ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ለሰዎች ምክር በመስጠት የታወቁ አንድ ብልህና ጨዋታ አዋቂ ሽማግሌ ነበሩ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን አንድ ጅል ዛፍ ጫፍ ላይ ሆኖ፤
“አባቴ እባክዎ ምክር ፈልጌያለሁ ይርዱኝ?” ሲል ይጠይቃል፡፡
“በጄ፤ ምን ልምከርህ?”
“ይቺን ቅርንጫፍ ልጥላት እዚች ጋ ልመታት ነው”
“መክረህ ጨርሰሃል ልጄ እንደውሳኔህ ቀጥል”
ይመታዋል፡፡ ቅርንጫፉ ይወድቃል፡፡
ሌላ ቅርንጫፍ ይጠቁምና፤ “ይሄኛውንም ቅርንጫፍ ለመጣል እዚህ ጋ ልሰነትር ነው” ይላል፡፡
“መክረህ ጨርሰሃል ልጄ እንደበጀህ ቀጥል” ይሉታል፡፡
ያለውን ቦታ ሲመታው ቅርንጫፉ ተገንጥሎ ይወድቃል፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለ ቅርንጫፎቹን ሁሉ በመጥረቢያ ገነጣጥሎ ይጨርሳል፡፡ ከዚያም፤
“አባቴ፤ ቀጥዬ የቱን ልምታ?” ይልና ይጠይቃል፡፡
“እንግዲህ የቀረህ አንተኑ ይዞ የሚወድቀውን መምታት ነው”
“መውደቁን ግን ይወድቃል?”
“አሳምሮ ይወድቃል”
“እንግዲያውስ አልምረውም!” ብሎ የተቀመጠበትን ግንድ ከበላዩ ይመታዋል፡፡ ተገንድሶ ሲወድቅ ራሱኑ ጭንቅላቱን መትቶ ይፈነክተዋል፡፡
“አባቴ፤ ግንዱ ሙሉውን አልወድቅ አለኝ ምን ይበጀኛል?”
“መፈንከቱ አልበቃህ ብሎ ነው? ምልክት መስጠቱ እኮ ነው፤ አልገባህም?”
“ዛሬ እሱን ሳልጥል ከእዚህ ንቅንቅ አልልም!”
“እንግዲህ በጄ አላልከኝም ክፉኛ- አክርረሃል፡፡ አናቱን ብለህ እምቢ ካለህ የቀረህ ግርጌው አደል?”
ሞኙ ከእግሩ ስር ያለውን ግንድ መከትከት ይጀምራል፡፡
“ልጄ፤ እኔ ወደምሄድበት ልሂድ ስመለስ መጨረሻህን አያለሁ”
“ምነው አባቴ እስከዳር አብረውኝ ላይቆዩ ነው? እስካሁን አብረን ቆይተን?”
“ያንተ አንሶ ለኔ እንዳይተርፍ ብዬ ነዋ! ግዴለህም ከሶስታችን አንዳችን ለወሬ ነጋሪ እንኳ እንቆይ፡፡ ኋላ መጨረሻህን ባይ ነው የሚሻለኝ!” ብለው ሄዱ፡፡
ሽማግሌው ሲመለሱ ግንዱም ሰውዬውም ወድቀው አገኟቸው፡፡ ሰውዬው እግሩ ተሰብሮ ወገቡ ተቀጥቅጦ ሲያቃስት ደረሱ፡፡
“ይሄውልዎት አባቴ ተሰበርኩ ግን ግንዱን ጥዬዋለሁ”
“እሱም አፍ ቢኖረው እንዳንተው ጣልኩት ነበር የሚለው፡፡ አይ የናንተ ነገር ተያይዞ መውደቅ እንጂ ተደጋግፎ መቆም አልሆነላችሁም” አሉት፡፡
***
መክሮ የጨረሰ የሌላ ምክር አይሰማም፡፡ ወይም አያስፈልገኝም ይላል፡፡ እራሱን ጭምር ይዞ የሚወድቀውን ግንድ በመጣል የሚረካ ብዙ ግብዝ አይተናል እያየንም ነው፡፡ ይህ ሂደት በፖለቲካ ፓርቲ፣ በመንግስታዊ መዋቅሮች፣ በየቢሮው ወዘተ የአዘቦት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ጉዟችን ሁሉ ደክሞ ደክሞ እንደገና ከዜሮ የመጀመር የሆነው አንድም በዚህ ሳቢያ ነው፡፡ “ቀጥዬ የቱን ልምታ?” ማለት እንጂ “ቀጥዬ የቱን ላድነው” የሚል ሰው አልተዋጣልንም፡፡ በዚህም ቁልቁል ማደግን ባህል አድርገነዋል፡፡ ሌላው ፈሊጣችን ደግሞ ብንቆስልም ብንደማም ካደረስነው ጥፋትና ከደረሰብን ጉዳትም ለመማር አለመቻላችን ነው፡፡ “ተሳስቼ ይሆን?” ከማለት ይልቅ፣ “ካለመስዋዕትነት ድል የለም” ማለትን እናዘወትራለን፡፡
አንድያችን ተንኮታኩተን ካልወደቅን “ያለምኩትን ብለቅ አይማረኝ” እያልን ሙጭጭ ማለት ነው፡፡ የእርግማን ክፉ ከትንሽም ከትልቅም ስህተት ፈጽሞ አለመማር ነው፡፡
ራስን በአዲስ መላ፣ በአዲስ መርህ፣ በአዲስ ፕሮግራም ከመውለድ ይልቅ ከትላንቱ ክታቤ ጋር ልሙት ማለትን ለደጉም ለክፉውም የምንምልበት ቃለ-መሀላ አድርገነዋል፡፡
የእኛ ነገር “ተፍቆ ጥርስ አይሆን፣ ተመክሮ ልብ አይሆን” ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
የትላንት ቂም፣ የትላንት ያደረ - ሂሳብ፣ አገር ላያለማ ነገር፣ ከእነ ግንዳችን ካልወደቅን ያሰኘናል፡፡ የቡድንና የቡድን አባቶች ብሎ ተቧድኖ “ከቦምብ ከመትረየስ” ከማለት ይልቅ፣ ቢያንስ “ከሰማይ በራሪ-ከምድር ተሽከርካሪ” ማለት መሻሉን ካላየን እድሜ -አለማችንን ጠብ-ጠማሽ ሆነን እንደመቅረት ነው፡፡ ከበረታን በዱሮ በሬ ማረስ ይቻላል ብሎ ቢነሱ እንኳ የዱሮ እልህ፣ የዱሮ ጉልበት፣ የዱሮ መሬትና የዱሮ የእህል ዘር እንደ ልብ ስለማይገኝ አርቆ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በአንፃሩ አዲስ በሬ በአቅልና በተገቢው ማሳ ላይ ይውላል ብሎ ማሰብም አዲስ ባዩ ቁጥር ጉሮ - ወሽባዬ ማለት ይሆናል፡፡ የወረት ውሻ ስሟ ወለተ - ጊዮርጊስ ነው እንዲሉ፡፡
በኢትዮጵያ የፖለቲካ አደባባይ ላይ የሚታዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ማህበራትና ቡድኖች “ሁሉን ጥዬ እኔ ልታይበት፣” “እኔ ልዩ የክት ልብስ አለኝ” ከሚለው እምነት ይልቅ የተግባር ቅደም -ተከተላቸውን መልክ በማስያዝ፣ የፖለቲካው ስር የሰደደ ችግር በጋራስ ሆነን ሊፈታ ይችላልን? ብለው፣ አስቀድሞ የተረጋጋ ማረፊያ ህዝቡ ውስጥ፣ ቀጥሎ በየፖለቲካ መዋቅሩ ላይ፤ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ የአየር ጠባይ አንፃር ሲታይ፣ ምንም ነገር ቀላል ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ጊዜ አለኝ ብሎ መዘግየትም ሞኝነት ነው፡፡ ከትላንት የምንበደረው ጊዜ እንኳ ቢገኝ መውሰድ ነው የሚባልበት ዓይነት ትግል ጠይቋል ወቅቱ፡፡ ከቶውንም ሁሉም የፖለቲካ ነገር በራስ የሚሰራ፣ የገዛ አፈርን እያሸተቱ ከህዝቡ ጋር ተሆኖ የሚሰራ እንጂ የማናቸውም ቴክኖሎጂ የሩቅ - መቆጣጠሪያ (Remote control) የሚከናወነው አይደለም፡፡ እንደ ዱሮው “በጠባቧ ቢሮአችን ተቀምጠን የሰፊውን ህዝብ የልብ ትርታ እናዳምጣለን /እንቆጣጠራለን!” የሚባልበት ወቅት አይደለም፡፡ የየቢሮውን ቀይ - ጥብጣብ ማሸነፍን ይጠይቃል፡፡ የህዝቡን ልብ በመንፈስም በዐይነ-ሥጋም ማሸነፍን የግድ ይላል፡፡
ይህን ሁሉ ካደረጉ በኋላ እንግዲህ “መቀመጫ ያገኘ እግሩን መዘርጊያ አያጣም” ለመባባል ይቻላል!!