የሚቆጣ፣ ቢስቁለትም የሚቆጣ ንጉሥ፣ የበላይ ኃላፊ፣ የፖለቲካ መሪ ወይም ግለሰብ አይጣል ነው፡፡ ከእኔ ጋር ካሳቅህ ትቀጣለህ፤ በራስህ ከሳቅህም ትቀጣለህ የሚል ደግሞ የበለጠ የከፋ ነው፡፡ ከቅኝቴና ከዜማዬ ውጪ የዘፈነ ወዮለት እንደማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለ ፍርሃት በዳመነበት አካባቢ ልባዊ አስተያየት፣ ግልፅነት፣ ሀቀኛ ግምገማ፣ እውነተኛ ሪፖርት አይኖርም፡፡ ስቆ መጠራጠር፣ አልቅሶም መጠራጠር ይበዛልና፡፡ የበላይን ፈገግታ እያዩ መሳቅ አብዛኛው ማግጠጥ ነው! ራስን መሆን ያቅታል፡፡ በየትኛዋ ደቂቃ ከወንበሬ እነሳ ይሆን እያሉ መወያየት ከምንጩ የዲሞክራሲ አካለ - ጎደሎ ነው! ፍርሃት፣ ቂም፣ ተንኮል፣ ሤራ፣ አስቀድሞ - ፍርድ (prejudice) ባለበት ዲሞክራሲ አይኖርም፡፡ ዲሞክራሲ ከሌለ ደግሞ እውነተኛ ሰላም፣ እውነተኛ ፍትህ፣ እውነተኛ ልማት ማምጣት እጅግ ሩቅ ህልም ነው፡፡
ከንጉሡ ጋር የሚስቁ ምሁራንና ባለሟሎች፣ ከአለቃ ጋር የሚስቁ የበታች ኃላፊዎችና ምንዝሮች፡- ለጊዜው በአርጩሜነት ቢያገለግሉ እንጂ አገርን ከጥፋት፣ ኢኮኖሚን ከድቀት፣ ህዝብን ከመራቆት አያድኑም፡፡ ይልቁንም ራሳቸው በተሻለ አርጩሜ የሚቀጡበት ቀን ሊመጣ እንደሚችል ከላይ ካነበብነው የአጫዋቹ ታሪክ ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡
 ማጫፈርና ማሟሟቅ ተስፋን አያመላክትም፡፡ መጠፋፋትን እንጂ ተደጋግፎ ማደግን አይጠቁምም፡፡ “በደህናው የማይጠቅም ሞቶ በህልም ይታያል” እንደሚባለው ካለፉ በኋላ ነበሩ ማለት ብቻ ይሆናል ትርፉ፡፡ ህዝብ ወይም ባለሟሉ ሲስቅ የሚስቅ ንጉሥ ወይም ባለስልጣን ማግኘት መታደል ነው፡፡ በእርግጥም በብዛት አያጋጥምም፡፡ አገራችን ለአቻ ሥራ አቻ ሰው (The Right Man at the Right Place) ዛሬም የተሳካላት አይመስልም፡፡ የሹም ሽር መብዛት፣ የእሥር መበርከት፣ የውይይት አለመቀጠል፣ የእቅዶች የአንድ ሰሞን ሞቅ ሞቅ ሆኖ መቅረት፣ የተወሰኑ ውሳኔዎ በቀላጤ መሻር፣ ባለሙያን አለማክበር፣ የበኩር ልጅን ምን ሰራህ አለማለት፣ የእንጀራ ልጅን የሰራውን አለማመስገን፣ ራስ ሳይጠና ጉተና ማሳደግ፣ ህዝቡን ለመለወጥ ከመጣር ይልቅ የራስን መንገድ ጥርጊያውን ማሳመር ወዘተ ሁሉ የሚያሳዩት ለአቻ ሥራ አቻ ሰው ማጣትን ነው፡፡ አለመታደልን ነው፡፡ “የምትኖር ሚስትና የሚያኖር ባል አንድ ገበያ እየዋሉ አይገኛኙም” እንደሚባለው ነው፡፡ እንዲህ ባለው ሰውና ሙያ ባልተገናኙበት አገር እበላ-ባዩ፣ አጫዋቹ፣ አንጓቹና አንጋቹ ይበዛል፡፡ በሥራ ከማገዝ ይልቅ በወሬ ማናቆር ይበረክታል፡፡ በእሾም ይሆናል ተስፋ ለራስም ለወገንም የማይበጅ የሲስቁ ልሳቅ ጥረት ይበዛል፡፡ “በጥገኝነት” እና በአድር - ባይነት “እኔ መንገዱን ላሳይ እችላለሁ” የሚሉ አብሪዎች አያሌ ይሆናሉ፡፡ ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ የሆኑት መንታ መንታ ይፈለፈላሉ፡፡ ይህም “ጥርስ የሌላት፣ ጥርስ ያላትን ነክሳ፣ አነካከስ ታስተምራለች” የሚለውን ተረት ያስታውሰናል፡፡ ዞሮ ዞሮ “የእናት ዓለም ጠኑ”ው ገራፊ ገብረየስ እንዳለው፤
“እድሜ ለእኔ፣ እኔ 40 ስገርፍ እያየ ከአንድ እስከ አርባ ቁጥር ተማረ!” መባሉ አይቀርምና አለመታደል ነው!
እንኳን ለ128ኛው የአድዋ ድል በዓል አደረሰን!!

Read 1191 times