Monday, 13 May 2024 20:08

የለምለም ኃ/ሚካኤል “ማያዬ” አዲስ የሙዚቃ አልበም የፊታችን አርብ ይለቀቃል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ከዚህ ቀደም ለህዝብ ባቀረበቻቸውና ከፍተኛ ተወዳጅነት ባገኘችባቸው ”ላሊበላ“ ፣ ”ገዳም“ ፣ ”በላልበልሃ“ በተሰኙ ነጠላ ዜማዎቿ  የምትታወቀው ድምጻዊት ለምለም ኃ/ሚካኤል፤ ”ማያዬ“ የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ አልበሟን የፊታችን አርብ ትለቃለች፡፡

ሰርቶ ለማጠናቀቅ ዘጠኝ ዓመት እንደፈጀ የተነገረለት አዲሱ የሙዚቃ አልበም 12 ያህል ዜማዎች የተካተቱበት ሲሆን፤ አንጋፋው ናሆም ሪከርድስ ፕሮዱዩስ አድርጎታል፡፡

በዚህ የሙዚቃ አልበም ውስጥ ኤልያስ መልካን ጨምሮ አንጋፋና ወጣት የሙዚቃ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል ተብሏል፡፡

አዲሱን የሙዚቃ አልበም  አስመልክቶ ዛሬ ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ረፋዱ ላይ ድምጻዊቷና የሙዚቃ ባለሙያዎች በማርዮት ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተነገረው፤ አበጋዝ ክብረወርቅ፣ ኤልያስ መልካ፣ ሚካኤል ሃይሉ፣ ታምሩ አማረ፣ አዲስ ፍቃዱና ብሩክ ተቀባ በቅንብር፤ ወንድወሰን ይሁብ፣ ናትናኤል ግርማቸው፣ ሀብታሙ ቦጋለ፣ ጥላሁን ሰማው፣ በግጥም ሲሳተፉ፤ ኤልያስ መልካ፣ አንተነህ ወራሽ፣ እሱባለው ይታየው፣ ብስራት ሱራፌል፣ ዘርአ ብሩክ ሰማው በዜማ ተሳትፈዋል፡፡ በሚክሲንግና ማስተሪንግ ሰለሞን ኃይለማርያም የተሳተፈ ሲሆን፤ በፕሮዱዩሰርነት ወንድወሰን ይሁብ እንደተሳተፈበት ታውቋል፡፡

”ማያዬ“ የተሰኘው የድምጻዊት ለምለም ኃ/ሚካኤል አዲስ የሙዚቃ አልበም የፊታችን አርብ ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም በናሆም ሪኮርድስ የዩቲዩብ ቻናል እንዲሁም በዓለማቀፍ የሙዚቃ መተግበሪያዎች ይለቀቃል ተብሏል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በባሌ አጋርፋ የተወለደችው ድምጻዊቷ፤ የሁለት ሴት ልጆች እናት ስትሆን፣ ላለፉት 10 ዓመታት በትወናና በድምጻዊነት የኪነጥበብ ዘርፍ ስታገለግል መቆየቷ ተጠቁሟል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቲያትር ጥበባት ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያገኘችው ለምለም ኃ/ሚካኤል፤ ከዚሁ የትምህርት ክፍል በቲያትር ፎር ዴቨሎፕመንት የሁለተኛ ድግሪ እጩ ተመራቂ ናት፡፡

Read 1199 times Last modified on Tuesday, 14 May 2024 05:48