Saturday, 09 March 2024 20:17

የፋና እና አዲስ ዋልታ የውህደት ፖለቲካ

Written by  ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ
Rate this item
(2 votes)

የአዲስ ዋልታው ጋዜጠኛ ስሜነህ ባይፈርስ ቅዳሜ የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ለንባብ በበቃው አዲስ አድማስ ጋዜጣ “ ‘ፍለጋው አያልቅም…’ የአዲስ ዋልታ የውህደት ፖለቲካ “ የሚል ጽሁፍ አቅርቦ በተለይ “የአዲስ ዋልታ የውህደት ፖለቲካ” የሚለው ሀሳብ ስቦኝ አነበብኩት ። ጋዜጠኛው “ከወንጭፍ”  ጋዜጣ እስከ “አዲስ ዋልታ” ቴሌቪዥን ያደረገውን የሙያ ጉዞ በነጠቅ ነጠቅ ገለጻ ያስቃኛል፡፡ በስተመጨረሻም አለቃውን (ዋና ሥራ አስፈጻሚውን አቶ መሀመድ ሀሰንን) አሞጋግሶና አንቆለጳጵሶ አሁን ባለው የቴሌቪዥን ጣቢያው ሰራተኛ ቡድን አንድ አባል በመሆኑ መኩራቱን ገልጾ ያበቃል፡፡  ጽሑፉን እንደገና አነበብኩት፡፡ ከዚያ ደግሞ ሙሉውን ማንበብ ሳይሆን እንደ ፍለጋ ርዕሱን በጽሑፉ ውስጥ ፈለግሁት፤ እናም አጣሁት፡፡ ጽሑፉን ማንበብ የጀመርኩት ራሱ ስለውህደት ፖለቲካው የሚሰጠኝ አዲስ መረጃ ቢኖር ብዬ ነበር ፡፡ ይሁንና  መረጃው ቀርቶ ጸሐፊው ሊል የፈለገው ምን እንደሆነ ሳይታወቅ  ጽሁፉ ይጠናቀቃል፡፡ “ፍለጋው አያልቅም” ብቻውን ነው ርዕስ መሆን የነበረበት፡፡ የውህደት ፖለቲካው በስሜነህ ጽሁፍ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአሁንታም መሬት ላይ ግልጽ የሆነ ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህ ርዕሱ በርዕስነት ከሚቀር ከጽሑፉ ተውሼ (ያለፍቃድ) የተሰማኝን ልበልበት ፡፡
ፋናም ሆነ አዲስ ዋልታ ቴሌቪዥኖች የቀድሞው ኢህአዴግ እና የአሁኑ ብልጽግና የኢንዶውመንት ንብረቶች ናቸው፡፡ ፋና ቴሌቪዥን ኢህአዴግ በረሀ እያለ በሬዲዮ መልክ የተወለደና የቀድሞ ስያሜውን ለውጦ “ፋና ራዲዮ” የተባለ ፣ ራዲዮው ሰፊ ተቀባይነትና ሀብት አፍርቶ “ፋና ቴሌቪዥን”ን የወለደ ነው፡፡ በአንድ ታጋይ ስም የተሰየመው “ዋልታ”ን የማውቀው በኢትዮጵያ  ቴሌቪዥን የአየር ሰዓት እየወሰደ የሚተላለፈው “ሀገሬ” ዶክመንተሪ ነበር፡፡ ከዚያ ከአንድ ዶክመንታሪ አቅራቢነት ወደ ቴሌቪዥን ጣቢያነት ተመዘዘ፡፡ ተመዘዘ እንጂ አላደገም፡፡ እውነቱን ለመናገር የቴሌቪዥን ጣቢያነት የቱ ጋ እንዳለ ሳይታወቅ ኖሮ አዲሱ ስራ አስፈጻሚ አቶ መሀመድ ሐሰን ወደ ጣቢያው ከመጡ በኋላ “ዋልታ” ወደ “ኢዲስ ዋልታ” የስም ለውጥ አደረገ፡፡ የስም ለውጡ ትርጉም አልገባኝም፡፡ ብዙ ሰዎችም አልገባቸውም፡፡
ቴሌቪዥን ጣቢያው እንደ ስያሜው አዲስ የመሆን ዓላማ እንዳለው ገምተን ሳናበቃ ወዲያው ደግሞ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ሊዋሃድ የመሆኑ ዜና ተሰማ፡፡ ስም ብቻ ሳይሆን ለጣቢያው ከፍተኛ ገንዘብ ተመድቦ፣ ብዙ ብርም ወጥቶ ራሱን ችሎ ለሚኖር ጣቢያ የሚደረግ የህንጻና ግቢ እድሳት እና ግዢ ተፈጽሟል፡፡ በርከት ያለ የሰራተኛ ቅጥር ተፈጽሟል፡፡ ይህ ሁሉም ሆኖ በግልጽ ባልተነገረ ሁናቴ የሁለቱን ቴሌቪዥኖች ጋብቻ ለመመስረት ሽማግሌ ተልኮ ፈቃድ ተገኝቷል፡፡ አዲስ ዋልታ ከፋና አንጻር ከፍተኛ ሊባል የሚችል ደመወዝ ለሰራተኞቹ ይከፍላል፡፡ ውህደቱ ሲፈጸም የአዲስ ዋልታን ሰራተኞች ደመወዝ መቀነስ ስለማይቻል የፋናዎቹ ያድጋሉ ማለት ነው ። ሁለቱን ጣቢያዎች አንድ የማድረጉ ስራ አዲስና ድንገተኛ ሳይሆን ቀደም ተብሎ የታሰበበት እንደሆነ እዚህም እዚያም ይነገራል፡፡ ነገ ፈርሶ ለሚዋሃድ ሚዲያ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስና ስሙን መቀየር ለምን እንዳስፈለገ ግልጽ አይደለም፡፡ ጋዜጠኛ ስሜነህ ባይፈርስ በጽሑፉ እንደ ውስጥ አዋቂ የውህደቱን አስፈላጊነት፣ መነሻና መድረሻውን፣ የውህደቱን ፖለቲካ ሊተነትንልን ይገባ ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ እኔ ሳስበው ስሜነህ ሊል የፈለገው ነገር አለ፡፡ እንዴት እንደሚል ነው መርጦ ያልወሰነው፡፡
በጽሑፉ ውስጥ “አዲስ ዋልታ ከሌሎች ጋር ተዋህዶ አዲስ ኩባንያ ይመሰርታል የሚል ጭምጭምታ መናፈስ ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል” የሚል ጥያቄ ብቻ የሆነ አረፍተ ነገር አስፍሯል፡፡  “ከሌሎች” ሲል ስንት ናቸው ሌሎቹ ? “ሌሎች” ካለ ቢያንስ ከአንድ በላይ ነው ማለት ነው፡፡ ከአዲስ ዋልታ  ጋር የሚዋሀደው የቀድሞ መ/ቤቱ (“የተራብኩትን ጋዜጠኝነት ጠገብኩት” ብሎ የገለጸው ፋና ቴሌቪዥን መሆኑን ስሜነህ አላወቀም ማለት ይቸግረኛል። ካወቀ የፋናን ስም መጥቀስ ለምን አልፈለገም ? ከሁለቱም ተቋማት ኮሚቴ ተዋቅሮ ጥናት እየተደረገ ውህደቱም ወደ ጫፍ እንደደረሰ እኔ እንኳን በወሬ ወሬ የሰማሁትን የአዲስ ዋልታው ስሜነህ ባይፈርስ አልሰማምና ነው የተዋሃጁን ስም ያልጠቀሰውንና የተረጋገጠውን “በጭምጭገታ” ያለው?
ስለ ውህደቱ ሲነገር በአንድ በኩል የአዲስ ዋልታ “ወደ ኪሳራ መሄድ “ አንድ ምክንያት ሆኖ ሲጠቀስ በሌላ በኩል ደግሞ “ ሁለቱን ጣቢያዎች አዋህዶ ሌላ ትልቅ የሚዲያ ተቋም  መመስረት” ዋናው የውህደቱ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሁለቱም ምክንያቶች ለእኔ ውሃ የሚያነሱ ሀሳቦች አይደሉም፡፡ የውህደቱ መነሻ ምክንያት ኪሳራ ከሆነ ከአሁን ቀደም ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ በፌስቡክ ገጹ እንዳለው፤ የከሰረና የሚያተርፍ ድርጅትን መቀላቀል ሁለቱም ተያይዘው እንዲወድቁ እንጂ አትራፊ እንዲሆኑ አይረዳቸወም፡፡ ሁለቱን በማዋሃድ ሌላ ትልቅ የብዙሃን መገናኛ ተቋም መመስረት ከሆነ ምክንያቱ የታሰበው ቁስሉ የሌለበት ቦታ ላይ መድሃኒት መቀባት ይባላል ፡፡ ሁለቱ ቴሌቪዥኖች (በነገራችን ላይ ሁለቱም የሬዲዮ ጣቢያዎች ስላሏቸው ሲዋሃዱ ቴሌቪዥኖቹ ብቻ ሳይሆኑ ሬዴዮዎቹም ጭምር መሆናቸው ልብ ይባል፡፡) ስለተዋሃዱ “ትልቅ የብዙሃን መገናኛ ተቋም” እንዴት ይወለዳል?
ሁለቱ ተቋማት በራሳቸው ትልቅ (ያ ሊፈጠር የታሰበው ተቋም) ያላከሉት ቀድሞውንስ ምን ጎድሏቸው ነበር ? ምን ቦታ አንሰው ነው የሁለቱ መዋሃድ የሚሞላው? እንደ ብዙሃን መገናኛ ለመሆኑ “ ትልቅ” ሲባል በምንድን ነው? በካፒታሉ? በሰው ሃይሉ? በህንጻው ግዝፈት ወይስ በምን? ሁለቱ ቢያስፈልግም ሌላ ሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቢዋሃዱ አሁን ባለው ተጨባጭ የሀገሪቱ ሁኔታ  ግዙፍ ብዙሃን መገናኛ መሆን ይችላሉ? ከነበሩበትስ ያድጋሉ ወይስ ጭራሹን ተያይዘው ይወድቃሉ? በመጀመሪያ ህመማቸው የቱ ጋ እንዳለ ታውቆ ነው ሁለቱ ቢዋሃዱ የሚድኑት? ውህደታቸው ብቻውን ህዝቡ ልብ ጋ ያደርሳቸዋል?
በእኔ ያልተጠና ግምት ሁለቱን ከማዋሃድ ለፋና የበጀት ድጎማ (ቢያንስ ለአዲስ ዋልታ የተሰጠውን ያህል ) እና ሙሉ ነጻነት ቢሰጠው ከውህደቱ የገዘፈ ትልቅ ተቋም መሆን ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ቢሆን በሙያው የሰለጠነ የሰው ሃይልና በጀት ቢመደብለትና የሰው ሃይል ቢጨመርለት፣ ዘመናዊ መሳሪያ ቢሟላለት ተፈላጊና ተመራጭ ቴሌቪዥን ጣቢያ መሆን ይችላል? እስካሁን ተፈላጊና ተመራጭ ያልሆነው የተጠቀሱት ስላልተሟሉለት ካልሆነ ቢሟሉለትም ካለበት ፈቅ አይልም፡፡ አዲስ ዋልታና ፋና ቴሌቪዥንም ከዚህ የተለየ እጣ ፈንታ ይኖራቸዋል ብዬ አላምንም፡፡
ሁለቱ ጣቢያዎችም ሆኑ ሁለቱ ተዋህደው “ይፈጠራል” የተባለው ቴሌቪዥን ጣቢያ በራሳቸው የሚያቅዱ፣ ከመንግስት የትኩረት አቅጣጫ “አጀንዳ” የማይቀበሉ፣ እውነትና አስፈላጊ እስከሆነ ለመስራት የማንንም ይሁንታ የማይጠብቁ፣ ተጠሪነታቸው ለሀቅ፣ ለሙያዊ ስነምግባራቸውና ለኢዲቶሪያል ፖሊሲያቸው ብቻ እስካልሆነ ድረስ በመዋሃድና በስብሰባ የሚፈታ ችግር አይኖርም፡፡ ችግሩ የገንዘብም፣ የሰው ሃይልም ሳይሆን የሙያዊ ነጻነት ነው፡፡ ሁለቱ ተዋህደው የሚፈጠረው ብዙሃን መገናኛ ለሙያው ታማኝ ሆኖ ከመንግስት አቅጣጫ ወጥቶ የራሱን አቅጣጫ ማስመር ይችላል? በመንግስት ተቀርጸውና ተቀናብረው በቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ በእኩል ቀንና ሰዓት እንዲተላለፉ የሚላኩ ፕሮግራሞችን ገምግሞ “ለተመልካቾቻቸን የሚሆን ከዚህ የተሻለ ይዘት ያለው ፕሮግራም ስላለን በዚህ ሰዓት አናስተላልፍም፡፡ ይህን በነገው ምሽት እናስተላልፈዋለን “ የማለት አቅም ይኖረዋል? በግል ባለሃብቶች በሙሉ ወጪ  የተቋቋመው “NBC ETHIOPIA” እንኳን መች ይሄን ቻለ? መቼ በራሱ ፈቃድ ይመራል? መቼ መንግስት ባይፈልገውም የሀገሪቱን ህግ አክብሮ በራሳቸው ፈቃድ የሚሰሩ ዜናዎችና ፕሮግራሞች  አሉት? እውነታው ይህ ሆኖ ከአዲስ ዋልታም ፣ ከፋናም አዲስ ይቋቋማል ከተባለውም የብዙሃን መገናኛ የሚጠበቅ  ትልቅነት የለም፡፡
“አዲስ ዋልታ ፈርሶ ከፋና ጋር ሊዋሃድ ነው”  እና “አንዳችን ፈርሰን በሌላው ስር የምንገባ ሳይሆን የምንጣመር ነን”  የሚሉት ሃሳቦች ሲያነጋግሩና ሲያከራክሩ ነበር፡፡ በቅርቡ  አዲስ ዋልታ “THE CEO” የሚል ዶክመንተሪ ማስታወቂያ  ላይ “አዲስ ዋልታ 3ኛ  ዓመት ላይ ገዝፎ እናየዋለን”የሚል የዋና ስራ አስፈጻሚው መሀመድ ሐሰን  መልዕክት ተላልፏል፡፡  “አዲስ ዋልታ ገዝፎ እናየዋለን” የሚለው አባባል ከውህደቱ በኋላ ይፈጠራል የተባለው  ጣቢያ ስያሜ “አዲስ ዋልታ” ይባላል ማለት ነው ወይስ አሁን ስላለው “አዲስ ዋልታ” ? ግልጽ አይደለም፡፡ ጣቢያዎቹ ቢዋሃዱ የተሻለና በተወዳዳሪነት ስሙን  የገነባው “ፋና” የሚለው  ስም ከወራት በፊት የተሰየመውና በተፈለገው መጠን ህዝብ ልብ ውስጥ  ያልገባው “አዲስ ዋልታ” ዋና መጠሪያ ይሆናል ብዬ አላምንም፡፡ በግሌ ስለሁለቱም ጣቢያዎች ከተመልካችነት የዘለለ ዝምድና የለኝም፡፡ ፋና ቴሌቪዥ ግን በአንጻራዊነት አሁን በስርጭት ላይ ካሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሁሉ የተሻለው ተመራጭ መሆኑን አለመመስከር አልችልም፡፡ ፋናን ከአዲስ ዋልታ ጋር እያወዳደርኩ አይደለም፤ ከሁሉም ጋር እንጂ፡፡ ይሁንና መሻል አንጻራዊ ነው ። ፋናም እንደ ሌሎቹ ጣቢያዎች ሁሉ ህዝባዊ ሳይሆን መንግስታዊ አቋም ያለው ጣቢያነቱና ጉድለቱ እንዳለ ነው፡፡
የፋናና የአዲስ ዋልታ የውህደት ፖለቲካ እንደ ጋዜጠኛ ስሜነህ ጽሑፍ ግራ የተጋባ ነው ። የስሜነህ ባይፈርስ ጽሑፍ ዋና ዓላማ፣ ዋና ስራ አስፈጻሚውን ማመስገን፣ ማሞገስ፣ ማንቆለጳጰስና የአለቃውን ጥሩ አለቃነት፣ ወጣትነት፣ ጣቢያውን እንደ ግል ሀብቱ ከማየቱ የተነሳ አዲስ የተወለደለትን ልጅ “ ዋልታ “ ብሎ ስም ማውጣቱ ፣ ብዙ መስራቱ ነገር ግን ከሰራው ይልቅ ሊሰራ የሚችለው እንደሚያጓጓው መግለጽ ነው፡፡ ይህንን በግልጽ ማስቀመጥ እየቻለ የራሱን የሙያ መንከራተት በሰፊው መግለጽ ለምን እንዳስፈለገው ግልጽ አይደለም ። ምናልባት ጥቅም አዳሪነት እንዳይመለስበት ሰግቶ ይሆናል፡፡ ለአለቃው ገጽታ ግንባታ ማሰቡም፣ መጻፉም ሀሳቡ እውነት እስከሆነ ክፋት የለውም፡፡እንደ ጽሁፉ ውህደቱም ግልጽነት የጎደለው ነው፡፡ ቢዋሃዱ አንዱ በሌላው ስር እስካልገባና አመራሩም አንድ እስካልሆነ ድረስ ወደፊት የሚመጣው ጣቢያ ከመሳሳብና መጓተት፣ ከፉክክርና መላፋት ወጥቶ ለትልቅነት ሊበቃ አይችልም፡፡ በኢህአዴግ ንብረት ውስጥ በአንድ ወቅት “ሜጋ የኪነጥበባት ማዕከል” እና “ሜጋ ማስታወቂያ” ተዋህደው ከስራ ይልቅ የሁለቱ ተቋማት የቀድሞ ዋና ስራ አስኪያጆችን ጉሽሚያና መጠላለፍ፣ “የአሰፋ ማሞ ቡድን” እና “የዕቁባይ በርሄ ቡድን “ ሁለት ቦታ ተከፍለው ሲቀጣቀጡ የዝሆኖቹ ጠብ፣ ሳሩን እየረጋገጠው ድርጅቶቹን መልሶ መሰንጠቅና ወደነበሩበት መመለስ ነው፡፤ በዚያ መሃል ግን ብዙ የሃገር ሀብት ባክኗል፡፡ የ”አዲስ ዋልታ” እና የ”ፋና” ቴሌቪዥኖች የውህደት ፖለቲካ ከቀድሞዎቹ ሜጋ የኪነጥበባት ማዕከልና የሜጋ ማስታወቂያ የውህደት ፖለቲካ “ሳይቃጠል በቅጠል” ቢማሩ መልካም ነው፡፡ እንደ አሰፋ ማሞ እና እቁባይ በርሄ ቡድኖች አሁንም “ የአድማሱ ዳምጠው ቡድን “ እና “ የመሀመድ ሐሰን ቡድን “ እንዳይመጣ ስጋት አለኝ፡፡ በርቀት የሚታዩት ስሜቶች ጣቢያዎቹ ተዋህደው አንድ ላይ መግዘፋቸውና መድመቃቸው ላይ ከወዲሁ ጥያቄ ያስነሳል፡፡
ከአዘጋጁ ፦
ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ፤ ሁለገብ የጥበብ ሰው ነው፡፡ 6 መጻሕፍትን አዘጋጅቶ ለአንባቢ አድርሷል፡፡ 4 የመድረክ ተውኔቶችን ፣ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ድራማዎችን ደርሶ ለዕይታ አብቅቷል ፤ ጸሃፌ ተውኔት ነው፡፡ በርካታ ምሁራንን፣ ፖለቲከኞችን፣ ደራሲያንን ወዘተ--- ቃለመጠይቅ አድርጓል፤ ጋዜጠኛ ነው፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ  በማናቸውም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ አስተያየቱን በነጻነት ያንጸባርቃል ፡፡

Read 1354 times