Sunday, 21 April 2024 00:00

የአባቴ ምስጢር (እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ)

Written by 
Rate this item
(7 votes)

የመጨረሻ አመት የኮሌጅ ተማሪ ነበርኩ፡፡ ለገና ወደ ቤተሰቦቼ ዘንድ ስሄድ ከሁለት ወንድሞቼ ጋር አስደሳች ጊዜ እንደማሳልፍ ጠብቄአለሁ፡፡ ሦስት ወንድማማቾች በመገናኘታችን ደስታችን ወደር የለሽ ነበር፡፡ አባትና

እናታችን በስራ ተወጥረው ለዓመታት ተዝናንተው አያውቁም፡፡
ስለዚህ እኛ መደብሩን ለመጠበቅ ተስማማንና ለጥቂት ጊዜ ወጣ ብለው እንዲዝናኑ ነገርናቸው፡፡ ሁለቱም አልተቃወሙም፡፡ ወደ ቦስተን ለመጓዝ ሻንጣቸውን መሸከፍ ያዙ፡፡
ከጉዟቸው አንድ ቀን በፊት አባቴ እጄን ይዞ በቀስታ ከመደብሩ ኋላ ወዳለችው ማረፍያ ክፍል ወሰደኝ፡፡ ክፍሏ ጠባብ ናት - አንድ ፒያኖና ታጣፊ አልጋ ብቻ ነው የያዘችው፡፡
በእርግጥ አልጋው ሲዘረጋ ክፍሉ ይሞላል፡፡ አልጋው ግርጌ ተቀምጦ ፒያኖ ከመጫወት በቀር አያፈናፍንም፡፡ አባቴ ከአሮጌው ፒያኖ ጀርባ እጁን ሰደደና ትንሽዬ ሳጥን ጐትቶ አወጣ፡፡
ከዚያም ሳጥኑን ከፍቶ አሳየኝ፡፡ ተከርክመው የወጡ የጋዜጣ ፅሁፎች ናቸው፡፡ በመገረም አፌን ከፍቼ ፅሁፎቹን እመለከት ጀመር፡፡ ብዙዎቹን የናንሲ ድሪው የወንጀል ምርመራ ታሪኮች አንብቤአቸዋለሁ፡፡ እዚያ ሳጥን

ውስጥ የተቀመጡበት ምክንያት ግን አልገባኝም፡፡
“ምንድናቸው?” አልኩት፤ አባቴን ቀና ብዬ እያየሁት፡፡
“እኔ የፃፍኳቸው ታሪኮች ናቸው፤ ለአዘጋጁ የፃፍኳቸውም ደብዳቤዎች አሉበት” ሲል መለሰልኝ፤ ኮስተር ብሎ፡፡
አባቴ እያፌዘ እንዳልሆነ ከድምፁ ቃና ተረድቼአለሁ፡፡ በመገረምና ግራ በመጋባት መሃል ሆኜ ጋዜጦቹን ሳገላብጥ፣ ከእያንዳንዱ ፅሁፍ ሥር “ዋልተር ቻፕማን ኢኤስ ኪው” ተብሎ የተፃፈውን አየሁት - የአባቴ

እውነተኛ ስም ነው፡፡ ሳላስበው ደሜ መሞቅ ጀምሯል፡፡ “ለምንድነው እስከ ዛሬ ያልነገርከኝ?”  ጠየቅሁት፤ ንዴቴን እንደምንም ተቆጣጥሬ፡፡
“እናትህ ስለማትፈልግ ነው”
“ምኑን?” ድምፄ መጮሁን ያወቅሁት ዘግይቼ ነው፡፡
አባቴ ድምፄን እንድቀንስ በምልክት ነገረኝና፣ አስገራሚውን ልቦለድ የሚመስል ታሪክ አወጋኝ፤ ዝግ ባለ የተረጋጋ ድምፅ፡፡
“እናትህ ጋዜጣ ላይ መፃፌን አትወደውም ነበር…”
“ለምን? ለምንድነው የማትወደው?”
አሁንም ድምፄን እንድቀንስ አሳሰበኝ፤ እናትህ ከሰማች ትገለናለች በሚል፡፡
“በቂ ትምህርት ስለሌለህ ባትሞክረው ይሻላል ብላ ደጋግማ አስጠንቅቃኛለች”
የእናቴ ነገር ገርሞኝ ጭንቅላቴን ስነቀንቅ አባቴ ቀጠለ፤
“አንድ ጊዜ በፖለቲካ ምርጫ ልወዳደር ፈልጌ ነበር… ይሄንንም ባትሞክረው ይሻልሃል አለችኝ”
“ቆይ ለምን?” አሁንም እንደ አዲስ ጠየቅሁት፡፡
“ተሸንፈህ ታዋርደናለህ.. ክብራችንን እንደጠበቅን ብንኖር ይሻላል አለችኝና ተውኩት” አለኝ፤ በቁጭት በታሸመ ቃና፡፡
እናቴን የማላውቃት ያህል ተሰማኝ፡፡ አባቴ አንጀቴን እየበላው፣ እሷ እያስጠላችኝ መጣች - በልቤ ውስጥ፡፡ ይሄን ያህል ጨካኝ እንደነበረች አላውቅም ነበር፡፡ በእጆቼ ላይ ካሉት የአባቴ መጣጥፎች አንደኛውን

ሳላውቀው ማንበብ ጀምሬ ነበር፡፡ በመሃላችን የነገሰውን ዝምታ የሰበርኩት ግን እኔው ነበርኩ፡፡ አይኖቼን ከጋዜጣው ፅሁፍ ላይ ነቅዬ አባቴን ቀና ብዬ እያየሁ ጠየቅሁት፤
“ታዲያ ይሄ ሁሉ ፅሁፍ እንዴት ታተመ?”
“እስቲ ልሞክር ብዬ እሷ ሳታውቅ መፃፍ ጀመርኩ… እያንዳንዱ ፅሁፌ ጋዜጣው ላይ ሲወጣልኝ ከርክሜ አወጣውና እዚህች ሳጥን ውስጥ እደብቀዋለሁ… አንድ ቀን ሳጥኗን ለአንድ ሰው እንደማሳየው አውቅ ነበር”
“ለማን?” ሳላስበው ከአፌ ተስፈትልኮ የወጣ ጥያቄ ነው፡፡
“ላንተ ነዋ!” አለኝ፤ በእውነተኛ የአባትነት ፍቅር ትክ ብሎ እያየኝ፡፡ ዓይኖቼን ሰብሬ የጋዜጣው ፅሁፍ ላይ ተከልኳቸው፡፡ ሁለት ፅሁፎቹን አንብቤ እስክጨርስ አባቴ ቁጭ ብሎ እየተመለከተኝ ነበር፡፡
ቀና ብዬ ሳየው ትላልቅ ሰማያዊ ዓይኖቹ በእንባ እርሰዋል፡፡ መሃረቡን ከኪሱ ውስጥ አወጣና ዓይኖቹን ከጠራረገ በኋላ፤ “ባለፈው ጊዜ ያለ አቅሜ ትልቅ ነገር ሞከርኩ መሰለኝ ይኸው ሦስት ወሩ… አልወጣም”

አለኝ፤ በፈገግታ፡፡
“ሌላ ነገር ፅፈህ ነበር?” ጠየቅሁት፤ በጉጉት፡፡
“አዎ ብሄራዊ መራጭ ኮሚቴ እንዴት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሊመረጥ እንደሚችል አንዳንድ ሃሳቦችን ፅፌ ለሃይማኖታዊ መፅሄታችን ልኬ ነበር፤ ግን እስካሁን አልታተመም… ትንሽ ያለ አቅሜ ሳልንጠራራ

አልቀረሁም”
ይሄ ጉዳይ እኔ የማላውቀው የአባቴ አዲስ ገፅታ ቢሆንም፣ አንድ ነገር ማለት ነበረብኝ፡፡
“አይታወቅም … ሊወጣ ይችላል” አልኩት
“ምናልባት ይወጣ ይሆናል…
ግን አይመስለኝም”
ቁራጭ ፈገግታ እያሳየኝ የጋዜጣ ቁርጥራጮቹን ሳጥኑ ውስጥ ከቶ ዘጋባቸውና፣ ከፒያኖው ጀርባ ባለው ክፍት ቦታ መልሶ ወሸቀው፡፡
በነጋታው ወላጆቻችን በአውቶብስ ተሳፍረው ወደ ሃቨርሂል ዲፖት ሄዱ፡፡ እዚያ ሲደርሱ በባቡር ተሳፍረው ነው፣ ወደ ቦስተን የሚጓዙት፡፡ እኔና ሁለት ወንድሞቼ ፣ጂምና ሮን መደብሩ ውስጥ ስንሰራ ዋልን፡፡ ቀኑን

ሙሉ ስለ አባቴ ሳስብ ነበር፡፡
የአባቴን የጋዜጣ ፅሁፎች ደብቃ ስለያዘችው ትንሽዬ ሳጥንም ማሰላሰሌ አልቀረም፡፡ አባቴ መፃፍ እንደሚወድ ፈፅሞ አላውቅም ነበር፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ለወንድሞቼ አልነገርኳቸውም፡፡
የአባቴና የእኔ ምስጢር ነዋ! የተደበቀችው ሳጥን ምስጢር!
የዚያኑ እለት ፀሃይ መጥለቂያዋ ላይ መደብር ውስጤ ቆሜ በመስኮት ስመለከት እናቴ ከአውቶብስ ስትወርድ አየኋት - ብቻዋን፡፡ አደባባዩን ተሻገረችና ጥድፍ ጥድፍ እያለች ወደ መደብሩ ገባች፡፡
“አባባስ?” ስንል በአንድ ድምፅ ጠየቅናት፡፡
“አባታችሁ ሞቷል” አለችን፤ አይኗ እንደደረቀ፡፡
ጆሮአችን የሰማውን በመጠራጠር ተከትለናት ወጥ ቤት ገባን፡፡ መሞቱ እውነት መሆኑን በደንብ አረጋገጥን፡፡ በፓርክ ስትሪት የምድር የውስጥ ለውስጥ ባቡር ጣቢያ በኩል ሲያልፉ ነው፣ ህዝብ መሃል አባታችን

ድንገት የወደቀው፡፡
አጐንብሳ ስትመለከተው የነበረችው ነርስ ወደ እናቴ እያየች፤ “ሞቷል!” አለቻት እንደዘበት፡፡
እናታችን በድንጋጤ እምታደርገው ጠፍቷት ዝም ብላ አጠገቡ ተገትራ ነበር፡፡ መንገደኞች ወደ ባቡር ጣቢያው ለመግባት ሲጣደፉ እየረጋገጡ አስቸገሯት፡፡ ለአንድ ሰዓት ያህል እግሯን አንፈራጣ የአባባን አስከሬን

ከመንገደኞች ስትከላከል ከቆየች በኋላ አምቡላንስ ደረሰ፡፡
እናታችንንና አስከሬኑን ይዞ በአካባቢው ወዳለው ብቸኛ የመቃብር ቤት ወሰዳቸው፡፡ ኪሱን ፈታትሻ ሰዓቱን አወለቀችለትና ባቡር ተሳፍራ ብቻዋን ወደ ቤት ተመለሰች፡፡
እናታችን ይሄን አስደንጋጭ ታሪክ የነገረችን አንዲትም እንባ ጠብ ሳታደርግ ነው፡፡
ሁሌም ቢሆን ስሜታዊ አለመሆን ለሷ የስርዓትና የክብር ጉዳይ ነው፡፡ እኛም ራሳችን እንድናለቅስ አልተፈቀደልንም፡፡ የመደብሩን ደንበኞች ተራ ገብተን ማስተናገድ ያዝን፡፡ አንድ የመደብሩ የዘወትር ደንበኛ መጣና፤
“ዛሬ ሽማግሌው የት ገባ?” አለኝ
“ሞተ” አልኩት “ኦው… በጣም አሳዛኝ ነው” ብሎ ሄደ፡፡
የደንበኛው አጠያየቅ አሳብዶኝ ነበር፡፡
 አባቴን እንደ ሽማግሌ አስቤው አላውቅም፡፡ በእርግጥ እሱ 70፣ እናቴ 60 ዓመቷ ነበር፡፡ ሁልጊዜም ጤናማና ደስተኛ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ ጤና የሌላትን እናታችንን አንዴም ሳይነጫነጭ ተንከባክቧታል፡፡  አሁን ግን

“ሽማግሌው ሞቷል፡፡”
በነጋታው ቁጭ ብዬ ለቤተሰቡ የተላኩ የሀዘን መግለጫ ካርዶችን ከፖስታ ውስጥ እየከፈትኩ ስመለከት አንድ የቤተ ክርስትያን መፅሄት አየሁኝ፡፡ ሌላ ጊዜ ቢሆን የሃይማኖት መፅሄት ትኩረቴን አይስበውም ነበር፡፡

ምናልባት የአባቴ ፅሁፍ ወጥቶ እንደሆነ ለማየት፣ መፅሄቱን ማገላበጥ ያዝኩ፡፡ የአባቴ ፅሁፍ ታትሟል፡፡ መፅሄቱን ይዤ ወደ ትንሿ ክፍል ሹልክ ብዬ ገባሁና በሩን ቆልፌ ተንሰቅስቄ አለቀስኩ፡፡ እስከዚያች ቅፅበት

ድረስ ራሴን አጀግኜ ነበር፡፡ አባቴ የሰጠው ደፋር ሃሳብና ምክር መፅሄቱ ላይ ታትሞ ስመለከት ግን ከአቅሜ በላይ ሆነብኝ፡፡ ጽሁፉን አነብና አለቅሳለሁ፤ ከዛ ደግሞ አነባለሁ፡፡
ከፒያኖው ኋላ የተወሸቀችውን ሳጥን አውጥቼ በውስጡ ያሉትን ፅሁፎች ማገላበጥ ጀመርኩ፡፡ ሳገላብጥ ከሰር ካቦት ሎጅ የተፃፈለትን ባለ ሁለት ገፅ ደብዳቤ ተመለከትኩ፡፡ አባቴ ለጻፈው  የምርጫ ዘመቻ ሃሳብ

የተላከለት የምስጋና ደብዳቤ ነበር፡፡ እስካሁን ስለዚህች ሳጥን ምስጢር  ለማንም ሰው አውርቼ አላውቅም፡፡ ምስጢሩ የእኔና የአባቴ ነው፡፡
(በኢየብ ካሣ “Chicken Soup For The Soul” መፅሐፍ ላይ የተተረጎመ)

Read 633 times