ከዛሬ 42 ዓመታት በፊት አንድ ጓደኛዬ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አባል ሆኖ ተቀጠረ። ዘመኑ ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብር ጋብ ያለበት፣ ወጣቱ ትውልድ ቅስመ ሰባራ የሆነበት፣ ምንም የሥራ እድል የሌለበት፣ ብሔራዊ ውትድርና የታወጀበት፣ አንድ ለእናቱ የሆነው ዩንቨርስቲ ጥቂት ተማሪዎች የሚቀበልበት ጊዜ ስለሆነ ቀይ ባህር እንደ ጓደኛዬ አርቆ ለሚያስብ ትውልድ ማለፊያ መሸሸጊያው ነበር።
መጀመሪያ በአስመራ ከተማ በሚገኘው ባህር ኃይል ማሰልጠኛ ማዕከል ከጓደኞቹ ጋር መሰረታዊ የመርከበኝነት ሙያን ሰለጠነ። ስምንት ወራት የሚወስደውን “ሪኩሪት” እና “ቤዚክ ኮርስ” እንደ ተማሩ የመጀመሪያውን ስልጠና አጠናቅቀው፣ ከጓዶቹ ጋር ለተግባር ልምምድ ወደ ቀይ ባህር ተዛወሩ። ጓደኛዬ በዚህ ወቅት በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የወሰደው Seamen ship የተባለው ትምህርት በጣም ቀልቡን ስቦታል። ይህንን እውቀት በተግባር የሚከውንበት እለት እየናፈቀው ነው፣ ወደ ምጽዋ የተጓዙት። 115 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን ርቀትና ጠመዝማዛውን ከአስመራ ምጽዋ መንገድ አጠናቀው ወደብ ከተማዋ ገቡ። ሙቀቱም ተቀበላቸው። በጦር መርከቦችና በምጽዋ ባህር ኃይል መደብ ተመደቡ። ጓደኛዬ እንደጓጓው በቃኚ ጦር ጀልባ P204 ላይ ‘ገነር’ ወይም መድፈኛ ሆኖ ተመድቦ ልምምዱን ጀመረ። በዚህም ከራስ ካሳር እስከ ራስ ዱሜራ የተንጣለለውን ቀይ ባህር ይቀዝፍበት ጀመር።
ይህ የባህር ክልል 1000 ማይል ወይም 1800 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። የባህሩ ገጽ እንደ አየር ሁኔታ የሚለዋወጥ ሲሆን፤ አንዳንዴ ልክ በመስታወት የተለበጠ ይመስል ጸጥ ብሎ እያብረቀረቀ ለዘላለሙ ያሸለበ ይመስላል፤ትንሽ ሲነፍስ ወዲያው እንደ ባለዛር ባህሪው ተቀይሮ በማዕበል ይናወጣል። በዚህ ጊዜ ይህ ወጀብ የማይስማማቸው መርከበኞች ይታመማሉ። ልብን የሚፍቅ ቅርሻትን ጨምሮ የበሉዋትን አንድም ሳያስቀሩ ማስመለስ አለባቸው፡፡ ይሁን እንጂ አንዱ በሌላው ላይ እያላገጠ፣ እየተሳሳቁ የህይወት ሂደት ይቀጥላል። እንዲሁ አንዱ በሌላው ላይ እያላገጡም፣ ጀልባዋ ያፈራችውን ምግብ ስታቀርብላቸው ጥርግ አድርገው ይበላሉ። ለማዕበል ብትር ጋሻው ያገኙትን መመገብ ነው። በፍጹም ሌላ መድሀኒት የለውም። የሚገርመው ጀልባዋ ማዕበሉን መጋተሩን ጋብ ማድረግ ስትሻ፣ ፊቷን አዙራ ከማዕበሉ ጋር ስትቀዝፍ የመርከበኞቹ ህይወት መረጋጋት ይጀምራል። የታመሙትም ነብሳቸው ፈውስን ታገኛለች። ያልነበረ ያህል በፍጹም ይረሳል። የሚገርመው ለሰአታት ፋታ ከሰጠች በኋላ፣ እንደገና ፊቷን ወደ ወጀቡ ስትመልስ ያው ስቃይ ከች ይላል።
ጀልባዋ ቅኝት ላይ ስትሆን ኮንትሮባንድ ከጫኑ ጀልባዎች ጋር ባህር ላይ መፋጠጥ ይገጥማቸዋል። ኮንትሮባንድ ነጋዴዎቹ ከዚህ ሲጓዙ ወንድ ፍየልና በግ ይዘው ሲሆን፤ ከቀይ ባህር ማዶ ሲመጡ ደግሞ የታሸጉ ምግቦችን፣ጁሶችንና አልባሳት ስለሚይዙ፣ ይህ አጋጣሚ ለመርከበኞቹ ‘ሠርግና ምላሽ ‘ ይሆንላቸዋል።
መርከበኛን ሲገልጹዋቸው፤ “Elephant appetite” ይሏቸዋል። አንድን መርከበኛ ውድቅት ላይ ቀስቅሰው ምግብ ቢያቀርቡለት ጥርግ አድርጎ መመገብ የአብዛኛዎቹ ባህሪ ነው። ጓደኛዬ ግን መጥኖ መመገብ አንዱ ባህሪው ነው። በምንም ተአምር ተገኘ ብሎ ያገኘውን አያግበሰብስም። ይህ መጥኖ መመገብ ክፉው ቀን ሲመጣ መከራውን ለመቋቋም አስችሎታል፡፡
በነገራችን ላይ አንድ ዝሆን በቀን 300 ኪሎ ግራም እጽዋት ይመገባል። ከዚህ ውስጥ ግማሹ በእበት መልክ ይወገዳል። የሚደንቀው ወደፊት የሚበቅለው ግራር ዋንዛ ወዘተ-- ዘር እበቱ ውስጥ አለ። እበቱ ደግሞ ማዳበሪያ ይሆንና የወደፊቱን ዕፅ ያበቅለዋል። አመጋገቡም ከተገኘ አንጀት አርስ ነው። ከጠፋም ግንዲላውን ገንድሶ ፍልጡንም ቢሆን ያሻምደዋል፡፡ በዚህ ነው ‘ዝሆን ቂጡን ተማምኖ ግንድ ይውጣል ‘ የምንለው።
ሌላው ከጓደኛዬ አንድ የምወድለትን ድንቅ ባህሪ ይዞ ነው፣ ወደ ቀይ ባህር የዘመተው።ይኸውም ጸጥ ያለ ስፍራ ላይ ብቻውን ከሆነ፣ ጋደም ባለበት ያገኘውን መጻሕፍት ያነባል። ይህን ባህሪውን በባህሩ ዓለም በቅጡ ዘለቀበት። በዚህ የማንበብ ዝንባሌውና ፍቅሩ፣ ከጓደኞቹም ጋር መጻሕፍት ይዋዋሳል። የመጻሕፍት ምንጮቹ አስመራ ከተማ ጓደኞቹ ሲሄዱ ገዝተው እንዲያመጡለት ያደርጋል። በሚኖርባት ወደብ ከተማም ካሌብ ሲኒማ ፊት ለፊት አንዲት ትንሽ የመጻሕፍት ኪዮስክ ነበረች። የዚህች ኪዮስክ ቋሚ ደንበኛ ነበር። በተጨማሪ በምጽዋ ባህር ኃይል መደብ የሚገኘውን ቤተ መጻሕፍት በአግባቡ ይጠቀምበታል። ረቡዕ የP 201 እስኳድሮን አባላት ለህክምና ወደ ሆስፒታል ሄደው የሚታከሙበት ቀን ስለሆነ “ያመኛል” ብሎ በበሽተኞች ‘ሊስት’ ይመዘገብና ጉዞ ጀምረው ልክ ቤተ መጻሕፍቱ ዘንድ ሲደርስ፣ “ወራጅ ሆስፒታሌ ደርሻለሁ !” ይል እና ወደ ንባብ ቤቱ ይገባል። ግማሽ ቀን ጋዜጣውን ፣ መጽሔቱንና መጻሕፍቱን ይመረምራል። ኢንሳይክሎፒዲያ ከተባለው የዓለም መረጃ ከየተደራጀበት ጥራዝም ጋር የተተዋወቀው በዚህ አጋጣሚ ነበር። ልክ የምሳ ሰዓት ሲደርስ ወደ ጀልባው ይመለስና ከጓደኞቹ ጋር ጀልባዋ ያፈራችውን እየተቋደሱ ውሎውን ለባልደረቦቹ ያወጋቸዋል። ይህ እዚህች ጀልባ ላይ ሆኖ እስከ ቀዘፈባት ሦስት ዓመታት ዝንፍ ሳይል የከወነው ባህሪው ነው። ይህ ፕሮግራም የሚስተጓጎለው ባህር ላይ በቀዘፋ ላይ ከሆነ ብቻ ነው።
“ዛሬ ምን አነበብክ ?” ይጠይቃል አንዱ።
“ሼክስፒርን”
“ሼክስፒር እኮ አቻህ ነው። ለመሆኑ ከባልንጀራህ ጋር ምን ተባባላችሁ ?”
ጨዋታው ይደራል። ይህ አይነቱ ጨዋታ በተለይም ቀዘፋ ላይ ከሆነ የማዕበሉን ፈተና ያስረሳል። እንዲህ አይነት ጨዋታ አዋቂዎችም የጀልባዋ የህይወት ቅመሞች ናቸው። ጓደኛዬም ይህንን ተወዳጅነት ጀልባው ላይ አፍርቶ ሦስት ዓመታት ገደማ ከቀዘፈባት በኋላ፣ ከP 204 ላይ ወደ ምድር ወረደ። ያ በሳምንት አንድ ቀን እየሄደ ያነብበት የነበረው ቤተ መጻሕፍት ሀላፊ ሆኖ ተመደበ። ይህ የንባብ ልምዱ ህይወቱን በሙሉ ከማይረሳው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጋር አስተዋወቀው። P 204 ላይ እያለ ከእለቱ በአንዱ ቀን ስለ ጆን ኤፍ ኬኔዲ ታሪክ (1917 - 1963 ) አነበበ። በነገራችን ላይ ቀደም ብሎ በአገራቸው የባህር ኃይል አባል ሆነው የአገልግሎት ጊዜአቸውን በተለያየ ምክንያት አጠናቀው ወደ ሲቪል ህይወት የተቀላቀሉ መርከበኞችን ታሪክ ስራዬ ብሎ ያነባል። በአያሌው ከእነዚህ ታሪኮችም ይማራል። አንዱ የሚከተለው ነው።
ኬኔዲ በወጣትነት ዘመኑ የአሜሪካ ባህር ኃይል አባል ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሌፍተናንት ማእረግ የቶርፒዶ ተኳሽ 109 ጀልባ አዛዥ ሆኖ ከአስራሁለት መርከበኞች ጋር በደቡብ ፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ሰለሞን ደሴት አካባቢ ቅኝት ያካሂዳል። (ቶርፒዶ ባህር ውስጥ የሚተኮስ በራሱ መንኮራኩር ‘ፕሮፔለር’ ቀዝፎ ሄዶ የጠላት መርከብን የሚያጋይ ግዙፍ የጥይት አይነት ነው። የቶርፒዶ አንድ ጥይት ሦስት የተቀጣጠሉ በርሜሎችን ያክላል። አንድ ጀልባ አራት ቶርፒዶዎች ይጠመድባቸዋል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጀርመኖች የፈጠሩት ቶርፒዶ ወገን አስተካክሎ በተኮሱት አቅጣጫ ቀዝፎ ሄዶ የጠላትን መርከብ ቢያጣ እየተመላለሰ ፈልጎ የሚያጋይ አድርገው ፈልስፈዉታል። በሌላ አባባል፤ እናትህ ማህጸን ውስጥ ተመልሰህ ብትገባም አታመልጠውም እንደሚሉት ነው።)
በዚህ አይነት ወታደራዊ ቅኝት ላይ እያሉ ከጃፓን ዲስትሮየር ከተባለ አጋይና ደምሳሽ መርከብ ጋር በአንድ ምሽት ፊት ለፊት ተፋጠጡ። የጃፓኑ ዲስትሮየር የጠላት ትንሽ የለውም በሚል ስሜት የቶርፒዶ ጀልባዋን በከባድ መሣሪያ መታትና እንደ አክርማ ስንጥቅ አድርጎ ግባእተ ባህሯ ተፈጸመ። በዚህ ጥቃትም ከኬኔዲ ከአስራ ሁለት መርከበኞቹ ሁለቱ ተሰው። የብስ ላይ፤
“የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ
ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ “ ይባላል። ባህር ላይ ቀባሪው ሻርክ ነው።
ሌፍተናንት ኬኔዲ የተቀሩትን አስተባብሮ ለአምስት ሰአታት በመዋኘት እራሳቸውን ለማዳን ሽሽቱን ጀመሩ፡፡ ፍልሚያው በምሽት መከናወኑ ለእነ ሌፍተናንት ኬኔዲ መልካም እድል ነበር ፤ ምክንያቱም ቀን ቢሆን መትረፋቸውን ጃፓኖች አስተውለው በመርከባቸው መቅዘፊያ ይቆራርጧቸው ነበር። ከአስሩ አንዱ መርከበኛ ቆስሏል። የተቀሩት ሁሉ ደህና ናቸው። ኬኔዲ የቁስለኛውን መርከበኛ በለበሰው አንሳፋፊ ጃኬት ላይ የፕላስቲክ ገመድ አስሮ በጥርሱ ገመዱን እየጎተተ፣ ወደ አቅራቢያው ደሴት መዋኘት ጀመረ። ባህር ላይ ጠብ ያለች ደም ሻርክ በሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት እንደሚያይ ይታወቃል። ይህን ጊዜ ‘ ለሃጢያን የመጣ ለጻድቃን ይተርፋል’ እንዲሉት ይሆናል። ለዚህ ደም ለሚፈሰው መርከበኛ ሲል የመጣ ሻርክ እኛንም ዋጥ ስልቅጥ ያደርገናል ብሎ ሳይሰጋ፣ ከረዥም የዋና ሰዓታት በኋላ አንድ ደሴት ላይ ደረሱ፡፡ ደሴቱ ላይ የሚኖር የጃፓኖች ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ያንገሸገሸው አሣ አጥማጅ አገኛቸውና፣ አሜሪካውያን መሆናቸውን ስላወቀ “ ምን ልርዳችሁ ?” አላቸው።
“ወደ አውላላው ውቅያኖስ ሂድና የእኛን አገር መርከብ ስታገኝ እዚህ እንዳለን ንገርልን “ አሉት ።
አሳ አጥማጁም የተማጸኑትን ከወነላቸው። በዚህም እነ ኬኔዲ ለዳግም ህይወት በቁ። ሌፍተናንት ኬኔዲ በኋላ ወደ ፖለቲካው ዓለም ሲቀላቀልና ለፕሬዚዳንትነት ስልጣን ሲወዳደር አንድ የረዳው ተግባሩ ይህ የባህር ላይ ጀብዱ ነበር። በወቅቱ መንግሥት “የማሪን ክሮፕ ሜዳላይ” ተሸላሚ አድርጎታል። በሂደትም በፖለቲካው ዓለም የርሱና የደጋፊዎቹ ጥረት ታክሎበት የተባበሩት አሜሪካን አገሮች 35ኛ ፕሬዚዳንት ሆነ። ይህንን ታሪክ ካነበበ ጀምሮ ጓደኛዬ ”አንድ ቀን ባህር ላይ እወድቅ ይሆናል፤ የዚያኔ እራሴን የማድነው በዋና ነው“ በሚል ስሜት ተግቶ ዋናውን ይለማመድ ጀመር። ምጽዋ መርከብ ላይ የስራ ሰአት የሚጠናቀቀው ከቀኑ ሰባት ሰአት ላይ ነው። ቀጣይ ፕሮግራም ምሳ በልተው መርከበኞቹ የሃሩሩን ጊዜ በእንቅልፍ ያሳልፋሉ። ጓደኛዬ ግን ምሳው እንዲቀመጥለት ለወጥ ቤቱ ያስታውስና፣ እርሱ የዋና ልብሱን ለብሶ ወደ ባህር ውስጥ ዘሎ በመግባት ተግቶ የዋና ልምምዱ ያጧጥፍ ጀመር። ይህ ልምምድ ጥሩ መሰረት ከያዘለት በኋላ በቅጡ ባህር ላይ እንዳሻው መንሳፈፍ፣ በጀርባው ለጥ ብሎ መተኛት ቻለበት። ረዥም ርቀት መቅዘፍ ጸጋው ሆነ። ይህንን ጸጋውን ጓደኞቹ እንዲጋሩት በማድረግ እነሱም አብረውት እንዲዋኙ አስተባበረ። ተሳካለትም፡፡ በርካታ መርከበኞች ተከተሉት።
“ከአፍ ሲያመልጥ እራስ ሲመለጥ አይታወቅም” እንዲሉ፣ ጓደኛዬ ከአዲስ አበባ ወደ ምጽዋ ሲዘምት የተናገረውን አልረሳም። አፉን ሞልቶ “ የመጨረሻው ጦርነት የሚካሄደው በምጽዋ ወደብ ነው። እኔም ይህንን ጦርነት ተካፍዬ እመለሳለሁ! “ ብሎኝ ነበር። ያ እንደዋዛ የተናገራት ቃል እውን ሆነ። ሻዕቢያ ከ12 ዓመታት በፊት በሽንፈት ያጣውን ድል ለማግኘት ያለ የሌለ ሀይሉን አሰልፎ በጥር መጨረሻ በ1982 ዓ.ም ጦርነቱን ጀመረ። ተፈጥሮም ለአማጺያኑ ያደላች ይመስላል። ክሳዑዲ አረብያ የተነሳው የአሸዋ አውሎ ነፋስ ቀይ ባህርን ጨምሮ ምጽዋና አካባቢውን እንደ ብልኮ አለበሰው። ይህ ደግሞ ለአየር ኃይል ጀት ጥቃት እንዳይሰነዝር ይጋርደዋል። በዚህም ለጠላት ግማሽ ድል ስለሆነ ፍልሚያውን ከስድስተኛ ክፍለጦር ጋር ያጧጡፉት ጀመር። (ይቀጥላል)
***
ከአዘጋጁ፡-
ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ከ6 በላይ መጻሕፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡ ከጥበባዊና ወጋዊ ጸሃፊነቱ ባሻገርም የህይወት ታሪኮችን (ባዮግራፊስ) በመጻፍም ይታወቃል፡፡ ዘነበ ወላ አርታኢም ነው፡፡ ደራሲውን በኢሜይል አድራሻው፡
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ማግኘት ይቻላል፡፡
Sunday, 24 March 2024 00:00
ማንበብ ከሞትም ያድናል!
Written by ዘነበ ወላ
Published in
ጥበብ