Sunday, 19 May 2024 20:12

መልካም ከሠራን መልካም ፍሬ እናገኛለን። ያልዘራነውን አናገኝም።

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አዲስ አበባ “ሕፃናትን ለማሳደግ ተመራጭ አፍሪካዊት ከተማ” ለማድረግ የተከናወኑ ሥራዎች ፍሬ አፍርተዋል፤ ከተማችን አፍሪካዊ እህቶቿንና ወንድሞቿን ተቀብላ ልምድ የምታጋራ ሆናለች። በዓለም አደባባይም በተምሳሌት እየተነሣች ነው ብለዋል የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አበቤ።
ለዚህም ነው፣ ከሰሞኑ በርካታ ከንቲባዎችና የሚኒስቴር ኀላፊዎች ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት  - ከደቡብ አፍሪካና ከሴራሊዮን፣ ከኬንያና ታንዛንያ ከመሳሰሉ ሀገራት።
ከንቲባ አዳነች በሀገራዊ ዜማዎችና ጭፈራዎች ታጅበው እንግዶቹን ከተቀበሉ በኋላ፣ ዐጠር ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሕፃናትን ለማሳደግ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ የሚል ራዕይ ይዘን ነው ሥራ የጀመርነው። የአፍሪካ ጎብኚዎች ይህን ሲሰሙ፣ “ይሄማ የኛም ምኞት ነው። ይሄንማ እኛም እናውቃለን” የሚል ስሜት ቢፈጠርባቸው አይገርምም። የልጆች አስተዳደግን ለማሻሻል መጣር እንደሚያስፈልግና መጪውን ዘመን የሚቀይር ኢንቨስትመንት  እንደሆነ እናውቃለን ብለዋል የሉሳካ ከንቲባ።
ራዕይን በጥቂት ቃላት እቅጩን መግለጽ መልካም ቢሆንም፣ ምኞትን ወደ ዝርዝር ዕቅድ መመንዘርና ሠርቶ ማሳየት ግን… ብዙ ጊዜ አይሳካም።
ከንቲባ አዳነች ዋና ዋና ዕቅዶችንም ባጭር ባጭሩ አንድ ሁለት ብለው ለመጥቀስ ሞክረዋል። ለነገሩማ የጉብኝቱ ዋና ቁም ነገር፣ “ገለጻ የማቅረብ” ጉዳይ አይደለም። የጎብኚዎቹም ፍላጎት ንግግር ሰምተው ለመረዳት ሳይሆን በየቦታው በአካል ተገኝተው በዐይናቸው ለማየት እንደሆነ መገመት አይከብድም። ለዚህም ይሆናል ከንቲባ አዳነች ገለጻውን ዐጠር አድርገው ያቀረቡት።
የሆነ ሆኖ አዲስ አበባ ለሕጻናት ዕድገት እንዲሁም ለወላጆች አመቺ እንድትሆን በሁሉም መስክ መከናወን ከሚገባቸው ሥራዎች መካከል ዋና ዋናዎቹን ጠቅሰዋል።
በሦስት ዓመት ውስጥ 1000 የሕፃናት ማቆያ ቦታዎችን ማዘጋጀት
ሕጻናት በአቅራቢያቸው የመጫወቻ ቦታ እንዲኖራቸው፣ ንጽህናቸው የተጠበቀና አስፈላጊ ቁሳቁስ የተሟላላቸው 12 ሺ የመጫወቻ ስፍራዎችን ማዘጋጀት
ከ1000 በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለሕጻናት አመቺና ማራኪ በሆነ መንገድ በአዲስ መልክ ማሰናዳት
97 የጤና ተቋማትም ሕጻናትን ተቀብለው የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ፣ ለልጆች መስተንግዶ ተስማሚና ማራኪ ቦታ እንዲያዘጋጁ፣ የመጫወቻ ቁሳቁሶች እንዲኖሯቸው ማድረግ
ቤት ለቤት ለወላጆችና ለአሳዳጊዎች የምክር አገልግሎት የሚሰጡ 5000 ሙያተኞችን አሰልጥኖ ማሰማራት
በሦስት ዓመት ውስጥ ይከናወናሉ የተባሉ ዕቅዶችን ከንቲባዋ አንድ ሁለት ብለው ሲጠቅሱ፣ በአድማጮች ዘንድ በርካታ ጥያቄዎችና የጥርጣሬ ስሜቶች እንደሚፈጠሩ ልትገምቱ ትችላላችሁ። አልተሳሳታችሁም።
ከታንዛንያ የመጡት የትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ሚኒስትር ለይላ መሀመድ ሙሳ እንዲህ ይላሉ። በመጀመሪያው ዕለት ከንቲባዋ ራዕያቸውንና ዕቅዳቸውን ሲገልጹላቸው ለማመን ተቸግረዋል። “ይሄ ሁሉ እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይችላል?” የሚል ጥርጣሬ ነበር የተፈጠረብኝ ብለዋል - ለይላ።
ከተማዋን ዞረው ካዩ በኋላ ደግሞ የታዘቡትን ይነግሩናል።
ከንቲባዋንና መንግሥትን ላሞግሳቸው እወዳለሁ በማለት ለይላ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ የሕጻናት አስተዳደግን ለማሻሻል ከንቲባዋ ያከናወኑት ሥራ የሚጨበጥ የሚዳሰስ ሥራ ነው ብለዋል።
“ከንቲባዋ የራዕይና የዕቅድ ብቻ ሳይሆን የተግባርም ሰው ናቸው። ራዕይ ከመያዝ ወይም ዕቅድ ከማውጣት ባሻገር ሥራውንም በአካል እየሄዱ ይከታተላሉ። በሄዱበት ሁሉ ሕጻናት ከንቲባዋን በደስታ ሲቀበሉና እየሮጡ ሲያቅፉ አይቻለሁ። ከንቲባዋ ለሥራው ምን ያህል ቅርብ እንደሆኑ ታዝቤያሁ” ብለዋል ለይላ።
ከንቲባ አዳነች ከሦስት ዓመት እቅድ ውስጥ በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ምን ያህል እንደተሳካ ሲገልጹ፣ የከተማችን የሕጻናት ማቆያ ማዕከላት 597 ደርሰዋል። ጥቂት ነው የሚቀረን። አንድ ሺህ እናደርጋቸዋለን ብለዋል።
በወላጆች ጤንነትና በሕጻናት አስተዳደግ ዙሪያ ቤት ለቤት የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች እስካሁን ከ2000 በላይ ሰልጥነው ሥራ እንደጀመሩ ከንቲባዋ ገልጸዋል። ሰሞኑን ደግሞ 3000 ሙያተኞች ስልጠናቸውን አጠናቅቀው ተመርቀዋል።
ለወላጆችና ለአሳዳጊዎች የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ሲመረቁም በአካል ተገኝተው እንዳዩ የተናገሩት የናይሮቢ የጤና ም/ሚኒስትር ሱዛን ሌንጌዋ፣ “ቤት ለቤት የምክር አገልግሎት የማድረስ አገልግሎት ለኛ አዲስ ነገር ነው፤ አዲስ ልምድ አግኝተንበታል” ብለዋል።
አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአዲስ መልክ እንዲሻሻሉ፣ የጤና ተቋማትም ለሕጻናት አገልግሎት አመቺና ማራኪ እንዲሆኑ በርካታ ሥራዎች እንደተከናወኑ ማየታቸውንም ተናግረዋል።
የተቀናጀ አሠራራቸው የሚደነቅ ነው። የትምህርት፣ የጤና፣ የትራንስፖርትና ሌሎች ዘርፎች ሁሉ፣ በከተማው አስተዳደር ትኩረታቸውን በመሰብሰብ ተግባራቸውን በማናበብ  በመሥራት ውጤት አግኝተዋል ብለዋል - ሱዛን።


Read 761 times