Monday, 01 April 2024 20:11

ማሕሌት፡ ዕንባዬ ምን ያረግልሃል?

Written by  -መኮንን ደፍሮ-
Rate this item
(1 Vote)

 ማሕሌት (1981) በአዳም ረታ የተጻፈ የአጫጭር ልብ ወለዶች መድበል ሲሆን ከኢትዮጵያ ብሉይ (classic) ሥራዎች መካከል አንዱ ተደርጎ የሚጠቀስ ነዉ፡፡ አዳም ረታ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ የፈጠረ ታላቅ ልብ ወለድ ደራሲ ነዉ፡፡ ደራሲዉ ለአራት አሥርት ዓመታት በዘለቀ የሥራ ዘመኑ በግሉ ስድስት የአጫጭር ልብ ወለድ መድበሎችን፡- ማሕሌት (1981)፣ አለንጋና ምስር እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች (2001)፣ እቴሜቴ ሎሚ ሽታ (2001)፣ ከሰማይ የወረደ ፍርፍር እና ሌሎች አጫጭር ልብወለዶች (2002)፣ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ (2003)፣ ሕማማትና በገና እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች (2004) እና አራት ረጅም ልብ ወለዶችን፡- ግራጫ ቃጭሎች (1997)፣ መረቅ (2007)፣ የስንብት ቀለማት (2008) እና አፍ (2010) ለህትመት አብቅቷል፡፡ ከሌሎች እዉቅ ልብ ወለድ ጸሐፍት ጋር ደግሞ አባ ደፋር እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች (1977)፣ ጭጋግና ጠል እና ሌሎች (1990)፣ አማሌሌ እና ሌሎችም (2009) እና አዲስ አበባ ኖይር (2012) የተሰኙ የአጫጭር ልብ ወለድ መድበሎችን ለህትመት አብቅቷል፡፡


በእዚህ ኂሳዊ መጣጥፍ ዉስጥ የምዳስሰዉ ማሕሌት አዳም በግሉ ያሳተመዉ የመጀመሪያ ሥራዉ ነዉ፡፡ ይህ የአጫጭር ልብ ወለዶች መድበል በዉስጡ አሥራ አንድ አጫጭር ልብ ወለዶችን ይዟል፡፡ ኂሳዊ መጣጥፉ የሚያተኩረዉ የመድበሉ መጠሪያ በሆነዉ ማሕሌት በተሰኘዉ አጭር ልብ ወለድ ላይ ነዉ፡፡ ይህ አጭር ልብ ወለድ ሥነ ልቡናዊ ልብ ወለድ (psychological novel) ነዉ፡፡
ማሕሌት በዋና ገጸባሕሪዋ (protagonist) ማሕሌት ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን ትረካ ነዉ፡፡ ትረካዉ የተጻፈበት ቋንቋ (literary diction) የነጠረ (high diction) ነዉ፡፡ በስም የተገለፁ በትረካዉ ዉስጥ የሚገኙ ገጸባሕሪያት ማሕሌት፣ እስጢፋኖስ፣ ዘመነ እና ሸጋዉ ናቸዉ። ትረካዉ በሦስተኛ መደብ ዉሱን ሁሉን አወቅ አኳያ (third person limited omniscient point of view) የተተረከ ነዉ። ቃናው (tone) ሆምጣጣ (serious) ነዉ፡፡ አንኳር ሴማው (theme) ሰዎች ላይ ሳይታሰብ የሚደርስ አሸባሪ ኩነት (traumatic event) ኅሊናቸዉ ላይ የሚፈጥረዉ መጥፎ ጠበሳ ነዉ፡፡ ይህ ሴማ የተገለፀዉ በማሕሌት ሕይወት ዉስጥ ነዉ፡፡


የልብ ወለዱ ታሪክ የሚጀመረዉ በማሕሌት እና በሠዓሊ እስጢፋኖስ ምልልስ ነዉ፤ ማሕሌት ጌታዋ ዘመነ ፎቅ ቤት ዉስጥ እስጢፋኖስ ተቀመጪ ባላት መልኩ ለሞዴልነት እርቃኗን ተቀምጣ፣ እስጢፋኖስ የወጠረዉ ሸራ ላይ የማሕሌትን ሸጋ ቁመና እየቀዳ፡፡ እስጢፋኖስ በሥራ ላይ እንዳለ ማሕሌት እሷን አቅፎ የሚስመዉ ምናባዊ ወንድ መልክና ቁመና ምን እንደሚመስል ትጠይቀዋለች፡፡ እስጢፋኖስም ለማሕሌት ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ከመመለስ ይልቅ ምን አይነት ወንድ እንዲሳል እንደምትፈልግ ይጠይቃታል፡፡ እሷም እንዲሳል የምትፈልገዉ ምናባዊ ወንድ ቀጭን፣ ረጅም፣ ፀጉረ ሉጫ፣ ሴታ ሴት መልክ ያለዉ መሆኑን ትነግረዋለች፡፡ እሱም የእሷ ምናባዊ ወንድ ከእሷ ሰዉነት ጋር አብሮ ስለማይሄድ ምርጫዋን እንዳልወደደዉ ይነግራታል (አዳም 1981፡ገጽ 39)፡፡ ይህ ምልልስ ደራሲዉ ስለ ቀጣዩ አንኳር ታሪክ ፍንጭ የሰጠበት ነዉ፡፡ ይህም የልብ ወለድ ዘዴ ንግር (foreshadowing) ተብሎ ይጠራል፡፡


ደራሲዉ የማሕሌት ህመም ሳቢያ (cause) የሆነዉን የሥር ታሪክ የሚነግረን ምልሰት (flashback) በምንለዉ የልብ ወለድ ዘዴ ነዉ። ማሕሌት በወላጅ አባቷና ሸጋዉ በተባለ ወጣት አባት መካከል በተደረገ የአድባር መሐላ መሠረት ለአቅመ ሄዋን ሳትደርስ ያለ ፈቃዷ ለሸጋዉ ትዳራለች፡፡ እናም ባሏ ጋር አንድ ጣራ ስር ልታድር ግድ ሆነ፡፡ ባሏም ወግ ነዉና አዉቋት የሚስቱን ማሕሌት ጨዋነት ለአደባባይ ሊያስመሰክር አብራዉ እንድትተኛ አባበለ። ማሕሌት ግን ከእሱ ጋር አንሶላ ለመጋፈፍ አሻፈረኝ አለች፡፡ ተስፋ የቆረጠዉ ሸጋዉ እኩለ ሌሊት ሲሆን፣ ልብሷን ቀዳዶ ደፈራት (አዳም 1981፡ገጽ 43)፡፡ ማሕሌት ሸጋዉ በጉልበት ሲደፍራት ራሷን ስታ ስለ ነበር ደራሲዉ እንደ ጻፈዉ፣ ““ብር አምባር ሰበረልዎ” ሲባልም፣ ሲዜምም አልሰማችም” (አዳም 1981፡ገጽ 43)፡፡ ማሕሌት ሸጋዉ ሕጓን በኃይል ከገሠሠበት ዕለት አንስቶ ለሳምንት ያህል ያነሳባትን የወሲብ ጥያቄ መቋቋም ባለመቻሏ ቤቱን ጥላ ወደ ዘመዶቿ አገር ቤት ኮበለለች፡፡
ማሕሌት ለሁለተኛ ጊዜ በአንድ የመኪና መካኒክ የወሲብ ጥቃት የደረሰባት አዲስ አበባ የሚኖር አጎቷ ጋር ለመኖር ከአገር ቤት ተመልሳ መጥታ ሳለ ነዉ (አዳም 1981፡ገጽ 43-44)፡፡
ዕድለ ቢሷና ረዳት የለሿ ማሕሌት ለሦስተኛ ጊዜ የወሲብ ጥቃት የደረሰባት ዘመነ ለተባለ ላጤ ግርድና በገባች ጊዜ ነዉ፡፡


ማሕሌት የደረሰባት ወሲባዊ ጥቃት (sexual assault) ኅሊናዋ ላይ መጥፎ ጠባሳ ፈጥሮ ስላለፈ ከደፈሯት ወንዶች ጋር ተመሳሳይ መልክ ያለዉን ማንኛዉንም ወንድ አምርራ የምትጠላ ሴት ናት፡፡ የመጀመሪያ ደፋሪዋ በጠባሳ የተዥጎረጎረ ፈርጣማ ክንድ ያለዉ ወንድ ነዉ። ሁለተኛ ደፋሪዋ ሲደፍራት በላብ የጠቆረ ነጭ ካናቴራ ለብሶ ነበር፡፡ ሦስተኛ ደፋሪዋ ባለ አፍሮ ፀጉርና ዐይነ ልም ነበር፡፡ አዳም የሚከተለዉን ጽፏል፦
ወደ አለበት አቅጣጫ ተመለከተች፡፡ መላጣዉን የሸፈነበት ባርኔጣ ወደ ሁዋላዉ ተንሸራቶአል፡፡ ግንባሩን አልቦታል፤ ከመነጽሩ ጀርባ ያሉት ትናንሽ ዐይኖቹ ፈዘዋል፡፡
“ምን አይነት ወንድ ነዉ የምትሥልልኝ? የምስመዉ ወንድ?”
“ነገርኩሽ’ ኮ!”
“ዐይኑ ምን ይመስላል?”
“ዐይኑን ስለሚጨፍነዉ አይታወቅም?”
“ሰዉነቱ ጡንቻማ ነዉ?”
“አዎ!”
“ለምሳሌ ክንዱ ላይ ልዩ ምልክት ይኖረዋል?”
“ምን አሳሰበሽ?”
“እንዲሁ፡፡”
“የክትባት ጠባሳ አለዉ፡፡”
በጥፍሮቿ ጭንዋን ቧጠጠች፡፡ አላያትም፡፡
“ፀጉሩስ?”
“ረዥም፡፡” እጁን ከፍ አርጎ አሳያት፡፡
“አልወደድኩትም፡፡”
“ለአንቺ’ ኮ አይደለም፡፡ ለአድናቂ ነዉ፡፡”
“ሌላ ወንድ ጠፋ እንዴ?”
ተደናገጠ፡፡ ግርምቡድ ላይ ተቀምጦ ወደ እስዋ እያየ፣
“ንገሪኝ አንቺ፡፡”
“ስለማላዉቀዉ ነዉ የጠየቅሁህ፡፡”


“ለምሳሌ- ልብስ ቢለብስ?”
“ምን?”
“ካናቴራ፡፡”
“ምን አይነት?” – በፍጥነት፡፡
“ነጭ፣ የቆሸሸ!”
“አይቻልም፡፡”
ተነስቶ ቆመ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ወደ ሸራዉ ጀርባ ጠፋ፡፡
“ሌላ ወንድ ሐሳብህ ዉስጥ የለም?” አለችዉ እስጢፋኖስን፡፡
“ምንም፡፡”
ጸጥ አለች፡፡
አፍዋን አሞጥሙጣ እንዳንጋጠጠች ዕንባ በጉንጮችዋ ወረደ፡፡
“ማሕሌት! … ማሕሌት!”
ዞር ብላ አየችዉ፡፡
“ምን ሆንሽ?”
“ምንም፡፡”
“ማልቀስ? … እባክሽን እንዳትጠርጊዉ … ግን ምን ሆነሽ ነዉ?”
“ዕንባዬ ምን ያረግልሃል?”
“ያላሰብኩትን በአጋጣሚ አመጣሽዉ፣ ‘ታንኪዩ!’
“የሚስመኝ ወንድ ያለቅሳል?”
“ለምን?”
“ለምን እኔ አለቅሳለሁ?”
“ፍቅር ሴት ላይ ይጠናል ይባላል – ማረጋገጫ ባይኖረዉም – ሴት ስታለቅስ ደግሞ ታሳዝናለች፡፡”
“ሁለታችንም እናልቅስ?”
“ይቅር አታልቅሱ፡፡”
“አይ የለም ላልቅስ፡፡ ሥዕሉ ላይ እንኳን ላልቅስ፡፡”
“አታለቅሽም፡፡”
(አዳም 1981፡ገጽ 46-48)
     ከእዚህ ታሪክ ሁለት ቁም ነገሮችን እናገኛለን፡፡ አንድ፣ ነፍሳችንን የሚንጡት ህመሞቻችን ሌሎች የማይረዷቸዉና የእኛኑ ያህል የሚፈጥሩትን ስቃይ ቀምሰዉ የማይመዙኗቸዉ መሆናቸዉን እንገነዘባለን፡፡ ሁለት፣ በተቃርኖ በፀናዉ በሰዉ ልጅ ሕይወት አንዱ ከሌላዉ ሰቀቀን ጥበብን እንደሚወልድ እንገነዘባለን፤ ከሐዘን የተቀዳዉ የማሕሌት ዕንባ የእስጢፋኖስን የኪነት ዐይን እንደ አበራዉ አይነት፡፡
***
 ከአዘጋጁ፡-
መኮንን ደፍሮ ልብወለድ ጸሐፊ፣ ገጣሚ እና የሥነ ጽሑፍ ኀያሲ ነው፡፡ የባችለር ድግሪውን በ2009 ዓ.ም፣ የማስተርስ ድግሪዉን ደግሞ በ2015 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍና አግኝቷል፡፡ በተማረው የሙያ መስክ በጅማ፣ በመቐለ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሠርቷል፡፡ ጸሐፊው አዲስ አድማስ ጋዜጣን ጨምሮ በተለያዩ መጽሔቶች ግጥሞቹንና የልብ ወለድ ሥራዎቹን አሳትሟል፡፡      መኮንን በርካታ የኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን ሥራዎች ላይ ኂሳዊ መጣጥፎችን ጽፏል፡፡

 

የቴሌግራም ቻናልችንን  በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Read 472 times