Saturday, 04 May 2024 11:02

ለራሱ ያልዳነ ለአማቱ መድኃኒት ይቆርጣል

Written by 
Rate this item
(7 votes)

በአንድ በረሀ ውስጥ ሁለት ሰዎች በፈረስ ሆነው ሜዳውን አቋርጠው በመሄድ ላይ ሳሉ ይገናኛሉ። ከሁለቱ የአንደኛው ፈረስ አንካሳ ነው። ባለ አንካሳው ፈረስ በረሀውን አቋርጦ አለሙ አገር ለመድረስ ፈረሱ አላስተማመነውም። ስለዚህም እንደምንም ብሎ ደህነኛውን ፈረስ ከሌላው ሰውዬ ለመውሰድ መላ ይፈልግ ጀመር።
በመጨረሻም እንዲህ አለው፡-
“ወዳጄ ሆይ፤ ፈረሶቻችን ከእኛው ጋር ለብዙ ጊዜ የኖሩ በመሆናቸው ጨክነን በአለንጋ አንገርፋቸውምና ፈጥነው ለመሄድ ዳተኝነት ይሰማቸዋል። ስለዚህ እንቀያየርና እንደልብ እየገረፍናቸው በረሀውን ፈጥነን እናቋርጥ።”
ባለ ደህነኛው ፈረስም ይህን አግባብ ያልሆነ የብልጠት ጥያቄ በብልሃት ሲመልስ፤
“ጥያቄህ መልካም ነበር። ነገር ግን የእኔ ፈረስ እንዳንተ ፈረስ ዳተኝነት የለበትምና ማንም እንዲገርፈው አልፈቅድም። የአቅሙን ያህል፣ ባለው ፍጥነት በረሀውን እያቋረጠ በመሄዱ ፈረሴ አንዳችም አለንጋ ሊያርፍበት አይገባም፤ የጭካኔ ተግባርም ሊፈፀምበት ተገቢ አይደለም” አለው።
ባለ አንካሳው ፈረስ ዘዴው ባለመሥራቱ ተናዶ ጠብ ለመጫር ፈለገ። ስለዚህም፣
“እኔ ነኝ ጨካኝ? ለሁለታችንም ጥቅም ባሰብኩ ጨካኝ ትለኛለህ? በጭራሽ ጭንቅላት የሌለህ ደደብ ሰው ነህ!” ሲል ነገር ጀመረው።
አንድ ሁለት ሲሉ ወደ ድብድብ ተሸጋገሩ። ባለ አንካሳው ፈረስ ጡንቻው ፍርጥም ያለ ነበርና ባለ ደህነኛውን ፈረስ በትግል ጥሎ፣ ፈረሱን ነጥቆት፣ የሱን አንካሳ ፈረስ ጥሎለት እየጋለበ ሄደ።
በትግል የተሸነፈው ሰው ግን ተስፋ ሳይቆርጥ ከወደቀበት ተነስቶ አንካሳው ፈረስ ላይ ወጥቶ መንገድ እያቆራረጠ ከሚቀጥለው መንደር ቀድሞ ገብቶ ለዳኛ ከሰሰው። የሰው ፈረስ የወሰደው ሰው ከዚያ መንደር ሲደርስ በዳኛ ተያዘና ተጠየቀ።
“ፈረሱ የገዛ ራሴ ፈረስ ነው። ያሳደግሁት፣ አብሮኝ የኖረ ፈረሴ ነው። ይሄንንም ሰው እንኳን ፈረስ ልወስድበት ዓይኑንም አይቼው አላውቅ!” ሲል ፍርጥም ብሎ መለሰ።
ዳኛው ሽማግሌና አስተዋይ ሰው ናቸው። ነገሩ የጉልበት ስራ እንዳለበት ገብቷቸዋል። ሆኖም ለተሰራው ተንኮል ምንም ማስረጃ አልነበራቸውምና ብዙ ካሰቡ በኋላ አንድ ዘዴ ታያቸው።
“በሉ ሁለታችሁም ፊታችሁን ዞራችሁ ቁሙ”
ሰዎቹ እንደተባሉት አደረጉ።
ዳኛው በርኖሳቸውን አውልቀው የደህነኛውን ፈረስ ፊት ሸፈኑት። ከዚያም ሰዎቹ እንዲዞሩ አዘዙና ያንን የሰው ፈረስ የነጠቀ ጉልበተኛ ፊቱ ወደተሸፈነው ፈረስ እያሳዩ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፡-
“ለመሆኑ ይሄ ፈረስ የግራው ነው የቀኝ ዐይኑ የታወረው?”
 ያም ጉልበተኛ ሰው ድንገተኛ ጥያቄ ስለሆነበትና ካልመለሰም እንደሚጋለጥ በማሰብ፤ በአቦ-ሰጡኝ
“የቀኝ ዐይኑ ነው!” ሲል መለሰ።
ዳኛውም በርኖሱን ከፈረሱ ፊት ገልጠው፤
“ይገርማል! ፈረሱ ዕውር ይሁን አይሁን እንኳ ሳታውቅ ነው፣ የእኔ ፈረስ ነው የምትለው። ፈረሱ ሁለቱም ዐይኑ ደህና ነው። ካንተ ጋር የኖረ ፈረስ ቢሆን ኖሮ ጥያቄውን በተገቢ መልኩ በመለስህ ነበር። ሆኖም የሰው ገንዘብ ነውና ልታውቀው አልቻልክም”
በማለት ፈረሱ ለባለቤቱ እንዲመለስለት አደረጉ።

***
“መውደዱ ጠንቶ አድልዎ ዕውር እንዳያደርገን፣
ጥላቻው ከሮ ህሊና እንዳያሳጣን እንጠንቀቅ” ብሏል አንድ ያልታወቀ ደራሲ። በየትም ቦታ፣ በማናቸውም ጉዳይ ላይ ብልሃትና እውቀት ከሌለ ዳኝነት መስጠት ከባድ ኃላፊነት፣ ከባድ ሥራ ነው። የተጣሉ ልጆች የተጣሉ ባልና ሚስት ከማስታረቅ ጀምሮ ተፎካካሪ ባለሙያዎችን አወዳድሮ ፍርድ እስከመስጠት ድረስ ርቱዕ ዳኝነት የሚሻ ጉዳይ ነው።
ትክክለኛ ዳኝነት በግፍ የሰው ንብረት እንዳይጠፋ፣ እንዳይወሰድ፣ አይጥ በበላ ዳዋ እንዳይመታ፤ ጉልበተኛ ደካማውን እንዳያጠቃ፣ መብት እንዲከበር፣ መልካም የሰራ እንዲመሰገን እንዲነሳሳ፣ ክፉ የሰራ እንዲወቀስ አለመሥራቱን እንዲያውቅ ያደርጋል። ለዚህ ደግሞ ተገቢውን ዳኝነት ለመስጠት የሚችሉ አስተዋይ ብልህ ዳኞች ያስፈልጋሉ። በተለይ ሽልማት የሚሰጥበት ዳኝነት ሲሆን ደግሞ፣ ከማቴሪያል እሴቱም ይልቅ ስም (ስምም ቢሉ ሙያዊ ስም) አለበትና የሽማግሌ እርጋታና ስክነት ያላቸው መክረው ዘክረው፣ አውጥተው አውርደው፣ ግራ ቀኙን አይተው፣ ያለ አድልኦ፣ ያለ ወገናዊነት ፍርድ የሚሰጡ ሰዎች ያስፈልጉታል። ይህን ሳያሟሉ አንድም ያለዕውቀት አንድም በድፍረት አሊያም በንዝህላልነትና ያለብስለት ተነስተው የተጣላ እናስታርቅ የሚፎካከርን እንዳኝ፣ ብርቱና ሰነፉን እንለይ ቢሉ፣ “ለራሱ ያልተገረዘ የሰው ዐይን ይይዛል” የተባለው ዓይነት ይሆናል።
መልካም ዳኛ ተገኝቶ፣ ሚዛናዊ ዳኝነት እንዲኖር የማስፈለጉን ያህል ደግ ያደረገን የሚያበረታታ ማሕበረሰብ መኖሩ ዋና ነገር ነው። ከአያሌ አሉታዊ ነገሮች መካከል ጥቂት አዎንታዊ ፋይዳዎችን አንጥሮ አውጥቶ እነሱን ለማጉላት የሚሞክር ህብረተሰብ፣ ለነገ የወደፊት ገንቢ ጥርጊያ መንገድ እንዲኖር ከወዲሁ ተመክሮውን ያነቃል። ጨለማ ከከበባት ህይወት መካከል ጥቂት የብርሃን ፍንጣቂ ሲያገኝ፣ ለዚያች ሰፊ ቀዳዳ የሚያበጅ ህብረተሰብ፣ ራእዩ ግቡን እንዲመታ የተለያየ መንገድ ይከሰትለታል። የሀሳብ አማራጭ፣ የመኖር አማራጭ፣ የትግል አማራጭ ይኖረዋል። ስለ ዛሬ ጨለማ ሳይሆን ስለ ነገ ብሩህ ህይወት ለማለም የአእምሮ ጭጋግ አይጫነውም። “የሚገድል ጦር ተኝቶም ይወጋል” ይሏልና ከመሰረቱ ቀና የሆነ ዜጋ የሚበጀውን ከጧቱ ማየት የነገውን በልበ-ሙሉነት መቅረጽ ለሰው፣ በህይወቱ እያለ ዋጋውን መስጠት፣ ለመልካም ስራ ወቅታዊ ውዳሴን አለመንፈግ አሉታዊ ማህበረሰብ ከመሆን ያድነናል። በዚህ መንገድ ጀግና ይፈጠራል። ኮከብ ይበራል። ለሀገር ዐይን የሚሆኑ ሰዎች ይፈልቃሉ - ይበቅላሉ - ይፀድቃሉ።
ግልጽ፣ የተረጋጋና ዲሞክራሲያዊ ህብረተሰብ እንዲኖር ቀና ቀናውን እንጂ ክፉ ክፉውንና ጉድፍ ጉድፉን ብቻ የሚያይ መሪ፣ ድርጅት፣ ፓርቲ አይደለም እሚበጀው። ከትንሿም እንቅስቃሴ ውስጥ ቢሆን ደግ ደጓን የሚያይ እንጂ መጥፎ መጥፎውን እሚያይ፣ ክፉ ክፉውን እሚያወራ ሰው ወንዝ አያሻግርም። አገር አያለማም። ህዝብ አያሳድግም። በመርፌም የሚለቀም ቢሆን ከእኛ ውጪ ባለው ሰው ወይም ቡድን ላይ ደህና ደህናውን ነገር መርጦ ማየት ከብዙ ደባ፣ ከብዙ መጠላለፍ፣ ከብዙ መጠፋፋት፣ ከብዙ ውድቀት ያድናል። የልብ አንካሳ እመንገድ ሲያድር፣ የእግር አንካሳ እቤቱ ደርሶ ያድራል እንደሚባለው መሆኑ ነው። ምን ነግሬ ላሳስቀው ከማለት ምን አድርጌ ላስለቅሰው የሚል ሲበዛ አሉታዊነት (Negativism) ይንሰራፋል። የሚሾም የሚሸለም ከማየት፣ የሚዋረድ የሚነጠቅ ማየት ያረካል። አሉታዊነት ሲከፋ አብሮ ማደግ ቀርቶ አብሮ መኖር የማያስችል አለመተማመንን ይፈጥራል። መግባባትን ያጨልማል። መቻቻልን ያዳፍናል። ፖሊሲ መቅረጽ፣ የአፈፃፀም አቅም መገንባት፣ ሙስና ማጥፋት፣ ድህነት ቅነሳ ሁሉም ያለ አዎንታዊ ፍቃደ-ልቡና፣ ያአመስጋኝና ወሮታ-ከፋይ ህብረተሰብ (Merit-Giving Society) አንድ ጋት አይራመድም።
ክፉ ክፉውን የሚያይ ሹም፣ ጉድፍ ጉድፉን የሚለቅም ባለስልጣን ለራሱ ብዙ ነጥብ ይሰጣልና ውሎ አድሮ ሌላውን ሁሉ አኮስሶ እያየ፣ ካለ እኔ ማን አለ ማለቱ አይቀርም። ህብረተሰቡም የእሱን ክፉ ስለሚመኝና የእሱን ጎዶሎ ስለሚፈልግ እንቅፋት ሲደረድርለት፣ መቃብር ሲምስለት፣ ቀን ሲጠብቅለት ነው የሚኖረው። በአሉታዊ ህብረተሰብ ውስጥ ሹሙ ከዜጋው፣ ደንጊያው ከቅሉ እንደተጋጨ እንደተላተመ ነው የሚከርመው። በእንዲህ ያለው ጊዜ ሰላም ይጠፋል። ሠርቶ ማደር ያቅታል። “ማክቤዝ እንቅልፍን ገደላት” እንዲል ሼክስፒር፣ ሹሙ ሁሉ በግፉ፣ በሙስናው፣ በአድሎአዊነቱ፣ በማን-አለብኝነቱ… ምክንያት እንቅልፉን ያጣል። ውሎ አድሮም ከዚህ ቀደም እንደታዩት ሹማምንት እዚያው የውድቀት ጉድጓድ ውስጥ ይገባል። ማህበረሰቡም የእጁን አገኘ ይለዋል። ከወደቀውም ሆነ ከራሱ ለነገዬ ብሎ የሚያኖረውም የእርምት ስንቅ የለም። ለአዲስ ሹም አጨብጭቦ፣ ደሞ ነገ ጥምብ- እርኩሱን አውጥቶ አንቅሮ ይተፋዋል። “ዛሬ ፈጥሮ ነገ ቀብሮ” እንዳለው ነው ደራሲው።
ህብረተሰብ ለእድገት እንዲሰለፍ አሉታዊ ባህሪን ማስወገድ አለበት። አዎንታዊ አስተሳሰብን (Positivism) ማዳበር አለበት። መልካም የሰራን ለማበረታታት፣ ለላቀ ለመሸለም፣ ያለ አድልዎ ለመፍረድ፣ ከልብ ለመደገፍ፣ ከልብ ለመንቀፍ፣ ግልጽ ለመሆን ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው። ከጽንፍ ወደ ጽንፍ ከመሄድ ይልቅ ሌላ አማካይና አማራጭ መንገድ ማየት ይገባል። ያለ ብሔረሰባዊ መንገድ የትም አልሄድም ብሎ ተከርሞ ድንገት የባነኑ እለት ብሔረሰብ ይውደም ወደማለት ከተሄደ አደገኛ ጽንፈኝነት ይሆናል።
ማንም ይሁን ማን ለረዥም መንገድ ከተነሳ ሆደ-ሰፊ መሆን አለበት። ለዚህም የተቻለው ጥረት ሁሉ ሊደረግ ይገባል። በተለይ ኃላፊዎች፣ ሹሞች፣ ባለአደራዎች፣ መሪዎች ጥብቅ አደራ የሚጣልባቸው ናቸው። አለበለዚያ ይህ ሳይኖራቸው በስሜታዊነትና በማን-አለብኝ ከተዋጡ፣ ለራሱ ያልዳነ ለአማቱ መድኃኒት ይቆርጣል እንደተባለው ይሆናልና ከወዲሁ እናስብበት።
ፋሲካውን በአዳዲስ ሃሳብ እንፈስክ!!
መልካም የትንሳኤ በዓል!!

Read 1198 times