Saturday, 11 May 2024 00:00

በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

”ከ5 ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ 6መቶ ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትኖር አንዲት ሴት ለህክምና እኔ ጋር መጣች። አስፈላጊውን ህክምና ከሰጠኋት በኋላ ወደ ምትኖርበት አከባቢ ተመልሳ ሄደች። ከ3 ወይም ከ4 ወራት በኋላ እርግዝና ተፈጠረ። ፅንሱ ወደ 6 ወር አከባቢ ሲደርስ የደም ግፊት አጋጠማት። የትዳር አጋሯ የህክምና እውቀት ስላለው የደም ግፊት እንዳጋጠማት በመረዳት ህክምና እንድታገኝ አደረገ። ነገር ግን የበሽታው ደረጃ ከፍተኛ ነበር። የህክምና ባለሙያዎች ፅንሱ መቋረጥ እንዳለበት ተናገሩ። ጥንዶቹ ይህን ፅንስ ያገኙት ከ6 ዓመታት ሙከራ በኋላ ስለነበር እናት ፅንሱን ማቋረጥ አልፈለገችም። እናም ፅንሱ ቀጠለ። ለ1 ወር ያህል ህክምና ስትከታተል ቆየች። 7ኛ ወር ሲሆናት ጉበቷ ላይ የደም መፍሰስ አጋጠመ። በዚህ ሂደትም ህይወቷ አለፈ። ፅንሱንም ማትረፍ አልተቻለም”  
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስ እንዲሁም ማተርናል ፌታል ሜዲስን ስፔሻሊስት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ


ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮ ስናነሳ በቀዳሚነት ከሚነሱ ጉዳዮች ውስጥ የእናት እና ልጅ ግንኙነት ወይም እርግዝና (ፅንስ) አንዱ ነው። በእርግዝና ወቅት ከሚያጋጥሙ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ ከሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት ይጠቀሳል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ8 እስከ 16 በመቶ የሚሆኑ ነፍሰ ጡር እናቶች በእርግዝና ጊዜያቸው የደም ግፊት ያጋጥማቸዋል። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊትት እንዲሁም በማተርናል ፌታል ሜዲስን(በእናት እና ፅንስ ላይ የሚደረግ ከፍተኛ ህክምና) ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሰኢድ አራጌ “ቀን በቀን ከሚያጋጥሙን የበሽታ አይነቶች ውስጥ ዋናኛው በእርግዝና ወቅት የሚመጣ ደም ግፊት ነው” በማለት ስለ በሽታው አሳሳቢነት ተናግረዋል። እንደ ዶ/ር ሰኢድ አራጌ ንግግር አንዲት እናት የደም ግፊቷ ከ140 በ90 በላይ ሲሆን በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት በሽታ አጋጠማት ይባላል። ይህ የደም ግፊት መጨመር በየትኛውም የእርግዝና ወቅት (ከተፀነሰበት እስከ ወሊድ) ሊያጋጥም ይችላል።


በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት አይነቶች
በእርግዝና የመጀመሪያ ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት (Chronic hypertension); ከጨው አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚመጣ የደም ግፊት አይነት ሲሆን ግፊቱን ያስከተለው እርግዝና አይደለም። እርግዝና በሌለበት ወቅት ሊከሰት ይችላል። እድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ በሆኑ ነፍሰ ጡር ሴቶች ላይ በይበልጥ ይከሰታል። በተለይ የመጀመሪያ እርግዝና ሲሆን የመጋለጥ እድል ይጨምራል።
በእርግዝና ምክንያት የሚከሰት ደም ግፊት (Gestational hypertension); የሚፈጠረው በእርግዝና ምክንያት ሲሆን ምልክቱ የደም ግፊት መጨመር ብቻ ነው። ከከፍተኛ ደረጃ የደም ግፊት አይነቶች ጋር አሲነፃፀር ጉዳቱ አነስተኛ ነው።
ፕሪኢክላሲያ (Preeclampsia); ከእርግዝና 20ኛ ሳምንት በኋላ የሚከሰት የደም ግፊት አይነት ነው። በዚህ ወቅት ግፊቱ የእናት የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል።
ኢክላምሲያ [Eclampsi]; ይህ የደም ግፊት አይነት (ደረጃ) ውስብስብ ችግሮችን የያዘ እና በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነው።
እርግዝና ከመፈጠሩ በፊት የነበረ የደም ግፊት ላይ እርግዝና ከተፈጠረ በኋላ የሚኖር የደም ግፊት መጨመር[ድምር] (Superimposed preeclampsia); ከሌሎቹ አይነቶች በይበልጥ አደገኛ እና ጉዳት የሚያደርስ ነው።  
በእርግዝና ወቅት ከሚያጋጥም የደም ግፊት ውስጥ የሚመደበው ፕሪኢክላምሲያ እና ኢክላምሲያ [Pre-Eclampsia and Eclampsia] በሽታ ከ5 ወር በላይ በሆኑ ነፍሰጡሮች እንዱሁም አንዳንድ ጊዜ ልጅ ከተወለደ በኋላ በእናት ላይ ይከሰታል። በሽታው በዓለምአቀፍ ደረጃ ከ20 ሳምንት(5ወር) በላይ በሆኑ ነፍሰጡሮች ላይ ከ3 እስከ 7 በመቶ የሚያጋጥም ሲሆን 25በመቶ ደግሞ ልጅ ከተወለደ ከ4ቀን እስከ 6 ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ይከሰታል። ዶ/ር ሰኢድ አራጌ እንደተናገሩት የፕሪክላምሲያ እና ኢክላምሲያ በሽታ ውስብስብ እንዲሁም ብዙ ችግሮችን የሚያስከትል ነው። የደም ግፊት መጨመር እንደ ምልክት ይቆጠራል እንጂ በሽታው ደም ግፊት ብቻ ነው ማለት አይቻልም።
በእርግዝና ወቅት የሚፈጠር የደም ግፊት መንስኤዎች
ከዚህ ቀደም በነበረ እርግዝና የደም ግፊት መኖር
ውፍረት
መንታ ፅንስ
በላቦራቶሪ (IVF) የተፈጠረ ፅንስ
የኩላሊት፣ የሳንባ፣ አስም፣ ስኳር እና የእንቅርት በሽታ
እድሜ (ከ35 ዓመት በላይ)
ጥቁር የቆዳ ቀለም መኖር
በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው ነጭ ቀለም ካላቸው ሰዎች በበለጠ ለደም ግፊት ተጋላጭ መሆናቸውን የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል። ለዚህ ልዩነት እንደ ምክንያት ያስቀመጡት ጥቁሮች ከነጮች በበለጠ ጨዋማ ምግቦችን መመገባቸውን ነው። ባለሙያው አክለው “እርግዝና መኖሩ ብቻ ለደም ግፊት ያጋልጣል። ሁሉም እናቶች በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት ተጋላጮች ናቸው” በማለት ተናግረዋል።
በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም ደም ግፊት ምልክቶች
ራስ ምታት
የዐይን ብዥታ
የሰውነት ማበጥ; የነፍሰ ጡር ሴት እግር ሊያብጥ ይችላል። ነገር ግን ከእግር ውጪ ባሉ የሰውነት ክፍሎች ላይ እብጠት ካለ የደም ግፊት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። በተለይም እጅ እና ፊት ማበጥ የደም ግፊት መጨመር ምልክት ሊሆን ይችላል።
የክብደት መጨመር; በ1 ወር ውስጥ ከ2 ኪሎ ግራም በላይ የሆነ ክብደት መጨመር የበሽታው ምልክት ነው።
እራስን ስቶ መውደቅ
ሳል እና ደም የቀላቀለ አክታ
የሽንት መጠን መቀነስ
የደም መቅጠን
ዐይን ቢጫ መሆን
በአፍንጫ እና በሌላ የሰውነት ክፍል ላይ ደም መኖር
እንደ ዶ/ር ሰኢድ አራጌ ንግግር በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም ደም ግፊት ምንም አይነት ምልክት ላያሳይ ይችላል። በሽታውን ማወቅ የሚቻለው የህክምና ተቋም ውስጥ በሚደረግ ምርመራ ነው። ለዚህም  የቅድመ ወሊድ የህክምና ክትትል ላይ የዓለም የጤና ድርጅት ማሻሻያ ማድረጉ ጠቃሚ መሆኑን የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም እናቶች 4 ጊዜ ሲያደርጉ የነበረው የቅድመ ወሊድ ክትትል ወደ 8 ከፍ ተደርጓል። የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊት እንዲሁም በማተርናል ፌታል ሜዲስን ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሰኢድ አራጌ እንደተናገሩት በሳምንታት(ቀናት) ልዩነት ውስጥ በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም ደም ግፊት ሊከሰት ይችላል። እናቶች የቅድመ ወሊድ የህክምና ክትትል በማድረግ በሽታውን አስቀድመው እንዲከላከሉ ዶ/ር ሰኢድ አራጌ ጥሪ አድርገዋል።


Read 369 times