Saturday, 25 May 2024 00:00

የፋይናንስ ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያግዝ ዲጂታል ፕላትፎርም ስራ ጀመረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በኢትዮጵያ ለሚገኘው የፋይናንስ ዘርፍ አጠቃላይ የመረጃና  ምልከታ ያለምንም ከፍያ የሚሰጥ  የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ፕላትፎርም ተከፈተ።
ፕላትፎርሙ የተጠቃሚዎችን  አቅም በማሳደግ  በኢትዮጵያ የፋይናንስ  ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በተቀናጀ ሚዲያ፣ መረጃ አቅርቦትና ትንተና እንዲሁም ማማከር አገልግሎት ላይ በተሰማራው  ሸጋ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት  የበለፀገው ፕላትፎርም፤  በዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ላይ ሰዎች ያላቸውን መተማመን በመገንባት፣ የፋይናንስ ተካታችነትን ለማሻሻል ያለመ ነው ተብሏል።
ከፍተኛ  የመንግሥት  የሥራ ኃላፊዎች፣ የአገር ውስጥና ዓለም እቀፍ የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት  በተከናወነው የፕላትፎርሙ ማብሰሪያ ሥነ ሥርዐት ላይ  እንደተገለጸው፤ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት የኢትዮጵያ ማዕከል መከፈት በተሻለ መጠን መረጃ መር ውሳኔ ሰጪነትን ለማቀላጠፍ፣ እንዲሁም በገጠርና አገልግሎቱ ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች የፋይናንስ ተካታችነትን በጥልቀት ለመደገፍ  ያስችላል ተብሏል።
ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂንና ጥራቱን የጠበቀ መረጃና ይዘትን በመጠቀም፣ ፕላትፎርሙ ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶችን የምናይበትንና የምንጠቀምበትን መንገድ እንደ አዲስ ለማቅረብ ቆርጦ የተነሣ  እንደሆነም ተገልጿል።
የሸጋ ኢንሳይትስ (Shega Insights) ማናጀር የሆኑት አቶ ናትናኤል ጸጋው፣ “የፋይናንስ ተደራሽነትና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በኢትዮጵያ እንዲለመዱ ለማገዝ ያለንን ቁርጠኝነት ማሳያ የሆነውን ይህንን ፕላትፎርም ይዘን በመምጣታችን ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል” ሲሉ በሥነ ሥርዐቱ ላይ ተናግረዋል። በተጨማሪም፣ ይህ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት የኢትዮጵያ ፕላትፎርም፣ ያለሟቋረጥ የሚለዋወጠውን የዲጂታል ፋይናንስ ዓለም ተጠቃሚዎች ያለ ስጋት እንዲዳስሱና እንዲጠቀሙ የሚያስችል ነው በማለት ገልጸዋል።
የአዲሱ ፕላትፎርም ዋንኛ  አላማ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምልከታዎች: በድርጅቱ ባለሙያዎች የተዘጋጁ ኦርጂናል አጫጭር ጽሑፎች፡ የተዛማጅ ነባራዊ ሁኔታ ጥናቶች (case studies) እንዲሁም ሪፖርቶችን በማቅረብና ዘርፉ ውስጥ ለሚገኙ ባለ ድርሻ አካላት የአገሪቱን ሁኔታ ያገናዘቡ መረጃዎችን  በመስጠት የኢትዮጵያን ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በውል እንዲረዱ ማስቻል   ሲሆን  ፕላትፎርሙ   ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ያላቸውና የተመረጡ የዜና ዘገባዎችን፣ ሪፖርቶችን፡ ምዘናዎችን እንዲሁም የኢትዮጵያ ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን የሚያብራሩ ልዩ ልዩ ግብዓቶችን አጠቃልሎ የያዘ በቀላሉ ተደራሽ የሆነ የመረጃ ምንጭ እንደሆነም ተገልጿል ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በ2025 እ.ኤ.አ ከአገሪቱ አዋቂ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሕዝብ 70 ከመቶው የፋይናንስ አገልግሎት ውስጥ ተካታች እንዲሆን፣ እንዲሁም ከፍያዎችን ለመፈጸምና ለመገበያየት ዲጂታል አካውንት አዘውትሮ እንዲጠቀም ግብ ሰንቋል። ለዚህ ግብ መሳካት ይህ ፕሮጀክት  ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

Read 1625 times