Monday, 11 March 2024 10:32

ፈተና ላይ መበርታትና “ፍኖተ ካርታው” አብረው አይሄዱም

Written by  ዩሃስ ሰ.
Rate this item
(6 votes)

ፍኖተ ካርታው፣ ከ”ዕውቀት” ጋር ብርቱ ጸብ አለው። “ዕውቀት ላይ ያተኮረ ትምህርት” እንደ አገር ጠላት ነው የተቆጠረው።
“ፈተና” ላይ መበርታት ደግሞ፣ ለዕውቀትና ለብቃት ደረጃ ክብር መስጠት ነው። ይሄ ነውር ነው - በፍኖተ ካርታው መነጽር።
     የሚኒስትሮች ስብሰባ እንዲህ ነው? ለአገሪቱ ካቢኔ የሚቀርቡ የግማሽ ዓመት ሪፖርቶችን ተጋብዘን አየንኮ።


የትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ፣ በተማሪዎች ቁጥርና በመማሪያ መጻሕፍት ሕትመት ዙሪያ አሀዛዊ መረጃዎችን አቅርበዋል። በፈተናዎች ላይ የሚወድቁ ተማሪዎች ብዛትንም ከየቦታው ጠቅሰዋል። ያስደነግጣል።
ግን “ድከሙ ሲላቸው” እንጂ፣ በጣምም የደነገጥን አይመስለኝም። ስለተላመድነው ሊሆን ይችላል። ማስደንገጥ ነበረበት በማለት እንለፈው።
ግን ምንድነው የትምህርት ሚኒስቴር ፈተና ላይ በረታሳ?
ባለፈው ጊዜ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች 96% ወድቀዋል ተባለ። “ትንሽ” ግር ስለሚል፣ ነገሩን ቀለል አድርገን ብንገልጸው ይሻላል።
ከመቶ ተማሪዎች መካከል፣ ፈተናውን ያለፉት 4 ብቻ ናቸው። ዘንድሮ ደግሞ፣ የክልል የትምህርት ቢሮዎች የ8ኛ ክፍል ፈተና አክብደውታል መሰል፣ ብዙ ተማሪዎች ወድቀዋል ተብሏል። በአማራ ክልል፣ ከመቶ ተማሪዎች 30ዎቹ ወደ ዘጠነኛ ክፍል አልተሸጋገሩም። በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ከመቶ ተማሪዎች 40 ያህል እንደወደቁ የትምህርት ሚኒስትሩ ለካቢኔ ገልጸዋል።
በዲግሪ የተመረቁ ተማሪዎችም እንደ ድሮው “እፎይ” ማለት አይችሉም። ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ለዲግሪ በቅታችኋል የሚላቸው እየጠፋ ነው። ወደ ፈተና የሚያስገባቸው “የመውጫ ፈተና” መጥቶላቸዋል። መጥቶባቸዋል።
የግል ዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች 14 በመቶ ያህሎቹ ናቸው የማለፊያ ውጤት ያገኙት ብለዋል ሚኒስትሩ። ማስተርስ ዲግሪ ለመማር ያመለከቱ ምሩቃንም፣ የመግቢያ ፈተና ከፊታቸው ተጋርጧል። 30 በመቶ ብቻ ናቸው ያለፉት ተብሏል።
እሺ፣ እሺ። የትምህርት ሚኒስትርና የክልል የትምህርት ቢሮዎች በፈተና ላይ በርትቷል። ገባን። ለጊዜው አምነናል። ለምን ፈተናን ላይ በረቱ ብለን ብንጠይቅ፣ የዚያኑ ያህል ብርቱ ማሳመኛ ምክንያቶች እንዲሚያቀርቡ መገመት ይቻላል። ጫፍ ጫፉንም ሰምታችሁት ይሆናል።
ያለ በቂ ዕውቀትና ያለ ብቃት ከክፍል ክፍል መሸጋገር ትርጉም የለውም። እንዲያውም ጉዳት አለው ተብሏል። የትምህርት ነገር እንደ ቀልድ እንዲታይ ያደርጋል። ዲግሪና የምስክር ወረቀትም “ከፎርጅድ” የተሻለ ትርጉም አይኖረውም።
ስለዚህ፣ ኮስተር ማለት ያስፈልጋል። ፈተና ላይ ከበድ! ቁጥጥሩም ላይም ጠበቅ! በቃ ይሄው ነው መፍትሔው?
የዕውቀትና የብቃት ደረጃን ማረጋገጥ ካስፈለገ፣ ፈተና ላይ መበርታ ነው መላው?
ተማሪዎች በፈተና ላይ ቀልድ እንደማይኖር ማየት ሲጀምሩ፣ በቁም ነገር ትምህርታቸውን ለመከታተልና ለማጥናት ከልብ ይተጉ ይሆናል። እውቀትን መጨበጥ፣ ብቃትን ማሳደግ እንደሚኖርባቸው ከምር መገንዘብ ሊጀምሩ ይችላሉ። ማን ያውቃል?
መልካም። በብዙ ጥያቄዎች የተከበበ ቢሆንም፣ ፈተና ላይ መበርታት “የትምህርት ጥራትን ወይም ብቃትን” ለማሻሻል የተወሰነ አስተዋጽኦ የሚኖረው ከሆነ መልካም ነው። እንደታሰበው ብዙ ለውጥ ባያስገኝ እንኳ፣ “የትምህር ነገር አሳስቧቸው” የመፍትሔ ሐሳቦችን ለማምጣትና ለመሞከር የሚደረግ ጥረት ክፋት የለውም።
ነገር ግን ችግር አለ። የትምህርት ፍኖተ ካርታው፣ ከዕውቀት ጋር ከባድ ጸብ አለው። የአገራችን ትምህርት፣ “ዕውቀት ተኮር” መሆን እንደሌለበት ይገልጻል። የፍኖተ ካርታው “ፊታውራሪ ዓላማ” ምንድነው ብለን ብንጠይቅ፣ መልሱ አከራካሪ የሚሆን አይመስለኝም።
ዕውቀት ላይ ያተኮረ ትምህርትን የማስወገድ ዓላማ  ነው “ግንባር ቀደም ዓላማው” ማለት ይቻላል። ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ትምህርት እንደ ዋና ጠላት ስለተቆጠረ፣ “በዕውቀት የታጨቀ ትምህርት” ተብሎ በፍኖተ ካርታው ውስጥ ተብጠልጥሏል። ትምህርት፣ “ዕውቀትን ማንቆርቆር አይደለም” ተብሎም መዘባበቻ ሆኗል።
ዕውቀትን ለማስጨበጥ ሳይሆን፣ ተማሪዎች በክህሎትና በፈጠራ ችሎታ እንዲራቀቁ ነው የምናስተምረው በማለት ያስረዳል - ፍኖተ ካርታው።
በእርግጥ፣ የፍኖተ ካርታው ዝግጅት የተከናወነው አሁን ካሉት ሚኒስትሮች በፊት፣ አሁን ካለው መንግሥትም በፊት ነው።
በዚያ ላይ አብዛኞቹ መምህራን ባያምኑበትም፣ በተግባር ትልቅ የትምህርት ዕንቅፋት ቢሆንባቸውም፣ አብዛኞቹ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ምሁራን፣ በተለይም ደግሞ ከውጭ የሚመጡ አማካሪዎች ግን ብዙውን ጊዜ “ዕውቀት ላይ ያተኮረ ትምህርትን” እንደ ማሪያም ጠላት ነው የሚያንቋሽሹት።
እናም፣ ፍኖተ ካርታው የብዙ ምሁራን ድጋፍ ያገኘ ወይም ሰፊ የምሁራን ድጋፍ ሊያገኝ የሚችል ሰነድ እንደሆነ አይካድም። ጠንካራ ትችት የሚያቀርብበት ምሁር ብዙ አይደለም። ከስንት አንድ ከተገኘ ነው።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ብዙ ምሁራን የሚደግፉት ከሆነ፣ መንግሥትና የትምህርት ሚኒስቴር፣ ፍኖተ ካርታውን በተቻለ ዐቅም ተግባራዊ ለማድረግ ቢረባሩ፣ በሌለ የውጭ ምንዛሬ አዳዲስ መጻሕፍትን በውጭ አገራት ለማሳተም ገንዘብ ፍለጋ ላይ ታች ቢደክሙ ምን ይገርማል?
እንዲያውም የብዙ ምሁራንን ምክር ችላ ቢሉ ነበር የሚያስወቅሳቸው።
ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው?
ዕውቀት ተኮር ሳይሆን፣ “ተማሪ ተኮር፣ ፈጠራ ተኮር፣ ተሟጋች ዜጋ ለመፍጠር ያለመ፣ ከዘመናዊው ዓለም ጋር እኩል የሚራመድ” ተብሎ የመጣው አዲስ ፈሊጥ፣ ይሄውና ስንት ዓመቱ ተማሪዎችን ከዕውቀት ጋር እያራራቃቸው ነው።
ደግሞም፣ ይህን ቀደም ብለው የተናገሩና ያስጠነቀቁ ዐዋቂዎች አልጠፉም። ጥቂት ቢሆኑም ገና በጥዋቱ መክረዋል። ዕውቀትን የጠላ፣ የመልመጃ ጥያቄዎችን እንደ ቆሻሻ ሸክም የሚቆጥር አዲስ ፈሊጥ አያዋጣችሁም ብለዋል። በመረጃና በጥናት መዘዙን አሳይተዋል።
የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች ቀላል ዐረፍተ ነገሮችን ማንበብና መረዳት እያቃታቸው ነው ብለው የዛሬ 12 ዓመት ጥናታቸውን በሰነድ አዘጋጅተው በይፋ አቅርበዋል።
በአዲሱ የትምህርት ፈሊጥ ብዙ ሕጻናት ትምህርት ቤት ገብተው ለመሀይምነት የተዳረጉ ይሆናሉ።
ሌላው ቢቀር ጥንታዊው “የየኔታ ትምህርት በጣም ውጤታማ እንደሆነ ማየት አትችሉም ወይ?” ብለው እዚያው ሰነድ ላይ ምክራቸውን አቅርበዋል። ለመንግሥት። ለትምህርት ሚኒስቴር።
ዛሬም ድረስ ሰነዱ በትምህርት ሚኒስቴር ድረ ገጽ ውስጥ ይገኛል። ዞር ብሎ የሚያየው ቢገኝ ነበራ! እንዲያውም ከዚያ በኋላ አጥኚዎቹ ሁለተኛና ሦስተኛ ዙር ጥናት የማካሄድ ዕድል አላገኙም። “አዲሱን የትምህርት ፈሊጥ” የሚያስፋፉ ተቋማት ናቸው አጥኚ ሆነው የመጡት።
ያው፣ ጥናቶች ተካሂደዋል። አዎ፣ ብዙ ተማሪዎች ለመሀይምነት እየተዳረጉ ነው ብለው አዲሶቹ አጥኚዎችም መስክረዋል።
94 በመቶ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ ዐጭር ዐረፍተ ነገር አንብበው መረዳት አይችሉም። ሢሦ ያህሉ ደግሞ፣ አንዲት ቃል ማንበብ አቅቷቸዋል።
አዳዲሶቹ አጥኚዎች ይህን አሳዛኝ እውነታ መካድ አይችሉም። አልቻሉም። ነገር ግን፣ “የፈለገው ይመጣታል እንጂ፣ ለዕውቀት ተኮር ትምህርትማ እጅ አንሰጥም” ብለው የማሉ የተገዘቱ ነው የሚመስሉት።
አሁን ጥያቄው ምንድነው?
ዕውቀት ላይ ያተኮረ ትምህርትን በሚያጥላላ መንገድ እየተጓዝን፣ የዕውቀት ደረጃን የሚመዝን ፈተና ላይ ብንበረታ ትርጉሙ ምንድነው?
አዳዲሶቹን መጻሕፍት መመልከት ትችላላችሁ። የሒሳብ መጽሐፍ ተብሎ በየንዑስ ርዕሱ ሁለት ሦስት የመልመጃ ጥያቄ ብቻ ጣል ጣል ማድረግ ምን ማለት ነው? ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ፣ አብዛኞቹ መጻሕፍት የመልመጃ ጥያቄ በተቻለ መጠን ከሦስት እንዳይበዛ በእጅጉ የሚጥሩ ይመስላሉ።
ማመሳከሰሪያ ከፈለጋችሁ፣ የትምህርት ውድቀትን ለመከላከል ተብለው ባለፉት 5 ዓመታት በካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ተዘጋጅተው የታተሙ የ11ኛና የ12ኛ ክፍል የሒሳብ መጻሕፍትን መመልከት ትችላላችሁ።
በየንዑስ ርዕሱ፣ ማብራሪያና ምሳሌ በወጉ ያቀርበሉ። ግን 3 ወይም 4 ጥያቄ ብቻ አንጠባጥበው ለማምለጥ አይሮጡም። ከ30 ከ40 በላይ የመልመጃ ጥያቄዎችን በእርከን አዘጋጅተው ይጠብቃሉ።
እንዲያውም፣ ትልቁ ቁምነገር ያለው፣ የመልመጃ ጥያቄዎቹን መሥራት ላይ ነው። ለዚያውም በጥንቃቄ የታሰበባቸው የመልመጃ ጥያቄዎች ናቸው። ለአንዳንድ ንዑስ ርዕሶችማ ከ60 በላይ የመልመጃ ጥያቄዎች ተዘጋጅቶላቸዋል። ይህም ብቻ አይደለም።
የምዕራፍ ማጠናቀቂያ ላይ ከመቶ የሚበልጡ መልመጃ ጥያቄዎች ታገኛላችሁ።
የመማሪያ መጻሕፍት ዝግጅት ውስጥ ከዋና ዋና መመዘኛዎች መካከል፣ በጥንቃቄ የተዘጋጁ የመልመጃ ጥያቄዎችን በብዛት የማሟላት መመዘኛ አንዱ ነው።
አለበለዚያ፣ እንኳንና ሒሳብ፣ እንኳንና ፊዚክስ ይቅርና፣ ሌላው ትምህርትስ ቢሆን፣ የመልመጃ ጥያቄዎችን በብቃት ሳያሟሉ ጥቅል ዕውቀትን በየአቅጣጫው እንዴት ተንትኖ ግንዛቤ መጨበጥና ማጽናት ይቻላል?
ለነገሩ ብዙዎቹ የአገራችን የመማሪያ መጻሕፍት ድክመት የቱን ያህል እንደወረደ ለመረዳት፣ እዚሁ ከአጠገባቸው ለስምንተኛ ክፍል የተዘጋጀ የሒሳብ መጽሐፍን እንደማነጻጸሪያ ማየት ይችላል። በጣም በጣም ይሻላል። የጥያቄዎቹን ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ የመልመጃ ጥያቄዎቹን ጥራት፣ እንዲሁም በእርከን ተቀናብረው የቀረቡበትንም ዘዴ ተመልከቱ። “ለካ ስላልተፈለገ እንጂ፣ ጥሩ የመማሪያ መጽሐፍ ማዘጋጀት የማይቻል ሆኖ አይደለም” ያስብላል።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ዋናው ቁም ነገር ትችትና ወቀሳ አይደለም። ፈተና ላይ መበርታት፣ ከበጎ ሐሳብ የመጣ ነው። ተማሪዎች ለዕውቀትና ለብቃት እንዲተጉ ሊያነሳሳ እንደሚችል አይካድም። የዕውቀት ደረጃን የመመዘን አስፈላጊነትም አያከራክርም።
ከሆነ አይቀር ግን፣ ትምህርቱም ከዕውቀት ጋር እንዲታረቅ መላ ቢፈለግለት፣ ቢያንስ ቢያንስ መላ ለማግኘት የምር ጥረት ቢጀመር፣… ባይጀመር እንኳ ቢታሰብበት መልካም ነው።  

Read 622 times