የእናት መክሊት የተባለውን እናቶች ከመውለዳቸው በፊት በእርግዝነና ላይ እያሉ እና ከወለ ዱም በሁዋላ ከህክምና ባለሙያዎች ጋር፤ እርስ በእርስ ከእናቶች ጋር ውይይት የሚያደርጉበ ትንና በአጠቃላይም ለህክምና ባለሙያዎች ፤እናቶች፤ልጅ አሳዳጊዎች የሚሰጠውን ስልጠና በተመለከተ ባለፈው እትም የተወሰነ ነገር ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ የጉዳዩን ምንነት በጥልቀት ለማስረዳት እንዲቻል በዚህ እትምም የምናነሳው ነጥብ ይኖረናል፡፡ ለመሆኑ የእናት መክሊት እንዴት ተጀመረ ስንል በረዳትነት ኃላፊነቱን ወስዶ በስራ ላይ ያለ ሰው ለዚህ እትም እንግዳ አድርገናል፡፡
ሙሉ ጂ የእናቶችና ህጻናት እንዲሁም ጠቅላላ ሆስፒታል ከባለቤታቸው ጋር በመተባበር የመሰ ረቱት ዶ/ር ሙሉአለም ገሰሰ ባለፈው ሳምንት እትም ለእናቶች መደረግ የሚገባውን እገዛ አስ መልክተው ሲገልጹ እንዲህ ነበር ያሉት፡፡
‹‹…እኔ የጨቅላ ህጻናት እስፔሻሊስት ሐኪም ብሆንም ላለፉት ሰላሳ ሰባት አመታት ከህጻናት ጋር ነው የኖርኩት፡፡ በየካቲት ሆስፒታል ብቻ የህጻናት ሐኪም በመሆን ለ30/አመታት ሰርቻለሁ፡፡ እናትየው በልጁዋ ላይ የምታደርገው ክትትል ሁሉ በልጁ ላይ ይታያል፡፡ እናትየው ጥሩ ልምድና ስልጠና ወይንም እውቀት ከሌላት ልጅዋ ይጎዳል፡፡ እናትየው ከወለደች በሁዋላ ሳይሆን ከመውለድዋ በፊት እንዲያውም ሳታረግዝ አስቀድሞ ሁሉ በህክምና ተቅዋም ብሎም ስልጠናው በሚሰጥባቸው ቦታዎች እንድትገኝ ያስፈልጋል፡፡ እናትየው በውስጥ ደዌ ህመም የተያዘች ከሆነ ለምሳሌ እንደስኩዋር፤ ደም ግፊት የመሳሰሉትን ለመከታተል ወይም በእርግዝናው ወቅት ችግር እንዳያስከትል ለመከታተል እንደሁም ሌሎች የአካል ብቃት ሁኔታዎችን ለማስተካከል እንዲረዳ አስቀድማ መታየት ይጠቅማታል፡፡ ከዚህም በላይ ትዳር ሲመሰረት ከማን ጋር የሚለውን በጤና ጉዳይም ይሁን በሌሎች ምክንያቶች እንድትዘጋጅ የሚያደርጋትን ስልጠና ከባለሙያዎች እንድታገኝ እራስዋን ማዘጋጀት አለባት፡፡ ስለዚህ ከማርገዝዋ አስቀድሞ፤በእርግዝና ላይ እያለች፤እንዲሁም ከወለደች በሁዋላ ስልጠናውን ማግኘት ከቻለች በጥሩ ሁኔታ ልጅዋን ማሳደግ ትችላለች፡፡ ህጻናቱ ጨቅላ ከሚባለው ጀምረው በየደረጃው የሚገጥማቸው ህመም በአብዛኛው ማለትም ወደ 80% የሚሆነው የሚከሰተው በኢንፊክሽን ወይንም በመመረዝ ስለሆነ ያንን ልጆቹ ሳይጎዱ በፊት ለመከላከል የሚቻለው ስልጠናው ወይንም እውቀቱ ሲኖር ነው፡፡ ኢንፌክሽንን በመከላከል ሊድኑ የሚችሉ ልጆች ሳይደረስላቸው በመቅረቱ በመሬት ላይ ሲንፉዋቀቁ ያየንበትን ጊዜ መርሳት አይቻልም፡፡ እንደዚህ የተጎዱ ልጆች ለራሳቸው፤ለቤተሰባቸው ብሎም ለሀገራቸው አሳዛኝ ውጤቶች ናቸው…››ነበር ያሉት፡፡
ይህንን መክሊት የተሰኘ የስልጠናና ማማከር ስራ በመጀመሩ ረገድ ልጃቸው ወጣት አቤል ገመቺስ ተጠቃሽ ነው፡፡ አቤል እንደሚለው ‹‹….ይህንን የስልጠና ስራ ከእናቴ ጋር በመሆን ነው የጀመርኩት፡፡ እኔ ተምሬ የተመረቅሁት በሌላ ሙያ ቢሆንም የህጻናትን ህክምና ግን ከእድገቴ ጀምሮ የማውቀው ነው፡፡ እናቴ በየካቲት ሆስፒታል ሕጻናትን በማከም ስራ ላይ እያለች ከእስዋ ሳንለይ ከስር ከስርዋ እያልን ሁኔታዎችን ሁሉ እንታዘብ ነበር፡፡ እናታችን ዶ/ር ሙሉአለም ገሰሰ በሆስፒሉ ተረኛ ሆና ስታድር ሁሉ አብረን በማደር ከአጠገብዋ አንለይም ነበር፡፡ በዚያ ወቅት ምንም እንኩዋን እኛ እንደአስዋ ትምህርቱን ባንወስድም በተግባር ግን እስዋ የምትሰራውን ሁሉ አብረን እየሰራን ልምዱ ፤ሀሳቡ፤እንዲኖረን አስችሎናል፡፡ እየዋለ እያደረ ግን እኛም ልጆችዋ እያደግን በመሄዳችን እና ስራውን በደንብ እንደሚፈለገው፤ወይንም እንዳሰቡት ለመስራት የግል ተቋም መመስረት ይሻላል ወደሚለው ሀሳብ አዘንብለን ይህንን ሙሉ ጂ የተባለውን የህክምና ተቋም ለመመስረት በቃን፡፡ ብሎአል ወጣት አቤል ገመቺስ፡፡
አቤል መክሊትን በሚመለከት ለማብራራት አንድ አባባል ጠቅሶልናል፡፡
…አንድ አባት ምግብ ቀርቦላቸው ለመመገብ ሲሉ ውሻ ይመጣን ይነካባቸዋል፡፡ ውሻውን ያባርሩና ደግመው ይባርካሉ፡፡ አሁንም ይነካባቸዋል፡፡ በሶስተኛው ግን ውሻውን እራሱን ባረኩት ይባላል፡፡…
ከዚህም በመነሳት አስቀድሞ ይሰጥ የነበረው ስልጠና ለጤና ባለሙያ ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን የጤና ባለሙያን ብቻ ከማሰልጠን ለምን እናቶች፤ልጅ አሳዳጊዎች፤ፍላጎቱ ያላቸው ቤተሰቦች አይሰለጥኑም የሚለው ሀሳብ ተጽእኖ በማሳደሩ የእናቶች መክሊት ተጀመረ፡፡ እናታችን ዶ/ር ሙሉአለም ገሰሰ ለህክምና ባለሙያዎች አስቀደማም ረዘም ላለ ጊዜ ስልጠና ትሰጣለች፡፡ አሁንም በተደራጀ መልክ ስልጠናውን ትሰጣለች፡፡ የእናቶች መሰልጠን ሀሳብ የመጣው እናቶች ይበልጥ ለልጆቻቸው ቅርብ የመሆን እና ውሎ አዳራቸውን የህጻናቱን ደህንነት በመከታተል በኩል ከፍተኛ ኃላፊነት ስላለባቸው ነው፡፡ የህክምና ባለሙያዎች በስራ ላይ ባሉ ጊዜ ለሚከናወኑ ድርጊቶችና ህጻናቱ ለክትትል በሚቀርቡበት ጊዜ ለሚኖረው አንዳንድ ችግር ምክር መስጠት የሚያስችላቸውን ቁምነገር የሚያገኙበት ሲሆን ለእናቶች እና አሳዳጊዎች ደግሞ በግላቸው …ስለአመጋገብ…ጽዳት አጠባበቅ…ኢንፌክሽን መከላከል የመሳሰሉትን እና ሌሎችንም ከህጻኑ ጋር በቀጥታ የሚያያዙ ነገሮችን ልጆቻቸው ሳይታመሙ አስቀድመው እንዲከላከሉ ለማድረግ የሚያስችል ስልጠና ይሰጣቸዋል ፡፡ እንደ ወጣት አቤል ማብራሪያ የህጻናቱ ጉዳይ ችግሩ መጀመሪያ የሚኖረው በቤት ውስጥ ነው፡፡ ጤና ተቋም የሚደርሰው ቀለል ብሎ ሊሆን ይችላል ስለዚህ እናቶች አስቀድመው ቢሰለጥኑ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
የእናት መክሊት ከተጀመረ አንድ አመት ከግማሽ ሆኖታል፡፡ ቀድሞ ታስቦ የነበረው እናቶች ጥያቄ ኖሮአቸው እስኪጠይቁ ሳይጠበቅ አማካሪ የሆነ ዶ/ር ቢኖራቸው እና እሱ እናቶቹን እየጠየቃቸው መፍትሔ ወደመሻቱ ቢኬድ የሚልም ጭምር ነበር፡፡ ይህንን ወደፊት ለማድረግ የሚያስችል ነገር ሲፈጠር የሚቀጥል ሲሆን ለአሁን ግን ስራውን ቀጥለናል፡፡ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው፡፡ በቴሌግራም ጭምር የውይይት ቻናል ተፈጥሮ እናቶች ከሕክምና ባለሙያዎች፤እናቶች ከእናቶች ልምዳቸውን እየተካፈሉ፤ጎደሉ የሚባሉትን ነገሮች እንዲሟሉ እየተደረገ ባጠቃላይም ህጻናቱ ጤንነታቸው እየተጠበቀ በማደግ ላይ ናቸው፡፡ በእርግጥ ገና ብዙ እናቶች እና ልጆች አሳዳጊዎች እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎች ለስልጠናውም ሆነ ለውይይቱ ይጠበቃሉ ብሎአል የእናቶች መክሊት አጋር መስራች አቤል ገመቺስ፡፡
ዶ/ር ሙሉአለም ገሰሰ የጨቅላ ህጻናት ህክምና እስፔሻሊስት እንደተናገሩት ህክምና ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ፡፡ እኔ በበኩሌ የህክምና ስራዬን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ አስቤውም አላውቅም፡፡ ወደፊትም አላስብም፡፡ የምሰራው ሁሉ ነገር በእግዚአብሔር እርዳታ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሙሉአለም የካቲት ሆስፒታል በነበሩበት ጊዜ አንድ የሚያስታውሱት ነገር አለ፡፡
‹‹ ጊዜዬን፤ጉልበቴን ሳልቆጥብ ለራሴ ወይንም ለቤተሰቤ ቅድሚያ ልስጥ ሳልል ሙሉ በሙሉ ህጻናቱን በመርዳት እና ባለሙያዎችን በማሰልጠን ላይ ስተጋ ስለሚያዩኝ በአስተዳደር በኩል ምንም ተጽእኖ አያሳድሩብኝም ነበር፡፡ ፊርማ አልፈረምሽም፤በዚህ ሰአት አልገባሽም የመሳሰለው ነገር ለእኔ በወቀሳነት አይቀርብም ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ግን በደንብ የሚቀርቡኝ ሰዎች…ግድየለም ወደፊት ሊያስወቅሰሽ ስለሚችል አንዳንዴ እንኩዋን ስብሰባ ሲጠራ ግቢ አሉኝ፡፡እኔም እሺ አልኩኝና አንድ ቀን ገባሁ፡፡ ለካስ ግምገማ ነበር፡፡ ሰብሳቢው ሲያየኝ….ዛሬ ዶ/ር ሙሉአለምም መጥታለች፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ብዙ ስራ ትሰራለች እናመሰግናለን፡፡ ግን አብረዋት ከሚሰሩ ባለሙያዎች የሚሰነዘር አስተያየት አለ፡፡ እሱዋን ስለሚፈሩአት ከበስተጀርባ በማማረር የሚናገሩት ነገር አለ፡፡ እሱም አንድም ልጅ አይሙት እያለች ሐኪምንም ነርስንም ታሰቃያለች ፡፡ ሰራተኞቹ ምግብ መብላት እስከማይችሉበት ድረስ ከታካሚዎች እንዳይለዩ ታደርጋለች…ወዘተ ፡፡ ስለዚህ እንዳይነግሩአት ይፈሩአታል እንጂ ሰራተኞቹ ቅሬታ አላቸው ተባለ፡፡ ከዚያም ተሰብስበው የነበሩ ሁሉ እኔን ለመደገፍ አስተያየት ለመስጠት እጃቸውን አወጡ፡፡ እኔም …የለም የለም…እኔ እራሴ መልስ እሰጣለሁ …እጃችሁን አውርዱ፡፡ አመሰግናለሁ አልኩኝ፡፡ በጊዜው በሆስፒታሉ የጥራት ቡድን አለቃም ነበርኩ፡፡ ስለዚህም ንግግሬን ስጀምር……የጥራት ቡድን አለቃ መሆኔን ታውቃላችሁ አይደለም ?አልኩአቸው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በሁዋላ ጨቅላ ህጻናት ወይም ህጻናት እንዲሁም እናቶች ብቻ አይደሉም እንዳይሞቱ የሚባሉት፡፡ እንዲያውም ከዛሬ ጀምሮ ማንኛውም ወጣት፤ አሮጊት፤ ሽማግሌው፤ወንድ ሴቱ ሁሉ፤እየተነፈሰ ለህክምና ወደሆስፒታሉ የሚገባ ሰው ሁሉ መሞት የለበትም አልኩኝ፡፡ ከዚያም የግምገማው ውጤት ምንም እንዳልተፈጠረ ሙሉ በሙሉ ጥሩ ውጤት ሲሰጠኝ…እኔ ደግሞ ልጅ አይሞትም ትላለች ያልከውን ጻፍልኝ፡፡ ተገምግሜአለሁ፡፡ እንደስህተት ተቆጥሮ ተነግሮኛል፡፡ ስለዚህ ጻፈው በማለት ብዙ ተዳርሰን በሁዋላ ሰውየው ተቀጥቶ ነገሩ ተቋጨ፡፡ ብለዋል ዶ/ር ሙሉአለም ፡፡
የዶ/ር ልጅ አቤል ገመቺስን ጨምሮ ያነጋገርናቸው እናቶች ምስክርነት ባጠቃላይ እናቶች ከእርግዝና በፊት፤በእርግዝና ጊዜ እንዲሁም ከወለዱ በሁዋላ ስልጠና ማግኘታቸው ምን ያህል ጠቃሚ ነው ለሚለው የእኛ ምስክርነት በቂ ነው ብለዋል፡፡
Saturday, 01 June 2024 20:59
አንድም ሰው መሞት የለበትም….
Written by ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Published in
ላንተና ላንቺ