Sunday, 24 March 2024 00:00

ዘውድ ሳይደፉ መንገስ (ክፍል 2)

Written by  ከእዝራ እጅጉ
Rate this item
(1 Vote)

 ባለፈው ሳምንት ጽሁፌ፣ ዘውድ ሳይደፉ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አይነተኛ ሚና ስለተጫወቱት ሰው በጥቂቱ አጫውቻችሁ ነበር፡፡ እኒህ ሰው  ጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሀንስ ሲባሉ፣ ራሳቸውን በማስተማር ከመካከለኛ ቤተሰብ ወጥተው በንጉስ ኃይለስላሴ ሥርአት ውስጥ ጉልህ ሚና ያበረከቱ ሰው ለመሆን በቅተዋል፡፡ ቃል በገባሁት መሠረት ቀሪውን ክፍል ዛሬ አጫውታችኋለሁ፡፡
“ዘውድ ያልደፋው ንጉስ“  በሚል ርእስ በጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ ሥራና ህይወት ላይ ያተኮረውን መጽሐፍ የጻፈው  ደረጀ ተክሌ፣ በወልደጊዮርጊስ የመጨረሻዎቹ  የስልጣን ዘመናት የነበረውን መንፈስ የመጓተት አዝማሚያ በስፋት የተስተዋለበት ነው ሲል ይገልጸዋል፡፡ በአጭር አገላለጽ፣ በአንድ በኩል አገር ከፍ ወዳለ የእድገት ደረጃ ላይ እንድትደርስ የሚሹ አሉ፡፡  በሌላ መልኩ፣ አንዱ ሌላውን ጠልፎ ለመጣል ሲያደርግ የነበረውን ግብግብ በግልጽ እንመለከታለን፡፡


ወልደጊዮርጊስ  ለ31 ዓመታት እናት ሀገራቸውን ካገለገሉ በኋላ ለዚያውም የሀገሪቱ ሁለተኛ  ሰው ሆነው ሳለ  ለምን ከጨዋታው ሜዳ ገለል እንዲሉ ተደረጉ? የሚለው የሁሉም ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ ለግለ- ታሪክ ጸሀፊው ደረጀ፤ ”ወልደጊዮርጊስ 31 ዓመት ካገለገሉ በኋላ  በግዞት መልክ  አሰላ በመሄዳቸው አላሳዘኑህም ወይ?” ስል ጠየኩት፡፡ ደረጀም ሲመልስ፤ “… እኔን አንጀቴን የበላቺኝ  ኢትዮጵያ ነች፡፡ ወልደጊዮርጊስማ በሚችሉት ሁሉ ለሀገራቸው ያለ አንዳች ስስት ሰሩ፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሳቸው መጠቀም አለመቻሏ  ይልቁንም በቁልቁለት መንገድ መጓዟ  ያሳዝነኛል” ሲል ምላሽ ሰጥቶኛል፡፡
ጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ ስልጣናቸውን በለቀቁበት ወቅት፣ በመኮንን ሀብተወልድና በወልደጊዮርጊስ  ወልደዮሀንስ መካከል ቅራኔ እንደነበር ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡  እንዲያውም ከሀብተወልድ ቤተሰቦች ውስጥ  ክቡር አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ ብቻ የወልደጊዮርጊስ ከስልጣን መነሳት ፍትሀዊ አይደለም ሲሉ ተቃውሞ አንስተው ነበር፡፡ ይህን ተቃውሞ በማሰማታቸውም አካለወርቅ ላይ ጥርስ መነከሱ አልቀረም፡፡
“የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት 1ኛ መጽሀፍ፤ ከ1923 እስከ 1948” የተሰኘውን መጽሐፍ የጻፉት አምባሳደር ዘውዴ ረታ፣  በመስከረም 1964 ፓሪስ በነበሩበት ጊዜ  ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድን  ለ10 ቀናት የማነጋገር እድል ገጥሟቸው ነበር፡፡ ታዲያ አምባሳደር  በዚህ ቆይታቸው ስለ ጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ  ስልጣንና ሽረት  ጠይቀዋቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሰፊ ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡ አክሊሉ ሀብተወልድ እና ጸሀፌ ትእዛዝ የተዋወቁት  በ1928 በስደቱ ዘመን ሲሆን፤ በጊዜው ወልደጊዮርጊስ የጃንሆይ ልዩ ረዳት ነበሩ፡፡ አክሊሉ ደግሞ  በ24 አመት እድሜያቸው በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ አንደኛ ጸሀፊ ሆነው ሲሰሩ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ከ52 አመት በፊት ስለ ወልደጊዮርጊስ ሲናገሩ፤ “…… ወልደጊዮርጊስ በችሎታቸው የሚተማመኑ፣ በስልጣናቸው ሳያመነቱ የሚወስኑ፣ ማንንም የማይፈሩ፣ የተፈጥሮ ብልህነት ያላቸው ጠንካራ ሠራተኛ ናቸው”  በማለት ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡
 ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ  እንደሚሉት፤ የጽህፈት ሚኒስቴርን ስልጣን በዘመኑ የፈጠሩት፣ ያሳደጉትም ያስፋፉትም ራሳቸው ወልደጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ታዲያ ይላሉ አክሊሉ ለአምባሳደር ዘውዴ ረታ በሰጡት ሀሳብ፤ ታዲያ ወልደጊዮርጊስ ይህን ከንጉሰ ነገስቱ ሳይዘጋጅ የተሰጣቸውን  ስልጣን በብልህነት ለማሳደግና ለማስፋፋት ዘዴ ነበራቸው፡፡ እንደ አክሊሉ እምነት፣ በወልደጊዮርጊስ ጊዜ ለጽህፈት ሚኒስቴር የተሰጠው ስልጣን ትልቅ ነበር፡፡  ከወልደጊዮርጊስ በፊት የነበሩት ጸሀፌ ትእዛዞች  እንደ እርሳቸው ትልቅ ስልጣን ኖሯቸው አያውቅም ሲሉ አክሊሉ ራሳቸውንም እንደ ዋቢ በማድረግ ይጠቅሳሉ፡፡
“…. ከእርሳቸውም በኋላ የተሾምነው አቶ ተፈራ ወርቅና እኔ  የእርሳቸውን ግማሽ እንኳን ስልጣን እንዳላገኘን  መታወቅ አለበት” ሲሉ  አክሊሉ ያስረዳሉ፡፡
ከ68 ዓመት በፊት የሀብተወልድ ወንድማማቾች ወልደጊዮርጊስን ከንጉሰ ነገስቱ ጋር አጣልተው  አሻሯቸው  እየተባለ በሰፊው ተወርቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከደራሲው ዘውዴ ረታ ጥያቄ የቀረበላቸው አክሊሉ ሲመልሱ፤ “…. የሀብተወልድ ወንድማማቾች  ወልደጊዮርጊስን ከስልጣን  አስነሱ መባሉን ራሳቸው ወልደጊዮርጊስ ሰምተው ከአካለወርቅ በስተቀር በሌሎቻችን ላይ ከፍ ያለ ጥላቻ አሳድረዋል፡፡ ይሄ በጣም ያሳዝናል፡፡ ይሁን እንጂ እውነቱ አንድ ቀን ተገልጦ እንደሚወጣ ብዙ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እርሳቸው ከመሻራቸው ከ1947 ቀደም ብሎ  ምናልባትም ከ6 ወር በፊት  ጃንሆይ  አውሮፓን በሚጎበኙበት ጊዜ ጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ  የተናገሩኝን አልረሳውም፡፡ ‘ አንተና ወንድምህ መኮንን ሀብተወልድ ዘመዳችሁን ሳህሉ ድፋዬን ጨምራችሁ እኔን ከጃንሆይ ጋር ለማጣላትና ከስልጣን ለማሻር  የምትሰሩትን ተንኮል ደርሼበታለሁ› ብለው ነበር” በማለት አክሊሉ ሀሳባቸውን  ገልጸው ነበር፡፡
ታዲያ አክሊሉ ለዚህ መሰረት ለሌለው  ወሬ  የእግዚአብሄርን ስም ጠርተው መልሱን ለወልደጊዮርጊስ ሰጥተው ነበር፡፡  ህሊናዬን   የሚቆጨው ነገር የለም ሲሉም ተናግረው ነበር፡፡  በዚህ ጉዳይ ላይ አክሊሉ ሀብተወልድ የሰጡትን  18 ገጽ የሚሆን ምላሽ “የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት” ከሚለው መጽሐፍ ከገጽ 773 እስከ 791 መመልከት ይችላሉ፡፡
 ድሮ ድሮ ከ1947 ቀደም ብሎ የወልደጊዮርጊስና የሀብተወልድ ቤተሰቦች እጅግ ቅርብ  ወዳጅ ነበሩ፡፡ ኋላ  ላይ ግን መጠነኛ ቅሬታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በሂደት ግን የወልደጊዮርጊስ ልጆችና የሀብተወልድ ቤተሰቦች ትልቅ እርቅ ፈጽመው  እንደ አዲስ ወዳጅነት መስርተዋል፡፡ ለዚህ እውነታ  እኔ የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ ጥሩ ምስክር ለመሆን እችላለሁ፡፡  የሚጠበቅባቸውም የሚፈለገውም ይሄው ነው፡፡
ወይዘሮ እጸህይወት ከወልደጊዮርጊስ  ልጆች አንዷ ስትሆን  አባቷ የቤተሰብ አሰባሳቢ እንደነበሩ ፈጽሞ አትዘነጋውም፡፡ “በትክክለኛ መስመር እንድንሄድ የረዳን ለሀገሩ የለፋ ታላቅ ሰው ነው” ስትልም ትገልጻቸዋለች፡፡ ወይዘሮ እጸህይወት በ1964 የባህር ማዶ ትምህርቷን ለመከታተል  ወደ ካናዳ ባቀናችበት ወቅት  አባቷ “ብቸኛው የስኬት መፍትሄ ትምህርትን ጠንክሮ መማር ብቻ ነው” ብለው ምክር ለግሰዋት ነበር፡፡  ልጅ እጸህይወት አባቷ ከባልደረቦቻቸው ጋር ሽኩቻ  በገቡበት ጊዜ ቤት ውስጥ በጨረፍታ ከሚወራው በስተቀር ነገሩ ፍንትው ብሎ አይታያትም ነበር፡፡  በጊዜ ሄደት እየበሰለችና በሂደት የዘመኑ የፖለቲካ እንካ ሰላንቲያ ሲገባት ሁሉን ተረዳች፡፡
ብዙዎች እንዳመኑት፣ የወልደጊዮርጊስ ተጽእኖ ፈጣሪነት ንጉስ ኃይለስላሴን ትልቅ ስጋት ውስጥ ከቷቸው ነበር፡፡ እናም ጃንሆይ ያለ ወልደጊዮርጊስ እውቅና ለየት ያለ የፖለቲካ ስልት መጫወት ነበረባቸው፡፡ ንጉሱ አንድ ጊዜ ወግ አጥባቂ ከሚባለው የመሳፍንቱ ወገን  ጋር ሲሆኑ፣ ደግሞ ሌላ ጊዜ  ወጣት የለውጥ አራማጅ ከሚባሉት ጋር በመሆን ስልጣናቸውን  አይነኬና አይደፈሬ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡  
“አባትሽ ወልደጊዮርጊስ ለንጉሱ ስልጣን የሚያሰጉ ይመስልሽ ነበር ወይ?” በማለት ወይዘሮ እጸህይወትን ስጠይቃት፤ “…. የማልክደው ሀቅ  አባቴ በሀገሪቱ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ይሻል፡፡ መፈንቅለ መንግስት የማድረግ ፍላጎቱም ህልሙም አልነበረውም፡፡ ደግሞም  አባቴ እስከመጨረሻው ድረስ ለንጉሱ ታማኝ ነበር”  ስትል መልስ ሰጥታኛለች፡፡
“አባቴ የንጉሱን ሞት የሰማው እንግሊዝ ሀገር ለህክምና በሄደበት ጊዜ  ነበር፡፡ ወዲያውኑ አልነበረም የንጉሱን ህልፈት የነገርነው፡፡ ቆይቶ ሰምቶ አዘነ”  ብላኛለች፡፡
ወልደጊዮርጊስ ከስልጣናቸው ተነስተው  አሩሲ  በግዞት መልክ ሲላኩ፣ እዚያም በየጊዜው ጸጉረ- ልውጥ እየተላከባቸው  አላስቆም አላስቀምጥ ብለዋቸው ነበር፡፡ ወልደጊዮርጊስ የአሰላ ጠቅላይ ገዥ በመሆን በ1947 ወደዚያው ሲያቀኑ ለትንሽ ጊዜ ሰርተው ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ይለቁ ይሆን? የሚለው ስጋት ብዙዎች ዘንድ  ነበር፡፡ እኔም ከ1947 እስከ 1954 ለ7 አመታት የነበረውን የግዞት ስልጣናቸውን እንዴት ተወጥተውት ይሆን ስል ለራሴ ጠይቄ ነበር፡፡ ያኔ አሰላ ሳሉ የተጻጻፏቸውን ደብዳቤዎችና ቴሌግራሞች ስመለከት ወልደጊዮርጊስ በሥራ ላይ ነበሩ፡፡
በመስከረም 1951 የእህል ነገር መሰረታዊ መሆኑን በማመን፣ ለሀገር ግዛት ሚኒስትሩ ለአቶ መኮንን ሀብተወልድ ፣ ወልደጊዮርጊስ  ይህንን ደብዳቤ ጽፈው ነበር፡፡
 ለክቡር አቶ መኮንን ሀብተወልድ   
ያገር ግዛት ሚኒስትር
ክቡር ሆይ፤    
በእህል  ሸመታ መወደድ ምክንያት ለእስረኞች  የተመደበው መኖ በአሁኑ ሰአት የማይበቃ ለመሆኑ በነሀሴ 26 1950 እንድናውቀው  የተደረገው  ደብዳቤ ብቻ ከሚደርሰን በስተቀር  ለጠየቅነው እስካሁን  ፈቃዱ አልደረሰንም፡፡ ደግሞም  ለሰራተኞች 158 ኩንታል ተኩል እንዲላክልን ጷግሜ  5 1950 በተጻፈ ደብዳቤ  አሳስበን ለነበረውም  እስካሁን  እህሉ ያልተላከ በመሆኑ  ሰራተኞች በብዙ ችግር ላይ የሚገኙ ስለሆነ  በጠየቅነው ልክ በቶሎ እንዲላክልን በማክበር አሳስባለሁ፡፡
 ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሀንስ  
                                   ፊርማ
ጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ በሀገሪቱ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጉዳዮችን ቀድሞ በመተንበይ ይታወቃሉ፡፡ በ1927 ገና ኢጣሊያ ወረራ ሳይፈጽም ለሀንጋሪው ጋዜጠኛ ፈራጎ ስለ ሰላማዊ ለውጥና  አብዮታዊ ነውጥ ልዩነት ባስረዱበት  ወቅት መንግስት የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል ካልቻለ ሀገሪቱ ለደም አፋሳሽ  አብዮት እንደምትዳረግ ተናግረው ነበር፡፡ ይህም አብዮት ባለስልጣናቱን  እንደሚፈጅ  አስጠንቅቀው ነበር፡፡  ትንቢቱን ከተናገሩ  ከ26 ዓመት በኋላ  የታህሳስ 1953ቱ መፈንቅለ መንግስት ተከሰተ፡፡
 የጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ ልጅ ወይዘሮ እጸህይወት  እንደምትለው፤  ደርግ ስልጣን ላይ ወጥቶ ያንን ሁሉ ንጹሀን  ያለ ፍርድ ሲረሽን  ወልደጊዮርጊስ ሃዘን ገብቷቸው ነበር፡፡  በ1968 ዓ.ም በእንግሊዝ ሀገር በህመም ሳሉ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚመጡላቸውን ጋዜጦች ወልደጊዮርጊስ ያነቡ ነበር፡፡
 ዘውድ ያልደፉት ንጉሥ ጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ፣ በሀምሌ ወር 1968 ዓ.ም  የዛሬ 48 ዓመት  75 ዓመት እንደሞላቸው ህይወታቸው አለፈች፡፡ እርሳቸው አቅማቸውን ሳይቆጥቡ ሀገራቸውን አገለገሉ፡፡ ትንሽ ቆጣ የሚሉ ሀይለኛ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ወልደጊዮርጊስ፤ ለንጉሱና ለሀገራቸው ታማኝ እንደሆኑ አለፉ፡፡ ኢትዮጵያ ለዚህ ውለታቸው ልታመሰግናቸው ይገባል ስል አስባለሁ፡፡ ዘመናዊቷን ኢትዮጵያ አምጠው ካዋለዱት አንዱ እርሳቸው ናቸው እና  ሁሌም ቢነገርላቸው  ቢዘከሩ ይገባቸዋል፡፡
እርግጥ ነው ይህች ሀገር ብዙ ያልተዘመረላቸው  ወልደጊዮርጊሶችን ይዛለች፡፡ የሁሉም የህይወት ገጽ ቢፈተሽ የዚህች ሀገር ዋና የታሪክ እውነቶች መገለጥ ይጀምራሉ፡፡
***
ከአዘጋጁ
 ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የከዛሬ 20 ዓመት ገደማ፣ ”ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን”ን የመሰረተ ሲሆን፤ እስካሁንም በዚህ ድርጅቱ አማካኝነት የ44 ባለውለታዎችን ታሪክ በሲዲ፣ የ14 ሰዎችን ታሪክ በመጽሐፍ አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡  በተጨማሪም የመጀመሪያውን የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ‹‹መዝገበ አእምሮ የሚድያ ሰዎች ታሪክን›› ያሳተመ ሲሆን፤ የመጽሐፍ፣ የሪል እስቴት፣ የሆቴልና ሌሎች ተቋማትን የምረቃና ክብረ በአል ስነስርአቶችን በማዘጋጀትም ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የ185 የኪነጥበብ ሰዎችን ታሪክ ለማሳተም በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 460 times Last modified on Monday, 25 March 2024 08:20