Saturday, 11 May 2024 00:00

“ከነገር ሁሉ ምን ትጠላለህ?” ቢለው፤ “ወደ ትላንትና መመለስ” አለ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ፕሉታርክ እንደጻፈው የሚከተለው አፈ-ታሪክ አለ።
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ454 ዓመት፣ ኮሪዮሳኑስ የሚባል የሮማ ወታደራዊ መሪ ነበር። በጥንታዊ ሮም ታላቅ ወታደራዊ ጀግና ነው የተባለ ነበር። በርካታ ጦርነቶችን አሸንፏል። በዚህም አገሪቱን ከብዙ ጥፋት አድኗታል ተብሎለታል። ብዙውን ህይወቱን በጦር ሜዳ ስላሳለፈ በአካል የሚያውቁት ጥቂት ሮማውያን ብቻ ናቸው። በዚህ ምክንያት ከሞላ ጎደል ወደ አፈ-ታሪክነት ተለውጧል። አፈ-ታሪክ ታሪኩ እነሆ።


በ454 (ከክ.ል.በፊት) ወታደራዊ መሪ ኮሪዩሳኑስ የጦር ሜዳ ዝናዬንና ስሜን ተጠቅሜ ፖለቲካው ውስጥ ልግባ ሲል አሰበ። ከፍተኛ የምክር ቤት እንደራሴ ለመሆን ለሚያበቃው ቦታም የምርጫ ተወዳዳሪ ሆኖ ቀረበ። የምርጫ ተወዳዳሪዎች ወደተወለዱበት ቦታ ሄደው፣ ለጎሳቸው ሰው ንግግር ማድረጋቸው የዚያን ጊዜ ባህላዊ ህግ ነበርና፤ ኮሪዮላኑስም ወደ ህዝቡ ቀርቦ 17 ዓመት ሙሉ ለሮም ሲታገል በጦር ሜዳ በጥይት የተመታባቸውን ከደርዘን በላይ የሆኑትን የሰውነቱን ጠባሳዎች እየገለጠ አሳየ። ከዲስኩሩ ይልቅ ህዝቡን እንባ በእንባ ያደረገው የሰውነቱን ጠባሳዎች ማየት ነበር። ኮሪዮላኑስ በምርጫው እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ መሰለ።
የምርጫው ቀን ሲደርስ ኮሪዮላኑስ በድፍን የምክር ቤት አባላትና በከተማው መኳንንት ታጅቦ ወደ ምርጫው ጣቢያ ገባ። ተራው ህዝብ ይሄ ሁሉ ጉራና እመረጣለሁ የሚል ልበ-ሙሉነት ከየት መጣ አለ በሆዱ።


ኮሪዮላኑስ አብረውት የሄዱትን አብዛኛዎቹን ወገኖቹን የሚጥም ንግግር አደረገ። ሆኖም፤ ዲስኩሩ ዕብሪትና ድፍረት የተሞላበት ከመሆኑም በላይ፤ በምርጫው ያለጥርጥር እንደሚያሸንፍ፣ የጦር ሜዳ ድሎቹን እንደሚኮራባቸው የሚያሳይ ሲሆን፤ ለሱ የገዢ መደብ ወገኖች ብቻ የሚገቡ ቀልዶችን በመጨመር እየፎከረ፤ ተቃዋሚዎቹንም በንቀት በማንገዋጠጥና በቁጣ  እየወነጀለ፤ ቢመረጥ ለሮም የበለጠ ሀብት እንደሚያስገኝ ደሰኮረ። በዚህ ንግግሩ ህዝቡ የአፈ-ታሪክ ጀግናችን ይለው የነበረው ታላቁ መሪ ተራ ጉረኛ መሆኑን ታዘበ። የሁለተኛው የጉራ ንግግሩ ይዘት በአገሩ ናኘና ህዝቡ ይሄንንማ አለመምረጥ ነው ተባባለ። እንዳለውም ህዝቡ ኮሪዮላኑስን ሳይመርጠው ቀረ።
ኮሪዮላኑስ በመሸነፉ ተናዶ ወደ ጦር ሜዳው ተመለሰ። ይሁን እንጂ ያልመረጠውን ህዝብ እንደሚበቀለውና ልክ- እንደሚያገባው በምሬት ዛተ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በትልቅ መርከብ ወደ ሮም የሚገባውን እህል ለተራበው ህዝብ በነፃ ለማደል የምክር ቤቱ አባላት አስበው በጉዳዩ ለመምከር ተሰባሰቡ። በመካከል ግን ድንገት ኮሪዮላኑስ ብቅ አለና መድረኩን ቀማቸው። ይህን እህል ማከፋፈል በአጠቃላይ ለከተማይቱ ጎጂ ነው ሲል ተከራከረ። ጥቂቶቹን አሳመነ። በዚያም አላበቃ። የዲሞክራሲን ፅንሰ-ሀሳብ ጭምር ኮነነው። የህዝብ ተወካዮቹንና አዲሶቹን ተመራጮች በማስወገድ የከተማዋን አገዛዝ ለቀድሞዎቹ ገዢዎች (ስፓትራሺያን) መስጠት ይኖርብናል ሲል ክፉኛ ተሟገተ።


የኮሪዮላኑስን የመጨረሻውን ንግግር ህዝቡ ሲሰማ ቁጣው ወሰኑን ጣሰ። የህዝቡ ተወካዮች ደግሞ ኮሪዮላኑስ ህዝቡ ፊት ይቅረብ አሉ። ኮሪዮላኑስ ግን አሻፈረኝ፣ ህዝብ ፊት አልወጣም አለ። ከተማይቱ በሁሉም አቅጣጫ በህዝብ አመጽ ተቀጣጠለ። ይሄኔ ምክር ቤቱ የህዝቡን እንቅስቃሴ በመፍራት እህሉ ይከፋፈላል በሚለው ላይ ወሰነ። ሸንጎው በዚህ ህዝቡን ያረጋጋና እፎይ ያለ መሰለው። ህዝቡ ግን ኮሪዮላኑስ ያነጋግረን! ይቅርታ ይጠይቀን! ማለቱን ቀጠለ። ከፀፀተውና ጠባዩን አሳምሮ ሀሳቡን የሚያነሳ ከሆነም ወደ ጦር ሜዳ እንዲሄድ እንደሚፈቅዱለት ተናገሩ።
በመጨረሻ ኮሪዮላኑስ ህዝቡ ፊት ቀረበና ንግግር አደረገ። በዝግታና ለስለስ ባለ ቃና ጀመረና ቀስ እያለ ወደ ይፋ ዘለፋ ተሸጋገረ። ቃናው ሁሉ የዕቡይ ሆነ። የህዝብን ክብር የናቀ ዲስኩር ሆነ። ሰውን ማዋረድ ጀመረ። እሱ የበለጠ በተሳደበ ቁጥር ደግሞ የህዝቡ ቁጣ የበለጠ ገነፈለ። በመጨረሻ በጩኸት አፉን አዘጉት።
ሸንጎው ኮሪዮላኑስን በማውገዝ የሞት ፍርድ ፈረደበት። ዳኞቹንም እንደተለመደው ከታሪፒያ ቋጥኝ ቁልቁል እንዲወረውርና የሞት ቅጣት እንዲፈፀምበት አዘዛቸው። ህዝቡንም ውሳኔውን ደገፈ። ሆኖም ፓትሪሺያንኖቹ ጣልቃ ገብተው በመደራደር የሞት ቅጣቱ ወደ “ዕድሜ ልክ ከሥራ መገለል” እንዲሻሻል ተደረገ። የሮማ ታላቅ የጦር መሪ፤ ሁለተኛ ሮማ ከተማ ድርሽ እንደማይል ተረዳው፣ ህዝብም መንገድ ላይ ወጥቶ በይፋ ጨፈረ። እንደዚህ ያለ ጭፈራና በዓል ከዚህ ቀደም በሮማ ታይቶ አይታወቅም። የሮማ ህዝቦች ወራሪ ጠላት ሲያሸንፉ እንኳን እንደዚህ ዓይነት ፌሽታ አድርገው አያውቁም።

***


ከ2000 ዓመታት በፊት የሆነን ነገር መለስ ብሎ ያስተዋለ አያሌ ትምህርት ያገኛል።
ስንቶቻችን ራሳችንን ደገምን? ስንቶቻችን ራሳችንን በአፈ-ታሪኩ ውስጥ እናያለን? ሁኔታዎችን ስናጤን ታሪክ ብቻ ሳይሆን አፈ-ታሪክም ራሱን ይደግማል ያሰኘናል። ራስንም ወደፊት ነው እየሄድኩ ያለሁት ወደኋላ? ብሎ መጠየቁ አይቀርም። ከትላንት እስከዛሬ ተጠይቀው በግማሽ-ጎፈሬ ግማሽ-ልጩ መልክ ተመልሰው ወይም ከናካቴው ሳይመለሱ ቀርተው፣ እስከዛሬ የሚያጨቃጭቁን አያሌ ጥያቄዎች ነፍስ-እየዘሩ፣ በአካል እየተፋጠጡን (“ዴጃ ቩ” (deja vu) እንደሚባለው) “የት ነበር ያየናቸው?” የሚያሰኝ ድግግም ስዕሎች ነበሩ ዛሬም አሉ። የድንበር ጥያቄ ትላንት ነበረ ዛሬም አለ። ሀሳብ የመግለፅ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ጥያቄ… ትላንት ነበረ ዛሬም አለ። የሰብአዊ መብት ጥያቄ ትላንት ነበረ ዛሬም አለ። የብሔር ብሔረሰብ ጥያቄ ትላንት ነበረ ዛሬም አለ፤ ወዘተ የሚገርመው ግን ታሪክ-ሰሪዎቹና የፖለቲካ መሪ ተናዋዮቹም ችግር ከሞላ ጎደል መደገማቸው ነው። መፈክሮችና መዝሙሮች ሳይቀሩ ሲደገሙ ማየት አስገራሚ ነው።
ለጉድ የጎለተው ሁሉንም ይታዘባል።
ገጣሚው እንዳለው፤
“ሲጨልም ስንነቃ፣ ሲነጋ ስንተኛ
እንቅልፍ እንኳ ካቅሙ መች ሞላልን ለእኛ።
ዘመን ተዘባርቆ ዓመት ተዟዟረ
ህልምም ወደ ኋላ፣ ማየት ተጀመረ”
ገዢው ፓርቲ በሙሉ አቅም የሚመራበት ሁኔታ ሲጠፋና፤ አዳዲሶች ፓርቲዎች በተደራጀ ሁኔታ የመምራት ሁኔታ ላይ ካልሆኑ፣ ሀገር ወደፊት መራመድ አቅቷት ወደኋላ እንዳትመለስ፣ ሀገር-ወዳዶች ሁሉ የሁኔታውን አሳሳቢነት መገንዘብ አለባቸው። ምን አይነት እገዛ ያስፈልጋል? ምን አይነት አቅም መፍጠር ይገባል? ብሎ ማሰብ ወሳኝነት ይኖረዋል። መድረክ ላይ ባሉ ፓርቲዎች ላይ አቃቂር ከመሰንዘር ባሻገር የእኛ አስተዋፅኦ ምን ይሁን ማለት ደግ ነው። የወቅቱ ጥሪ ይሄው ነው።
ሶስት ታዋቂ ሰዎች ስለታሪክ እንዲህ ይሉናል።
ታሪክ ራሱን ይደግማል። የታሪክ ጸሐፊ ግን አንዱን ይደግማል። (ፊሊፕ ጉዳላ- እንግሊዛዊ ፀሐፊ)
ታሪክ ራሱን አይደግምም። የታሪክ ጸሐፊ ግን አንዱን ይደግማል። (የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር)
ታሪክ ራሱን ይደግማል። ከታሪክ ስህተቶችም አንዱ ይሄ ነው (ክላርንስ ዳሮው የፈረንሳይ ጠበቃ)
ታሪክ መልኩን እየለዋወጠ ራሱን ይደግማል። በየጊዜው ግን የሚያስከፍለን ዋጋ እየጨመረ ነው የመጣው።
(ቶማስ ቤይሌ አሜሪካዊ የታሪክ ባለሙያ)
እንግዲህ የሚሰማንን መውሰድ የእኛ ፋንታ ነው።
በ1966 ዓ.ም የነበረውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ፣ በ1983 የነበረውን የሽግግር ሁኔታና ዛሬ በሪፎርም ማግስት ያለንበትን ወቅት በሚገባ ስናጤን፣ ወደኋላ እንድናይ የሚያመላክቱ የበዙ ሁኔታዎች ስዕል እናገኛለን። ይሄ ደግሞ አሳሳቢ ነው። “ከነገር ሁሉ ምን ትጠላለህ?” ቢለው “ወደ ትላንትና መመለስ” አለ፤ የሚባለው የዚሁ ማገናዘቢያ ነው።

Read 891 times