Saturday, 10 March 2012 09:26

“የአዲስ አበባ ምስጢር ተጋለጠ”

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

በባሉን ለመብረር ቀጠሮ ስለነበረን ሁላችንም መንገደኞች ከጧቱ 12 ሰዓት በፊት ጃንሜዳ ደርሰን እየተጠባበቅን ነው፡፡ ጉዞውን የሚያመቻቹ ሌሎች ሰዎችም ነበሩ፡፡ አንድ ድንኳን ለመትከልና ለመንቀል የሚያስፈልገውን የሰው ኃይልና ያለውን ጫጫታ አንባቢ ያውቀዋል፡፡ ለንጽጽር ያህል 30 ሜ ቁመትና 20 ሜ ስፋት ያለውን ባሉን መሬት ላይ ዘርግቶ ለበረራ ማዘጋጀትና ሲያርፍ ደግሞ አጣጥሮ ወደ መያዣው ለመክተት ያለውን ሥራ አስቡት፤ ቀላል እንዳይመስላችሁ - ራሱን የቻለ ሥራ ነው፡፡

ባሉኑ ከተዘረጋጋ በኋላ ያለው ሥራ ቀላል ነው፤ አየር ማስገባትና ማሞቅ ነው፡፡ አየር በፋን (በአየር መሳብያ) በኃይል እየተገፋ ወደ ባሉኑ ይገባል፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ሥራ የጋዝ መንደኛው ነው - ኃይለኛ ነበልባል ወደ ባሉኑ ውስጥ ይረጫል፡፡ አየሩ ሲሞቅ ባሉኑ ከሬት መነሳት ጀመረ፡፡

ከመሬት ከፍ እያለ በሄደ ቁጥር የሚሰማውን የደስታ ስሜት በጣም ይማርካል፣ በጣም ደስ ይላል…ከማለት በስተቀር እንዲህ ነው ብሎ በቃላት ለመግለጽ ይከብዳል፡፡ ጃን ሜዳ ፊት ለፊት ያሉትን ቤቶችና ሕንፃዎች ጣራ እያየን ስድስት ኪሎን አለፍን፡፡ አፍንጮ በርን አቋርጠን ሰሜን ሆቴል እንዳለፍን ኢ/ር አሃዱ በዛ በስተግራችን የምናየው ዮሐንስ ቤተክርስቲያን መሆኑን ነገረን፡፡ ከዚያ ደግሞ አበበ ቢቂላ ስታዲየም፣ የት/ቤቶችን ሜዳ፣… እያየን ተጓዝን፡፡

መጀመሪያ አካባቢ ጐለተው ይታዩን የነበሩት ቤቶች፣ መንገዶች፣ እንስሳት ከፍ ባልን ቁጥር እያነሱና እየቀጨጩ ሄዱ፡፡ መንገዶች ግን በደንብ ይታያሉ፣ ይለያሉ፡፡ ዊንጌት አካባቢ፣ የጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተክርስቲያን የቀብር ስፍራ አልፈን ቀለበት መንገድ ስንደርስ ውበቱ በጣም ይማርካል፡፡ አዲሱን የአምቦ መንገድ እያየን ጉዟችንን ቀጠልን፡

ለማረፍ ስንቃረብ፣ ዝቅ እያለ በመምጣቱ፣ ሁሉም ነገር በግልጽ ማየት ጀመርን፡፡ ሕፃን የታቀፉ እናቶች፣ ወደ ት/ቤት የሚሄዱ ልጆች፣ አዋቂ ወንዶች…”ምን ጉድ ነው?” በማለት ወደ ላይ አንጋጠው ሲያዩ ባሉኑ ሰዎችን አሳፍሮ እየሄደ መሆኑን ሲረዱ፣ እጃቸውን ማውለብለብ ጀመሩ፡፡ እኛም አፀፋውን መለስን፡፡ ይበልጥ ዝቅ ስንል እየተሯሯጡ የሚጫወቱ ውሾች፣ የተጫኑ አህዮች፣…በደንብ ይታዩን ጀመር፡፡

የገፈርሳን ውሃ በስተግራ ትተን ትንሽ እንደተጓዝን የግድብ ቦይ የሚመስል ብዙ ደረጃዎች ያሉት፣ ውሃ ግን የማይወርድበት በሲሚንቶ የተሠራ ቦይ አየን፡፡ ከዚያ አለፍ እንዳልን ለአመል እንኳ የውሃ ጠብጣ የማይታይበት ረባዳ ስፍራ በደለል ተሞልቷል፡፡ በመሃሉ በአራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው የሚያምር ግንብ ቆሟል፡፡ ምንድነው በማለት ብጠይቅም ምላሽ አላገኘሁም፡፡ ያንን ስፍራ አልፈን ሜዳ ላይ አረፍን፡፡ ባሉኑን አይተው መጥተው ከከበቡን ልጆች መካከል አንዱን፣ ያረፍንበት ስፍራ ምን እንደሚባል ጠየኩት፡፡ “ለገዳዲ” አለኝ፡፡ አካባቢው ሁሉ ለገዳዲ ነው፤ የተለየ የቀበሌ ስም የለውም አልኩት፡፡ “ለገዳዲ ሦስት” በማለት አጭር መልስ ሰጠኝ፡፡

ባሉኑ ከማረፉ በፊት በደለል ተሞልቶ ያየሁበት ስፋራ ሦስተኛው የለገዳዲ ግድብ እንደበር ገመትኩ፡፡ የመልስ ጉዞ እንደጀመርን በአካባቢው የሚለማመዱ አትሌቶችን በርቱ እያልን አለፍን፡፡ ታላቁ አትሌት ኃይለ ገ/ሥላሴም በዚያ አካባቢ ይለማመዳል፡፡ ታዲያ በቅርቡ ባደረግነው ቃለ ምልልስ በአገሪቱ ስላለው የውሃ ችግር ሲናገር “የገፈርሳ ውሃ በጣም ቀንሷል፤ የአካባቢው ምንጮችም ደርቀዋል፡፡ ይኼ ለአዲስ አበባ በጣም አሳሳቢና አስጊ ችግር ነው” ነው ብሎ ነበር፡፡

ቀደም ሲል የነበረኝና አሁን አየር ላይ ሆኜ ያየሁትና ያገኘሁት ደስታ በጣም የተለያዩ ናቸው ያለው የአስጐብኚ ድርጅት ባልደረባው ፍሰሐ ታዬ ነው፡፡ “አነሳሳችንና የአዲስ አበባን መንገዶችና ሌሎችንም ነገሮች ቁልቁል ሳይ የተሰማኝን ስሜት እንጃ እንዴት እንደምገልፀው፤ በቃ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ በአራችን ብዙ ሰው ያላገኘውን ልምድ በማግኘቴ በጣም ዕድለኛ ነኝ፡፡ ሁላችንም እንደ አንድ ቤተሰብ ሆነን ጉዟችንን በሰላም በማጠናቀቃችንና ከአዳዲስ ሰዎች ጋር መልካም የትውውቅ ጊዜ ስለሆነኝ በጣም ደስ ብሎኛል” በማለት ደስታውን ገልጿል፡፡

“ከፍታ ላይ ሆኖ መብረት በጣም እንደሚያስደስት ነው ያየሁት” ያለችው ወጣቷ ወ/ሮ አስቴር፣ አየር ላይ ስትወጣ የመጀመሪያ ጊዜዋ ነው፡፡ ከላይ ሆና ከተማዋን ቁልቁል ስትመለከት ሁሉን ነገር ማየት በመቻሏ፣ ልዩ ስሜት እንዳደረባት ተናግራለች፡፡  የሚያስፈራ ወይም የሚናወጥ ነገር ይፈጠራል ብላ በመስጋቷ ለመቅረት ሁሉ አስባ ነበር፡፡ ነገር ግን “ፀጥታና ዝግ ያለ በጣም የሚያስደስት የተረጋጋ ጉዞ ነበር፡፡ በጣም ነው የወደድኩት፤ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ቀርቼ ቢሆን ኖሮ ይቆጨኝ ነበር” ብላለች አስቴር አየር ላይ ሆና ከተማዋን ቁልቁል ስታይ ያስገረማት ነገር አለ፡፡ “በጣም ያስደነቀኝ ነገር በጣም የሚያስደስቱና አዳዲስ የሚመስሉ ቤቶች፣ ከላይ ሆነህ ስትመለከታቸው በጣም አርጅተው የደከሙ፣ ሆነው ነው የምታያቸው፡፡ ይህ ሁሉ የመዲናችን ምሥጢር የተገለጠው ከፍ ብለን ከአናቷ በማየታችን ነው፡፡ ብቻ ሁሉም ነገር በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡” በማለት ተናግራለች፡፡

ለካራፍ ኮንስትራክሽን የሚሠራው ሚ/ር መሐመድ ሰይድ ግብፃዊ ነው፡፡ አዲስ አበባ መኖር ከጀመረ ሦስት ዓመት ስለሆነው ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ሚ/ር መሐመድ አዲስ አበባ መኖሩን ወዶታል፡፡ “ደስ ብሎኝ እየኖርኩ ነው፤ የሕዝቡ አቀባበል ወዳጃዊ ስለሆነ “አመሰግናለሁ” ብሏል በተኰላተፈ አማርኛ፡፡ “በአገሬ እንዲህ ዓይነት ድርጅቶች ብዙ ስላሉ አውቀዋለሁ፡፡ ነገር ግን እዚህ በማግኘቴ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ወድጄዋለሁ፡፡ በባሉን መብረር የሚፈጥረውን ስሜትና ደስታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መጋራት አለበት” ሲል ወዳጃዊ ምክሩን ለግሷል፡፡ ምሥራቅ መላከ ሕይወት ከእህቷ ከትዕግሥት ጋር በመሆን፣ ቶሮንቶ ገስት ሃውስ ከፍተው እየሠሩ ነው፡፡ ባሉን ሲንሳፈፍ ብዙ ጊዜ ማየቷን የምትናገረው ምሥራቅ፣ በባሉን ስትበር ግን የመጀመሪያ ጊዜዋ ነው፡፡ “አውሮፕላን ላይ ብዙ ጊዜ ከተማ ላይ በርሬአለሁ፡፡ ይኼኛውና የአውሮፕላን በረራ ብዙ ልዩነት አለው፡፡ አውሮፕላን ዝግ ሲሆን ይኼኛው ክፍት ነው፡፡ በተጓዝንበት መስመር ያሉትን የአዲሳባ መንደሮች በሙሉ በማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል፣ የተለየ ልምድም አግኝቻለሁ፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህን ልምድ ቢጋራ በጣም ደስ ይለኛል” ብላለች፡፡ አቶ አሸናፊ በዛ 15 ዓመት ሆላንድ ኖሮ ወደ አገሩ ከተመለሰ ሦስት ዓመቱ ነው፡፡ በግል ንግድ የሚተዳደረው አቶ አሸናፊ በፋይናንስ ኤም ቢ ኤ ዲግሪ ስላለው በትርፍ ጊዜው ያስተምራል፡፡ በባሉን ሲንሳፈፍ የመጀመሪያው ሲሆን አዲስ ልምድ በማግኘቱ መደሰቱን ተናግሯል፡፡ “በተለይ ባሉኑ ሲነሳና ሲያርፍ የሚሰጠው ስሜት በጣም ደስ ይላል፡፡ ከላይ ሆኖ ከተማዋን ወደ ታች ማየትም በጣም ደስ ይላል፡፡ እንደ አሞራ መብረር ስለሆነ ሁሉም ሰው ቢሞክረው ጥሩ ልምድ ያገኛል የሚል እምነት አለኝ” ብሏል፡፡

የበረርነው፣ ከባህር ወለል በላይ በ10ሺ ጫማ እንደሆነ የተናገረው ደግሞ የባሉኑ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር አሃዱ በዛ “”10ጫማ ከ3ሺ ኪ ሜ በላይ ነው፡፡ አዲስ አባ ከባህር ወለል በላይ ከሁለት ሺ ሜትር በላይ ስለሆነ እኛ ከመሬት ወደላይ የወጣነው ከ1000 እስከ 1500 ሜትር ይሆናል፡፡ አንድ ፎቅ 3 ሜትር ይረዝማል ብንል፣ ምን ያህል ፎቅ እንደወጣን መገመት ይቻላል፡፡ ለነገሩ የሲቪልአቪዬሽን ባለሥልጣን ከፊታችን አውሮፕላን እየመጣ ስለነበር ዝቅ ብላችሁ ብረሩ ስላለን ነው እንጂ ከዚህ በላይ መውጣት እንችል ነበር፡፡” ብሏል፡፡ባሉኑ እንዳረፈ፣ ሻምፓኝ ተቀዳና ለመንገደኞች ሁሉ ተሰጠን፡፡ ከዚያም ፓይሌቱ ትንሽ ገለባ በሁላችንም አናት ላይ አስቀምጦ፣ ትንሽ ሻምፓኝ በየተራ በራሳችን ላይ አፈሰሰ፡፡ ከዚያም ጉዟችንን በሰላም በማጠናቀቃችን ብርጭቆአችንን አንስተን “ቺርስ” በማለት ሻምፓኛችንን ጠጣን፤ ፎቶግራፍ ተነሳን ወደ ቢሮ ተመልሰን ደግሞ ቁርስ ተጋበዝን ሰርቲፊኬትም ተሰጠን፡፡ ለመሆኑ ይህ ባህል ከየት የመጣ ነው? በ1783 ዓ.ም በፈረንሳይ ሞንጐቪዬ የተባለ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፡፡ ልጆቹ አንድ ቀን እሳት አንድደው እየጠጡ ሲዝናኑ አንዲት ሴት በባህላዊ አለባበስ ተሽሞንሙና ወይን ታቀርብላቸው ነበር፡፡ ወንድማማቾቹ እየጠጡ ሳለ የሞቀ ባሉን የሚፈጥረውነ ተአምር ተገነዘቡ፡፡ ተአምሩ ቀላል ነበር፡፡ ባሉን ውስጥ ያለ አየር ሲሞቅ ባሉኑ መንሳፈፍ ጀመረ፡፡ ከዚያም ወንድማማቾቹ እየተለማመዱ ዘዴውን በሚገባ አወቁት፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ ነገር በመሆኑ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ስለማይታወቅ ሊበሩበት አልደፈሩም፡፡ ከዚያም እንስሳት በባሉን ልከው ምንም ሳይሆኑ በሰላምታ መሬት ላይ አረፉ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ በሰው ለመሞከር ከታዋቂው የፓሪስ ወህኒ ቤት ሁለት እስረኞች መረጡ፡፡ በወቅቱ የነበረው ንጉሥ ግን እስረኞቹን ትቶ ሁለት መኳንንቶች እንዲሞክሩት አዘዘ፡፡ ባለኑ ሙቀት የተሰጠው በጠመንጃ ባሩድ ሲሆን፣ ሰዎቹም ምንም እውቀትና ልምድ አልነበራቸውም፡፡ በዚህ የተነሳ ባሉኑ ከፍና ዝቅ እያለ ቆይቶ ሲወርድ ከመሬት ቢጋጭም ሰዎቹ የከፋ ጉዳይ ሳይደርስባቸው ተረፉ፡፡ የሰዎቹን መትረፍ ምክንያት በማድረግ ባህላዊ የሻምፓኝ ግብዣ ሥነ ሥርዓት ተደረገ፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ ያንን ሥነ-ሥርዓት ለመዘከር ምንጊዜም ባሉን ካረፈ በኋላ ባህላዊ የሻምፓኝ ግብዣ እንደሚደረግ የባሉኑ ፓይሌትና የድርጅቱ ሸሪክ ሚ/ር ብራም አስረዳን፡፡

 

 

 

Read 3893 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 09:31