Sunday, 28 April 2024 21:11

የእንቁላል ማምረቻ (እንቁልጢ) ካንሰር

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

  “የእንቁላል ማምረቻ (እንቅልጢ) ካንሰር ከዚህ ቀደም ዝምተኛ ገዳይ ተብሎ ይጠራ ነበር”
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመራቢያ አካላት ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መሰረት ኦላና
***
ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር፤ ከሁካታ እስከ ሹክሹክታ፤ ከፌሽታ እስከ የፀብ እሩምታ፤ ከረሀብ እስከ ጥጋብ፤ ከሀሳብ ውጥን እስከ ታላላቅ ክንውን በመንደሩ የግል አይደለም። የፀጉር ዘለላ የመቁጠር ያህል አንዱ ስለአንዱ ጥቃቅን ነገር ያውቃል። እንደ ገደል ማሚቶ ከአንዱ ጫፍ የተነገረ እና የተደረገ ሁሉ ወደ ሌላኛው ጥግ ያስተጋባል። መልካምም ይሁን እኩይ ተግባር በደቦ ይከወናል። ታዲያ ከዚህ መንደር በማንኛውም ሁኔታ ተለይታ የምትኖር ሉሊት የተባለች ሴት ትገኛለች። ውሎ እና አዳሯን ባደረገችበት አከባቢ ውስጥ ዐይኖቿ አይተው እንዳላዩ፤ ጆሮዎቿ ሰምተው እንዳልሰሙ፤ እግሮቿም ከእራሷ ቤት ውጪ ወደ ሌላ አቅጣጫ መራመድ እንዳይችሉ ከተደረጉ ዓመታት ተቆጥረዋል። ለነገሩ ሉሊት ብቻ ሳትሆን የመንደሩ ሰውም የሉሊት ቤት ቢቃጠል ወይም በጠና ብትታመም እንኳን ወደ እሷ አቅጣጫ የሚመለከት አይኖርም።
ሉሊት በብቸኝነት ከመንደሩ ተገልላ ከሱሶቿ ጋር መኖር ከጀመረች 20 ዓመታት ተቆጥሯል። እድሜዋም ወደ ጉልምስና እየተጠጋ ነው። ሉሊት የእድሜዋን መግፋት ያስተዋለችው ግን የመንደሩ ሰው ብቻ ሳይሆን ሰውነቷም እየከዳት መሆኑን ስታስተውል ነው። ምግብ የመብላት ፍላጎቷ ከጠፋ ሰንበትበት ብሏል። ሆዷ አከባቢ ህመም ይሰማታል። የበላችው ምግብም አይስማማትም። እናም ክብደቷ ቀንሷል። ለወራት ይህ ምልክት አብሯት ቢቆይም ወደ ሆስፒታል ለመሄድ አይደለም ከቤት ለመውጣት ብራታቱን አጣች። የመንደሩ ሰው ሲሳለቅባት ታያት። ግን ደግሞ በቤት ውስጥ ተደብቆ መሞት ይበልጥ ሽንፈት መሆኑን ስታስብ ፀሐይ ሳትወጣ በሌሊት ወደ ህክምና ተቋም ለመሄድ አሰበች። ከእራሷ ጋር ቀጠሮ ይዛ አልጋው ላይ ጋደም እንዳለች የጩኋት ድምፅ ተሰማ። ከጉዳይም ሳትቆጥረው ከእንቅልፏ ጋር ግብግብ ጀመረች። ግን እየተደጋገመ የሚሰማው ጩኋት፣ እልልታ እና የተደበላለቀ ድምፅ ይሁን ወይም የሚሰማት የህመም ስሜት እንቅልፍ በዐይኗ ሳይዞር ነጋ።
ከህመሟ ጋር እየታገለች በቡሩ አጮልቃ ሰው አለመኖሩን ከተመለከተች በኋላ ከቤቷ ወጣች። የመንደሩ ሰው የተለያየ ቁሳቁስ ይዞ መተረማመስ ጀመረ። ሌሊት የነበረው ጩኋት እና እልልታ ለምን እንደሆነ ተገለፀላት። ከመንደሩ አንዲት ሴት ወልዳለች ማለት ነው። ይህን ደስታ አብሮ ለመቋደስ ደግሞ የመንደሩ ሰው ወፎች እስኪንጫጩ እንኳን አይጠብቅም። ሉሊት እንደተለመደው የሰውን እንቅስቃሴ እንዳላየ ሆና ለማለፍ ስትሞክር አንድ ህፃን ልጅ “ሉሊት አንቺም ሆድ ውስጥ ሚጣ አለች እንዴ” በማለት ተናገረ። አላስተዋለችውም እንጂ ሰውነቷ ገርጥቶ ሆዷ ብቻ ተወጥሯል። ይህ ሁኔታ ለእሷ ብቻ ሳይሆን ለመንደሩ ሰው ትልቅ ዜና ነው። መንገዱ ላይ ያለው ሰው በሙሉ ትኩረቱን ወደ እሷ አደረገ። ፊትለፊታቸው መቆሟን ዘንግተው መንሾካሾክ፣ ማሽሟጠጥ እና መሳለቅ ጀመሩ። ይህ ትዕይንት ለሉሊት አዲስ ነገር አይደለም። የሚሰማት የህመም ስሜት ግን በህይወቷ ተሰምቷት አያውቅም። ትንሽ ለመራመድ ስትሞክር አቅም ስላነሳት ተደናቅፋ ወደቀች። የመንደሩ ሰው ዙሪያዋን ከቦ መመልከት ጀመረ።
ሉሊት ለመንደሩ አዲስ (እንግዳ) ሰው አይደለችም። ቅድመ አያቶቿ ከመንደሩ መስራቾች ውስጥ ናቸው። እሷም ተወልዳ ያደገችው በዛው መንደር ነው። እንደ ማንኛውም የአከባቢው ሰው ቤተሰቦቿ ሀዘን እና ደስታ ከመንደሩ ሰው ጋር ተጋርተዋል። በቤተሰቦቿ እግር ሉሊት ከተተካች በኋላ ግን ነገሮች ተለዋወጡ። ከመንደሩ ሰው ጋር ከምትመሳሰልበት ይልቅ ምትለይበት ነገሮች በዙ። ትዳር አለመመስረቷ እና ልጅ አለመውለዷ ከእኮዮቿ ጋር በሚኖር መሰባሰብ ውስጥ እንዳትመሳሰል አደረጋት።  ከአከባቢው ያፈነገጠችው ዘሯን ባለማስቀጠሏ ብቻ ግን አይደለም። የእራሷ የሆነ የህይወት ዘይቤ አላት።  ይህ ገለልተኝነት ልክ ባልሆነ መንገድ በሰው ህይወት ጣልቃ ላለመግባት ብቻ ሳይሆን እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ጭምር ሆነ። እያደገም በተለያየ ሱሶች ውስጥ እንድትደበቅ አደረጋት። እናም እንደተወገዘ ሰው ከመንደሩ ተገለለች።
አሁን ግን ሉሊት ያጋጠማት በሽታ የመንደር ሰው እጅ ላይ ጣላት። የአከባቢውም ሰው በሽታ እጁን እንዲዘረጋ አደረገው። ሉሊት ለዓመታት ሱስ ውስጥ መቆየቷ፣ ልጅ አለመውለዷ እና እድሜዋ እየገፋ መምጣቱ ለእንቁላል ማምረቻ ካንሰር አጋለጣት። እናም እራሷን ስታ በወደቀችበት እለት ልጅ ያገኙት ጥንዶች ወደ ህክምና ተቋም ይዘዋት በመሄድ ህክምና እንድታገኝ አደረጉ። ጥንዶቹ ወደ ዓለም እና ወደ መንደሩ ያቀላቀሉት ልጃቸውን ብቻ ሳይሆን የሉሊትንም ህይወት ጭምር ሆነ።
መረጃዎች እንዳስቀመጡት በዓለም አቀፍ ደረጃ የእንቁላል ማምረቻ ካንሰር (ovarian cancer) ሴቶችን ከሚያጠቁ የካንሰር አይነቶች ውስጥ በ8ኛ ደረጃ ተቀምጧል። ከ3 መቶ 13ሺ በላይ ሴቶች በካንሰሩ ተጠቅተዋል። የማህፀን አካል የሆነው የእንቁላል ማምረቻ(ovary) እንቁላል ለማምረት፣ በእርግዝና ወቅት ሆርሞን ለማመንጨት እና ለውበት ይጠቅማል። በዚህ የሰውነት ክፍል ላይ የሚከሰት ካንሰር የእንቁላል ማምረቻ (እንቁልጢ) ካንሰር ይባላል። የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመራቢያ አካላት ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መሰረት ኦላና እንደተናገሩት ከ1 መቶ ሴቶች መካከል 2 ሴቶች በእንቁላል ማምረቻ ካንሰር(ovarian cancer) ይጠቃሉ። እንዲሁም በቤተሰብ ውስጥ በዚህ ካንሰር የተጠቃ ሰው ካላቸው 10 ሴቶች ውስጥ 5 ሴቶች በካንሰሩ የመያዝ እድል አላቸው።
ለእንቁላል ማምረቻ (እንቅልጢ) ካንሰር አጋላጭ ሁኔታዎች
በቤተሰብ ውስጥ የእንቁላል ማምረቻ (ovarian) ወይም የጡት ካንሰር ተጠቂ መኖር
እድሜ መግፋት
ልጅ አለመውለድ
ትንባሆ ማጭስ[ሱሶች]
እንደ ዶ/ር መሰረት ኦላና ንግግር የእንቁላል ማምረቻ ካንሰር ከዚህ ቀደም ዝምተኛ ገዳይ ተብሎ ይጠራ ነበር። ብዙ እናቶች ምልክቱን ሳይረዱ ቆይተው ደረጃው ከፍ ካለ በኃላ ነው ወደ ሆስፒታል የሚሄዱት። የህክምና ባለሙያው ለዚህ ችግር እንደ ምክንያት ያስቀመጡት የበሽታው ምልክቶች ከሌሎች የተለመዱ ተለያዩ ስሜቶች ጋር መመሳሰላቸውን ነው።
የእንቁላል ማምረቻ (እንቅልጢ) ካንሰር ምልክቶች
የሆድ እብጠት
የምግብ ፍላጎት መቀነስ
ክብደት መቀነስ
ምግብ ቶሎ አለመፈጨት
ታችኛው የሆድ ክፍል ላይ ምቾት ማጣት(ህመም)
በወርአበባ ወቅት ከሚኖር ስሜት ጋር የሚመሳሰሉ ስሜቶች
ከዚህ በተጨማሪ ደረጃው ከፍ እያለ (እየተሰራጨ) ሲሄድ ሌሎች ምልክቶች ይኖራሉ። የተሰራጨው ወደ ሳንባ ከሆነ ሳል፣ ወደ ጉበት ከሄደ ዐይን ቢጫ መሆን፣ ወደሽንት ቱቦ ከተሰራጨ ሽንት እና ሰገራ ላይ ደም ማየት ይኖራል። የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት እነዚህ ምልክቶች ከተደጋገሙ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ አስፈላጊ ነው።  “ሌላ ቦታ ክብደታቸው እየቀነሰ ግን ሆዳቸው አካባቢ ሲያድግ ብዙ ጊዜ ሴቶች እንደ ቦርጭ ይቆጥሩታል። ነገር ግን ወደ ሀኪም ቤት ሄዶ መታየት ይጠቅማል” ብለዋል ዶ/ር መሰረት ኦላና።
ለእንቁላል ማምረቻ ካንሰር የሚሰጠው ህክምና ቀዶ ጥገና እና የካንሰር መድሃኒት (ኬሞቴራፒ) ነው። እንዲሁም መውለድ የምትችል (የምትፈልግ) ሴት ከሆነች በቀዶ ጥገና ሙሉበሙሉ የእንቁላል ማምረቻውን እንዲወጣ ከማድረግ ይልቅ ሌሎች ህክምናዎች እንድታገኝ ሊደረግ ይችላል። በተጨማሪም ካንሰሩ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ከተሰራጨ የተጎዳው ክፍል በቀዶ ጥገና እንዲወጣ ይደረጋል። የሚሰጠው የህክምና አይነት እንደ ካንሰሩ ደረጃ ይለያያል።  ዶ/ር መሰረት ኦላና እንደተናገሩት 75 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የበሽታው (ካንሰር) ደረጃ ከፍ ካለ በኋላ ነው ወደ ህክምና ተቋም የሚሄዱት። ከፍ ያለ ደረጃ የሚባለው ደረጃ 3 እና 4 ነው። ደረጃ ሲጨምር የሚሰጠው ህክምና ውጤታማነት ይቀንሳል።
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመራቢያ አካላት ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መሰረት ኦላና እንደተናገሩት ልጅ መውለድ እና የሚዋጥ(እንክብል) የወሊድ መቆጣጠሪያ መውሰድ በካንሰሩ የመያዝ እድልን ይቀንሳል። የእንቁላል ማምረቻ ካንሰርን አስቀድሞ ለመከላከል በቤተሰብ ውስጥ በካንሰሩ የተጠቃ ሰው ካለ ወይም ምልክቶች ሲኖሩ የህክምና ባለሙያ ማማከር አስፈላጊ ነው።Read 571 times