Saturday, 16 March 2024 21:19

ኢትዮጵያ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን ማዘጋጀት አለባት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

* በ36 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች 285 ሜዳልያዎች (107 የወርቅ፣ 115 የብርና 63 የነሐስ) ተገኝተዋል፤ የሻምፒዮናውን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት የኢትዮጵያ አትሌቶች ናቸዉ።
* አትሌት ቀነኒሣ በቀለ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ታሪክ 27 ሜዳልያዎችን (16 ወርቅ፣ 7ብር ና 2 ነሐስ) በመሰብሰብ ከዓለም አንደኛ ነው፡፡  በሴቶች ምድብ ደግሞ አትሌት ወርቅነሽ ኪዳኔ 21 ሜዳልያዎችን (11 የወርቅ፣ 6 የብር እና 4 የነሐስ) በመሰብሰብ ዓለምን ትመራለች፡
45ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከ2 ሳምንት በኋላ   በሰርቢያዋ ዋና ከተማ  ቤልግሬድ ላይ ይካሄዳል። በሻምፒዮናው የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን ከ2 ሳምንት በፊት ተሰባስቦ የመጨረሻ ዝግጅቱን በአዲስ አበባና  በዙርያዋ በሚገኙት ከተሞች ሲያከናውን ቆይቷል።
ይህ የስፖርት አድማስ ዘገባ ለዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ቡድን ስለሚያደርገው ዝግጅት፤ ስለ አዘጋጇ ቤልግሬድ መሠናዶ፤ ስለቀረበው የሽልማት ገንዘብ፤ ስለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጤት ታሪክና ስለ ዓለምአቀፍ ሻምፒዮናው አዘጋጅነት የሚዳስስ ነው።
የኢትዮጵያ ቡድን ዝግጅት
የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያን ቡድን 28 አትሌቶች (14 ወንድና 14 ሴት ) ይገኙበታል። ይህን ቡድን ለመምረጥ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጃን ሜዳ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ የተመዘገበውን ውጤት ዋና መነሻ አድርጓል። በአገር አቀፍ ሻምፒዮናው ላይ በአዋቂና ወጣት  የውድድር መደቦች ላይ
ያሸነፉና ደረጃ ውስጥ የገቡ አትሌቶችን የሚያካትት ነው። ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት የሚመሩት አንጋፋው አሰልጣኝ ሁሴን ሸቦ ሲሆኑ በምክትል አሰልጣኝነት ደግሞ ቶሌራ ዲንቃ አብሯቸው ይሰራል። በኢትዮጵያ  ቡድን ዝግጅት  ከቤልግሬድ የዓየር ንብረትና መልክአ ምድር ጋር የተጣጣሙ የልምምድ መርሐግብሮችን የተከተለ ነው።  ባለፈው ሰሞን ቡድኑ ወደ ሰንዳፋ በመውጣት የመስክ ልምምድ ያከናወነ ሲሆን በትራክ ላይ መጠነኛ የፍጥነት ልምምዱን ደግሞ በኢትዮጵያ ወጣቶቹ ስፖርት አካዳሚ ሰርቷል። በሳምንቱ አጋማሽ ላይ  በአሸዋማ ስፍራ ገላን አካባቢ የቀጠለው ዝግጅት ትናንት ወደ እንጦጦ በመውጣትም ተጠናክሮ መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል።
ቤልግሬድ ከፍተኛ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል በተጠበቀው ቡድን በተለይ በወንዶች በሪሁ አረጋዊ በአዋቂ 10ኪሜ ውድድር ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ሲሆን ቦኪ ድሪባና ታደሰ ወርቁም ከፍተኛ ተፎካካሪዎች ሆነው ተጠቅሰዋል። በሴቶች ደግሞ ለኢትዮጵያ ስኬት ግምት የተሰጣቸው በጃንሜዳውው ውድድር ያሸነፉ አትሌቶች ናቸው። የኢትዮጵያ ቡድን ባለፉት 4 ሻምፒዮናዎች  በነበረው ተሳትፎ የተቀዛቀዘውን የውጤት  የበላይነት እንደሚመልስ ተስፋ የተጣለበት ሲሆን ዘንድሮ በተለይ በአዋቂዎች ውድድር በሁለቱም ፆታዎች የራቀውን የወርቅ የሜዳልያ  በማግኘት ታሪኩን ማደሱ ይጠበቃል።
የቤልግሬድ መሠናዶ
45ኛውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የምታስተናግደው  ቤልግሬድ ከ2 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ከዓለም አንደኛ ደረጃ ይዘው የደመቁባት ከተማ ናት።
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው 60 በላይ አገራትን የሚወክሉ ከ500 በላይ አትሌቶችን ተሳታፊ ናቸው። ቤልግሬድ ውስጥ በሚገኘው ፍሬንድሽፕ ፓርክ ውድድሩን በብቃት የሚያስተናግድ ሲሆን አቀበት የበዛበት መሮጫው  አትሌቶችን እንደሚፈትን ተወስቷል። ሰርቢያ ከ2022 ወዲህ የዓለም አትሌቲክስ 2 ትልልቅ ውድድሮች ለማዘጋጀት የቻለች አገር ሆናለች። በ2022 እ.ኤ.አ ላይ 18ኛውን የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናን  በማስተናገድ በአውሮፓ አትሌቲክስ ላይ ከፍተኛ መነቃቃት ነበር የፈጠረችው።
የቤልግሬድ 24 አዘጋጅ ኮሚቴ ለሻምፒዮናው የተዘጋጁትን ሜዳሊያዎች ከሳምንት በፊት አስተዋውቋል።
“ሜዳሊያዎቹ የብረት ቁርጥራጭ ብቻ አይደሉም። በሻምፒዮናው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች ሁሉ የጥረትና የትጋት ምልክት ናቸው ”በማለት ለዓለም አትሌቲክስ ማህበር ድረገፅ የተናገሩት የኮሚቴው ፕሬዝዳንት ስሎቦዳን ብራንኮቪች ናቸው። የሰርቢያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሻምፒዮናው በፊት በአለም እና በአውሮፓ ደረጃ  ውድድሮችን በብቃት ማዘጋጀቱን በመጥቀስ ከሜዳሊያ ዲዛይን አንስቶ በመስተንግዶ ብቃት ልዮና የተዋጣለት ሻምፒዮና  እንዲሆን  እንፈልጋለንንም ብለዋል።
310ሺ ዶላር የገንዘብ ሽልማት
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ለሻምፒዮናው በድምሩ ከ310 ሺ ዶላር  በላይ የሽልማት ገንዘብ ያዘጋጃል፡፡  በግልና በቡድን  ከ1ኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች የሽልማት ገንዘቡ ይከፋፈላል፡፡ በአዋቂ አትሌቶች የሁለቱም ፆታዎች የውድድር መደቦች በግል  ውጤት ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች ለ1ኛ 30ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 15ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 10ሺ ዶላር፣ ለ4ኛ 7ሺ ዶላር፣ ለ5ኛ 5ሺ ዶላር እንዲሁም ለ6ኛ ደረጃ 3ሺ ዶላር ይበረከታል፡፡ በቡድን ውጤት ለሚያሸንፉ አገራት ደግሞ ለ1ኛ 20ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 16ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 12ሺ ዶላር፣ ለ4ኛ 10ሺ ዶላር፣ ለ5ኛ 8ሺ ዶላር እንዲሁም ለ6ኛ ደረጃ 4ሺ ዶላር የሚታሰብ ሲሆን በሁለቱም ፆታዎች ድብልቅ የዱላ ቅብብል ውድድር ለ1ኛ 12ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 8ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 6ሺ ዶላር፣ እንዲሁም ለ4ኛ 4ሺ ዶላር እንደሚሸለም ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች ከፍተኛ ውጤትና አዘጋጅነቱ ወደፊት
ኢትዮጵያ ከቤልግሬድ በፊት  ከተከናወኑት 44 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች በ36 ለመካፈል በቅታለች። የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የስታትስቲክስ መፅሐፍ እንደሚያለክተው ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው 36 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች 285 ሜዳልያዎች (107 የወርቅ፣ 115 የብርና 63 የነሐስ) በማግኘት በከፍተኛ ውጤት  ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ናት።
የኢትዮጵያ አትሌቶችም በሻምፒዮናው ታሪክ ከፍተኛውን የሜዳልያ ስብስብ በማግኘት ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ አትሌት ቀነኒሣ በቀለ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ታሪክ 27 ሜዳልያዎችን (16 ወርቅ፣ 7ብር ና 2 ነሐስ) በመሰብሰብ ከዓለም አንደኛ ነው፡፡  በሴቶች ምድብ ደግሞ አትሌት ወርቅነሽ ኪዳኔ 21 ሜዳልያዎችን (11 የወርቅ፣ 6 የብር እና 4 የነሐስ) በመሰብሰብ ዓለምን ትመራለች፡፡
የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና  በኢትዮጵያ   ታላላቅ ውጤቶች የተመዘገበበት ውድድር ከመሆኑም  በላይ  በኦሎምፒኮችና በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ታላላቅ ስኬት ያገኙ አትሌቶችም    ተገኝተውበታል፡፡
ይህ ታሪክ ውድድሩን በኢትዮጵያ ለማስተናገድ ምክንያት መሆን አለበት።
የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው በማዘጋጀት የአውሮፓና የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ድርሻ ይወስዳሉ።
በአፍሪካ እህጉር ሻምፒዮናው ለሶስት ጊዜያት ተዘጋጅቷል፡፡ ከ7 ዓመት በፊት የሻምፒዮናውን አዘጋጅነት የምስራቅ አፍሪካዋ ኡጋንዳ አግኝታ በተሳካ ሁኔታ ማስተናገዷ የሚታወስ ሲሆን ከዚያ በፊት በ1998 በማራካሽ ሞሮኮ እንዲሁም በ2007 እኤአ በሞምባሳ ኬንያ ሻምፒዮናው ተካሂዷል፡፡ በ2026 እኤአ ላይ 46ኛውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በአሜሪካ ታሀላሴ እንዲካሄድ ተወስኗል። በአፍሪካ አህጉር ለ4ኛ ጊዜ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን በ2028 ወይንም በ2030 ለማዘጋጀት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን መስራት ይኖርበታል፡፡
የዓዎች አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ከመላው ዓለም  ከ140 በላይ ሚዲያዎች በስፍራው ተገኝተው የሚዘግቡትና በዓለም አቀፍ የቲቪ ስርጭት ከ5 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾችን የሚያገኝ ነው።፡
 በዋናዎቹ ውድድሮችና ሌሎች መርሃ ግብሮች ከ2ሺ በላይ ተሳታፊዎች ያሉት ሲሆን ከመላው ዓለም ተሰባስበው አዘጋጅ ከተማ ድረስ የሚገኙ ከ10ሺ በላይ የአትሌቲክስ አፍቃሪዎአ ናቸው።  ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር በሰራው ጥናት የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት አስፈላጊውን የመወዳደርያ ስፍራና የስፖርት መሰረተልማቶች ከማሟላት ባሻገር እስከ 2.3 ሚሊዮን ዶላር በጀት መመደብን ይጠይቃል፡፡     ከስታድዬም የመግቢያ ትኬቶች፤ ከስፖንሰርሺፕ እና ከሚዲያ መብት በአጠቃላይ ከ 3.07 ሚሊዮን ዶላር በላይ በቀጥታ ገቢ ይሆንበታል።

Read 445 times