Wednesday, 06 March 2024 10:33

ሰዋሰው መልቲሚዲያ እና አድ ቴክ ሶሉሽን በጋራ ለመስራት ተስማሙ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ውስጥ ከሚገኙ አለም አቀፍ ተቋማት ጋር  በጋራ እየሰራ የሚገኘው ሰዋሰው መልቲሚዲያ፣ በትውልደ ኢትዮጵያውያን በተመሰረተውና በተለያዩ የአሜሪካን ግዛቶች በስፋት በዲጂታል ማስታወቂያው ዘርፍ ላይ እየሰራ ከሚገኘው አድ ቴክ ሶሉሽን ጋር  በጋራ ለመስራት በዛሬው ዕለት ከስምምነት ላይ ደረሱ፡፡

የዛሬው ስምምነት ኢትዮጵያውያን አርቲስቶችን ወደ ዓለም አቀፉ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ እንዲሁም በሙዚቃው ዘርፍ የተሰማሩ ግዙፍ አለም አቀፍ ተቋማትን ደግሞ ወደ ሀገራችን የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ለማስገባት አልሞ ለሚሰራው  ሰዋሰው መልቲሚዲያ ወሳኝ ምዕራፍ ነው ተብሏል፡፡

በተለያዩ የአሜሪካን ግዛቶች በኢትዮጵያውያን በሚዘጋጁ ትልልቅ ፕሮግራሞች፣ በአብዛኞቹ የሀገሪቱ ግዛቶች በሚገኙ ሞሎች፣ አደባባዮች፣ ሆቴሎችና በርካታ ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው ጎዳናዎች ላይ የዲጂታል ማስታወቂያ ስራን የሚሰራው አድ ቴክ ሶሉሽን፣ በሰዋሰው በኩል የሚወጡ አልበሞችን፣ የተለያዩ አርቲስቶችን ስራዎች እንዲሁም ከሰዋሰው ጋር በጋራ የሚሰሩ ተቋማትን አገልግሎቶች የሚያስተዋውቅ ይሆናል፡፡

የሰዋሰው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሀብቱ ነጋሽ፤ በመላው አለም የሰዋሰው አርቲስቶችንና ስራዎችን ለማስተዋወቅና ለማስፋፋት ከምናደርጋቸው ስራዎች መካከል ይህ አንደኛው መሆኑን ጠቅሰው፣ በስምምነቱም ደስተኛ መሆናቸውን ገልፃዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአድ ቴክ ሶሉሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አማኑኤል ኪዳኔ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በተለየ መልክ ለማሻሻልና ለመለወጥ ከሚሰራው ሰዋሰው ጋር በጋራ ለመስራት በመስማማታችን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል፡፡

ሁለቱ ድርጅቶች በቀጣይ በአውሮፓ የተለያዩ ሀገራት በጋራ የመስራት ውጥን እንዳላቸውም ተጠቁሟል፡፡

Read 1203 times