በእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ፣ የወተት ላሞች እርባታና የወተት ማቀነባበሪያ ሥራ ላይ የተሰማራው ርሆቦት ኃ.የተ.የግል ማህበር፤የፊልም ተዋናይዋን አርቲስት ራሄል እንግዳን የእናት ወተት ብራንድ አምባሳደር አድርጎ ሾማት፡፡
በዛሬው ዕለት ከሰዓት በኋላ በሸራተን አዲስ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ርሆቦት ኃ.የተ.የግል ማህበርና አርቲስት ራሄል እንግዳ በጋራ ለመሥራት ተፈራርመዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተጠቆመው፣ አርቲስቷ በርሆቦት ኃ.የተ.የግል ማህበር ሥር ከሚተዳደሩት አንዱ የሆነው የእናት ወተት የብራንድ አምባሳደር ሆና ምርቱን ታስተዋውቃለች ተብሏል፡፡
በመጋቢት 2010 ዓ.ም የተመሰረተው ድርጅቱ ዓላማው፣ ኢትዮጵያን የወተት ማማ ማድረግና የወተት እጥረትን መቅረፍ መሆኑን ይገልጻል፡፡
ድርጅቱ፤ ትኩስ (ፍሬሽ) ወተት፣ፕሌን ዮገርት፣ የተለያዩ ጣዕም ያላቸው ፍሌቨሮች፣ ሁሉም ዓይነት የቺዝ ምርቶች እንዲሁም የምግብና የገበታ ቅቤ የሚያመርት ሲሆን፤ ምርቶቹን በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ፣በኦሮሚያ ቡራዩ፣ ገላን፣ ዱከም፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆና አዳማ እንደሚያከፋፍል አስታውቋል፡፡
አርቲስት ራሄል እንግዳ ከፊልም ተዋናይነቷ ባሻገር ለዓላማዋ የጸናች ትልቅ የጥበብ ባለቤት መሆኗን የገለጸው ድርጅቱ፤ የእናት ወተት አምባሳደር ሆና ብራንዱን በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ ሚና እንደምትጫወት እምነቱን ገልጧል፡፡
Published in
ዜና