Wednesday, 15 May 2024 19:34

የኮሎኔል መርሻ ወዳጆ የሦስቱ መንግስታት ዕድሎችና ተግዳሮቶች መጽሐፍ እሁድ ይመረቃል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የአገራችንን የግማሽ ምእተ አመት የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ  እንቅስቃሴ የሚያስቃኘው  የኮሎኔል መርሻ ወዳጆ አዲስ መጽሐፍ፣ የፊታችን እሁድ ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም  ከቀኑ 8 ሰአት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት ኤጀንሲ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ የመጽሐፉም ርእስ  ”በሦስቱ መንግስታት ያጋጠሙኝ እድሎችና ተግዳሮቶች”  የሚል ነው፡፡

ደራሲው፣ ከፖሊስ መኮንንነት አንስቶ እስከ ሚኒስትርነት ባለው የሥራ ህይወታቸው  ኃላፊነታቸውን በብቃት ለመወጣት የቻሉ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ (አባዲና)  ዋና አዛዥ በመሆን ያገለገሉት ኮሎኔል መርሻ፤ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ  የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል  ሳይንስና  በኢኮኖሚክስ ያገኙ ሲሆን፤ በአሜሪካና በህንድም  የሁለተኛ ዲግሪ  ትምህርታቸውን  ተከታትለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ሰራዊት የላቀ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ካደረጉት ከብርጋዴር ጄነራል ጽጌ ዲቡ ጋር በቅርበት የመሥራት እድል ያገኙት  ኮሎኔል መርሻ ወዳጆ፤ ከጄነራሉ ጋር በመሆንም ሰራዊቱን የማቋቋም ሚና ተጫውተዋል፡፡

ኮሎኔል መርሻ፣ የማእከላዊ ፕላን ኢንስፔክሽን መምሪያ ኃላፊ ሆነው የሰሩ  ሲሆን፤ በ1977 ዓ.ም  የአገር ውስጥ ንግድ ሚኒስትር በመሆንም አገልግለዋል፡፡

በ423 ገጾች የተቀነበበው  መጽሐፋቸው 3 ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያሳለፉትን ህይወት  ዳስሰውበታል፡፡ ይህንን የሥራና የህይወት ታሪካቸው የተካተተበት መጽሐፍን አዘጋጅቶ ለማሳተም 3 ዓመት ያህል እንደወሰደባቸውም ኮሎኔሉ ተናግረዋል፡፡

”በሦስቱ መንግስታት ያጋጠሙኝ እድሎችና ተግዳሮቶች” የተሰኘው የኮሎኔል መርሻ ወዳጆ መጽሐፍ በ750 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

የፊታችን እሁድ የሚካሄደውን  የመጽሐፍ ምረቃ መርሐ-ግብር የሚያዘጋጀውና የሚያስተባብረው  ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን መሆኑ ታውቋል፡፡

Read 1135 times