Tuesday, 28 May 2024 16:03

ሙጭሊት (አጭር ልብወለድ)

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ምንጩን ተከትሎ የሚጓዘው አረንጓዴ ውሃ ፣ በጠፍጣፋ ቡናማ ድንጋዮች ዙሪያ ትናንሽ የኳስ  አረፋዎች እየፈጠረ በጸጥታ ይፈስሳል። በወንዙ ዳርቻ የበቀሉትና ትካዜ ያጠላባቸው የሚመስሉት ዛፎች በውሃ ውስጥ ነጸብራቃቸው ይስተዋላል። ማርኒ ሳሩ ላይ ተቀምጣ ወደ ኩሬው ድንጋይ ትወረውራለች። ከዚያም እየሰፉ የሚመጡትን ክቦችና በጭቃማው የኩሬው ዳርቻ የሚፈጠሩትን ትንንሽ ሞገዶች ታስተውላለች። ማርኒ ስለ ሙጭሊቶቿ (የድመት ግልገሎቿ) እያሰበች ነበር። ባለፈው አመት ስለተወለዱት ሙጭሊቶች ሳይሆን በዚህ ዓመት ስለተወለዱት ሙጭሊቶች  ነበር  የምታስበው። እናቲቱ ድመት - ፒንኪ የዛሬ ዓመት የወለደቻቸው ሙጭሊቶች  ወደ ሰማይ ቤት መሄዳቸውን  ለማርኒ የነገሯት ወላጆቿ ነበሩ፡፡  አዲስ የተወለዱትን ድመቶች ሳትጠግባቸው ነበር ያጣቻቸው፡፡ ሙጭሊቶቹን ከሦስት ቀን በላይ ለማየት አልታደለችም።
“እግዚአብሔር በገነት አብረውት እንዲኖሩ ወስዷቸዋል።” ነበር ያሏት አባቷ።
ማርኒ አባቷ ያሏትን  ልትጠራጠር አትችልም፡፡ አባቷ ሃይማኖተኛ ናቸው። የእግዚአብሔር አገልጋይ፡፡ ሰንበት ት/ቤት በየሳምንቱ ያስተምራሉ። በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥም ትልቅ ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። ከምእመናኑ የተሰበሰበውን ገንዘብ እየቆጠሩ በአንድ ትንሽ ቀይ መዝገብ ላይ ያሰፍራሉ። በአዘቦት  ቀናትም እንዲሰብኩ ተመርጠዋል። ማታ ማታ ለቤተሰባቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ምዕራፍ ያነባሉ። ማርኒ ባለፈው ምሽት ለንባብ ፕሮግራሙ በሰዓቱ ባለመድረሷ ከአባቷ ዋጋዋን አግኝታለች። አባቷ “ልጅ ካልተቀጣ መረን ይለቃል” የሚሉት ፈሊጥ አላቸው። እናም ማርኒ አባቷን በፍፁም ልትጠራጠር አትችልም። ለእሷ፤ስለ ሙጭሊቶቹና ስለ እግዚአብሔር የሚያውቅ ፍጡር ካለ እሳቸው ብቻ ናቸው፤ አባቷ።
ሆኖም ማርኒ ለብዙ ጊዜያት ድንገት ስለተሰወሩት ሙጭሊቶች እያሰበች መገረሟና ግራ መጋባቷ አልቀረም፡፡ በዓለም ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የድመት ግልገሎች እያሉ እግዚአብሔር ለምን አራቱንም የእርሷን ሙጭሊቶች ለመውሰድ መረጠ?  እግዚአብሔር ይህን ያህል ራስ ወዳድ ነው እንዴ?
ባለፉት አሥራ ሁለት ወራት ግን ስለ ሙጭሊቶቹ እንዳታስብ የሚያደርጓት በርካታ ጉዳዮች ተከናውነዋል። ትምህርት ቤት የገባችበት የመጀመሪያ ዓመቷ ነበር። ለመጀመሪያው የትምህርት ቀን ስትሰናዳም ሆዷን ባር ባር ብሏታል - ትንሽ ተሸብራ ነበር፡፡ ደብተር፣ እርሳስና መጽሐፍት መገዛት ነበረባቸው። በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ትምህርቱን ወድዳው ነበር። ከፊደላትና ቁጥሮች ጋር ያደረገችው የመጀመሪያ ትውውቅ አስደስቷታል። ውሎ አድሮ ግን ማርኒ ትምህርት እየሰለቻት ሲመጣ፣ የገና በዓል በአንፀባራቂ የበረዶ ብናኞች ታጅቦ ከተፍ አለ። የገና ስጦታ ሸመታው፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰማያዊ መብራቶቹ፣ ወዲህና ወዲያ እየተንገዳገዱ ከአንዱ ጥግ የቆሙት  የገና አባት፣ እንዲሁም በዋዜማው የሚከናወነው የቤተ ክርስቲያን የሻማ ስነ-ስርዓት፡- እነዚህ ሁሉ ክንዋኔዎች ማርኒ ስለ ሙጭሊቶቹ እንዳታስብ አድርገዋት ነበር።
በመጋቢት ወር፤ ጎላ ያሉ እንቅስቃሴዎች እየተዳከሙ ሲመጡ፣ የማርኒ እናት መንታ ህፃናትን ወለደች። ማርኒ መንትዮቹ መጀመሪያ ላይ እንዴት ትንንሽ እንደነበሩና ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ግን እንዴት በቀስታ እያደጉ እንደመጡ አስተውላ ተገረመች። በሰኔ ወር ላይ መንትዮቹ ሦስት ወር ሆኗቸው ነበር። በዚህ ወቅት ህፃናቱ በደንብ አድገዋል። የማርኒ ትምህርት ቤት ተዘግቷል። የገና በዓልም ተመልሶ የማይመጣ በሚመስል ሁኔታ ካለፈ ረዥም  ጊዜ አስቆጥሯል። ሁሉም ነገር ለማርኒ አሰልቺ መሆን ጀምሯል። በዚህ ወቅት ነበር ማርኒ ድንገት ያልጠበቀችውን ዜና የሰማችው፡፡ ፒንኪ ሌሎች ትንንሽ ድመቶችን በቅርቡ ትወልዳለች ተባለ፡፡ ይህን ዜና አባቷ ለእናቷ ሲነግሩ የሰማች ዕለት ደስታዋን መቆጣጠር አልቻለችም ነበር። ወዲያው ነበር አዳዲስ ለሚወለዱት ድመቶች ቁርጥራጭ ጨርቆችና የጥጥ ልብሶች ማዘጋጀት የጀመረችው፡፡ የሚተኙበትም ሳጥን አዘጋጀችላቸው፡፡
ሁሉም ነገር ተፈጥሮአዊ ሂደቱን ጠብቆ በመጓዝ ላይ ነበር፡፡ አንድ ምሽት ላይ  ፒንኪ ወደ በረቱ ተደብቃ በመሄድ ስድስት የድመት ግልገሎችን ተገላገለች።  ግልገሎቹ ግራጫና በችኮላ የተረጨ የሚመስል ጥቁር ነጠብጣ ቀለም ያለባቸው ናቸው፡፡ ማርኒ ግልገሎቹን ከመጠን በላይ ወደደቻቸው፡፡ ሆኖም እጅግ ፈርታና ስጋት ገብቷት  ነበር። እግዚአብሔር እንዳለፈው ዓመት ቢወስዳቸውስ ?
“ማርኒ! ምን እየሰራሽ ነው?”
ወደ ኋላዋ ዞራ መመልከት አልነበረባትም። ማን እንደሆነ አውቃለች- አክብሮቷን ለማሳየት ግን ዞር አለች፡፡ ከአባቷ የተቆጣ ፊት ጋር ነበር የተፋጠጠችው፡፡
“ድንጋይ እየወረወርኩኝ እየተጫወትኩ ነው” ስትል ማርኒ በቀስታ መለሰች።
“ዓሳዎቹ ላይ?”
“አይደለም አባዬ። ዝም ብዬ ነው የምወረውረው”
“ከሀይማኖት ትምህርታችን የድንጋይ ውርወራ ሰለባ ማን እንደነበር እናስታውሳለን አይደል?” አሉ አባቷ የአዋቂነት ፈገግታ በፊታቸው ላይ እየተነበበ።
“ቅዱስ እስጢፋኖስ” አለች ማርኒ።
“በጣም ጥሩ” አሉ አባቷ፤ ፈገግታቸው ከፊታቸው ላይ እየጠፋ።
ወዲያው፤ “እራት ደርሷል” አሏት።
ማርኒ በአሮጌው ቡናማ ደረቅ የብረት ወንበር ላይ ተቀመጠች። አባቷ በጥቁር ቆዳ የተለበጠውን የቤተሰቡን የድሮ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነቡ በጥሞና የምትከታተል ትመስላለች። መጽሐፍ ቅዱሱ የተላላጠና በርካታ ገጾቹም የተቀዳደዱ ናቸው፡፡ እናቷ ከአባቷ ጎን እጆቿን ጭኖቿ ላይ አደራርባ ተቀምጣለች። “አምላክ እንዴት ጥሩ ነገር ቸሮናል” የሚል ፈገግታ ተፈጥሮአዊ ውበት በተቸረው ፊቷ ላይ ይነበብ ነበር።
“ህፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግስት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና” ብለው ንባባቸውን ጨረሱና በዝግታ መጽሐፍ ቅዱሱን አጠፉት። ለብዙ ደቂቃዎች ማንም ምንም ነገር ሳይተነፍስ በዝምታ  ቆየ።
“ማርኒ፤ የትኛውን መጽሐፍና የትኛውን ምዕራፍ ነው አሁን ያነበብነው?”
“ቅዱስ ማርቆስ፤ ምዕራፍ አስር” አለች ማርኒ፤ በቅንነት በተቃኘ ድምጸት፡፡
“ደህና!” አሉ አባቷ።
የማርኒ እናት፤ “የክርስቲያን ቤተሰብ ማድረግ ያለበትን ተግባር ነው የፈጸምነው።” የሚል ፈገግታ በፊታቸው ላይ ይስተዋላል።
“ሜሪ፤ ለእኛ ቡና፣ ለማርኒ ደግሞ አንድ ብርጭቆ ወተት ብታዘጋጂስ?” አሉ የማርኒ አባት ሚስታቸውን።
“እሺ!” አሉ እናቷ  ከተቀመጡበት ተነስተው ወደ ወጥ ቤት እየተራመዱ።
የማርኒ አባት አሮጌውን መጽሐፍ ቅዱስ እያገላበጡ ይመረምሩታል። የተቀዳደደውን ገጾች በጣታቸው ይደባብሱታል። ከቢሊዮን ዓመት በፊት የኖሩት ዘር ማንዘሮቻቸው ድንገት በመጽሐፍ ቅዱሱ ገጾች ላይ ያፈሰሱትን የወይን ጠጅ በአትኩሮት እየተመለከቱ ነበር።
“አባዬ” አለች ማርኒ፤ በተጣደፈ ቅላጼ፡፡ ከመጽሐፉ ላይ ቀና ብለው ተመለከቷት። በፊታቸው ላይ ቁጣም ሆነ ፈገግታ አይስተዋልም።
“የድመቷ ልጆችስ?”
“እነርሱ?” አባቷ በሆዳቸው ነገር የያዙ ይመስላሉ።
“አሁንም እግዚአብሔር ይወስዳቸዋል?” ጠየቀች  ማርኒ።
“ምናልባት” አሉ አባት። ከዚህ ሌላ ምንም መናገር  አልቻሉም።
“አይችልም! አይወስዳቸውም!” ማርኒ ማልቀስ ጀመረች።
“እሜቴ! እግዚአብሄር ማድረግ የሚችለውና ማድረግ የማይችለውን ነገር አለ እያልሽ ነው እንዴ?” አሉ አባቷ።
“አይደለም አባዬ” አለች ማርኒ።
“እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ያደርጋል!” አሉ አባቷ።
“አዎ እሱማ ያደርጋል” አለች በተቀመጠችበት እየተቁነጠነጠች። “ግን ለምን የእኔን ትንንሽ ድመቶች በድጋሚ ይወስዳል? ሁልጊዜ ለምን የእኔን ብቻ?”
“እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ይብቃ። አሁን ፀጥ በይ ማርኒ!” አሉ አባቷ፤ በቁጣ።
“ግን ለምን የእኔን?” ማርኒ ጥያቄዋን ቀጠለች።
አባቷ ድንገት ከተቀመጡበት እመር ብለው ተነሱና ወንበሩን ተሻግረው ወደ እርሷ አለፉ። ያንን ድምቡሽቡሽ የልጅ ፊቷን በጥፊ አጮሉት!! ደም ከከንፈሯ ጠርዝ ላይ በቀጭኑ መፍሰስ ጀመረ። በእጇ መዳፍ ደሟን ጠራረገች።
“ስለ እግዚአብሔር ለመጠየቅ አንቺ ገና ልጅ ነሽ”  ምራቃቸው ከንፈራቸው ላይ ተዝረክርኮ ነበር።
ክንዷን በእጃቸው አንጠልጥለው ከተቀመጠችበት አስነሷት። “አሁን ፎቁ ላይ ውጪና ቶሎ ወደ መኝታ!” አሏት በቁጣ።
ማርኒ ለመከራከር አልዳዳትም፡፡ እንደገና መፍሰስ የጀመረውን ደሟን እየጠራረገች ደረጃውን መውጣት ጀመረች። ደረጃውን ስትወጣ የእንጨት መደገፊያውን በእጆቿ እያሻሸች በእርጋታ ነበር የምትራመደው።
“ወተቱ ይኸው” ብላ እናቷ ስትናገር ማርኒ ሰማቻት።
“አያስፈልግም!” አባትየው ቁርጥ ያለ መልስ ሰጡ።
ማርኒ ከፊል ብርሃን የተላበሰው ክፍሏ ውስጥ አልጋዋ ላይ ተጋድማ ነበር። በመስኮቱ የሚገባው ብርቱካናማ ቀለም ያለው የጨረቃዋ ብርሀን፣ ግድግዳው ላይ በተሰቀሉት ሃይማኖታዊ ሥዕሎች ላይ እያንፀባረቀ ክፍሉን ከድቅድቅ ጭለማ ነፃ አውጥቶታል። ወላጆቿ መኝታ ክፍል ውስጥ እናቷ ከመንትዮቹ ጋር የምታወራ ይመስል እያጉተመተመች፣ የሽንት ጨርቃቸውን እየቀየረችላቸው ነበር። “የእግዚአብሔር ትንንሽ መላዕክት” አለች እናቷ፡፡ አባቷ ህጻናቱን እየኮረኮሩ ያስቋቸዋል፡፡ ማርኒ፤ “መላእክቱ“ ሲስቁ እየሰማች ነው። ከወፍራም ጎሮሯቸው እየተንደቀደቀ የሚወጣውን ጥልቅ ሳቅ እያዳመጠች ነበር፡፡
በዚህ ምሽት አባቷም ሆኑ እናቷ ደህና እደሪ አላልዋትም። እንደውም ከነአካቴው ወደ መኝታ ቤቷ ድርሽ ያለ ሰው አልነበረም። ማርኒ ቅጣት ላይ ናት።
 በበረቱ ውስጥ ከግልገል ድመቶቹ ጋር ጨዋታ ይዛለች፤ ማርኒ፡፡ ከአስር ደቂቃ በፊት እናቷ የላከቻትን መልዕክት ሳታደርስ እዚሁ በረት ውስጥ አንዷን ግራጫ ድመት እያጫወተች ነው፡፡ የድርቆሹ ሽታ አየሩን በሙሉ አውዶታል። አገዳዎቹ ወለሉን በሙሉ ስለሸፈኑት እግር ያደናቅፋሉ። ሁለቱ ላሞች እግራቸው በሽቦ በመቁሰሉ እንዲያገግሙ ግንቡ መጨረሻ ላይ ነው የታሰሩት፡፡ ትንንሾቹ ድመቶች ከማርኒ አገጭ ስር ያለውን አየር በፊት መዳፎቻቸው እየዳሰሱ ይጮሃሉ።
“ማርኒ የት ነች?” ከቤቱና ከበረቱ መካከል ቆመው አባቷ አምባረቁ፡፡
ቤት ውስጥ የእናቷን ጥሪ ስትሰማ ማርኒ መልስ ለመስጠት ከጅላ ነበር።
“የሄለንን የምግብ ሙያ መጽሐፍ እንድታመጣ ብራውን ጋ ልኬያታለሁ። ከሄደች ሃያ ደቂቃ ሆኗታል።” አለች እናቷ።
“ብዙ ሰዓት አለፈኮ”  አሉ አባቷ። አባቷ በአቧራማው መሬት ላይ ሲራመዱ የትልቁ ጫማቸው ኮቴ ወታደራዊ ምት ያስተጋባል።
አንድ ችግር እንዳለ ማርኒ አውቃለች። ማየት የሌለባት ነገር ሊፈጸም መቃረቡን ተረድታለች። የድመት ግልገሎቹን ወደ ቀዩ ወርቃማ ሳጥናቸው ከተተቻቸውና ሁኔታውን ተደብቃ ለመመልከት ወደ አገዳው ክምር እየዳኸች ሄደች።
አባቷ ወደ በረቱ ውስጥ ገቡና ከቧንቧው ውሃ በባልዲ ሞልተው ትንንሽ ድመቶቹ ፊት ለፊት አስቀመጡ። እናትየዋ ድመት ፒንኪ “እስ” ብላ የቁጣ ድምጽ አሰማችና፣ ጀርባዋ ላይ ጉብታ ፈጠረች። አባቷ ፒንኪን በእጃቸው አንስተው ባዶ ገረወይና ውስጥ ዘጉባት። ከፒንኪ የወጣው አሰቃቂ ቁጣና ጩኸት ቦታውን የአሜሪካ የእርሻ ስፍራ ሳይሆን፣ የአፍሪካ የእንስሳት መጋለቢያ ሜዳ አስመስሎት ነበር።
ማርኒ በሁኔታው በሳቅ ፈረሰች። ሆኖም የአባቷን በሥፍራው መኖር አሰበችና ሳቋን ወዲያው ገታች።
አባቷ የድመት ግልገሎቹ ወደ ተቀመጡበት ሳጥን ዞረው ተመለከቱ። አንዷን  ግልገል በጥንቃቄ ማጅራቷን ይዘው ከሳጥኑ ውስጥ አወጧት። አሸት አሸት አደረጓትና የባልዲው ውሃ ውስጥ በጭንቅላቷ ደፈቋት። ግልገሏ ድመት ባልዲው ውስጥ በስቃይ ስትንፈራፈር ይሰማ ነበር፤ የውሃ ፍንጥቅጣቂዎችም አየሩ ላይ ሲፈናጠሩ ይስተዋላል። የማርኒ አባት ፊታቸውን አጨፍግገው ግልገሏን ሙሉ በሙሉ ወደ ውሃው ውስጥ ጨመሯት። ደፈቋት! ወዲያው ግልገሏ መንፈራገጡን አቆመች። ማርኒ በፍርሃት የሲሚንቶውን ወለል በጣቶቿ እየቧጠጠች ነበር። በዚህም  ሳቢያ ጣቶቿ ክፉኛ ቆሰሉ፡፡
ግን ለምን? ለምን? ለምን? ለምን?
ወዲያው አባቷ ከባልዲው ውስጥ የተዝለፈለፈውን የግልገሏን በድን አወጡት፡፡ ደም የመሰለ ነገር ከድመትዋ  አፍ ላይ ተዝለግልጎ ይታያል፡፡ ምላሷ ይሁን አንጀቷ፤ ማርኒ አላወቀችም።
የማርኒ አባት ስድስት በድን የፀጉር ኳሶች የመሰሉ ነገሮች ማዳበሪያ ከረጢት ውስጥ ጨመሩ። ስድስቱም ግልገሎች ከመቅጽበት ተጠናቀቁ። በመጨረሻም፣ እናትየዋን ከገረወይናው ውስጥ አወጧት። ፒንኪ እየተንቀጠቀጠች ነበር፡፡ በደከመ ድምጽ “ሚያው” ብላ እየጮኸች ሰውየውን ተከተለቻቸው። ሰውየው ዞር ብለው ሲመለከቷት “እስ!” እያለች ቁጣዋን ታሰማለች፡፡
ማርኒ ለረዥም ሰዓት ሳትንቀሳቀስ ባለችበት ተቀምጣ ቆየች፡፡ ስለሌላ ስለምንም ጉዳይ እያሰበች አልነበረም። ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ስለተፈጸመው አሰቃቂ የሞት ፍርድ እያሰበች ነበር። በትናንሽ ድመቶቹ  ላይ ተግባራዊ ስለሆነው የሞት ፍርድ!! ጠቅላላ ሁኔታውን ለመረዳት የተቻላትን ሁሉ ሙከራ አደረገች። አባቷን የላከው እግዚአብሔር ነው? ግልገሎቿን እንዲገድል የነገረውስ እርሱ ነው? ግልገሎቿን ከእሷ እንዲቀማ ያዘዘው እግዚአብሔር ነው? እውነት እግዚአብሔር ከሆነ ዳግመኛ ከመንፈሳዊው ፊት ቀርባ ቁርባን አትቆርብም፡፡ ከሲሚንቶ ጋር የተቀላቀለ ደም ከጣቶቿ ላይ እየተንጠባጠቡ ከተቀመጠችበት ተነስታ ወደ ቤት ውስጥ ገባች።
“የምግብ አሰራር ሙያ መጽሐፉን አመጣሽ?” ጠየቀቻት እናቷ፤ ማርኒ የወጥ ቤቱን በር ዘግታ ስትገባ። “ሚስ ብራውን አላገኘችውም። ነገ እልከዋለሁ ብላለች።” ውሸቷ ራሷን ማርኒን አስገርሟታል።
“ሙጭሊቶቼን  እግዚአብሔር ወሰደብኝ!” ብላ  ድንገት ማርኒ ጮኸች። እናቷ የተደናገረች ትመስል ነበር። “አዎ” ብቻ ነበር መልሷ፡፡
“እግዚአብሔርን እበቀለዋለሁ!! እርሱ እንዲህ ሊያደርግ አይችልም! አይችልም!” እያለች ከወጥ ቤቱ ተስፈንጥራ ወጥታ የፎቁን ደረጃ መውጣት ጀመረች።
እናቷ ቆማ እየተመለከተቻት ቢሆንም፣ እንቅስቃሴዋን ግን  መግታት አልቻለችም።
ማርኒ ኮውፊልድ ደረጃውን ስትወጣ በዝግታ  እየተራመደችና ለስላሳውን የእንጨት መደገፍያ በእጇ እየታከከች ነበር።
ቀትር ላይ ዋልተር ኮውፊልድ ከእርሻ ቦታ ሲመጡ፣ የሳህንና የብርጭቆ ኳኳታ ከዋናው ቤት ሰሙ፡፡ በፍጥነት ወደ ሳሎኑ  አመሩ፡፡ ደረጃው ስር ሚስታቸውን ወድቃ አገኟት። ጠረጴዛው ተገለባብጧል። እቃዎች  ተበታትነዋል፡፡ ሳህኖች ተሰባብረዋል።
“ሜሪ! ሜሪ! ተጎዳሽ?” አሉ ዋልተር፤ በፍጥነት ወደ ሚስታቸው ጎንበስ ብለው።
የማርኒ እናት ዓይኖቿ በእንባ ጭጋግ ተሸፍነው “ዋልት! የፈጣሪ ያለ! ዋልት- ውድ መላዕክቶቻችን- ገንዳ ውስጥ -አዎ! ውድ መላእክቶቻችን!!!” አለች የእንባዋ ጎርፍ በፊቷ ላይ እየፈሰሰ።




Read 783 times