Saturday, 01 June 2024 21:05

እኛ ያለነው እንደኛ ክፋት ሳይሆን እንደህዝቡ ቸርነት ነው”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 ምሁራን በ”ብሄርተኝነት” መፅሀፍ ላይ የፓናል ውይይት አካሄዱ          በዶ/ር በብርሃኑ ሌንጂሶ የተደረሰው “ብሔር-ተኝነት” የተሰኘው መጽሐፍ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በዓድዋድልመታሰቢያ፣ ፓን አፍሪካ አዳራሽ የተመረቀ ሲሆን። በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ታዋቂ ግለሰቦች ታድመዋል።
በምረቃቱ ሥነስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ጽሑፍ ያቀረቡት ደራሲ፣ መምሕርና የሚዲያ ባለሙያ አቶ ታጠቅ ከበደ ከደራሲው ጋርስለነበራቸው የልጅነት ትውስታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተዋል።
 መጽሐፉ በኢትዮጵያ ስለሚስተዋሉ የብሔረተኝነት ዓይነቶች የሚቃኝ መሆኑን የተናገሩት አቶ ታጠቅ፣ ከመጽሐፉ የተወሰኑ ጥቅሶችን በንባብ አቅርበዋል።
በመጨረሻም “ብሔር-ተኝነት” መጽሐፍ በአሁኑ ወቅት የአጀንዳ ማሰባሰብ መርሃ ግብር እያካሄደ ለሚገኘው ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በግብዓትነት የሚያገለግሉ ምክረ ሃሳቦችን ማካተቱን ጠቅሰዋል፡፡
ደራሲው ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ የብሔረተኝነት ብየና አወዛጋቢ መሆኑን በመጥቀስ፣ የብየናውን ሁለት ተቃራኒ ጎኖች በስፋት አብራርተዋል። “የብሔርተኝነትን ጥሩ ጎን ካጎለበትነው፣ ጥቅም አለው” ያሉት ደራሲው፣ መጽሐፉ ብሔረተኝነትን ከስሜት አላቅቆ በሚዛኑ ለማየት እንዲያግዝ በማሰብ  እንዳዘጋጁት ተናግረዋል።
ብርሃኑ (ዶ/ር) ስለ ብሔርተኝነት ምሳሌ ሲያቀርቡ፣ “በተለምዶ ‘የ3 ሺህ ዓመት ታሪክ’ የምንለው የነገስታት ታሪክ ውስጥም የብሔረተኝነት ቀለም ይስተዋላል” ብለዋል።
“መጽሐፉን ለማዘጋጀት ወደ አምስት ዓመት ገደማ ፈጅቷል” ሲሉ ንግግራቸውን የቀጠሉት  ደራሲው፤ “በምረቃው ዕለት በሁለት ነገሮች ደስተኛ ሆኛለሁ። አንደኛ አድዋ መታሰቢያ መመረቁ ነው። ምክንያቱም በዓለም ላይ የዕውነተኛ አገራዊ ብሔረተኝነት ቢፈለግ፣ ከዓድዋ ውጭ የለም። ሁለተኛው ደግሞ፣ በመጽሐፉ የመጨረሻ ምዕራፍ የተገለጸው ሃሳብ ከአገራዊ ምክክሩ ጋር ተገናኝቷል።” በማለት አስረድተዋል።
በመጨረሻም፣ የመጽሐፉ ሽያጭ ገቢ “በወጣቶች ልማት ላይ ትኩረት ያደረጉ” ላሏቸው፣ በሁሉም ክልሎች ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች እንደሚውል በማስታወቅ ደራሲው ንግግራቸውን ቋጭተዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከአትሌት ደራርቱ ቱሉና ከሌሎች የክብር እንግዶች ጋር በመሆኑ መጽሐፉን መርቀዋል። አቶ አገኘሁ ከምረቃው አስከትለው ባደረጉት ንግግርም፣ “ጎንደርን የሚያውቅ...ፎገራን የሚያውቅ ነው” በማለት ደራሲውን ሲያሞካሹ፤ “ከእኔ በላይ ጎንደርን ያውቀዋል. . .የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ የተሳሰርን ነን” ብለዋል።
ለደራሲውና ቤተሰባቸው መልካም ምኞታቸውን የገለጹት አቶ አገኘሁ፣ መጽሐፉ ከሶስዮሎጂ ባሻገር፣ የተለያዩ የዕውቀት ዘርፎችን እንደሚነካ ተናግረዋል። በአጠቃላይ የመጽሐፉን ይዘትና የኢትዮጵያን አገራዊ ገጽታም በንግግራቸው ዳስሰዋል።
“እኛ ያለነው እንደ እኛ ክፋት ሳይሆን እንደ ሕዝቡ ቸርነት ነው” ሲሉ ንግግራቸውን የቀጠሉት አቶ አገኘሁ፣ “የአሁኖቹ ልሂቃን ወይ በታሪክ ተወቃሽ ወይም ተመስጋኝ እንሆናለን” ሲሉ አመልክተዋል።
አቶ አገኘሁ ስለ አገራዊ ምክክሩ አጠቃላይ ገለጻ ሰጥተው፣ ከመጽሐፉ ጋር ያለውን ግንኙነት በመጥቀስ ንግግራቸውን አሳርገዋል።
በመጽሐፉ  ላይ የፓናል ውይይትም የተካሄደ ሲሆን የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የሕግ መምሕሩ ታደሰ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ መንግስቱ አሰፋ (ዶ/ር) እና ዕውነቱ ሃይሉ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ነበሩ።
“ብሔር-ተኝነት” መጽሐፍ በአማርኛና ኦሮሚኛ የተዘጋጀ ሲሆን፤ የአማርኛው መጽሐፍ በ5 ክፍሎችና በ15 ምዕራፎች የተዋቀረ ነው። የኦሮሚኛው መጽሐፍ ደግሞ፣ በ16 ምዕራፎች የተቀነበበ ነው።
ዶ/ር ብርሃኑ ሌንጄሶ  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ናቸው።   

Read 735 times