Saturday, 20 April 2024 11:03

ሰውዬው ዓለማየሁ፣ ከደራሲው ይልቃል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አልነጋም፤ ካሳንቺስ ሰውዬው መኖሪያ ቤት በር ላይ ደርሰናል።
ደወልን፤ ስልክ አነሳ። አሁን ልቤ ዐረፈ። ብዙ ጊዜ መንገድ ስለመኼድ ስንመካከር ደስ ብሎት ይሰማል። ዐልፎ ዐልፎ ደግሞ ይሳተፋል። “እዚኽ ደርሰን እንዲኸ አድርገን” ዓይነት። ከዚያ ጠዋት እንቀጣጠራለን። በሰዓቱ ግን የእሱ ስልክ አይሰራም።
ሻንጣውን አንጠልጥሏት ወጣ።
መንገዳችንን ቀጠልን።
እንዲህ ሆነን ማፌድ ደርሰናል። ዛሬም ድረስ ዓሌክስ እግሩ ከቤት ይውጣ እንጂ፣ የሆነ ቦታ ሲደርስ ለቦታው ስርዓት እንደምን ተገዢ እንደሆነ ያየሁበት ጉዞ ሆነ።
መስቀል ልናሳልፍ የደጉ ሰው ነዳ ሽጉሞ ቢሎ እንግዶች ሆነናል። መስከረም እኩል ሲሆን እኖር፣ ማፌድ ባሩኝ የምትባለው ትንሽ መንደር ገባን።
ከዚያ በኋላ አምስት ቀናት ቆየን። ዝም ብዬ ሳስበው ይደንቀኛል። ዓለማየሁ ገላጋይ ጥቂት ሰአት ከሰው ጋር ሲያሳልፍ የዚያን ሰው ሁሉን ነገር የነጠቀ የሚመስለው፣ ሽቁጥቁጥ ነው። በእኔና የማፌድ ቀናት ግን መሰልቸት አልታየበትም። ያደምጣል፤ ደግሞ እግሩ አይድረስ እንጂ፣ ንባቡ የደረሰበት ቀዬ ብዙ ነውና፣ ከሚያውቀው እያነሳ ይጠይቃል።
የስነ-ሰብ ጥናት ባለሙያዎች እንደ እሱ ያሉትን ሰዎች Cultural Intelligence ያላቸው ይሏቸዋል። ዓሌክስ እንዲህ ያለ ሰው እንደሆነ አምናለሁ። ባህልን የሚረዳው በብልሃት ነው። በዚያ ላይ ትርጉም የሚሰጥበት ብቃት ያስቀናኛል።
ደመራ የለኮሰን ቀን ከቤቱ አባወራዎች ጋር ረዥሙን የችቦ ጫፍ እሳት አስነክሶ፣ በዚች የባሩኝ መንደር ጀፈሮ ላይ ሲራመድ፣ አንድ መስቀል ከቀዬው ያልተለየ ጉራጌ ይመስል ነበር።
ዓሌክስ ሌላ አካባቢ ሲቀላቀል ሰላማዊ ስለሆነ አይረብሽም። በአካባቢውም ላለመረበሽ ራሱን ከስፍራው ጋር በጣም ያቆራኛል። ከጉራጌ ምድር ስንመለስ፣ የጉዟችን ምክንያት ለሆነው ወንድማችን ሃይሉ ሰለሞን “ሰውዬው እሺ ብሎ ከቤቱ ይውጣ እንጅ ቆይታውን ማጣጣም የሚችል የጉዞ ሰው ነው” አልኩት። ተሳሳቅን።
አካባቢን የሚረዳበት መንገድ በስራዎቹ ላይ ፍንትው ብሎ ይታያል። ለምሳሌ “የሞጆ ቀትሮችን” በ”የብርሃን ፈለጎች” ላይ ሳነብ፤ የኢኮሎጂ ትዝብቱና የገለፃ ርቀቱ ደራሲው በእርግጥም መቼቱን ማሳወቅ ብቻ ሳይሆን፣ ሳይንሳዊ በሆነ ሚዛን መረዳት ላይም የሚከበር ሰው ነው እላለሁ።
ከተፈጥሮ ያለውን ዝምድና በሥራዎቹ ተመልክቻለሁ። መራር ድምፆች በሰው በአካባቢና በተፈጥሮ ህልውና መስተጋብር ተጋምደው ይሰማሉ። “ታለ፤ በእውነት ስም” ላይ “ከተማ ሙቀት እና ጩኸት ነው.” ይላል። ይኼ አሁን የረቀቀው የተፈጥሮ ጥበቃ የሳይንስ ሊቃውንት ይዘውት ብቅ ያሉት የአካባቢ ፍልስፍና ነው። ዓለማየሁ በአጭሩ የGlobal Warming እና Sound  Pollution ችግር ከከተሜነት ቅጥ ማጣት ጋር የተሳሰሩበትን ቀውስ ትብታብ ያሳየናል። ወረድ ብሎም፤ “… ህይወት በከተማ ውስጥ ቅጥ አጥታለች፤ ተፈጥሮ ህብረ ዝማሬዎቿን ይዛ ተሰድዳለች። ወፎች- አይዘምሩም፣ ውሆች ፀናፅናቸውን አያንሿሹም፣ ዛፎች ከነፋሳት ጋር አይላፉም። ከዚህ በመነሳት፣ ዓለም አረንጓዴ ትችት ለሚለው ዘመነኛ አብዮት ዓለማየሁ Ecocriticismን በፈጠራ ሥራዎቹ በማሳየት ለአካባቢው የቀረበበትን ስሱ ልብ እንድናይ አድርጎናል።
ብዙ ጉዞዎችን አብረን ተጉዘናል። ለቀናት ቆይተናል። ምርጫው ያለበትን ቦታ በቅጡ መረዳት እንደሆነ አይቻለሁ። በእድሜ ጠና ካሉ ሰዎች ጋር መጨዋወት ይመርጣል። ብዙ ሰአት ወስዶ ራሱን እየነቀነቀ ያደምጣቸዋል።
ብዙዎች Bibliophile or Bookworm ስለሆነው ዓለማየሁ ያውቃሉ። እሱ ግን Empathetic የሚሉት ዓይነት ሰው ነው። ጥልቅ ብሎ ያደምጣል፤ ይረዳል። ከተረዳው ነገር ጋር አብሮ ይኖራል። ደጋግሞ “ለተፈጥሮ ግድ የለኝም። ፏፏቴ ለማየት ገደል ባልወርድ እመርጣለሁ” ይለኛል። ይሄንን እንዳልቀበል ያደረጉኝ ጉዞዎች ግን ነበሩን። ተራራው አጠገብ አብረን ስንቆም፣ ተራራውን የተመለከተበትን ስስት አልረሳውም።
ወደ አንኮበር አብረን ተጉዘናል። እመ ምህረት ተራራ አጠገብ ቆመን ለተፈጥሮው እጅ ሲሰጥ አይቻለሁ። ከዚያ የማያቆም ጥያቄ ቀጠለ፤ መኪናው እንዲቆም አሳሰበ።
“ቁንዲ የምትታይበት እንቆምና ፎቶ እንነሳለን፣” ይለናል። በእርግጥ ወደ ቁንዲ እንሂድ አይበል እንጂ ቁንዲ አጠገብ መድረስ ግን መሻቱ እንደሆነ ተረዳሁት። እንዲያ ባይሆን፣ ቅንብቢት በዚያ መልኩ መች ትገለጽ ነበር? ያለፈባቸውን ብቻ የሸኖ ጎዳናዎች በዚያ መልኩ ሊረዳቸው እንደምን ይችላል?
ተራራ ብቻ ሳይሆን፣ ውኃም ትንፋሹን ስትር አድርጎ ተፈጥሮን ያደምጥ ዘንድ ያደርገዋል። ወደ ጣና አብረን ተጉዘናል፤ በተደጋጋሚ። ጀልባ ላይ ከወጣ በኋላ ዐይኑን ባሕሩ ላይ ተክሎ ዝም ይላል። ያን ዓይነት ምሳጤውን የማስታውሰው፣ በሰዎች መካከል ሆኖ ዐልፎ ዐልፎ እጁን አፉ ላይ ያደርግና በሐሳብ ሩቅ ሲሄድ ነው። ይሄንን አይነት ስሜት በሀዋሳ የሀይቅ ዳርቻ አሞራ ገደል አረፍ ብለን ስንጫወት፣ እሱ ዐይኖቹን ሰድዶ ከፍቅር ሐይቁ ጋር ሲነጋገር አይቼበታለሁ። በጥልቅ ስለሚረዳው አካባቢ አንዳች ነገር ሲገልጽ ይነዝራል። ጎንደርን “የህልሜ ከተማ” ሲላት የቀናሁት ቅናት አሁንም አልለቀቀኝም። ወደ ጎንደር ስንሄድ ብዙ ጊዜ ሳይደርስ መመለስ የማይፈልግበት ቦታ ሞኝ መቆሚያ ነው። ለምን እንደሚወደው አላውቅም። ቦታው የጉልበት ሠራተኞች አሰሪ ጥበቃ የሚቆሙበት ሲሆን፣ ዓሌክስ በጎንደር ቆይታው አንዱን ቀን ሞኝ መቆሚያ ደርሰን እንምጣ ሳይለን አይቀርም።
ገና የፋሲል ከተማ ሲደርስ “ዋሴ ነጋሽ ሞኝ መቆሚያ ደርሰን አንመጣም?”ይጠይቃል። እንስቃለን። ወግ አጥባቂዎቹ አካባቢዎች አብረን ስንቆይ ወግ አክባሪው ዓለማየሁ ስፍራውን መስሎ የብዙ አባቶችን ልብ በልቶ ይመለሳል። ትዝታዎቹ ሆነው ይቀራሉ። ዓሌክስ ወደ ፀሐይ መውጫ ሲሄድ ደግሞ ቀላልና ተግባቢ ሰው ሆኖ ይገለጣል። የባሕር ዳር ልጆች የሚያውቁትን ዓሌክስ የድሬ ልጆች ኤውቁትም፤ ሁለቱንም የሚያውቀው ዓሌክስ ግን ቦታን፣ ሰውንና ባህልን የሚረዳበት መንፈሱ ድንቅ ነው።
በነገራች ላይ፣ ኣለማየሁ ገላጋይ ደርሼ ጥምድ ያደረኩት ሰው ነበር። በእልህ ሥራዎቹን አላነብም ብዬ ብዙ አመጽኩ። በጣም ብዙ ጊዜ። ለምን እንዲያ እንደሆንኩ  ሳስበው ብቻዬን ፈገግ እላለሁ። በሰዎች ጥያቄና ምልጃ አንድ መጽሐፉን ለማንበብ ተስማማሁ። “ወሪሳ”ን አነበብኩ። ከዚያ በኋላ በሆነው ተቃራኒ ስሜቴ በጣም እገረማለሁ።
ዓለማየሁ አምጰርጵርን ብቻ ሳይሆን፣ እኔንም አምጰረጰረኝ። ያለ ዕረፍት ሌሎቹንም ስራዎቹን አከታትዬ አነበብኩ። አንድ ቀን ሳገኘው ነገርኩት። አቀርቅሮ አድናቆቴን እንደ ሸክም ቆጥሮብኝ ዐለፈ። የጋራ ወዳጆች ነበሩን። አስደናቂው ነገር ግን  ትውውቃችን የጠነከረው በጉዞ ሆነ። ወደ ባሕር ዳርና ጎንደር አብረን ተጓዝን፤ ለወዳጅነታችን የማዶ ለማዶ በራፉን የገነጠልንበት ቆይታ ሆነ። እንዲህ እንደ ቀልድ አመት ዓመቱን እየወለደ፣ ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን አብረን የምንውል ወዳጆች ሆንን።
“ወሪሳ” አስማት የሆነ ሥራው ነው፤ ብዙ ሰውም ይጋራኛል። “በፍቅር ስም”፣ “ታለ፤ በእውነት ስም” እና “ሐሰተኛው፤ በእምነት ስም” እጅግ የወደድኳቸው ስራዎች ናቸው። ከኢ- ልቦለዶቹ “ኢሕአዴግን እክሳለሁ” ያስገርመኛል፡፤ “ውልብታ” ሳትገባኝ የቀረች ስራ ናት።
በወዳጅነታችን የደረስኩበት ድምዳሜ ሰውዬው ዓለማየሁ፣ ከደራሲው ዓለማየሁ በላይ አስደናቂ ሰው ነው የሚል ነው። ስሱ ልብ አለው፤ ትልልቆቹን ያከብራል፤ ከነክብራቸው በደስታ ያልፉ ዘንድ ቁጭት መሰናክላቸውን የሚያነሳ መንገድ ጠራጊ ነው። ታዳጊዎችን አቅጣጫ ለመምራት መንገድ ቆሞ ይጠብቃል። ራሱን ዝቅ አድርጎ ከፍ የሚሉበትን ይመራል። ኣለምን ይንቃታል። ስስት አያውቅም፤ ጊዜውን፣ ገንዘቡን፣ ፍቅሩን የማይሰስት ወዳጅ ነው።
ምንጭ፡ -“መልክአ ዓለማየሁ” ፤ቴዎድሮስ አጥላው (አርታኢ)

Read 835 times