Monday, 25 March 2024 00:00

በከብቶች ቁጥር ከዓለም 4ኛ? ምነው ታዲያ ድኻ ሆነች?

Written by  ዩሃስ ሰ.
Rate this item
(2 votes)

የአገራችን በሬዎች፣ ከጃፓንና ከአሜሪካ በሬዎች ጋር ሲነጻጸሩ ሩብ በሬ ናቸው። ትልቅ በግ እንደማለት ነው?
ባለፈው ሳምንት በእህልና በሥጋ ምርት የአገራችንን ታሪክ አውርተን የለ? የእህል ምርት ባለፉት ኻያ ዓመታት በጥቂቱም ቢሆን ተሻሽሏል። በአማካይ ለአንድ ሰው 150 ኪሎ ይመረት ነበር። በ2008 ወደ 250 ኪሎግራም ደርሷል። አሁንም እዚያው ግድም ነው።
መቼም በጣም እጅግ ዝቅተኛ ምርት ቢሆን ነው በየዓመቱ በርካታ ሚሊዮን ሰዎች በረሀብ የሚሰቃዩት። ዓለማቀፍ መረጃዎችን በቁጥር ስናነጻጽር ግን፣ የኢትዮጵያ የእህል ምርት “እጅግ በጣም ትንሽ ነው” ብለን ለመናገር የሚያስደፍር አይመስልም። አዎ ትንሽ ነው። ቢሆንም ግን…
እስቲ የተትረፈረፈ እህል የሚያመርቱ አገራትን ጭምር እንመልከት። በዓመት በአማካይ ለአንድ ሰው ብናሰላው፣ የእህል ምርታቸው ስንት ስንት ይደርሳል ብለን እንጠይቅ።
    ዓመታዊ የእህል ምርት በአማካይ ለአንድ ሰው
(በኪሎ ግራም)  
ዩክሬን      2000 ኪሎ
የአሜሪካ    1300 ኪሎ
ካናዳ       1200 ኪሎ
የአውሮፓ  አገራት    750 ኪሎ
የዓለም አማካይ    400 ኪሎ
የአፍሪካ         150 ኪሎ
የኢትዮጵያ      250 ኪሎ


የአፍሪካ የእህል ምርት እዚያው ባለበት ቦታ ሲረግጥ፣ የኢትዮጵያ ምርት ከተሻሻለ እንዴት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ረሀብ የሚበዛው?
በእርግጥ፣ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ውስጥም ብዙ ረሀብ አለ። በርካታዎቹ ግን ለረሀብ አይጋለጡም። ለምን? ገሚሶቹ የነዳጅ ምርት አላቸው። በረሐማ የሰሜን አፍሪካ አገራት ብዙ እህል ባያመርቱም እንኳ አይራቡም። እህል ከውጭ ገዝተው ያስገባሉ። ግብፅም ጭምር።
አንዳንዶቹ ደግሞ የአልማዝና የወርቅ ማዕድናትን ወደ ውጭ ይልካሉ። እህል ያስገባሉ። የምግብ ችግራቸው ከኢትዮጵያ ሻል ቀለል ይላል።
እንደዚያም ቢሆን፣ የኢትዮጵያ የእህል ምርት ከዓለም አማካይ የእልህ ምርት ጋር ሲነጻጸርም በጣም የተራራቀ አይደለም። 250 ኪሎና 400 ኪሎ በጣም ይበላለጣል? ዓመቱን ሙሉ 365 ቀናት መብላትና 300 ቀናት ብቻ መብላት፣ ብዙ ልዩነት እንደሚያመጣ አይካድም።
ቢሆንም ግን፣ ከ250 ኪሎ ምርት ወደ 400 ኪሎ ምርት ለመድረስ ምን ያህል ያስቸግራል? በዚህ አይን ስናየው በጣም ሩቅ አይመስልም።
ከአውሮፓም ቢሆን የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ አይደለም። የአውሮፓ የእህል ምርት ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸር 3 ዕጥፍ ገደማ ነው።
የአሜሪካ የእህል ምርት ከኢትዮጵያ አምስት ዕጥፍ ይሆናል። የካናዳም እዚያው አካባቢ ነው። በእህል ምርት በእጅጉ የምትታወቀው ዩክሬን፣ ወደ 8 ዕጥፍ ይደርሳል። ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸር ማለቴ ነው።
ልዩነቱንና ትርጉሙን በተግባር እናውቀዋለን። ዩክሬን የዳቦ ቅርጫ ናት ይሏታል። በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮን ኩንታል የሚቆጠር ስንዴ ለዓለም አገራት ትሸጣለች። ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከዓለም ዙሪያ ለተራቡ ዜጎች የእህል እርዳታ ትጠይቃለች።
እንደዚያም ሆኖ፣ የእህል ምርታቸው በቁጥር ሲታይ፣ ያን ያህል የተራራቀ ነው ወይ? የአሜሪካና የካናዳ፣ የእንግሊዝና የጀርመን ኢኮኖሚ በትክክል ከተሰላ… ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸር ከ50 እስከ መቶ ዕጥፍ ገደማ ይደርሳል። ይሄ ብዙ ነው። የእህል ምርት ላይ ግን 5 ዕጥፍ ብቻ!
ታዲያ ምነው የኑሮ ልዩነታችን የረሀብና የምቾት ሆነ?
የእህል ምርት በተፈጥሮው ከተወሰነ መጠን በላይ ከተሻገረ ይትረፈረፋል። ሰዎች፣ ሦሶት አራት ቅያሪ ልብስ ወይም ሠላሳ አርባ ቅያሪ ልብስ ሊኖራቸው ይችላል።
ከሦስት ጊዜ በላይ በየቀኑ መመገብ ግን ያስቸግራል። ቢበዛ አራት አምስቴ መብላት ይቻላል ብንል እንኳ፣ ከዚያ በላይ አይሻገርም። የሰዎች የምግብ ፍጆታ በተፈጥሮ አስገዳጅነት የተገደበ ነው።
በዚያ ላይ፣ የምግብ መጠን ብቻ ሳይሆን፣ የአይነትና የጥራት ደረጃ ላይም፣ በጣም የተለጠጠ የልዩነት ርቀት የለም።
ያው ስንዴ እንደሆነ ስንዴ ነው። እንቁላልም ያው እንቁላል ነው።
የልብስና የመኪና ዐይነት ግን፣ ጥራቱ ይለያያል። እንደ ስንዴና እንደ ዳቦ አይደለም። የአሜሪካ ስንዴና የኢትዮጵያ ስንዴ ምን አለያየው? የመኖሪያ ቤትና የመገልገያ ቁሳቁሶች ብዛትና ጥራት ግን ሰማይና ምድር ድረስ ሊለያይ ይችላል። በቁጥርና በጥራት፣ የጣሪያ ገደባቸው ሩቅ ነው።
ብልጽግናና ድኽነት እጅግ ይራራቃሉ። ኀምሳ እና መቶ እጥፍ ድረስ ሊለያዩ ይችላሉ።
በምግብ ዕጦት በረሀብ መሰቃየትና የተትረፈረፈ ምግብ ማግኘት ግን፣ ብዙ አይራራቁም። በቀን የአንድ ኪሎ እህል ልዩነት በጣም ከባድ ነው። የጥጋብ ኑሮና የረሀብ እልቂት ከዚህ የበለጠ ልዩነት የላቸውም።
በእርግጥ፣ በተወሰነ ደረጃ የኢንዱስትሪ እድገት ከሌለ፣ እጅግ አብዛኛው ሰው ገበሬ ከሆነ፣ የእህል ገበያው በጣም ትንሽ ስለሚሆን፣ የሰዎች ምርት ከእጅ ወደ አፍ መሆኑ አይቀርም። ትንሽ አስበልጠው ካመረቱ፣ የእህል ዋጋ ያሽቆለቁላል። ይከስራሉ። ትንሽ አሳንሰው ካመረቱ፣ በረሀብ ይሞታሉ።
በሌላ አነጋገር፣ የምግብ ዕጥረትና የምግብ መትረፍረፍ በጣም ተቀራራቢ ቢሆኑም፣ ያለ ኢንዱስትሪ ዕድገት ከረሀብ ወደ ምቾት መሸጋገር ከባድ ነው። ወደ ኋላ ተመልሶ መንሸራተትም ይኖራልና።
በብልጽግና ቀድመው ከተራመዱት አገራት ጋር ሲነጻጸር፣ የኢትዮጵያ የእህል ምርት እጅግ ባይራራቅም፣  “ጥልቀቱ ረዥም ነው” ማለት ይቻላል።
የሥጋ ምርት ላይም ነገሩ ተመሳሳይ ነው።
ድሮ፣ ኢትዮጵያ በከብት ብዛት ከዓለም 10ኛ ናት ይባል ነበር። ዛሬ፣ አራተኛ ናት። ከብራዚል፣ ከህንድና ከአሜሪካ በመቀጠል ማለት ነው። በኢትዮጵያ 70 ሚሊዮን ገደማ ከብት አለ።
በሥጋ ምግብ አቅርቦት ግን ከዓለም ሥር ናት። ለምን?
በሌሎች አገራት፣ በየዓመቱ 20 በመቶ ያህል ከብት ለዕርድ (ለምግብነት) ይውላል። በመላው ዓለም ከ1.5 ቢሊዮን ከብት አለ። ከዚህ ውስጥ በዓመት 330 ሚሊዮኑ ለምግብነት እንደሚውል የፋኦ መረጃ ይገልጻል።
በኢትዮጵያ ግን፣ ከ70 ሚሊዮን ከብት ውስጥ 20 በመቶ (ማለትም 14 ሚሊዮን ከብት) በዓመት ለምግብነት አይውልም። 4 ሚሊዮን ብቻ ነው ወደ ዕርድ የሚሄደው። ለምን?
አንደኛ፤ በርካታ በሬዎች ለእርሻ ሥራ ያስፈልጋሉ።
ሁለተኛ፤ በየዓመቱ ከ3 ሚሊዮን በላይ ከብቶች በበሽታና በአደጋ ይሞታሉ።
በዚያ ላይ፣… የኢትዮጵያ ከብቶች የደለቡ አይደሉም።
በሬ ወይስ ትልቅ በግ?
ኢትዮጵያ በከብት ብዛት ከዓለም አራተኛ መሆኗ በጀ እንጂ፣ የበሬ ሥጋ የሚሉት ነገር ለአይናችንም አናገኝም ነበር። በቁጥር ብዛት ካልተካካሰ በቀር፣ የአንድ በሬ ሥጋ በጣም ትንሽ ነው። የደለቡ አይደሉማ። በዚህ መነጽር እንይ ከተባለ፣ ከዓለም አገራት ተርታ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ ከታችኛው ወለል ላይ ከሚገኙ 15 አገራት መካከል አንዷ ናት።
ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ በሬ አማካይ የሥጋ መጠን 108 ኪሎግራም ብቻ ነው ይላል ፋኦ።
መቶ የሚሆኑ አገራት ውስጥ ግን፣ የአንድ በሬ ሥጋ ከ200 ኪሎግራም በላይ ነው።
የገሚሶቹም ከ300 እስከ 400 ኪሎግራም ይደርሳል።
በአጠቃላይ፣ ሦስቱ ምክንያቶች ተደራርበው ነው ኢትዮጵያ ውስጥ፣ የሥጋ ምግብ ብርቅ እየሆነ የመጣው። በከብት ቁጥር ከዓለም 4ኛ ብትሆንም፣ ብዙ ከብት ለምግብነት አይውልም። በበሽታም ያልቃሉ፡፡ የደለቡም አይደሉም።
እንዴት ብንገልጸው ይሻላል?
አንድ በግ በአማካይ፣ የ10 ዶሮ ያህል ሥጋ ይኖረዋል ይላሉ አንዳንድ የሙያው ዐዋቂዎች። (ከ12 ዶሮ ጋር የሚያስተካክሉትም አሉ)።
አንድ በሬ ደግሞ በአማካይ፣ የ10 በግ ያህል ሥጋ ይኖረዋል ይባላል።
የአገራችን በሬዎች ግን፣ ከጃፓንና ከአሜሪካ በሬዎች ጋር ሲነጻጸሩ ሩብ በሬ ናቸው። ትልቅ በግ እንደማለት ነው?
እንዲህም ሆኖ፣ ልዩነታችን በጣም ሩቅ ለሩቅ አይደለም። በኢኮኖሚ ልዩነታችን፣ በብልጽግና ከፍታና በድኽነት ዝቅታ  እንደ ተራራና ሸለቆ ልንሆን እንችላለን።
በእህል ምግብና በእንስሳት እርባታ ግን፣ ልዩነታችን ሰማይና ምድር አይደለም። ግን ምን ዋጋ አለው? የምግብ ጉዳይ ላይ በትንሽ ልዩነት ነው ጤንነት የሚሟላው፣ ወይም ደግሞ ረሀብና በሽታ የሚመጣው።


Read 439 times Last modified on Monday, 25 March 2024 11:51