Saturday, 01 June 2024 20:48

ብርሀነ መስቀል ረዳ፤ በኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ሲታወስ

Written by  ደረጄ ጥጉ (የአለም አቀፍ ህግ መምህር)
Rate this item
(3 votes)

ልጅነትና እድገት
ብርሀነ መስቀል ረዳ መስከረም 18 ቀን 1936 ዓ.ም በድሮው አጠራር በትግራይ ጠቅላይ ግዛት፤ በአክሱም አውራጃ፤ በብዘት ወረዳ ተወለደ፡፡ አንድም ወንድ እንደ ብርቅ ሲጠበቅበት ከነበረ ቤተሰብ ውስጥ በመወለዱ፤ሁለትም ቤተሰቡም ወንድ በመጠበቅ ሀዘን ላይ ወድቆ የነበረ በመሆኑ፤ ሦስትም ውልደቱ በመስቀል ቀን ስለነበር ብርሀነ መስቀል የሚለው ስም ወጣለት፡፡ ባለቤቱ ታደለች ኀ/ሚካኤል በ”ዳኛው ማነው?”  መፅሐፍ ላይ እንዳሰፈረችው፤ በእናቱና አባቱ እቅፍ የመታቀፍ በረከትን ብዙም ሳያጣጥም ገና በህፃንነቱ አያቱ ቀኛዝማች ረዳ ከቤተሰቡ በአደራ ተረክበው፣ እሳቸው ጋር ደሴ ወስደው አሳደጉት፡፡ አያቱ በጊዜው የደሴ ከፍተኛ ፍርድቤት ዳኛ ነበሩ፡፡
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በደሴ አካለወልድ ት/ቤት ጀምሮ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ዝነኛ የተማሪ ንቅናቄ መሪዎችን ባፈራው በአንጋፋው ወ/ሮ ስሂን ተከታተለ፡፡ አያቱ ቀኛዝማች ረዳ የደሴ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ስለነበሩ እቤታቸው ለአቤቱታ የሚመጡ ገበሬዎችን እሮሮና የሚደርስባቸውን በደል ብርሀነ በቅርብ ይከታተል ነበር፡፡ በአያቱ ስር ሆኖ ገበሬዎች የሚያቀርቡትን አቤቱታ ጉዳዬ ብሎ በመከታተል የገበሬውን ብሶት፤ እሮሮና ያለባቸውን ችግር ቀጥተኛ ባለጉዳይ ሆኖ በህሊናው መዘገበው፡፡ በፖለቲካ ህይወቱና ብርሀነ በኋላ ባነሳሳው የተማሪዎች ትግል ላይ በጎ ተፅእኖውን ያሳደረውን አያ ሙሄ የተባለውን ደሀ ገበሬ የተዋወቀው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ የልጅነት እድሜው ነው የወደፊቱን የትግል ሀሳቡን የወጠነለትን መሬት ላራሹ የሚለውን ሀሳብ እንዲቀምር ምክንያት የሆነውን አያ ሙሄ የተዋወቀው፡፡ አያ ሙሄ የኢትዮጵያ ገበሬዎች ህይወት ምን እንደሚመስል በተግባር ያሳየው እንደነበር ብርሀነ እንደነገራት ታደለች ኀ/ሚካኤል በመፅሐፏ ላይ ገልፃለች፡፡


በታደለች ኀ/ሚካኤል መፅሐፍ ላይ እንደሰፈረው፤ በአያቱ ትእዛዝ በጨፋ እና ቃሉ ከሚገኘው የአያቱ መሬት በገበሬዎች ተጭኖ የሚመጣውን እህል እየመዘገበ የሚረከበው ብርሀነ ስለነበር ብዙ ጊዜ ከገበሬዎችና ጭሰኞች ጋር ለመቀራረብና ልብ ለልብ ለማውራት ቻለ፡፡ ከሁሉም ከልቡ እንዳይወጣ ሆኖ የቀረው ከላይ የጠቀስነው አያ ሙሄ ነበር፡፡ ብርሀነ በታደለች ብእር በኩል ከአያ ሙሄ ጋር የነበረውን ግኝኙነት ሲነግረን እንዲህ ይላል፤ “ሰውየው ሲመጣ በጣም ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ጨዋታውን ሲጀምር ተሜ ታድያስ ወረቀቱ ምን አለ ይለኛል?” የህይወቱን አቀበትና ቁልቁለት እያዋዛ ፤ አንዳንዴም ልብን በሚሰረስር ሀዘን ቀብቶ አስከፊውን የህይወቱን መልክ ይነግረዋል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ገበሬዎችን አሰከፊ የህይወት ገፅታ በዚህ ሰው የህይወት መነፅር መነሻነት ተመለከተው፡፡ የገበሬው ህይወት ምን እንደሚመስል በተግባር ተረዳ፡፡ ገበሬው በጉልበቱ መገበሩና ማረሱ ሳያንሰው ካመረተው የማይጠቀምበት አስከፊና ሰብእናን የሚያጎድፍ አኗኗር ነበር የሚገፋው፡፡


በአንድ የህይወት አጋጣሚ አያ ሙሄ ያጫወተው መራር እውነት እድሜ ዘመኑን የተሸከመውንና የታገለለትን አላማ  አስታቀፈው፡፡ አያ ሙሄ እንደ ልማዱ እህል ገቢ ሊያደርግ በመጣበት ብርሀነ ይሆናል ብሎ ያልጠበቀውን አያ ሙሄ አረዳው፡፡ ሚስቱ ወልዳ በተኛችበት የሚያቀምሳት እህል ሳያስቀር ይዞ መጥቶ፤ “ከሚስቴ አፍ ነጥቄ ነው ያመጣሁት” አለው፡፡ ታደለች ስትተርክልን፤ “ፊቱን ለወትሮ ሳየው ቀይና  አፍንጫው ግትር ያለ ቢሆንም ፀሀይ አቃጥሎት የተለበለበ ቀይ ሸክላ ነው የሚመስለው፡፡ ይልቁን ግንባሩ ላይ የሚውተረተሩት ስሮች ሁሌም ድካሙን ያሳብቁበታል፡፡ የዚያን እለት ግን ፊቱም ወዘናውም ፈካ ብሏል፡፡ “እንዲያው ቅር እያለኝ ነው አጃውን ከአፏ ነጥቄ--” ብርሀነ ለምን እንደማያስቀር ሲጠይቀው፡-  “የእኩል አራሽ አይደለሁ ወይ የሲሶ ምን ብዬ ነው የማስቀር? መቼም ሌላ ሌላውን እህል ለምግባችን ያህል የምናስቀረውን እናስቀራለን፤ ግን በትናንሽ ማሳ ላይ የምናርሰውን ምስሩንም ሆነ ተልባውን፣ አጃና ሌላውን ያው ለባለመሬቱ በፍላጎቱ መጠን እናርሳለን፡፡ አይ ተሜ ለጌቶች የተመረተውማ አይቀርም፤ ማስረክብ አለብኝ”፡፡ ይሄ አጋጣሚ ብርሀነን እድሜ ዘመኑን ስለ ገበሬው ህይወት እንዲያስብ አደረገው፡፡
የፖለቲካ ንቃት
 የአያ ሙሄ ንግግር ስለ አራሹና የመሬቱ ባለቤት ስላላቸው ግንኙነት፤ በአጠቃላይ የመሬት ስርአቱ ምን እንደሚመስል እንዳውቅ አይኔን ከፈተልኝ ይላል ብርሀነ፡፡ ከዚያች ቀን በኋላ ሁል ግዜ አያ ሙሄ በመጣ ቁጥር ቁጭ ብለን የምናወራው ስለዚሁ መሬት ስሪት ሆነ፡፡ የመሬት ስሪት የሚለውን ቃል ሁሉ የሰማሁትና ምንነቱን ያወቅኩት ከዚሁ ገበሬ ነበር፡፡ ከአያ ሙሄ ጋር የጀመረውን ውይይት ከሌሎች ገበሬዎች ጋር በመቀጠል የገበሬው ህይወት በፍፁም ከሚያስበው በላይ አስከፊ መሆኑን ተረዳ፡፡ “የእኩል አራሽ ብሆን፤ የራሴ መሬት ቢኖረኝ ወይም የምጠምደው በሬ ቢኖረኝ ኑሮዬ ተዚህ መሻሉ የት ይቀር ነበር”፡- እያለ አያ ሙሄ ይቆጫል“ ትላለች ታደለች ኀ/ሚካኤል በመፅሐፏ፡፡ ይህ የገበሬው ህይወት ብርሀነን ስለ መሬት ስሪትና ገበሬው የመሬት ባለቤት ስለሚሆንበት ስርአት እንዲያስብ አስገደደው፡፡ ብርሀነ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበረበት ጊዜ something በተሰኘው መፅሄት ላይ ”የገብረ አረጋዊ ተስፋ“ የተሰኘውን በእንግሊዘኛ የተፃፈ አሳዛኝ ግን አይን ከፋች አጭር ልቦለድ ፅሁፍ ለተማሪው አስተዋወቀ፡፡ ፅሁፉን ሲፅፍ አያ ሙሄን እያሰበ እንደሆነ ፅሁፉን ላነበበ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የገብረ አረጋዊ ተስፋ  አያ ሙሄን እያሰበ የተፃፈ ትያትርና በዩኒቨርስቲው ለሚከበረው የኮሌጅ ቀን የቀረበ ነበር፡፡ የገብረ አረጋዊ ተስፋ የተሰኘው ድርሰቱ በዘመኑ የነበረውን የገበሬና የመሬት ባለቤቶች ግንኙነት ብሎም ሀይማኖት የተጫወተውን ህዝብን የማደንዘዝ ሚና በደንብ አንፀባርቋል፡፡

የሀይማኖት ሰባኪዎች አሁንም ድረስ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ በሆነው ስብከታቸው፣ ሰው ሰራሽ የሆነውን ረሀብ መለኮታዊ ቅጣት ነው ብለው ገበሬውን ለሌላ የህሊና ፀፀት እንዲዳረግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ረሀብና እርዛቱን እግዚአብሄር ያመጣው ቁጣ ነው በማለት ህዝቡ በየቤተ ክርስቲያኑ እየተሰበሰበ እግዚኦታውንና ምህላውን እንዲያደርስ ያስገድዱት ነበር፡፡ አሁንም ብዙ የተለወጠ ነገር የለም፤ ባለህበት እርገጥ ነው፡፡
መሬት ለአራሹ የሚለውን መፈክር በኮሌጅ ቀን ግጥሞች ፅፎ ባዘጋጀው ትያትር ላይ አስተዋወቀ፡፡ ታደለችም ሆነች ሌሎች እንደፃፉት፤ ተማሪም ሰልፍ በወጣ ቁጥር የሰልፉ አድማቂ ከነበሩ ጥቅሶች መሀከል ይህ የብርሀነ “መሬት ለአራሹ” ይገኝበታል፡፡ በብርሀነ አእምሮ የተፀነሰው እየሰፋ ሄዶ በለውጥ ፈላጊ ወጣቶችና ተማሪዎች እስከመቀንቀን ደረሰ፡፡ በ1957 ዓ.ም በተከበረው የኮሌጅ ቀን ግጥሞች ላይ ከቀረበው የብርሀነ መሬት ላራሹ ትያትር ላይ “መሬት መሬት ለአራሹ ፤ተዋጉለት አትሽሹ”  የሚለውን አንጓ መፈክር የቀዳማዊ ኃይለስላሴና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በመምዘዝ የንጉሱ ፓርላማ ድረስ በመሄድ ስሜታቸውንና ቁጣቸውን አሰምተዋል፡፡ ታደለች ኀ/ሚካኤል በመፅሐፏ እንደገለጠችልን፤ መሬት ላራሹ የሚለውን  መፈክር ለመጀመሪያ ግዜ የቋጠረውና ያስተዋወቀው ብርሀነ ነው፡፡ ደርግን ምስጉን ካደረጉ ውሳኔዎች አንዱ የሆነውን የመሬት ለአራሹን አዋጅ ባነሳን  ቁጥር ልናስበውና ልንዘክረው የሚገባው ብርሀነ ነው፡፡
በ1950 እና 60ዎቹ የነበሩ ሁሉም የትግል እንቅስቃሴዎች የመሬትን ጉዳይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቢያቀነቅኑትም ፈር ባለው መልኩ የቀረጸውና የመራው ግን ብርሀነ ነበር፡፡ እውነትም ገበሬው አፈር ገፊና የበይ ተመልካች ነበር፡፡ ብርሀነ ለደርግ በሰጠው ቃል እንዳረጋገጠው፤ መሬት ለአራሹ የሚለውን ስልፍ አደራጅና መሪ ነበር፡፡ ደሴ እያለ ከገበሬዎቹ ጋር ባደረጋቸው ውይይቶች የገበሬው ህይወት የችግሩ መንስኤዎች “ገበሬው የሚያርሰው የራሱ መሬት ስለሌለው፤ የሲሶም ይሁን እኩል የሚካፈልበት የማምረቻ መሳሪያ የሆኑት መሬት፤ በሬና ሌሎች አስፈላጊ የቁስ ሀብት አለመኖር ነበሩ”፡፡ ገበሬው በድህነት እንዲኖር የፈረደበት ማንም ሳይሆን ጨቋኝ የነበረው የፊውዳል ስርአት ነበር፡፡ ይህ ስርአት አሁን ድረስ ጠበቆችና ተቆርቋሪዎች ቢኖሩትም ፀረ-ሰብ ከመሆኑ በተጨማሪ ሀገሪቱን አንቆ ለመግደል ሲውተረተር የነበረ ነው፡፡ በገበሬው ጉልበትና ባመረተው ላይ አዛዦቹ ፈውዳሎቹ ብቻ ነበሩ፡፡ ታሪካችን ይህን የነገስታት ግፍ አይቶ እንዳላየ አልፎታል፡፡ ለዘመናት ከመቆየቱ የተነሳና ህዝብ ላይ ባደረሰው ግፍ ስሩ በስብሶ በቀላሉ ሊወድቅ ቻለ፡፡ ገዝግዘው ከጣሉት የተማሪና አብዮት አንቀሳቃሾች መሀል አንዱ ብርሀነ ነው፡፡
የብርሀነ ሰብእና
ብርሀነ ከልጅነቱ ጀምሮ ባዳበረው የንባብ ልምድ በመታገዝና በተሳተፈባቸው የክርክር መድረኮች የተከራካሪነት ክህሎቱን አሳደገ፡፡ እስከ መጨረሻ የህይወቱ ምእራፍ የታወቀበትን የክርክር ክህሎቱን እራሱን በመሞረድ ቅርፅ አወጣለት፡፡ በዚህም የተነሳ በ1960ዎቹ ተሰጥኦ ያላቸው ተከራካሪዎች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ነበር፡፡ የዚያ ዘመን የሃሳብ መሪዎችና የሀሳብ ክርክር ዋልታዎች የሚባሉት እንድሪያስ እሸቴና ብርሀነ ነበሩ፡፡
የነገርን ስርና ምንጭ ለመረዳት በነበረው መሻት የተነሳ አጥብቆ ጠያቂም ነበር፡፡ ባለቤቱ ታደለች ኀ/ሚካኤል እንደምታጠናክርልን፤ “ከየት መጣሽ? የት አየሽ?---የነገርን መነሻ ማጥናት አንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ከሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የሚለየው በነዚህ ጥያቄ መሰረት ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት ነው”- ይል ነበር ብላለች፡፡ ታደለች ኀ/ሚካኤል በመፅሐፏ ላይ እንደጠቀሰችው፤ ይሄ ልማድ ስለተጠናወተው  ያመነውን ነገር በማስረዳት ለማሳመን ብዙ ጥረት ስለሚያደርግ፣ አንዳንዶች አልበገር ባይ አድርገው ይስሉታል፡፡ በወዳጆቹም በነቃፊዎቹም እንደተመሰከረለት፤ ብርሀነ አንደበተ ርእቱና የሚናገረውንም የሚያውቅ ነበር፡፡ አሰፋ ጫቦ ከጋዜጠኛ መአዛ ብሩ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ እንደመሰከረው፤ በአንደበተ ርእቱነታቸው የማስታውሳቸው ብርሀነንና የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት የነበሩትን ካሳ ወልደማርያም ነው ብሎ ነበር፡፡ ክፍሉ ታደሰ በ”ያ ትወልድ“ መፅሐፉ ላይ እንዳሰፈረው፤ “ብርሀነ አንደበተ ርእቱ ተናጋሪ” ነበር፡፡ ህይወት ተፈራ እንደምትለው፤ “ብርሀነ የአንድ ዘመን ተማሪን ህይወት የቀየረ ገናና እና ህያው ተደርጎ የሚወሰድ ነበር” ብላለች፤ ”ማማ በሰማይ“ በተሰኘ መፅሐፏ፡፡ መንግስቱ ኀ/ማርያም ከገነት አየለ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የማውቃቸው ጓደኞቹ ስለ ብርሀነ ነገሩኝ ብሎ እንደገለጸው፤ “ብርሀነ ግትርና በአላማው ፅኑ፣ ጎበዝ ነበር”፡፡ ይህ ለአላማ መቆምና መታመን  በኋላ በትግል ህይወቱ ላይ ይዞት የመጣውን አሉታዊ ውጤት እናያለን፡፡
የብርሀነ የድርጅት ተሳትፎ
በመጀመሪያ ከሀገር ውጪ ኢህአድን በኋላም በሀገር ውስጥ ኢህአፓን ካዋለዱ የዘመኑ ቀደምት ተማሪዎች መሃል አንዱ ብርሀነ ነው፡፡ ከእነ ጌታቸው ማሩ ጋር እሱ የመሰረተውን ኢህአድ ይዞ ኢህአፓን መሰረተ:: ብርሀነ እስከ አሁን ድረስ የ1960ዎቹ የትግል ምልክት ተደርጎም በጓደኞቹ ይወሳል፡፡
“በኢትዮጵያ ፖለቲካ በህዝብ ዘንድ ታማኝ  ለመሆን ቀዳሚ መሆን ያለበት ግብ እንዲሁም የተማሪው ወሳኝ  ሚና ፅናትና ወደ ኋላ አለማለትን የሚጠይቅ እንጂ በጉሩምሩምታና በመዘባነን የሚደረስበት አይደለም” ብሎ ያምን እንደነበር ባለቤቱ ታደለች ኀ/ሚካኤል በመፅሐፏ ጠቅሳለች፡፡ ፕሮፌሰር  ባህሩ ዘውዴ በአንድ ፅሁፉ እንዳሰፈረው፤ በ1965 (እ.ኤ.አ) በበርሊን ከተማ በተካሄደ የመጀመሪያው አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ጉባኤ ላይ በሀይሌ ፊዳና በብርሀነ መሀከል ሰፊ ልዩነትና ክርክር ተፈጥሮ ነበር፡፡ በዚህ ክርክራቸውም “ትግሉ ቢዳከም የታሪክ ተጠያቂ ትሆናለህ እየተባባሉ የግምባር ደም ስራቸው እስኪወጣጠር ድረስ ሲጨቃጨቁ ነበር” ብሏል፡፡ ብርሀነ የሰጋውም  አልቀረም፤ ድርጅቶቹ ውስጥ በተከሰተው መዝረክረክ በተከታታይ ትውልድ ውስጥ የኢህአፓ እና መኢሶን ጥፋት ሲታወስ ይኖራል፡፡ ብርሀነ አፅንኦት እንዲሰጠው ያሳሰበው ወርቃማ መልእክት ሰሚ አጥቶ በኋላ ለደረሰው የፖለቲካ ትግል ምስቅልቅል ምክንያት ከመሆን በተጨማሪ ሁለቱን ድርጅቶች ለምት እና  ለክስመት ዳረጋቸው፡፡
እነ ብርሀነን አንጃ ብለው ከፈረዱባቸው ውስጥ አንዱ የሆነው ክፍሉ ታደሰ፣ በ”ያ ትውልድ“ ቅፅ ሁለት መፅሐፍ ላይ፤ “ብርሀነ መስቀል በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ አንጋፋ መሪና ለእንቅስቃሴውም ያደረገው አስተዋፅኦ ግዙፍ መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ ከዚህም በላይ ከ1962 ዓ.ም እስከ 1964 ዓ.ም ድረስ በነበረው ጊዜ ኢህአድ/ ኢህአፓን ለመመስረት በተደረገው ትግልና ርብርብ የብርሀነ መስቀል ሚና እጅግ አይነተኛ ነበር፡፡ የብርሀነ መስቀል እውቅና እና ዝና የስርነቀል ለውጥ ደጋፊዎችን በመሰብሰብ ረገድ በአያሌው ረድቷል፡፡ ብርሀነመስቀል በኢህአሰ አስኳል ውስጥ ከነበሩት መሪ አባላት መካከል አንዱ ነበር፡፡ የኢህአድን ዋና ዋና ሰነዶች በማርቀቅ በኩል ያበረከተው ድርሻ ወደር አይገኝለትም” በማለት አስተዋፅኦውን በሚገባ አስፍሯል፡፡
የኢህአፓ ማእከላዊ ኮሚቴ ፖሊት ቢሮ ባካሄዳቸው የተለያዩ ስብሰባዎች ላይ ብርሀነ ያመነበትን አቋሙን አንፀባርቋል፡፡ ያመነበት ሀሳብ በአብላጫ ድምፅ እንዲለወጥ የሚያደርግ ሰብእና ስላልነበረው በሂደት ከመሰረተው ፓርቲ፤ ከማእከላዊ ኮሚቴው ብሎም ከፖሊት ቢሮው አባልነቱ ቀስ በቀስ እየተገፋ እንዲነጠልና የሴራ ሰለባ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ብርሀነን ልዩነት ውስጥ የጣሉት አቋሞቹ የሚከተሉት ናቸው፡-
በ1967 ዓ.ም ለደርግ እጃቸውን በሰጡ የኢህአሰ አባላት ላይ እሱ ያስተላላፈውን የሞት ቅጣት ውሳኔ ፓርቲው በማገዱ ቅሬታ ተሰምቶታል፡፡ የኢህአፓ ወታደራዊ ክንፍ የሚመራበትን የወታደራዊ ህግ ተግባራዊ እንዲደረግ አጥብቆ ቢጠይቅም አልሆነለትም፡፡ ለደርግ በሰጠው ቃል ላይ እንደመሰከረው በአንድ የድርጅታቸው ውይይት ላይ የተከሰተውን ሲጠቅስ፤ “የዚህ ውይይት ዋና አላማ ሰዎቹ የጠፉት (ኢህአስን ከድተው ለደርግ እጃቸውን የሰጡትን ለመጠቆም ነው) በፖለቲካ መስመር ልዩነት ሳይሆን፣ በእኔ የአስተዳዳር ብልሹነት መሆኑን ለማሳመን ነበር፡፡ ይህ ክስ የመጣው ከታጠቀው ቡድን በመጣ ሪፖርት ላይ በተመሰረተ ሳይሆን ተስፋዬ ደበሳይ የተቀሩትን የማእከላዊ ኮሚቴ አባሎች ለብቻው በመገናኘት ያስፋፋው የሀሜት ዘመቻ” መሆኑን ጠቅሷል፡፡ በሌለበት የደረሰበትን እንዲህ አይነት የስም ማጥፋት ዘመቻ ለመከላከል ጓዳዊ ሂስና ግለሂስ ፕሮግራም እንዲካሄድ አጥብቆ ቢጠይቅም፣ በማያሳምኑ ምክንያቶች ውትወታው ፍሬ ሳያፈራ ቀረ፡፡ ቅሬታም አደረበት፡፡


በክፍሉ ታደሰም፤ በታደለችም፤ እሱም ለደርግ በሰጠው ቃል ላይ እንደሰፈረው፤ በ1967 ዓ.ም  መጨረሻ ላይ በተካሄደ አንድ የማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ በፓርቲው አመራር ውስጥ የዋና ፀሀፊነት ቦታ እንዲሰረዝ የቀረበውን የማሻሻያ ሀሳብ ብርሀነ ተቃወመ፡፡ በዚያን ወቅት ብርሀነ የፓርቲው ዋና ፀሀፊ ነበር፡፡ ለደርግ በሰጠው ቃል ላይ እንደሰፈረው፤ “መጠነ ሰፊው ኮንፈረንስ በ1967 ነሐሴ ሲካሄድ የፓርቲው ፀሃፊ የሚለውን ሰርዞ በምትኩ የማእከላዊ ኮሚቴ ፀሀፊ የተሰኘ እርከን ፈጠረ፡፡ ከዚህ ተከትሎ በተካሄደ ስብሰባ ተስፋዬ ደበሳይ የማእከላዊ ኮሚቴው ፀሀፊ ሆኖ ተመረጠ”፡፡ ከዛም በመከተል ብርሀነን ያልጨመረ አዲስ ፖሊት ቢሮ ተቋቋመ፡፡ ለደርግ በሰጠው ቃል ላይ፤ “ድርጅቱ ባካሄደው መለስተኛ ጉባኤ ላይ ስለሚቀርቡት ሪፖርቶች ስንነጋገር በየትኛውም ሌላ ማርክሲስት ሌኒኒስት ፓርቲ ትራዲሽን የሌለ ፕሮሲጀር አቀረቡ፡፡ ይኸም በህጋዊ መንገድ ከሀላፊነቱ ያልተነሳ ዋና ፀሀፊ እያለ ሌላ ተራ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ጉባኤውን እንዲከፍት የሚል ነበር፡፡ በኔ በኩል ያኔ በእኔ ላይ ፐርሰናል ቅሬታ ስላላቸው እንጂ ከማእከላዊ ኮሚቴ በስተጀርባ የተቋቋመ ክሊክ በመመስረቻ ጉባኤ የተመረጡትን የፓርቲው መሪዎች ዘዴኛና ድብቅ በሆነ መንገድ ለማውረድ ማቀዳቸውን አልገመትኩም ነበር፡፡ ስለሆነም ጥያቄ ሳቀርብ ይሁን አንተ ክፈተው ቢሉም ፈፅሞ ከኮሚኒስት ስነምግባር ውጪ የሆነ ከአንገት በላይ ስምምነት መሆኑን ለኔ ክብር ካልተሰጠኝ ያልኩ ያስመስላል በሚል ፍራቻ ሳልከፍት ቀረሁ” ብሏል፡፡ ብርሀነ በዚያው ሰሞን አጠቃላይ የፓርቲ ኮንግረስ ስብሰባ እንዲጠራ አጥብቆ ጠይቋል፡፡ ግን ሳይሆን ቀረ፡፡ ያልሆነበትን ምክንያት ሲያብራራ፤ “በታህሳስ 69 ይመስለኛል ተስፋዬ ደበሳይ ከምኖርበት ቤት ድረስ መጥቶ አነጋገረኝ፡፡ በኔ በኩል ስብሰባው እንዲጠራ ደጋግሜ ጠየቅሁ፡፡ የሰጠኝም መልስ ስብሰባ ያስፈልጋል የምትሉት ሁለት ሰዎች ብቻ ስትሆኑ የተቀሩት አያስፈልግም ብለዋል የሚል ስለነበር ስብሰባው ለምን እንደሚያስፈልግና የቱን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ለተቀሩት የማእከላዊ ኮሚቴ አባሎች ገልፀን ለማሳመን የምንችለው ስንገናኝ ብቻ ስለሆነ የምንገናኝበትን መንገድ አዘጋጅልን አልኩት፡፡  ይህን እሞክራለሁ ነገር ግን የሚሳካ አይመስለኝም  ምክንያቱም አንተ የማታውቀው ሌላ ከባድ ነገር አለ አለኝ፡፡ ክሊኩ ብቻ የሚያውቀው ምክንያት ቢኖር ነው አይሆንም ያለው” የሚል እምነት አደረብኝ፡፡ ምንአልባት ብርሀነ ያሳሰበው ጉባኤው ተጠርቶ ቢሄን ኖሮ ፓርቲውም አባላቱም አመራሮቹም ከጥፋት በዳኑ ነበር፡፡ በፓርቲው ውስጥ በተፈጠረ ልዩነት ምክንያት ስም በማጠልሸት የሰዎችን ሀሳብ ውድቅ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ እስከዚህ ድረስ ብርሀነ የማእከላዊ ኮሚቴም የፖሊት ቢሮውም አባል ነበር፡፡


ሚያዝያ 1968 ደርግ ባቀረበው የግንባር  ጥሪ ላይ ብርሀነ የተለየ አቋም ያዘ፡፡ ከደርግ ጋር ህብረት መፈጠር አለበት ሲል አቋም ያዘ፡፡ ከዚህ በተከተሉት የማእከላዊ ኮሜቴ ስብሰባዎች ላይ ከጌታቸው ማሩ ጋር የተለየ ሀሳባቸውን አንፀባረቁ፡፡ የሶማሌ ወራሪ የምስራቁን ክፍል በተቆጣጠረበት ሁኔታ የደርግ የህብረት ግንባር ጥሪ ማለፍ አይገባም በሚል  የደርግን የሰላም ጥሪ እንቀበል ማለታቸው ሁለቱን ጥርስ ውስጥ ከተታቸው፡፡
መንግስቱ ኀ/ማርያም ላይ እርምጃ ይወሰድ የሚለውን የፖሊት ቢሮ ውሳኔ ጌታቸውና ብርሀነ ተቃወሙት፡፡ ምክንያታቸውም “አንድን ግለሰብ በመግደል ፓርቲያችንን ከጥፋት አናድነውም፡፡ ዞሮ ዞሮ መንግስቱን በመግደል የመንግስት ግልበጣ አመጣለሁ በሚል እምነት ነውና ፑቲሸዝም ነው፡፡ ለውጥ ካለማምጣቱም በላይ ሕዝባዊ ተሳትፎ የሌለው ስለሆነ ተቀባይነት የለውም” ብለው ተከራከሩ፡፡
ብርሀነ ለደርግ በሰጠው ቃል ከብዙ ጊዜ በኋላ ጥር 17 ቀን 1969 ላይ የማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ጥሪ ደረሳቸው፡፡ ብዙ የሚያነጋግሩ የሚነሱ ጉዳዮች ስላሉ ለነዚያ ተዘጋጅተው ቢሄዱም የስብሰባው የመጀመሪያ አጀንዳ እነሱን የሚመለከት ሆነ፡፡ ስለፈፀሙት ወንጀል ምክክር ተጀመረ፡፡ ይህ ስብሰባ እነሱን እስከ ወዲያኛው ከፓርቲው አመራርነት አስወገዳቸው፡፡ እስከዚህ ጊዜ ድረስ የጌታቸውና የብርሀነ እምነት፤ ግልፅ ውይይት በማድረግ ፓርቲው የጀመረውን የስህተት መንገድ ማስተካካል ይቻላል የሚል ነበር፡፡ ብርሀነ ላይ የቀረቡት ክሶች የሚከተሉት ነበሩ፡--
ፖሊት ቢሮው ከስልጣኑ በላይ ተግባሮችን ከማካሄዱም በላይ የማእከላዊ ኮሚቴውንና የጉባኤውን ስልጣን ወስዷል (እውነትም ከላይ እንደሰፈረው ጉባኤው የሰጠውን የዋና ፀሀፊነት ስልጣን ፖሊት ቢሮው ብርሀነን ነጥቆታል)፡፡
ከመዋቅር ውጪ የፓርቲ አባሎችን እያነጋገርህ በፓርቲው የፖለቲካ መስመር ላይ ትርጉም ትሰጣለህ (የራስህን ሀሳብ አንፀባርቀሀል)፡፡
የፓርቲው የጥቃት ቡድን ሀላፊዎች የሚወስዱትን እርምጃ ትክክል አይደለም በማለት ተፃራሪ ትእዛዝ ሰጥተሀል (ከላይ እንደተጠቀሰው በመንግስቱ ኃ/ማርያም ላይ የተወሰነውን የግድያ እርምጃ አጥብቆ አውግዟል)፡፡
የማእከላዊ ኮሚቴ እስረኛ ነኝ ብለሀል፡፡ (ከነሐሴ 30 ቀን 1968 እስከ መስከረም 15 ቀን 1969 በአካልም ሆነ በስልክ ከማንም አልተገናኘም ነበር፡፡ ይህንን ድርጊት ነው ብርሀነ የቁም እስረኛ መሆን ያለው፡፡)
መኢሶን ከኛ ጋር የሚመሳሰል የፖለቲካ ፕሮግራም ስላለው እንደጠላት ልንቆጥረው አይገባም ብለሀል፤ የሚሉ ውሀ የማይቋጥሩ ክሶች ነበሩ፡፡
 እነ ብርሀነ ክሊኩ የሚሉት የእነ ክፍሉ ታደሰ ቡድን በመስከረም 1969 ዓ.ም ከፓርቲው እውቅና ውጪ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የአመፅ ጥሪ አድርጎ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ወደ አመፅ ተሸጋገረ፡፡ ታደለች  ብርሀነ ለመርማሪ የሰጠውን ቃል ስታብራራ፤ “አንተ አልገባህም፤ የማታውቀው ብዙ ነገር አለ እኮ ነው ያለኝ”  ያለውን የተስፋዬ ደበሳይ ንግግር የሚያጠናክርልን፣ ታደለች በመፅሐፏ ያሰፈረችው “ዘርኡ ክህሽን ለክሊኩ ብቻ የሚታዘዝ የከተማ ታጣቂ ቡድን ከፓርቲውም ሆነ ከማእከላዊ ኮሚቴው እውቅና ውጪ እንዳደራጁ” ለሀይሌ ገሪማ የሰጠው ቃለምልልስ ነው፡፡
እነ ብርሀነ ክሊኩ ብለው የፈረጁት ቡድን ፓርቲውን አንቆ የገደለ መሆኑ በሂደት ተረጋገጠ፡፡ አጥብቆ የተከራከረለት ችግርን በውይይት መፍታት ተገፍቶ የአብላጫ ድምፅ ውሳኔ (ቡድንተኝነት) ፓርቲውን ጭቃ ውስጥ ጨመረው፡፡ ብርሀነ ለፓርቲው ያበረከተው አስተዋፅኦ ግዙፍ የነበረ ቢሆንም አንጃ ተብሎ ለግድያ ተፈለገ፡፡ ፓርቲዊ እራሱን እየገደለ ነው ያለው እውነት መሆኑን ለመታዘብ ብዙ ጊዜ አልጠየቀም፡፡ ከ1969 ዓ.ም በኋላ ኢህአፓ አመድ ሆነ፡፡

Read 718 times