Saturday, 25 May 2024 00:00

ደረቁ ከበደኝ እያልኩ እርጥብ ያሸክመኛል

Written by 
Rate this item
(5 votes)

አንዳንድ እውነተኛ ታሪክ እንደተረት ይነገራል። የሚከተለውን ዓይነት ነው።
ናፖሊዮን ከስፓኒሽ ጦርነት ሲመለስ (1809) በጣም ተበሳጭቶና እየተቅበጠበጠ ነበር ይባላል። የቅርብ ሰዎቹና አፍ- ጠባቂዎቹ፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩና የፖሊስ አዛዡ ሲያሴሩበት እንደነበር ሹክ ይሉታል። ገና ወደ መዲናይቱ እንደገባ ወደ ቤተ-መንግሥቱ በማምራት፣  የሚኒስትሮቹንና የበላይ ባለሥልጣናቱን ስብሰባ ጠራ። ገና እየገቡ ሳሉ ከተሰብሳቢዎቹ ኋላ ኋላ እየተከተለ ወዲህ ወዲያ እንደ ግሥላ መንቆራጠጡን ቀጠለ። ከዚያም ሴረኞች እሱን በመቃወም እንደሚያደቡ፣ አሻጥረኞች የገበያ ዋጋ እንደሚሸቅቡ፣ ህግ አርቃቂዎች ፖሊሲውን እንደሚያዘገዩና፣ የገዛ ሚኒስትሮቹ እሱን ዝቅ አድርገው መመልከት እንደጀመሩ ያልተያያዘ ዓረፍተ ነገር በሚመስል ማጉተምተም ተናገረ።
የውጪ ጉዳዩ ሚኒስትሩ ታስራንድ ጠረጴዛው ላይ ዘመም ብሎ ተቀምጧል። አይሞቀው አይበርደው ዓይነት።
ናፖሊዮን ወደ ታስራንድ እያየ፡- “ሚኒስትሮች ራሳቸውን ለጥርጣሬ ዕድል ከሰጡት፤ ክህደት ጀምረዋል ማለት ነው” አለ።
“ክህደት” የሚለውን ቃል ሲጠራ አፍጦ ወደ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ እያየ ነው። ይደነግጣል ወይም ይፈራል ብሎ ጠብቋል። ሚኒስትሩ ግን ፈገግ ብቻ ነው ያለው። ፀጥና ስልችት ያለ መልክ ነው የሚታይበት። ይሄ ናፖሊዮንን ቅጥል አደረገው።
በመጨረሻ ናፖሊዮን ፈነዳ። ወደ ታስራንድ ቀርቦ  ፊቱ ላይ አፍጦ፤
“አንተ ፈሪ ነህ። ምንም ዕምነት የሌለህ። ለአንተ ምንም የተባረከ ነገር የለም። የገዛ አባትህን ከመሸጥ የማትመለስና አሳልፈህ የምትሰጥ ነህ። በሀብትና በንብረት አንቆጠቆጥኩህ፤ ግን መልሰህ እኔን ከመጉዳት በስተቀር ምንም የምትሰራው ነገር የለህም። የበላህበትን ወጪት ሰባሪ ነህ።”
ሌሎቹ ሹማምንት ዐይናቸውንም፣ ጆሯቸውንም ማመን አቃታቸው። ድፍን አውሮፓን ያንቀጠቀጠው ዕውቁ ጄኔራል እንዲህ ሆኖ አይተውት አያውቁም።
ናፖሊዮን ቀጠለ፣
“አንተን እንደ መስታወት አንክትክት ማድረግ ነው። ያንን ለማድረግ ደግሞ እኔ ፍፁም ሥልጣን አለኝ። ግን ላንተ በጣም ጥላቻው ስላለኝ ልጨነቅብህ አልፈልግም። ለምን ገና  ዱሮ እንድትለቅ እንዳላደረግሁ አይገባኝም። ግን ግዴለም ጊዜ አለኝ!” አለ። ትንፋሹን ጨርሶ ንግግሩ ቁርጥ ቁርጥ እያለ፣ ፊቱ ቲማቲም  መስሎ፣ ዓይኑ ካፎቴ ወጥቶ እየተጉረጠረጠ፤ “አንተ ትቢያ ነህ። የሀገር ውስጥ ትል።… ሚስትህስ ብትሆን? ሳን ካርሎስ ውሽማዋ መሆኑን መች ነግረኸኝ ታውቃለህ?” አለ።
ታሴራንድም፡
“እንደሚመስለኝ ጌታዬ፣ ይሄ መረጃ በክቡርነትዎም  ሆነ በእኔ ክብር ላይም ለውጥ ያመጣል ብዬ ስላላመንኩኝ ነው” አለ እርግት እንዳለና፣ ካለበት ንቅንቅም ሳይል።
ናፖሊዮን ጥቂት ተሳድቦ ወጥቶ ሄደ።
ታሴራንድ ተነስቶ እንደተለመደው ቅስስ ባለ አረማመዱ ክፍሎቹን እያቋረጠ፤ ከእንግዲህ ዐይኑን አናየውም በሚል የመሸማቀቅ  ቆፈን ውስጥ ወዳሉት ሚኒስትሮች ዘወር ብሎ፡-
“ጎበዝ፤ እንዲህ ያለ ታላቅ ሰው፤ እንዲህ ያለ ከንቱ ፀባይ ይዞ ሲገኝ አያሳዝንም?!” አለ። ናፖሊዮን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩን አላሰረውም። ከሥልጣኑ ግን አነሳው። ውሎ አድሮም አባረረው። ህዝቡ ግን ታላቅ ንጉስ የነበረ መሪውን፣ ከርሞ፣ ከርሞ ትንሽ-ትልቁ ነገር ሲያበሳጨው ለመጀመሪያ ጊዜ አስተዋለ።
ይህን ሁሉ ረጋ ብሎ የታዘበው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ታሴራንድ፣ ቆይቶ አንድ ታሪካዊ ንግግር ተናገረ፡-
“ይሄ የፍፃሜው መጀመሪያ ነው” አለ።
***
በማንኛውም ደረጃ ያለ መሪ ትዕግሥት ከሌለው፣ ለበታቾቹ  ንቀት  ካደረበትና ራሱን መቆጣጠር ካቃተው፤ ክብሩንና ቦታውን የሚጠብቅ በሳል ቀላል ሰው በቀላሉ ያሸንፈዋል።
“የፍፃሜው መጀመሪያ” መሆኑን ይነግረዋል። ውጥረት በበዛና ችግሮች በተወሳሰቡ ሰዓት ስሜታዊነት ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሂደት ውስጥ አያሌ ችግሮች ተደቅነው ጉዳዩ የሚመለከታቸው መሪዎች እያስጨነቋቸው መሆኑ ይታያል። ስሜታዊነት የሚያጠቃቸው  መሪዎች ረጋ-ባሉ መሪዎች መተካት ይኖርባቸዋል።
የጋሉትን ለማብረድ፣ የበረዱትን አሰልጥኖና ገርቶ እንዲተኩ ማድረግ ብልህነትና በሳልነት ነው። ነጋ ጠባ እየተካረሩና እየተወሻሹ የትም አይደረስም። በአንፃሩ ዐይን ያወጣ ሸፍጥና የፊት ለፊት አሻጥርን ምን ግዴ ብሎ  እጅን አጣጥፎ መቀመጥም አያዋጣም። “ብትርህን የምታውሰው መልሰህ  መውሰድ ለምትችለው ሰው ብቻ ነው” የሚባለውን የሶማሌ ተረት በቅጡ ማጤን ይጠበቅብናል። በክንድ ርቀት ሆኖ መታየት ያለባቸውንና ተጨባብጦ መተማመን የሚገባቸውን ጉዳዮች በንቁ ዐይን ማየት ያስፈልጋል። በየትኛውም የፖለቲካ መስክ ትግልን ለዕድል መተው የማያዋጣበት ጊዜ አለ። “ጎረቤቶችህ በጀርባህ ላይ ጥጃ ሲያሸክሙህ እሺ ብትል፤ ላሚቱንም ጨምረው ይጭኑብሃል” ይሏልና ቆራጥነትን ከብልህነት፤ አስተውሎትን ከስሜታዊነትና ከቁጡነት፤ በአጭር ጊዜ በራሱ ሂደት የሚሟሽሸውን፤ ከረዥምና በታቀደ፣ ያለመታከት ጉዞ፤ ለፍሬ የሚበቃውን መለየት፣ አስፈላጊ ሲሆን፤ አዋህዶ የመራመድን ዝግጅት ማሟላትም ተገቢ የሚሆንበትን ወቅት ማወቅ ግድ ነው።
የፖለቲካ ሂደት እንደየወቅቱ ተለዋዋጭ ቢሆንም በተለይ የሀገራችን ፖለቲካ እንደ ኳስ ጨዋታ፣ ኳስ ባለችበት አካባቢ ብቻ በማተኮር የምንጓዝበት አይደለም። እንደዚያ ካደረግን ኪሳራ ይበዛል። የጨዋታው ቦታ አራምባ ሲመስለን ቆቦ፣ የካ ሲመስለን መካ የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ስለሆነ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ሁለት ጎል ብቻ ያለው አይደለምና።
ነጋ ጠባ የሚባባስ ሁኔታ፣ ነጋ ጠባ የማንማርበት የፖለቲካ ጨዋታ፣ ነጋ ጠባ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የምንልበት መዳከር ለሀገርና ለህዝብ አይበጅም። አጥብቀን የምንይዘውን እንወቅ። ስለጋራ አገር እናስብ። እኔ ባቀናሁበት አገር ማንም አይኖርበትም የሚል ራስ-ወዳድነት የማይገዛ እንደሆነ ሁሉ፣ ሌላ ያቀናው  ላይ መኖር አልፈልግም ማለትም የአፍራሽ እልህ ነው። በዚህ ሁሉ የፖለቲካ ሂደት ማህል ከዛሬ ነገ የተሻለ ውጤትና የተሻለ እርምጃ፣ የተሻለም ተስፋ ሲጠብቅ፣ ከቅራኔ ክረትና ከመበቃቀል ህልም እንዲሁም ከአለመተማመን አረንቋ፣ የማንወጣ ከሆነ፡ “ደረቁ ከበደኝ እያልኩ እርጥብ ያሸክመኛል” ይለናልና፤ ለዘለቄታው ህዝብን ላለማጣት ቆም ብሎ ማስተዋል ይሻላል።

Read 740 times