Saturday, 18 May 2024 21:25

አዲስ ሕይወት ለመቀበል ስልጠና ያስፈልጋል፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

ከአሁን ቀደም ሙሉ ጂ የተባለ ሆስፒታል በመገኘት ከሆስፒታሉ ባለቤቶች አንዱዋን ማለትም የጨቅላ ህጻናት እስፔሻሊስት የሆኑትን ዶ/ር ሙሉአለም ገሰሰን አነጋግረን ለንባብ የሚሆን ቁምነገር ማጋራታችን ይታወሳል፡፡ ሙሉ ጂ ሆስፒታል የዶ/ር ሙሉአለም ገሰሰ እና ዶ/ር ገመቺስ ማሞ (ባልና ሚስቶች ናቸው) ሆስፒታል ነው፡፡
ወደሆስፒታሉ ከማምራታችን በፊት በሆስፒታሉ ልጅዋን ከተገላገለችው እናት ወ/ሮ አዲስ አለም ብርሀኔ እና አባት ዶ/ር ያየህይራድ አየለ ጋር በነበረን ቀጠሮ መሰረት ልጅን ማሳደግ ምን ይመስላል በሚል ርእስ ዙሪያ ተነጋግረናል፡፡ ወ/ሮ አዲስ አለም የማህበራዊ ሰራተኛ ስትሆን ዶ/ር የህይራድ ደግሞ ጠቅላላ ሐኪም ነው፡፡ ለዚህ እትም የባልና ሚስቶቹን አስተያየት እና ልምድ ለንባብ ካልን በሁዋላ የባለሙያዎችን እና ሌሎች እናቶችን ሀሳብ ለመጋራት ወደሆስፒታሉ እናመራለን ፡፡
ሙሉ ጂ ሆስፒታል ለሐኪሞች እና እናቶች እንዲሁም ለአሳዳጊዎች በሚሆን መልኩ ቅድመ ወሊድ እና ድህረ ወሊድ ስልጠና ለመስጠት መክሊት የሚባል የስልጠና አሰራር ዘርግተው በመስራት ላይ ናቸው፡፡ በሆስፒታሉ ልጃቸውን ለመውለድ ለሚሄዱ እናቶች ስልጠናው በፈቃ ደኝነት ይሰጣል፡፡ ይህች እናት የስልጠናው ተሳታፊ እንደነበረችና እንዳልነበረች እንድትነግረን ነበር አስቀድመን የጠየቅናት፡፡ እስዋም የሚከተለውን ነበር የመለሰችው፡፡
በእርግጥ ልጄን የተገላገልኩት በሙሉ ጂ ሆስፒታል ነው፡፡ ከአሁን ቀደም የመመሪያ ልጄን ያዋለደኝ ዶ/ር ወደሙሉጂ መግባቱን ስሰማ ወደዚያ በመሄዴ ነበር ሙሉጂን ያገኘሁት፡፡ እናም ክትትል በማደርግበት ጊዜ ስልጠና እንደሚሰጥ እና እንድሳተፍ ተነግሮኛል፡፡ ነገር ግን ስልጠ ናው የሚሰጥት ቦታ ትንሽ ስለራቀኝ መሄድ አልቻልኩም ነበር፡፡ እናም አልሰለጠንኩም፡፡ ብላለች፡፡
ስልጠናው ቢሰጥ ምን ያህል ጠቃሚ ነው ብላችሁ ታስባላችሁ? ለባልና ሚስቶቹ የቀረበ ጥያቄ ነበር፡፡ ዶ/ር ያየህይራድ እንደሚከተለው አስተያየቱን ሰጥቶአል፡፡ በእርግጥ ስልጠናው መሰጠቱ በጣም ጠቃሚ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እንዲያውም ስልልናው ለእናትየው ብቻ ሳይሆን ለአባትየውም ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፡፡ የመጀመሪያው ነገር የእርግዝናውን ወቅት ምንም እንኩዋን ልጁን የተሸከመችው እናትየው ብትሆንም አባትየውም የሚጋራው ነገር እንደሚኖር በተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን በስልጠና የሚያ ውቅበት መንገድ ቢኖር ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከውልደት በሁዋላም ላለው ነገር ኃላፊነት መጣል ያለበት ለእናትየው ብቻ ሳይሆን አባትየውም ኃላፊነት ያለበት መሆኑን እንዲያውቅ የሚረዳው ስልጠና ቢያገኝ ጥሩ ነው፡፡ ከወሊድ በሁዋላ እንቅልፍ ማጣትን ጨምሮ ከስራ ጋር ተያይዞ ብዙ ጫና ሊኖረው እንደሚችል አስቦ አስቀድሞ ለመዘጋጀት የሚያስችለው ስልጠና የምክር አገልግሎት ከሚስቱ ጋር አብሮ የሚያገኝበት መንገድ ቢኖር እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ብሎአል፡፡
ወ/ሮ አዲስአለም በበኩልዋ ስልጠናውን ሳታገኝ ልጅዋን ብትወልድም ስልጠናው ግን ጠቃሚ መሆኑን ትመሰክራለች፡፡
እናትነት በተፈጥሮ መንገድ አርግዞ ልጅ መውለድ ብቻ የሚመስለን ከሆነ ተሳስተናል፡፡ እናትነት ልጁን በተፈጥሮአዊ መንገድ ከመውለድ በተጨማሪ የእናትነት ስሜትን ይፈልጋል፡፡ ብዙ ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸው እንደወለዱ ወይም ከፍ ከፍ ሲሉላቸው በፎተግራፍ እየሳቁ እንደሚያሳዩን እውን ስሜታቸው የደስታ ነው ወይንስ? የሚለውን ብንጠይቅ ምናልባት መልሱ ካሰብነው ውጭ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ የመጀመሪያ ልጄን የወለድኩ ጊዜ መቼ ነው ሳላስመስል ከእውነት ከልቤ የምስቀው ብዬ እራሴን እጠይቅ ነበር፡፡ ጥርስ ስለታየ ብቻ ተሳቀ አይባልም፡፡ ከስሜት ሲሆን ይለያል፡፡ ዙሪያዬን ያለ ቤተሰብ ፤ጉዋደኛ፤ጎረቤት ሁሉ ከእውነቱ ተደስቶ ሲስቅ ሲዝናና እኔ ግን ምንም እንኩዋን ልጅ በመውለዴ ደስተኛ ብሆንም ግን እንደሌላው ሰው አልነበርኩም፡፡ የልጁ ለቅሶ፤ጡት ማጥባት፤ለማስተኛት መታገል፤ምን ይሆናል ብሎ በስጋት መከታተል ፤እንደልብ ለመተኛት አለመቻል፤እንዳይታመም አስቀድሞ መጠንቀቅ፤ ሌሊትና ቀኑ መቀላቀሉ፤ በትክክል መመገብ አለመቻል (ሳትወልድ ብላ) …ወዘተ የመሳሰሉት ነገሮች ሁሉ በድንገት ከነበርኩበት አለም ወደሌላ አለም ስለከተቱኝ እጅግ በጣም ብቻዬን ስንገላታ እንደነበር አልረሳውም፡፡ የነበረኝን ድብርት ባለቤቴ እንኩዋን እንዳያውቅብኝ የእውሸት መደሰቴን ነበር የቀጠልኩት፡፡ በዘጠኝ ወር እርግዝና ወቅት እራሴን የምጠይቀው መቼ ይን ልጁ ተወልዶ እኔ ወደራሴ የምመለሰው…ልብሴን ለብሼ የምታየው….የሚል ነበር እንጂ ልጁ ሲወለድ ከዚያ የበለጠ እንቅልፍ እንደማጣ ፤ትግል እንደሚገጥመኝ፤ኃላፊነት እንደሚኖርብኝ …አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ ብላለች፡፡ ወ/ሮ አዲስ አለም ስለስልጠናው ስትቀጥል፡-
የእናቶች ከወሊድ በፊትና ከወሊድ በሁዋላ ስልጠና ለምን ይጠቅማል የሚለውን ጥያቄ ከራሴ ልምድ ተነስቼ ለመመልከት እወዳለሁ፡፡ ለምሳሌ
ልጅ ከወለዱ በሁወላ ለተወሰኑ ወራት ወጥ በሆነ መንገድ መተኛት እንደማይቻል ከስልጠናው ወይም ለስልጠናው ከመጡ ሰዎች ልምድ ይገኛል፡፡
ጡት ማጥባት ለእትየውም ይን ለህጻኑ ምን እንደሚጠቅም ፤በተሳካ ሁኔታ ጡት ማጥባት እንዴት እንደሆነ ማወቅ ቀላል ነገር አይደለም፡፡
ህጻናቱ በየስንት ሰአቱ ከእንቅልፋቸው ይነቃሉ የሚለውን አሰቀድሞ ማወቅ ለስነልቦና ዝግጅት ይረዳል፡፡  
ዲያፐር በየስንት ሰአቱ መቀየር አለበት፤ ልጁ በየስንት ሰአቱ መመገብ አለበት …ወዘተ የመሳሰሉትን ሁሉ አስቀድሞ አውቆ ልጅን መውለድ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
ለዶ/ር ያየህይራድ አንድ ጥያቄ አንስተን ነበር፡፡ አባቶች አንዳንድ ጊዜ አዲስ የተወለዱ ህጻናትን በመፍራትም ይሁን ፈቃደኝነትን በማጣት ወይንም ይህ የእናትየው ስራ እንጂ የእኔ አይደለም ከሚል ስሜት በተለያዩ ምክንያቶች በማሳበብ ምንም እርዳታ ከማድረግ ይቆጠባሉ፡፡ ጨቅላ ህጻን የእናቱ ኃላፊነት እንጂ የእኔ አይደለም ሲሉም ይስተዋላሉ፡፡ ይህ ምን ማለት ነው ብለን ነበር፡፡ መልሱ የሚከተለው ነው፡፡
ጨቅላ ህጻናት ወደቤታች ሲመጡ ብቻ ሳይሆን ከመምጣታቸውም በፊት ገና በእርግዝናው ወቅት ስለልጁ ደህንነት አባትተው ሊጨነቅ ፤አስፈላጊውን እገዛ ሊየደርግ ይገባዋል፡፡ እናትየው በማጸንዋ የተሸከመችው ልጅ ከአባትየው የተረገዘ መሆኑን መርሳት አይገባም፡፡ ሴትየዋ ያረገ ዘችው ልጅ በጥሩ ጤንነት ላይ ሆኖ ተፈጥሮአዊ ሂደቱን ጨርሶ እንዲወለዱ ተሳትፎ ካደረጉ በሁዋላ ልጁ ሲወለድ ደግሞ ጡት ከማጥባት በስተቀር በሚችሉት መንገድ ሁሉ ልጃቸውን ማስተናገድ ይገባቸዋል፡፡ አባቶች ዲያፐሩን ገዝቼ ካመጣሁ መቀየሩ የእናትየው ስራ ነው የሚል ሃሳብ ሊኖራቸው አይገባም፡፡ እናትየውን ለመርዳት ተብሎ ሳይሆን ልጁ የእኔ ነው… እኔን አባቱን ልጄ በደንብ ሊያውቀኝ ይገባል ከሚልም ሙሉ ፍቅር ሰጥቶ ገላውን በማጠብ፤ ዲያፐር በመቀየር፤እንቅልፍ እንዲተኛ በማድረግ …ወዘተ አባትየው ግዴታውን መወጣት እንዳለበት መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህ ለእናቶች ቅድመ ወሊድና ከወሊድ በሀዋላ የሚሰጥ ስልጠና ለአባትየውም አብሮ ቢሰጥ እንዚህ ያለውን ግዴታ፤ለቤተሰቡ መስጠት ያለበትን ፍቅር እና አገልግሎት የመሳሰሉትን ሁሉ እንዲረዳ ያስችለዋል ብዬ አምናለሁ ብሎአል ዶ/ር፡፡
አዲስ አለም የመጀመሪያ ልጅዋን ስታረግዝና ስትወልድ የተለያዩ ስሜቶች ነበሩአት፡፡ ለምሳሌ ከእውት የመነጨ ሳቅ መሳቅ አለመቻልዋን ሁሉ አጋርታናለች፡፡ በሁለተኛው የነበራት ስሜት ምን እንደነበር ከስልጠናው ጋር አያይዛ እንደሚከተለው ነበር ያብራራችው፡፡
የሁለተኛውን ልጄን ሳረግዝ አስቀድሜ ነበር የተዘጋጀሁት፡፡ ለምሳሌ በእርግዝናው ጊዜ ሰውነቴ እንዳይሰነጣጠቅ ፤ጡቴ እንዳይቆስል ክሬም ማዘጋጀት፤ምናልባት ጡት ማጥባት ባልችል ከሚል ማለቢያውን ማዘጋጀት፤ለልጁ የሚሆኑኝን እቃዎች ወልጄ ሳልተኛ በፊት መገዛዛት የመሳሰ ሉትን ሁሉ አድርጌአለሁ፡፡ ስለእንቅልፌ፤ስለምግቤ፤ስለእረፍቴ ሁሉ የነበረውን ነገር አስታውሼ በደንብ ተዘጋጅቼበት ነው ልጄን የወለድኩት፡፡ የመጀመሪያው ልጄ ገጠመኝ ለሁለተኛው ልጄ ልምድ ሆኖኛል ፡፡ ስለዚህ ሴቶች ልጅ ለመውለድ በሚፈልጉበት ጊዜ አስቀድመው ወደ ህክምና ቦታ መሄድ የሚያስፈልጋቸው አዲስ ህይወትን ስለሚጀምሩ ነው፡፡ ስለዚህ፡-
ልጅ በማርገዝ ወቅት ከእራሳቸው ጤንነት ጋር በተያያዘ እና በእርግዝና ላይ ያለው ልጅ ደህንነት በምን ሁኔታ ሊመራ እንደሚባው እንዲያውቁ ይረዳቸዋል፡፡
በቤታቸው ውስጥ አዲስ ህይወት እንደሚመጣ እና ህይወታቸው እንዳይዛባ እንዲሁም ከባለቤታቸው ጋር ተስማምተው አዲሱን ሕይወት ማለትም ልጃቸውን እንዲያሳድጉ ስለሚረዳቸው ነው፡፡ ብላለች፡፡

Read 433 times