Sunday, 19 May 2024 20:06

ጎብኚዎቹ - በራሳቸው አንደበት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ቻርለት ኬሪች (ናይሮቢ፤ የፋይናስና ኢኮኖሚ ቢሮ ኀላፊ)
ዐይን ገላጭ ልምድ ነው ያገኘነው። ከተሞችንን ለሕጻናት አመቺ ለማድረግ፣ የግድ ሰፋፊ ቦታዎች ያስፈልጋሉ ማለት እንዳልሆነ አይቻለሁ።
የከንቲባዋ ራዕይ አዲስ እይታን የሚፈጥር ነው። በተወሰኑ ቦታዎች ትልልቅ የሕጻናት መጫወቻዎችን ከመገንባት ይልቅ በየአካባቢያቸው በቅርባቸው በሺ የሚቆጠሩ የመጫወቻ ስፍራዎችን ለማዘጋጀት ነው እየሠሩ ያሉት።
የሕጻንነት ዕድሜ ለአካላዊና ለአእምሯዊ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ አለው። ሦስት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ በየሰፈራቸው በየአቅራቢያቸው ከቤት ውጭ ምቹ የመጫወቻ ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ በጣም ትልቅ ሥራ ነው። ትምህርት ቤት ሲገቡ ዕውቀት የመጨበጥ ዐቅማቸው ጥሩ ይሆናል። ዕድሜ ልክ የሚያገለግል ኢንቨስትመንት ነው ማለት ይቻላል።
እነዚህ ሕጻናት ሲያድጉ፣ በትክክል የተገነባ አዲስ ትውልድ ይኖራችኋል ብዬ እጠብቃለሁ።
ዪቮኔ ኢኪሳውዬር - የፍሪታውን ከንቲባ፡
የመዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤቶችን አይተናል። ለትናንሽ ሕጻናት የተዘጋጁ የመጫወቻ ቦታዎችንም ጎብኝተናል። አንዲት እናት አግኝቼ እንደነገረችን፣ ቦታው አቧራማ ነበር። ሕጻናትን ለጤና ጠንቅ የሚያጋልጥ ነበር። አሁን ግን ንጹሕ ነው። በልምላሜ አረንጓዴ ለብሶ ደስ ይላል። የመጫወቻ ቁሳቁሶችም ተዘጋጅተውለታል። በዚህም የአካባቢው ሰው ደስተኛ ነው።
ከተሞችን ለሕጻናት አመቺና ተስማሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግ እንገነዘባለን። የፕሮጀክት ሰነድ ማዘጋጀትም ጥሩ እንደሆነ እናውቃለን። ትልቁ ቁም ነገር ግን በተግባር መሥራት ነው። እኔን ያስደሰተኝና ያስደነቀኝ፣ ሐሳቦችና ሰነዶች በተግባር መሬት ላይ ተሠርተው ማየቴ ነው።
ቺላንዶ ናካሊማ ቺታንጋላ - የሉሳካ ከንቲባ፡
ለልጆች ዕድገት የምንሠራቸው ነገሮች መጪውን ዘመን የሚቀይሩ ኢንቨስትመንቶች እንደሆኑ ይታወቃል። እዚህ አዲስ አበባ በተግባር እየተሠራ ነው። እኛንም ለሥራ አነሣሥቶናል።
ለወላጆችና ለአሳዳጊዎች የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው ሲመረቁ አይተናል። ያልተለመደ ነገር ነው። ገርሞኛል። የከተማው አስተዳደር ለሕጻናት አስተዳደግ በሁሉም መስክ ብዙ ኢንቨስት እያደረገ እንደሆነ ተረድቻለሁ። የአፍሪካ የከተማ ከንቲባ እንደመሆኔ፣ ጥሩ የልምድ አጋጣሚ ሆኖልኛል። አፍሪካ በፍጥነት የምታድግ አህጉር ናት። በሕፃናት ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለብን።
ሱዛን ሌንጌዋ - የናይሮቢ የጤና ም/ሚኒስትር፡
ሁሉንም ዘርፍ ያካተተ የመንግሥት አሠራር ይደነቃል። በትምህርት፣ በጤና፣ በትራንስፖርትና በሌሎችም ዘርፍ ሁሉ ትኩረታቸውን በመሰብሰብ ተግባራቸውን በማናበብ እንዲሠሩ የከተማው አስተዳደር  የተቀናጀ አሠራር አለው።
አዲስ አበባን ለልጆች አስተዳደግ ምቹ ለማድረግ ሁሉንም መስክ አቀናጅቶ መሥራት እንደሚያስፈል ብቻ ሳይሆን እንደሚቻልም ነው ያየሁት። ትምህርት ቤቶችን፣ የመጫወቻ ቦታዎችን፣ የሕጻናት ማቆያ ስፍራዎችን አይተናል። ለወላጆች የምክር አገልግሎት የሚሰጠሩ ከ3ሺ በላይ ባለሙያዎች ሰልጥነው ሲመረቁም በአካል ተገኝቼ ተመልክቻለሁ። ለኛ አዲስ ነገር ነው። አዲስ ልምድ እናገኝበታለን።
ለይላ መሀመድ ሙሳ (የትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ሚኒስትር)፡
ከንቲባዋንና መንግሥትን ላሞግሳቸው እወዳለሁ። የሕጻናት አስተዳደግን ለማሻሻል ያከናወኑት ሥራ፣ የሚጨበጥ የሚዳሰስ ሥራ ነው። የሕጻናት ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ በአግባቡ ትምህርት እንዲያገኙ፣ የጤና አገልግሎት እንዲሟላላቸው ለማድረግ ብዙ እንደተሠራ አይቻለሁ።
ዛሬ እጃችው ውስጥ ባለ አነስተኛ ዐቅም ተጠቅመን ውጤት ለማምጣት አስተማማኝ አመራርና የተቀናጀ አሠራር አስፈላጊ እንደሆነ በተግባር ተመልክተናል።
በመጀመሪያው ዕለት ከንቲባዋ ራዕያቸውንና ዕቅዳቸውን ሲያስረዱን፣ ይሄ ሁሉ እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄና ጥርጣሬ ነበር የተፈጠረብኝ። ከንቲባዋ የራዕይና የዕቅድ ብቻ ሳይሆን የተግባርም ሰው ናቸው። ሥራውንም በአካል እየሄዱ ይከታተላሉ። በሄዱበት ሁሉ ሕጻናት ከንቲባዋን በደስታ ሲቀበሉና እየሮጡ ሲያቅፉ አይቻለሁ። ከንቲባዋ ለሥራው ምን ያህል ቅርብ እንደሆኑ ታዝቤያለሁ።


Read 1363 times