Saturday, 01 June 2024 20:55

“አይጢቱ ድፍን ቅል ውስጥ ገብታ ወለደች!” ቢለው፤ “በምን ገብታ?” “እኸ! ጉዱ ምን ላይ ነው?”

Written by 
Rate this item
(9 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን አሦች በግዛታቸው ላይ ከፍተኛ ቅሬታና መከፋት ተሰማቸው። አንዱ አሣ ሌሎችን በአጠገቡ የማሳለፍ ፍቃደኝነት አላሳይ አለ። ሁሉ በዘፈቀደ ወደ ግራ ወደ ቀኝ፣ ሽቅብ ቁልቁል ያለሥርዓት ይምዘገዘጋል፤ ውሃውን ያደፈርሳል። በሰላም በቡድን ሆነው ለመቆም በሚሞክሩት መካከል እየሰነጠቁ ማቋረጥና አንዳችም ይቅርታ አለመጠየቅ ተለመደ። የሌሎችን መንገድ ዘግቶ መቆም ተዘወተረ። ጠንካሮቹ ደካሞቹን በጭራቸው እየገረፉ ማለፍ እንደደግ ባህል ተቆጠረ። ጭራሽ አልፈው ተርፈውም ትልልቆቹ ትንንሾቹን ዐይናቸውን እንኳ ጨፈን ሳያደርጉ መዋጥ መሰልቀጥ ጀመሩ።
“ኧረ ህግና ሥነ-ስርዓት የሚያስከብርልን ንጉሥ ይኑረን?” ይላል አንደኛው አሣ።
ሁለተኛው አሣ፤
“ኧረ እስከመቼ ነው እንዲህ ሥርዓተ-አልባ ሆነን የምንኖረው?” ይላል።
አዛውንቱ አሣ ቀጠለ።
“ለመሆኑ እንዲህ ኃይለኛው ደካማውን እያጠቃ ጠቅላላ ማህበረ- አሣው ሳይከባበር አንዱ አንዱን እያንጓጠጠ፣ አንዱ ሌላውን እየሸነቆጠ፣ ሌላው ሌላውን ቁልቁል እያየና እየበጠበጠ፣ እንዴት ሊዘልቅ ነው። ህብረተ-አሣው ህልውናውን ለማስጠበቅም ሆነ መብቱን ለማስከበር አንድ መላ መፍጠር ይገባዋል። አለበለዚያ እንዲህ መላ ቅጣችን ጠፍቶና ኑሯችን ተመሰቃቅሎ ልንዘልቀው አንችልም” አለ።
ከዚያም ሁሉም በአንድ ድምጽ፤
“የንጉሥ ያለህ! ሥነ-ስርዓት የሚያስከብር ንጉሥ ያለህ!” አሉና ጮሁ።
በመካያው “ለምን የራሳችንን ጥሩ ንጉሥ አንመርጥም?” ተባባሉ። በዚህም መሰረት አንድ ውሃውን እንደልቡ በፍጥነት እየሰነጠቀ የሚጓዝ፣ ደካሞች ከመርዳት ወደኋላ የማይል መሪ መረጡ። በጣም ረጅም ቁመት፣ ስል ጥርስ ያለውና ካፉና ካፍንጫውም ረዥም-ሹል ቅርፅ ያለው ነው። በባህሩ ዳርቻ አሳዎቹ ሁሉ ተሰልፈው ሳሉ መሪው አሳ በጭራው እንዲንቀሳቀሱና የሩጫ ውድድር እንዲያደርጉ ነገራቸው። ሁሉም መሮጥ ጀመሩ። ርቀው ሄዱ።
መሪው አሣ እንደቀስት እየተወረወረ ሄደ። ከሱም ጋር ጨረር አሣ፣ አምባዛ፣ ሻርክ፣ ኢል ወዘተ እየተከታተሉ በረሩ። ፍላውንደር የተባለው ጠፍጣፋ አሳ ሁሉን ቀድሜ አሸንፋለሁ የሚል ተስፋ ነበረው። ግን አልተሳካለትም።
በዚህ መካከል በድንገት ጩኸት ተሰማ፤
“በእሽቅድምድሙ ትንሿ ብርማ አሣ ቀደመች! ትንሿ ብርማ አሣ ቀደመች!” አለ የጩኸቱ ድምጽ።
ጠፍጣፋው ቁጠኛና መቀደም የማይሻው ፍላውንደር እጅግ ወደ ኋላ ቀርቷል። በጣም ተናዷል። ከሱ ወደ ኋላ መቅረት የትንሿ መቅደምና አንደኛ መውጣት  ነው ያበገነው። “ማነው የቀደመው?” እያለ በንዴትና በቁጣ ጠየቀ።
“ትንሿ ብርማ አሣ ናታ! ትንሿ ብርማ አሣ!” የሚል ምላሽ ከግራም ከቀኝም አገኘ።
“ይቺ ራቁቷን ያለችው? ወይኔ ፍላውንደር” እያለ ዛተ፤ “በጊዜ በልቻት ቢሆን ኖሮ እንዲህ ጉድ አልሆንም ነበር!” አለ፤ ፍላውንደሩ በቅናት።
ይኸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፤ በዚህ ጥፋቱ ምክንያት ምንጊዜም ሲንቀራፈፍ በቀላሉ የሚበላ አሣ እንዲሆን ተፈርዶበታል።
***
በራሱ መንቀራፈፍ ሳይቆጭ የሌላው መቅደም ንዴት ላይ የሚጥለው ለራሱም፤ ለሌላውም ለሀገሩም የማይበጅ ነው። ከዚያ የሚከፋው ደግሞ፤ ከዚህ ቀደም አጥፍቼው ቢሆን ኖሮ ዛሬ እንዲህ አልሆንም ነበር የሚል በጭካኔ የተሞላ ፀፀት ነው። እንደህ ያለ ፀፀት ከትላንቱ ክፋቱና ውጤቱ ያልተማረ ሰው ፀፀት ሲሆን፤ አድሮ የሚገጥመው ውጤትም ከትላንቱ የከፋ ውጤት መሆኑ አይቀሬ ነው። ጊዜያዊ ማታለልን እንደዘለዓለማዊ ስትራቴጂ የሚያስብ “ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ነው”። የፖለቲካን ችግር ኢኮኖሚያዊ ምላሽ በመስጠት፣ ለኢኮኖሚያዊ ችግር ፖለቲካዊ ምላሽ በመስጠት፤ ፍፁም ፖለቲካዊ ለሆነው ጥያቄ የዲፕሎማሲ ጭምብል መድፋት፣ ፍፁም ዲፕሎማሲዊ ለሆነው ጥያቄ ደግሞ፣ ልምድ የፖለቲካ ምላሽ ማላበስ፣ የአገር-ውስጡን ችግር ፣ ለዓለም-አቀፉ፣ የዓለም አቀፉን ለመንደሩ መፍትሔ መስጠት፤ “የሆድን በሆድ ይዞ! ሰባኪ ምላስ መዝዞ” እንደሚባለው ያለ አቋራጭ ይሆናል። ለየችግሮቻችን የምናቀርበው መፍትሔ ከተጨባጩ እውነታ በራቀ ቁጥር፤ ማንኛውንም ምንም ሳንጨብጥ አገርም ውልቅ የምትቀርበትና ኩም የምትልበት ሁኔታ ውስጥ እንዳትገባ መጠንቀቅ ተገቢ ነገር ነው።
“ለብልህ ጀምርለት አይስተውም፤ ለሞኝ በግልጽ ንገረው አይገባውም” ነው፤ ነገራችን ሁሉ።
ከቶውንም በበር ሲያቅት በመስኮት፤ በመስኮት ሲነቃ በፊት ለፊት በር፤ ፍላጎትን የማስፈፀም ፖለቲካዊ መንገድ፤ ረጅም ጎዳና የሚያስኬደን አይደለም። ባሁኑ ጊዜ በማናቸውም የፖለቲካ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ዘመናዊ ዘዴ ጥንት የእጅ-አዙር አገዛዝ ይባል እንደነበረውያለ ነው፤ ለማለት ይቻላል።
አንዳንዶች “ፖለቲካ የመዋሸት ጥበብ ነው (መቦጥለቅ ነው) ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ “ፖለቲካ ራሱ ውሸት አይደለም ወይ?” ሲሉ ይጠይቃሉ። ሌሎች ደግሞ “”ፖለቲካ የማሳመኛ ዘዴ ነው። ውሸት አይደለም። ውሸት የሚመጣው የማሳመኛ ዘዴ ሁሉ ሲያልቅ ነው” ይላሉ። ቶማስ ማን የተባለው ጀርመናዊ ፀሐፊ ደግሞ “ፖለቲካና የፖለቲካ ዕምነትን እጠላለሁ። ምክንያቱም ሰዎችን ዕብሪተኛ፣ ቀኖናዊ፣ ግትርና ጨካኝ ያደርጋቸዋል” ይለናል።
ለማንኛውም በሀገራችን “ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጥፋ” ማለት ደግ ጸሎት ነው። ዲፕሎማሲውም ያው ነው፡፡ ኦስትሪያዊው ጸሐፊ ካርል ክራውስ “ዲፕሎማሲ ማለት ተደራዳራሪዎቹ አገሮች ንጉሦቻቸው መሄጃ-መላወሻ ሲያጡ (Checkmated) እንደሚባለው፣ የሚያጋጥሙበት የቼዝ ጨዋታ ነው” ያለውን ዓይነት ይመስላል። የተሻለ ቼዝ እንዲያጋጥመን እንመናለን።
መቼም ሀገራችን ዕድሜዋ በረዘመ ቁጥር የመነጋገሪ አጀንዳዋ እየበዛና እየተወሳሰበ ይሄዳል። የዲሞክራሲ መስፈን አጀንዳ፣ የዕድገት መኖር አለመኖር አጀንዳ፣ የውጪ ዕርዳታ መኖር አለመኖር አጀንዳ፣ የፖለቲካ ዕውነት መሆን አለመሆን አጀንዳ፣ የፖለቲካ ምህዳር መስፋት አለመስፋት አጀንዳ፣ የዲፕሎማሲ መሳካት አለመሳካት አጀንዳ፣ የአገራዊ ምክክር ገለልተኛ የመሆን ያለመሆን አጀንዳ፣ ግጭት መቆም አለመቆም አጀንዳ፣ የፖለቲካ እሥረኞች መፈታት አለመፈታት አጀንዳ፣ የውጪ አገር አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ዝም ማለት አለማለት አጀንዳ፣ ….ቃለ-መጠይቅ፣ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የእንደ-ፓርቲ አስተያየት፣ እንደ-ግል አስተያየት…ወዘተ ከዚያም የመረጃ እጥረት ከሌለ በስተቀር… የሰሚ ስሚ እንደሰማነው…እኔ እስከማውቀው ድረስ… ራሱ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል እስኪነግረን ድረስ ለጊዜው ይሄው ነው።… እኔ መረጃ እንደደረሰኝ… ስህተት ካለ እናስተካክላለን… የሚባለው ያ ነበር ግን ምን ያደርጋል ይሄ ሆነ ወዘተ… ማለት ብቻ ይሆናል ውጤቱ።
ነገሩ ሁሉ እቅጩነት ያለው መልስ ሳያገኝ፣ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ሳይሰጠው፣ መሰንበት ባህሉ ሆነ። ብቻ የማታ ማታ
“አይጢቱ ድፍን ቅል ውስጥ ወለደች” ቢለው
“በምን ገብታ?” ብሎ ገርሞት ጠየቀው።
“እኸ! ጉዱ ምን ላይ ነው?” ብሎ ጨረሰው፤ የሚለው ምሳሌ ዓይነት እንዳይሆን ያሰጋል።Read 865 times